Thursday, May 30, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ እንቀበለው!

አዲስ ዓመት ሲመጣ ሁሌም በተስፋ የመቀበል ፅኑ ፍላጎት አለ፡፡ አሮጌው ዓመት ተሸኝቶ አዲሱ ሲጠባ ሁሌም መንፈስን ማነቃቃትና ጥሩ ጥሩ ነገሮች መመኘት የተለመደ ነው፡፡ በአሮጌው ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁትን በሞራል ተነሳስቶ ለማሳካት፣ አዳዲስ ዕቅዶችን ውጤታማ ሆኖ ለማጠናቀቅ፣ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በብልኃት ተሻግሮ ካሰቡበት ለመድረስ ተስፋን የመሰለ ስንቅ የለም፡፡ ጥረት የሚያሳዩበት ተስፋ፡፡ አዲሱን ዓመት በተስፋ ለመቀበል ውስጥን መፈተሽ፣ ችግሮችን ነቅሶ መለየት፣ ድክመትና ጥንካሬን ማወቅ፣ ካለፉ ስህተቶች መማር፣ ዓላማን ለማሳካት የሚረዱ አዋጭ ዘዴዎች መቀየስ፣ ወዘተ. በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንን በአገር ደረጃ ስናሳድገው ደግሞ ገዘፍ ያለ ምሥል ይፈጥራል፡፡ በመንግሥት በኩል ያለፉትን አሥር ዓመታት መለስ ብሎ በመቃኘት፣ ስኬቶችንና የጎደሉ ነገሮችን በማገናዘብ ለአዲሱ ዓመት የተሻለ ስኬት በአዲስ መንፈስ ለመነሳሳት ለአሥር ቀናት ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች እየተከናወኑ ነው፡፡ ‹‹መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› የሚል መሪ ቃልም ተይዟል፡፡ ካለፉት ስህተቶች በመማር የተሻሉ ተግባራት ለማከናወን ቁርጠኝነቱ ካለ መልካም ሐሳብ ነው፡፡

ሁሌም እንደምንለው ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ የታላቅ ሕዝብም አገር ናት፡፡ ይቅር ባይነት፣ መተሳሰብ፣ መተጋገዝ፣ አገርን በጋራ መጠበቅ፣ ከልዩነቶች ይልቅ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ቅድሚያ መስጠት፣ ታማኝነት፣ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት፣ ወዘተ. የታደለ ኩሩ ሕዝብ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዓለም ተወዳዳሪ የሌለው ተምሳሌት በመሆን ለጥቁር ሕዝቦች መመኪያ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህች ታላቅ አገር በገጠሟት ፈተናዎች ምክንያት ደግሞ የረሃብ፣ የኋላ ቀርትነት፣ የማይምነት፣ የግጭትና የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆና ማሳለፏ ደግሞ የታሪክ ጠባሳችን ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ ከድህነት አረንቋ ውስጥ የዘፈቃትን መርገምት ተረት ማድረግ የሚቻለው፣ የጥንታዊያኑን ጀግኖች አባቶችና እናቶች የአገር ፍቅር ወኔ ወደ ልማቱ ማዞር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህ ልማት ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግናን በጋራ የያዘ  እንዲሆን ደግሞ ከጨለምተኝነት መላቀቅ ይገባል፡፡ ጨለማን እያለሙ ብርሃን እንደማይገኝ ሁሉ፣ አምባገነንነትን እየፈለጉ ዴሞክራሲን ማስፈን አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታው ጫፍ ማድረስ የሚቻለው በመላ ዜጎቿ ስምምነት ብቻ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ የሁሉም ዜጎች ምኞት መሆን አለበት፡፡ ተግባራዊ የሚሆን ምኞት፡፡

