Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዓለም በመስቀለኛ መንገድ ላይ

ዓለም በመስቀለኛ መንገድ ላይ

ቀን:

 በጥሩነህ ዜና (አምባሳደር)

በዓለም ላይ እ.ኤ.አ በ1940 ከነበረው 2.3 ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ 60 ሚሊዮን ያህል የተገደለበትና የሰው ልጅ በሺሕ የሚቆጠሩ ዓመታት ፈጅቶ ከገነባው ሥልጣኔ ገሚሱን ያህል  በአምስት ዓመታት  ውሰጥ  ያወደመውን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት በአሸናፊነት የተወጡ ኃያላን አገሮች፣ ተመሳሳይ እልቂት ለወደፊት እንዳይከሰት ለማድረግና የበላይነታቸውን አረጋግጠው ለማቆየት የገነቡት ዓለም አቀፍ ሥርዓት ባለፉት ሰባት አሥርተ ዓመታት አንፃራዊ ሰላም፣ መጠነ ሰፊና ጥልቀት ያላቸው የፖለቲካ የሶሻልና የኢኮኖሚ ዕድገቶች በምድራችን እንዲከሰቱ አስችሏል፡፡ በተለይም የቴክኖሎጂና የፋይናንሰ አብዮት ተከትሎ የመጣው የግሎባላይዜሽን ማዕበል በዓለም ከተስፋፋ ወዲህ የዓለም ሀብት በአራት ዕጥፍ ጨምሯል፡፡

ሆኖም ይህ ከግሎባላይዜሽን ጋር ተያይዞ የመጣው እጅግ የላቀ ዕድገት ሁሉንም ወገኖች እኩል ተጠቃሚ አላደረጋቸውም፡፡ በፋይናንስ ሊበራላይዜሸን ምክንያት ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በሰከንዶች ውስጥ በብዙ ቢሊዮን የማንቀሳቀሰ ዕድል የተፈጠረለት ካፒታል እንቅስቃሴው በተገደበው ሠራተኛ ላይ በተጎናፀፈው ተጨማሪ የበላይነት ምክንያት፣ ከጠቅላላ ምርት የሚያገኘው ድርሻ እየደገ ሲሄድ የሠራተኛው ወገን ድርሻ በአንፃሩ አሸቆልቁሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ዕድገት ተከትሎ የመጣውና ሠራተኛን በሮቦት የመተካቱ ሒደት ሠራተኞች ከሥራቸው እንዲፈናቀሉ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች በብዙ የበለፀጉ አገሮች 20 በመቶ የሚሆኑ ሀብታሞች ከጠቅላላ የአገሮች ሀብት 80 በመቶ የሚሆነውን ለፍጆታቸው ሲያውሉ፣ 80 በመቶ ለሚሆነው ሠራተኛ ሕዝብ የሚደርሰው 14 በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡ ይህ ጥቂቶች ከጠቅላላው የአገሮች ሀብት አብዛኛውን አምርተው ያንን ያህሉን ለፍጆታቸው የሚያውሉበትና (ከ80 እስከ 90 የሚሆነው) የአብዛኛው ዜጋ ድርሻ እያሽቆለቆለ የሚሄድበት የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ ከቀድሞ የካፒታሊስት ሥርዓተ ምርት የተለየ አንዳንድ ሊሂቃን  ‹‹Plutonomy›› የሚሉት ነው ፡፡

ይህ  በኢኮኖሚ መስክ ያለው ክስተት በፖለቲካም ጉልህ ተፅዕኖ እያደረገ ነው፡፡ለዚህም ዋና  ምክንያት  የምርጫ  ውጤት በእነዚህ አገሮች የሚወሰነው ከሞላ ጎደል በገንዘብ ኃይል እየሆነ መሄዱ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 በአሜሪካ ለፕሬዚዳንትነት በተደረገው ምርጫ ሁለቱ ተፎካካሪዎች ለቴሌቪዥን ማስታወቂያና ለተለያዩ ምርጫ ነክ ጉዳዮች ያወጡት ገንዘብ (2.3 ቢሊዮን ዶላር) በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ ነው፡፡ ሀብታሞች ይህን ያህል ለምርጫው ያዋጡት ዓላማቸው እንዲሳካ እንጂ የመንግሥተ ሰማያት በር እንዲከፈትላቸው አይደለም፡፡ ከምርጫም በኋላም በፓርላማ የሚወጡ ሕጎችንና ሌሎች የመንግሥት ውሳኔዎችን በፈለጉት መንገድ ለማስለወጥ (Lobby) ሀብታሞች የከፈሉት ገንዘብ እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 3.14 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ ልሂቃን ዴሞክራሲ ቀስ ብሎ ወደ (Plutocracy) ሀብታሞች አገዛዝ እየተቀየረ ነው የሚሉት፡፡፡