በአዲሱ ዓመት ለዘመናት እየተንከባለሉ ለሚያስቸግሩ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች የማያዳግም መፍትሔ ሊኖር ይገባል፡፡ አንደኛው ችግር የሚመነጨው ከተዛባው ታሪካችን ነው፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን የነገሥታቱንና የገዥዎችን ሥራዎች እየመዘዝን ከመወቃቀስ ይልቅ፣ ጠቃሚ የሚባሉትን ተቀብለን የማይረቡትን ደግሞ ለታሪክ ዶሴ መተው ይገባል፡፡ ይህ ትውልድ ካለፉ ስህተቶች ተምሮ የራሱን ደማቅ ታሪክ መጻፍ ሲገባው፣ ባልነበረባቸው ዘመናት በተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ መነታረኩና መወቃቀሱ እርባና የለውም፡፡ ይልቁንም መልካም ነገሮችን የጋራ እሴት በማድረግ፣ እኩይ ድርጊቶች ደግሞ በዚህ ዘመን እንዳይፈጸሙ ኃላፊነትን መወጣት የእዚህ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ ይቅር ባይነትና አስተዋይነት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ባህል በሆነበት አገር ውስጥ፣ የታሪክ ጠባሳዎችን እየመዘዙ መነታረክና አልፎ ተርፎ ሌላ ቀውስ ለመፍጠር መጣደፍ ሊያሳፍር ይገባል፡፡ ማንም ባልነበረበት ዘመን ድርጊት ምክንያት ሊወቀስ አይገባም፡፡ ያለፉትን ዘመናት ጥፋቶች በዛሬው መነጽር ብቻ ለማየት መሞከርም ተገቢ አይደለም፡፡ ታላቁ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ዘመነ አፓርታይድን ከመበቀል ይልቅ፣ በፍቅርና በይቅርታ ማለፍ ይገባል በማለት ብሔራዊ እርቅ ማስፈናቸው እንዴት ይዘነጋል? በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኙት ክብር እንዴት ይረሳል? ይቅር ተባብሎ አገርን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ? ወይስ በዘር እየተቧደኑ አገርን ማጥፋት? ለትውልዱ የቀረበለት ምርጫ ነው፡፡ የአዲስ ዓመት ምርጫ፡፡

አዲሱ ዓመት የአዲስ ምዕራፍ መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥትና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በመጀመሪያ ከዚህች ከተከበረች ታላቅ አገር ሸፍጥ፣ አሻጥር፣ ቂም በቀል፣ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ሌብነት፣ ዘረኝነት፣ ትምክህትና የመሳሰሉ አውዳሚ ነገሮች ሊወገዱ ይገባል፡፡ በተጨማሪም እስራት፣ መፈናቀል፣ ሞት፣ የንብረት ውድመትና እንግልቶች መቆም አለባቸው፡፡ የሚደግፈኝ ወዳጄ የማይደግፈኝ ጠላቴ የሚባለው አስተሳሰብ ሊበቃው ይገባል፡፡ ለብጥብጥ፣ ለግጭትና በአጠቃላይ ለሰላም መደፍረስ ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶች አያስፈልጉም፡፡ ስሜታዊነት በምክንያታዊነት ሊታረም ይገባል፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ የበላይነት ተማምነው በሰላምና በፍቅር፣ እንዲሁም በእኩልነት የሚኖሩበት ሥርዓት እንዲፈጠር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ መግባባት ይፈጠር ዘንድ የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ማንፀባረቅ የምትችለው ዜጎቿ በነፃነት እየኖሩ፣ በፈለጉበት ሥፍራ እየሠሩና ሀብት እያፈሩ፣ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ እየሆኑና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሲከበሩላቸው ብቻ ነው፡፡ እነሱም ለዕድገቷና ለብልፅግናዋ በሚደረገው ጥረት የሚፈለግባቸውን አገራዊ ግዴታ ሲወጡ ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት የሚወገደው በዚህ መንፈስ መመራት ሲቻል ነው፡፡ ያኔ በእርግጥም የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ይሆናል፡፡