 በአንዳንድ ታዳጊ አገሮችም እየታየ ያለው ሁኔታ በይዘት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል ናይጄሪያን ብንወስድ፣ ከነዳጅ ብቻ 80 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የምታገኘው፣ 20,000 ሚሊዮነሮች ያሉባት፣ ከእነዚህም ውስጥ አምስት ቢሊነሮች ያሏቸው 26 ቢሊዮን ዶላር ብቻ (በኦክስፋም ሪፖርት መሠረት) 112 ሚሊዮን (ወይንም ከጠቅላላው 61 በመቶ) በፍፁም ድህነት ሥር የሚገኙ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ በቻለ ነበር፡፡ ለዚህ በጣት በሚቆጠሩት እጅ የአገሪቱ ሀብት ተሰብስቦ ሌላው ደሃ የሆነበት ዋናው ምክንያት ሙሰኝነት እንደሆነ ይነገራል፡፡

 እነዚህ ክስተቶች በጉልህ የሚታዩት እንደሚባለው ዲክታተሮች በሚገዟቸው ታዳጊ አገሮች ውስጥ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሊበራል ዴሞክራሲና ነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት ቁንጮ በሆኑ በበለፀጉና ከመላ ጎደል ፈለጋቸውን እየተከተሉ ነው ተብለው በሚሞገሱ ታዳጊ አገሮች ውስጥም ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር በግሎባላይዝድ ዓለም  ዴሞክራሲና ነፃ ገበያ ብቻቸውን በዜጎች መካከል ጫፍ የወጣ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር እንደማያግዱና ተያይዞ የሚመጣውን ቀውስ እንደማያስቀሩ ነው፡፡ ለዚህ ነው  ሕዝቦች በብዙ አገሮች የሥርዓቱ ዋልታ ሆነው ለረዥም ጊዜ በቆዩ መዋቅሮች ጭምር እምነት ያጡት፡፡

ይህን ሁኔታ በግልጽ ለመረዳት የአሜሪካን ምሳሌ ብንወስድ፣ እ.ኤ.አ. በ2016 በፌዴራል መንግሥታቸው ላይ እምነት ያላቸው አሜሪካኖች ቁጥር 19 በመቶ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅት በምክር ቤቱ ላይ ያላቸው እምነት ዘጠኝ በመቶ ብቻ ነበር፡፡ እንዲሁም በዋናዎች የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ማለትም በጋዜጦችና በቴሌቪዥኖች ላይ ያላቸው ከ20 እስከ 21 በመቶ  ብቻ  ነበር፡፡ በሃይማኖት ተቋማት ላይ ቢሆንም ሕዝቡ ያለው እምነት 41 በመቶ የዘለለ አይደለም፡፡ ሀብት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ (በአሜሪካ እንደታየው ከ80 እስከ 90 በመቶ) በጣት በሚቆጠሩ ሀብታሞች እጅ መሰባሰቡ በኢኮኖሚው ላይ ያሰከተለው ቀውስ፣ በኅብረተሰቡ ውሰጥ የፈጠረው ሥርዓት አልበኛነትና የሰላም ዕጦት ሕዝቡ በነባሩ ተቋማት እምነት እንዲያጣና (ጫፍ የወጡ) ፕሬዚዳንት ትራምፕና አምሳያዎቻቸው ወደ ሥልጣን ማማ እንዲወጡ እንዳስቻላቸው ነው፡፡

በአገር ደረጃ ሲታይም ግሎባላይዜሸን ሊብራል የኢኮኖሚ ፈለግ ከሚከተሉ የበለፀጉ አገሮች የበለጠ መንግሥት በኢኮኖሚያቸው ውስጥ ጠንከር ያለ ሚና የሚጫወቱ  ቻይናና  ሌሎች የእስያ ታዳጊ አገሮችን እንደጠቀመ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌም ያህል እ.ኤ.አ. በ1978 ኢኮኖሚዋን ሪፎርም አድርጋ ዓለምን ስትቀላቀል ከጠቅላላ የዓለም ምርት የነበራት ድርሻ ሁለት በመቶ ሆኖ በምርት መጠን ስትለካ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ቻይና፣ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛ ደረጃ ይዛ 15 በመቶ  ታመርታለች፡፡ አንዳንድ ሊሂቃን የቻይና ጠቅላላ ምርት የገንዘባቸው ትክክለኛው የመግዛት አቅም ተስተካክሎ ሲለካ ከአሜሪካ ጠቅላላ ምርት በልጦ አንደኛ ደረጃ ይዟል የሚሉ አሉ፡፡ ከጠቅላላው የዓለም ንግድ የቻይና ድርሻ 37 በመቶ ደርሷል፡፡ እንዲሁም ቻይና ከታዳጊ አገሮች በተለይም ከአፍሪካ ጋር እያደገች ያለችው የኢኮኖሚና የንግድ ቁርኝት አገሪቱን በአኅጉሩ የምትታመን አጋር እያደረጋት ነው፡፡ በወታደራዊ ረገድም ቻይና እንደ ሌሎቹ ኃያላን ሁሉ የጦር ሠፈር በአፍሪካና በእስያ እየገነባች  ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በሁሉም መስክ ጡንቻዋን እያፈረጠመች ብትሆንም፣ ቻይና ዋና ዓላማዋ ከሁሉም ጋር በመተባበር ልማትን ማፋጠንና የኢኮኖሚ ጥቅሞችን ማስጠበቅ በመሆኑ፣ እንደ ሶቪዬት ኅብረት በርዕዮት ዓለም ጎራ ለይታ ለመቆም ፍላጎት ያላት መስሎ አይታይም፡፡

የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከዓለም ጠቅላላ ምርት እ.ኤ.አ. በ1980ዎች ከነበረበት 34 በመቶ ድርሻ በአሁኑ ጊዜ ወደ 22 ዝቅ ብሏል፡፡ አሜሪካ በንግድ፣ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት፣ እንዲሁም ለታዳጊ አገሮች በምታድርገው ዕርዳታ መጠን የነበራት የበላይነት ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወረደ ሄዷል ፡፡ ሆኖም አሜሪካ አሁንም በወታደራዊ መስክ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የላትም፡፡  ያላትን ከፍተኛ ዕምቅ የነዳጅ ምርቶችን ተጠቅማ ኢኮኖሚዋን ከአራት እስከ አምስት በመቶ ካላሳደገችና የውስጥ ዕዳ (15.9 ትሪሊዮን ዶላር)፣ የውጭ ዕዳ (3.9 ትሪሊዮን ዶላር ከዚህ ውስጥ 1.101 ትሪሊዮን የቻይና) ቀንሳ ኢኮኖሚዋን ጤናማ ካደረገች እንደ ቀድሞውም ባይሆንም፣ በተለይም በቴክኖሎጂና በፋይናንስ መስክ ያላትን የበላይነት ይዛ ረዥም መንገድ ልትጎዝ እንደምትችል ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ይህም ሆኖ  ብቸኛ ኃያል አገር አያድርጋትም፡፡  

 በመሆኑም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በሁለት ኃያላን (Bipolar Superpower System) ማለት በአሜሪካና በሶቪዬት ኅብረት፣ እንዲሁም ከሶቪዬት መፈራረስ በኋላ ከሞላ ጎደል በአንድ ኃይል (Unipolar Superpower) ስትመራ የቆየችው ዓለም፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምራ ወደ ብዙ (Multipolar Power System) አመራር በመዞር ላይ ነች፡፡ ለዚህም መሠረታዊ ምክንያቱ አገሮች በኢኮኖሚ ረገድ ያላቸው ደረጃ እየተቀራረበ መምጣቱ ሲሆን፣ የትራምፕ መመረጥ ደግሞ ወቅታዊ ምክንያት ነው ለማለት እንችላለን፡፡