ከታሪካዊው ድህነትና ኋላ ቀርነት መላቀቅ የሚቻለው ለትምህርት በሚሰጥ ፅኑ እምነት ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ በትምህርት ተቋማት ከሚቀስመው ዕውቀት በተጨማሪ፣ ከኅብረተሰቡ የሚማራቸው በርካታ አገር በቀል ዕውቀቶች አሉ፡፡ ትምህርት ማስተዋል ከሌለበት ከንቱ እንደሚሆነው ሁሉ፣ አገርም በማስተዋል ካልተመራች ከሚታሰበው ከፍታ ልትደርስ አትችልም፡፡ መንግሥት ወጣቱ ትውልድ እንዲያስብ፣ እንዲያሰላስልና የተሻሉ ሐሳቦችን እንዲያፈልቅ ዕድሎችን ከማመቻቸት በተጨማሪ መሠረታዊ መብቶቹን ማስከበር አለበት፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ያለ ስስት ወጣቱን ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መረዳዳት ሲኖር ለዘመናት የነገሡት ጨለምተኛ አመለካከቶች በብርሃናዊ አስተሳሰቦች ይተካሉ፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚባለው ጊዜ ያለፈበት ጎታች አመለካከት ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ይሆናል፡፡ በመርህ ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎች ሲነሱ ሳይንሳዊ ምላሽ ያገኛሉ፡፡ የታሪክ እንከኖችን እያመነዠኩ ግራ ከመጋባት ተወጥቶ አዲሱ ትውልድ የራሱን ታሪክ ይሠራል፡፡ ዘረኝነት ሥፍረ አይኖረውም፡፡ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ይመክናሉ፡፡ ዘመናዊና ተራማጅ አስተሳሰቦች በአገር በቀል ዕውቀትና ማስተዋል እየተብላሉ እናት አገርን ከከፍታው ማማ ላይ ያደርሷታል፡፡ ምኞትን ወደ ተግባር ለመለወጥ ግን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ሌብነትን፣ አምባገነንነትን፣ ክፋትንና ራዕይ አልባነትን የሚታገል ቁርጠኝነት፡፡

ኢትዮጵያችን እንድታግና እንድትበለፅግ ብቻ ሳይሆን የፍትሕና የርትዕ አገር እንድትሆን ይቅር መባባል ያስፈልጋል፡፡ በተዛነፉ የታሪክ ማስታወሻዎች ላይ ተንጠልጥሎ ቀውስ ከመፍጠር በቅን ልቦና ሆድን ሰፋ አድርጎ መነጋገርና ለአዲስ ጅማሮ መነሳት ተገቢ ነው፡፡ ከምንም ነገር በፊት መንግሥት እጁን ለይቅርታና ለምሕረት መዘርጋት አለበት፡፡ ይቅርታና ምሕረት የበጎነት መገለጫ ነው፡፡ ‹‹መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› የሚል መሪ ቃል አንግቦ ይቅር ባይነትን ማሳየት ደግሞ ታላቅነት ነው፡፡ ዜጎች በእናት አገራቸው ጉዳይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥርጊያውን ማመቻቸት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ቅሬታዎች ተወግደው በመከባበር መንፈስ መነጋገር መቻል ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ስደት በጣም እንዲቀንስ ወይም ጨርሶ እንዲጠፋ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከማንም በላይ ሕግ የማክበርና የማስከበር ትልቁ ግዴታም የእሱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአጠቃላይ ሕዝቧ እርካታ መፍጠሪያ መሆን የምትችለው የሕግ የበላይነት ኖሮ ዜጎች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው፡፡ የምታመነጨውም ሀብት በፍትሐዊነት መዳረስ ሲችል ነው፡፡ ግዴታቸውንም በሙሉ ፍላጎት የሚወጡባት ዜጎች ሲኖሯት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ከፍታው ጫፍ እንድትደርስ በሚደረገው ሁለገብ ጥረት ከሸፍጥ የፀዳና ሥርዓት ያለው የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ እርስ በርስ በጠላትነት መፈራረጅ ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና መላ ማኅበረሰቡ ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት አለባቸው፡፡ መጪው ጊዜ ብሩህ ሆኖ የኢትዮጵያን ትንሳዔ ማምጣት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ መጀመር የሚያስፈልገው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...

እኛ ኢትዮጵያውያን ከየት መጥተን ወዴት እየሄድን ነው?

በአሰፋ አደፍርስ ኢትዮጵያውያን ከየትም እንምጣ ከየት እስከ 1445 ዓ.ም. እስላማዊና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዲጂታል ቴክኖሎጂው የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር ይዋል!

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የዲጂታል ሪፎርም ሥራን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት፣ የፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ስድስት ዓመታት...

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...