 በመሆኑም በሚቀጥሉት ዓመታት አሜሪካ የበላይነቱን አስጠብቃ ለመቆየት  ቻይናና የአውሮፓ ኅብረት (የጀርመንና የፈረንሣይ ጥምረት) በዓለም ላይ ጉልህ የአመራር ሚና ለመጫወት፣ ሌሎች ሩሲያ፣ ህንድና ብራዚል የመሳሰሉ አገሮች በዓለም  በተለይም በየአካባቢያቸው ጎልተው በመውጣት የተለያዩ አገሮችን በጎናቸው በማሠለፍ አዲስ ቅንጅት፣ አዲስ ቡድን ለመፍጠር የሚታገሉበት ወቅት እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በዚህና ተቀባይነት ያለው አንድ መሪ በዓለም ደረጃ ባለመኖሩ በየአካባቢው በአገሮችና በሕዝቦች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በዓለም ላይ ያለው ውጥረት  በሚቀጥሉት  ዓመታት ወደ ቀውስ (Crisis or Upheaval ) እንደሚለወጥ መገመት ይቻላል፡፡ ለዚህ ነው በቅርቡ የጀርመን ቻንስለር አንገላ መርከል ለሕዝባቸው ሲናገሩ፣ ‹‹በውስጥ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በሚቀጥሉት ዓመታት ሥራ አጥነትን አስወግደን የጀርመን ኢኮኖሚ የበለጠ ጠንካራ ለማድረግ እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ባለው አሳሳቢ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ምክንያት ጀርመን ምን እንደምትሆን ለማወቅ አልችልም ፤›› ያሉት፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአካባቢያችን ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ቱርክ በመሀላቸውና እንዲሁም ኢራንን በጋራ ለመቋቋም በሚያደርጉት ትግል ያለመረጋጋት መፍጠራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ አካባቢ ለነዳጅ ስትል አንፃራዊ ሰላም እንዲኖር ስትሠራ የቆየችው አሜሪካ የነዳጅ ምርትዋ ከውስጥ ፍጆታዋ አልፎ ለአውሮፓና ለእስያ አገሮች ለመሸጥ በዝግጅት ላይ ነች፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ከእንግዲህ በአካባቢው የሚኖራት ዋናው ዓላማ በቅርብ ግዜ እንደታየው የጦር መሣሪያ መሸጥ ስለሚሆን፣ ያለውን ያለመረጋጋት ማብረድ ሳይሆን የመባባስ ሚና መጫወት ሊሆን ይችላል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይም ሆነ በአካባቢያችን እየተፈጠረ ያለው ያለመረጋጋት እንደ አውሎ ንፋስ የአጭር ጊዜ ጉዳት አስከትሎ የሚያልፍ ኃይል ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት እንዲሁም የጂኦፖለቲካል  የኃይል አሠላለፍ ላይ ጉልህና የሚታይ ለውጥ ፈጥሮ ለብዙ ዓመታት የሚቆይ ክስተት እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ስለዚህ የለውጦች ይዘት ምን ይመስላል? ከእነዚህ መካከል የሚጎዱንና የሚጠቅሙን የትኞቹ ናቸው? በጎ በጎዎችን አሟጠን ለመጠቀምና ጎጂዎችን ለመመከትስ ምን ማድረግ አለብን? ለሚሉት ጥያቄዎች በጥናት የተደገፈና አስተማማኝ መልስ በማግኘት ተዘጋጅቶ በጥንቃቄ መጓዙ የሚመከር ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በመንግሥትና በሌሎች የጂኦፖለቲካ ተንተኞች ጠለቅ ያለ የሥጋት ትንተና እንደተከናወነና የማዕበሉ አቅጣጫም በውል ስለማይታወቅ፣ ይኸው ትንተና በየጊዜው የሚከለስ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እንደመሆኑ መጠን ለጠቅላላ ሕዝብ ግንዛቤና ውይይት መነሻ እንዲሆኑ ቀለል ያሉ አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳቱ ጠቃሚ ነው፡፡

የውጭ ፖሊሲን በተመለከተ

ኢትዮጵያ አሁን የምትከተለውና የአገርን ጥቅም መሠረት ያደረገ ከሁሉም ወገን ጋር ተቀራርቦ የመሥራቱ ፖሊሲ ለወቅቱ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ ምቹ መሆኑን፣ ከአፍሪካ አገሮች ዘንድ እያገኘች ያለው አክብሮትና ተቀባይነት፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለገብና በጣም ጥሩ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንዲቻል ኢትዮጵያን መጠነ ሰፊና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመመሥረት ከተመረጡ ጥቂት አገሮች አንዷ ማድረጓ፣ እንዲሁም የዓለም የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ባሽቆለቆለበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው በ240 በመቶ ማደጉና መሪዎችዋ በየጊዜው በታላላቅ ጉባዔዎች አፍሪካን ወክለው መከፈለቸው፣ እንዲሁም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው፣ ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባልና የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆና መመረጧ ያረጋግጣል፡፡

ይህ መሠረታዊ ፖሊሲ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉት የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም ከሁሉም ጎረቤት አገሮች ጋር የበለጠ መተማመንን በመፍጠርና በማስተባበር አኀጉራችን በተለይም ምሥራቅ አፍሪካ አዳዲስና አሮጌ ኃያላን ጉልበታቸውን ለመፈተሽ የሚጠቀሙበት ሜዳ እንዳትሆን፣ አገራችን የሰላምና የልማት ደሴት ሆና እንዲትቆይ መከላከል የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት ታሪካዊ  ግዴታቸው ነው፡፡

 ከአካባቢዋ ውጪ ኢትዮጵያ ከራሷ መሠረታዊ ጥቅም አልፋ የሌላውን ሠልፍ ለማድመቅ የትም ዘላ እንደማትገባ ይታመናል፡፡ አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠርም እንኳ  በተለይ ከሰሃራ በታች ያለውን አፍሪካ አማክራና ቢቻልም አስተባብራ፣ በታሪክ የገጠሟትን በጎ ያልሆኑ ክስተቶችን አገናዝባ፣ በመጥፎ ወቅት ከጎኗ ቆመው ከጉዳት የተከላከሏትን አገሮችና ሕዝቦች ሳትረሳና መርህን በተከተለ ሁኔታ እንደሚሆን ብዙም የሚያጠራጥር  አይሆንም፡፡

የአደጋ ተጋለጭነትን ስለመቀነስ

የፀጥታ ጉዳይን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጦርነት ወዲህ ለውጭ ጥቃት  ያላትን ተጋላጭነት በሚያስተማምን ሁኔታ ከመቀነስ አልፋ፣ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ጉልህ ሚና እየተጫወተች ያለች አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በአካባቢያችን ለብዙ ጊዜ የቆየው ግጭትና የሸብርተኞች አደጋ ባልረገበበት፣ ጠንካራና የሰከነ አመራር በዓለም ላይ በታጣበት፣ በየቦታው መቻቻል ጠፍቶ መጠፋፋት ባየለበትና በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ እየነደደ ያለው እሳት አይሎ የባህር  መውጫችንን ጭምር  ቢሸፍን  በኅብረትና በተናጠል መወሰድ ካለባቸው  ዕርምጃዎች አንፃር የአደጋ ተጋላጭነት ደረጃ በስፋት ሊለወጥ ይችላል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

በተጨማሪም ሰላም በሌለበት ዓለም ሁሉም በየበኩሉ አገሩን ለመከላከል በሚያደርገው ጥዲፊያ የጦር መሣሪያ ውድድር ይጧጧፋል ተብሎ ከሚታመኑ አካባቢዎች አንዱ፣ ምናልባትም ከሩቅ ምሥራቅ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ሊታይ የሚችለው መካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ነው፡፡ ይህ የመሣሪያ ውድድር የኑክሌር ኃይልን የሚጨምር እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ይህ በቅርባችን እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገሮች ጋር ከነበራትና ካላት ግንኙነት አንፃር ሲመዘን የመከለከያና ተያያዥ የፀጥታ ኃይላትን አቋምና የሕዝቦችን አንድነትና ኅብረት በማጠናከር ረገድ ወቅቱ የሚጠይቀውን ከባድ ኃላፊነት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት በውል የሚያውቁት ጉዳይ ነው ብዬ እወስዳለሁ፡፡

የኢኮኖሚ ሁኔታን በተመለከተ ከዚህ በላይ በተጠቀሰውና በዓለም ላይ እየተከሰተ ባለው አዲስ የኢኮኖሚ የበላይነት ሽግሽግ ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ  ያለመረጋጋት ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ ምልክቶች አሉ፡፡

ስለሆነም ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ  የውጭ ንግድ ያለው ተፅዕኖ በሒደት እንዲቀነስ መሥራት እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ኢትዮጵያ በየጊዜው በድርቅ የምትጠቃ አገር ነች፡፡ በአሁኑ ወቅት በዕርዳታ የሚኖሩ  ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አሉ፡፡ ሁኔታውም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለፉት ሁለት ዓመታት አይተነዋል፡፡ መረጋጋት በሌለበት ዓለም ምግብ በዕርዳታ መልክ የሚያቀርብ ቀርቶ በግዢም ለማግኘት ምቹ ሁኔታዎች ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ ለዚህም በቅርቡ በኳታር ላይ የተፈጠረውን ሁኔታ በዓይነ ልቦና መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በማይጨው ጦርነት ወቅት የጦር መሣሪያ ከውጭ እንዳታስገባ ተከልክላ እንደነበረና በትናንትና የዛይድ ባሬ ወረራ ወቅትም የጂቡቲ ወደብ አገልግሎት የተቋረጠበት ሁኔታ እንደነበረ መረሳት የለበትም፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ተለዋጭ የባህር በር እንዲኖር፣ በተለይም ከተለያዩ የጎረቤት አገሮች ጋር ወደቦችን በጋራ ለማልማት እየደረገ ያለው ጥረት አርቆ አስተዋይነት የሚያንፀባርቅ ተግባር ስለሆነ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እጅግ የሚያደንቁት ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ በተጎናፀፈችው ድል ምክንያት ጥቁር ሕዝቦች በየቦታው ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ጋር በተለያየ መንገድ ሲያገናኙና በተምሳሌነት ሲወስዷት ቆይተው፣ በርካታዎቹ ራሳቸውን ለማግለልና ከዜጎቿም ብዙዎች ለስደት ከተዳረጉበት ምክንያቶች አንዱ ድርቅና ተከትሎ የመጣው ውርደት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡

ከድርቅና የዓለም ሁኔታ በተጨማሪ በአገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ማለት  በኢንዱስትሪና በትምህርት መስፋፋትና በኑሮ መሻሻል የተነሳ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልቀው የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድና ከአገር የተሰደዱ በርካታ ዜጎች ተገደውና በፈቃዳቸው ወደ አገራቸው የመመለሱ ሁኔታ ቀጣይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

 መንግሥት በአሁኑ ወቅት በግብርና መስክ ለአነስተኛ ገበሬዎች እያደረገ ያለው ማበረታቻ ፍሬያማ ነው፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ድጋፍ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ በግል ባለሀብቶች የሚካሄዱ ትልልቅ እርሻዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑና ለወደፊቱም አስተማማኝ ይሆናሉ ብሎ ለመገመት ስለሚያስቸግር፣ መንግሥት ድርቅን ለመቋቋምና አስፈላጊም ሲሆን የእህል ዋጋ ንረት ለመቆጣጠር፣ በየጊዜው ለእህል ግዢ የሚወጣውን  ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማዳን እንዲችል በየክልሉ ሰፋፊ እርሻዎች ቢያቋቁም ከበርካታ አደጋዎች ራሳችንን ለመከላከል እንችላለን፡፡ በዚህ ረገድ የክልል መንግሥታትና እንዲሁም ይህ ጉዳይ ከአገር ህልውና ጋር የተያያዘ እንደ መሆኑ መጠን በየቦታው ያሉ የመከላከያ ሠራዊታችን፣ መሪ ሚና እንዲጫወቱ ቢደረግ ‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ› እንደሚሉት ይሆናል፡፡

ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ አሳሳቢና ለረዥም ጊዜ ይዘልቃሉ ተብለው የሚታሰቡ ሌሎች ተግዳሮቶች ለወጣቱ የተፈለገውን ያህል ሥራ ለመፍጠርና በፍጥነት እያደገ ላለው ኢኮኖሚ በቂ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለመቻል ናቸው፡፡ እነዚህንና  የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከውጭ በተለይ ለፍጆታ የምናስገባቸውን  ሸቀጦች መጠን መቀነስ፣ እነዚህ ምርቶች በአገር ውስጥ ባለሀብቶችና በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲመረቱ ማድረግ፣ ወጣቱ ሥራ እንዲያገኝና የውጭ ምንዛሪም ለአገር ዕድገት ወሳኝ በሆኑ መስኮች እንዲውል ያስችላል፡፡

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከሚከተለው ኤክስፖርት መር ከሆነውና  ውጤትም እየሰጠ ካለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጎን ለጎን፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመከላከል ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች በአገር ውስጥ የሚመረቱትን እንዳያቀጭጩ የበለጠ  ከለላ መስጠት የግድ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው ከለላው በጥንቃቄ ካልተያዘ አገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከምታድርገው እንቅስቃሴ አንፃር ችግር ሊፈጥር  ይችላል፡፡ መንግሥትም ከገቢ ግብር የሚያገኘውን የታክስ ገቢ ለጊዜው ሊቀንስ ይችላል፡፡ግን በአንክሮ መጤን ያለበት በዓለም ላይ ይደርሳል ተብሎ ከሚገመተው አደገኛ ሁኔታ በተጨማሪ፣  ከኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ ይህን ፈለግ ሳይከተል ወደ ብልፅግና ማማ የወጣ አንድም አገር በዓለም ላይ እንደሌለ ነው፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዛሬ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በብዙ ታዳጊ አገሮች ጎልቶ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ለወደፊቱም በየጊዜው (ከመጠን በላይ  በባንኮች ስግብግብነት እንደፊኛ ያበጠውና በዴሪቬቲብ ላይ የተመሠረተው የስቶክ ማርኬት ገበያ ሲፈነዳ) ከሚከሰተው የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስና ያለመረጋጋት አንፃር፣ ችግሩ እየባሰ የሚሄድ እንጂ መፍትሔ የሚኖረው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እያደገና በዚያው መጠን የዓለምን ኢኮኖሚ እየተቀለቀለ ነው፡፡ በመሆኑም ለዓለም አቀፍ ቀውስ ያለው ተጋላጭነት በዚያ መጠን እንደሚሰፋ ግልጽ ነው፡፡  እንዲህ ዓይነት ችግር ሲከሰት እ.ኤ.አ. በ1980ዎች በላቲን አሜሪካ፣ በ1990ዎች በእስያ እንደታያው የችግሩ ገፈት ቀማሾች ታዳጊ አገሮች እንደሚሆኑ የተመለከትነው ጉዳይ ነው፡፡

እርግጥ ነው ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማዳንና ሥራ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተሻሻለ ነው፡፡ ግን አሁን እየተከሰተ ካለው የዓለም አቀፍ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በጣም መጠናከር እንዳለበት ነው፡፡

በፖለቲካ ረገድ

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ላለው ሰላምና ዕድገት ዋንኛው ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፈው እኩልነትና ተያይዞ የመጣው አንድነት እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ይህን ወሳኝ ጉዳይ አስተዳደራዊ ሁኔታዎችን በማሻሻል ለማጠናከር  ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ፣ የሥርዓቱ ዋልታ የሆኑ ሕጎች፣ ሕገ መንግሥቱ ጭምር ለአገር አንድነትና ለሕዝቦች ኅብረት ጥንካሬ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ በዝርዝር በማጥናት፣ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ለማረም ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎችን በየጊዜው መውሰድ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሊረባረቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው ፡፡

አንድ አገር ለጥቃት ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሕዝቦች አንድነትና ኅብረት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በውል የሚያውቁት ነው፡፡ ሆኖም በብዙ አካባቢዎች በሕዝቦች መካከል በሚደረጉ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ሕይወትና ንብረት ከመጥፋቱም በላይ፣ ለውጭ ጠላቶች ጥቃት በር ከፋች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቶች የሕዝቦች አሠፋፈርና ታሪካዊ ሁኔታ፣ በሕዝቡ ለሚነሳው የማንነት ጥያቄ በወቅቱ መልስ  ያለመስጠት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የልማት ሥራ እጅግ ደካማ መሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የፌዴራልና ሌሎች የአስተዳደር ወሰኖች በወቅቱ የሕዝብን ጥያቄ ተከትለው ያለመካለላቸው፣ በፍጥነት እያደገ ያለው የሕዝብ ቁጥርና  ለግል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም በሚደረግ ሹክቻና ፍትሕ የጎደለው አስተዳዳር እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

ስለሆነም የችግሮችን ምንጭና ሕዝቦች በችግሮች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ (Real or Apparent Perception) በማጥናት ወቅታዊና ተገቢ ዕርምጃዎች ችግሩ ከመከሰቱ በፊት መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲና መንግሥት ችግሮች ሲከሰቱ ፈጣን ዕርምጃ በመውሰድ ለችግሮች መፍትሔ እንደሚያስገኙ ብዙዎቻችን የምንቀበለው ቢሆንም፣ ችግሮቹ እንዳይከሰቱ ሁለገብ ዕርምጃ ቀድሞ በመውሰድ ረገድ የሚደረገው ጥረት ግን ዘገምተኛ መስሎ ይታያል፡፡    

ከዚህ በላይ የተጠቀሱና ቀላል የማይባሉ ችግሮች ቢታዩም በአሁኑ ወቅት በሕዝቦች መካከል እያደገ ያለው አንድነትና ሰላም አለ፡፡ ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ዘላቂነት እንዲኖረው ለማስቻል በሕዝቦች መካከል ከፖለቲካ በተጨማሪ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ለሁሉም እኩልና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ቀደም ተብሎ እንደተገለጸው በአሜሪካና በናይጄሪያ ያለው ዓይነት  በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች የአገሪቱን ሀብት ጠቅለው ይዘው፣ ሌላው በድህነት እየማቀቀ አገር አንድ ሆና ትቀጥላለች ማለት ያስቸግራል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ገና ጀማሪና በግለሰቦች እጅ ያለውም ሀብት ከናይጄሪያ ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡

 ሆኖም የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማፋጠንና ባለሀብትን ለማፍራት የሚደረገው ጥረት ወደዚያ እንዳይገፋን ሕዝቡ እንደ አቅሙ አክሲዮን ገዝቶ ሊሳተፍ የሚችልባቸው አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች በመንግሥት ድጋፍ ቢቋቋሙ፣ ያሉትም ላይ ሕዝቡ በተመሳሳይ ሁኔታ  እንዲሳተፍ ቢደረግ (በዚህ ረገድ በፌዴራል መንግሥት በኩል ምንም እንቅስቃሴ ባይታይም በአንዳንድ ክልሎች አርቆ አስተዋይነት የሚንፀባረቁ ተግባራት በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ናቸው)፣ እንዲሁም አሁን በሒደት ላይ ያለው ወጣቱን ባለሀብት ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት በጥናት ተደግፎ ቢጠናከር፣ እንደ ጀርመኖች አነስተኛና መካካለኛ ኢንተርፕራይዞች በኢኮኖሚው የጎላ ሚና እንዲጫወቱ ቢደረግ በዓለም ላይ እያንዣበበ ካለው ቀውስ ራሳችንን ለመከላከል ይረዳናል፡፡ እንዲሁም ከሀብቱ ድርሻ  አለን የሚሉ  መካከለኛ ገቢ ያላቸው  ዜጎች ቁጥር  በማበራከት፣  በአገሪቱ ያለው ሰላምና መረጋጋት ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ እንችላለን፡            ለማጠቃለል

ይህ ጽሑፍ ለማሳየት የሚሞክረው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የጎላ ችግር ስላለባት አጣዳፊ ዕርምጃ ወስደን አንታደጋት ለማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት (አንዳንድ ችግሮች ቢታዩባትም) የራሷን ሰላም ማስፈን ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው መረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገች ያለች አገር ነች፡፡ በኢኮኖሚ ረገድም በታሪኳ ተወዳዳሪነት የሌለው የድርቅ አደጋ አጋጥሞ እንደ ከአሁን ቀደሙ የራሷንም ሆነ የዓለምን ሕዝብ በልመና ሳትሰለች በአብዛኛው ከመንግሥት ካዝና በወጣ ገንዘብ የዜጎቿን ሕይወት ለመታደግ መብቃቷ ይታወቃል፡፡ ይህን ችግር ተቋቁሞ በአሁኑ  ወቅት በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ የአፍሪካም ሆነ የዓለም አገሮች ቀዳሚ ሥፍራ ይዛ እየተጓዘች ያለች አገር ነች፡፡ ከአንድ አገር ወደ ሌላው የሚፈስ ኢንቨስትመንት አፍሪካን ጨምሮ በአብዛኛው ዓለም ባሽቆለቆለበት እ.ኤ.አ. በ2013 ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የገበው የመዕለ ንዋይ ፍሰት (FDI) በ240 በመቶ አድጎ 953 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ 3.2 ቢሊዮን አሻቅቦል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በታሪክ በልማትም ሆነ በፖለቲካ እንዲህ የተመቻቸ ሁኔታ የገጠማት ወቅት አልነበረም ለማለት ይቻላል፡፡ ይህን አመቺ ሁኔታ ተጠቅመን ሁሉን በሚያቅፍ ልማት ድህነትን ቀነስንና በሒደትም አስወገድን፣ የሕዝቦችን አንድነትና የበላይነት በውል ካረጋገጥን ሌሎች ችግሮች ቢከሰቱ እንኳ የሚያሳስቡ አይሆኑም፡፡

ታዲያ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ምንድነው ቢባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ መጪው ዘመን ብዙ በርካታ ለውጦችን ያረገዘና በጎ ያልሆኑ ክስተቶችን ያስከትላል  ተብሎ የሚታሰብ ነው፡፡ አንድ አገር ለማናቸውም የውጭ አደጋ ተጋለጭ የሚሆነው የሚታይ የውስጥ ድክመት ሲኖር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም አስፈላጊ ዕርምጃዎችን በጋራና በትብብር በመውሰድ፣ ውስጣዊ አሉታዊ ሁኔታዎችን በማስወገድ  በብዙ ዜጎች ደምና ላብ ከድህነት አረንቋ ወጥታ ራሷን ቀና በማድረግ ላይ ያለች አገር፣ በዓለም ላይ በሚፈጠረው ቀውስ ምክንያት ወደ ነበረችበት እንዳትመለስ እንከላከላት ለማለት ነው፡፡

     ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀድሞ ኮሚሽነር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

           

 

          

   

 

 

 

 

                                                                      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...