- የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ
– በተጓደሉ ሚኒስትሮች ምትክ ሹመት ተሰጥቷል
የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ያዳበሩትን ተቀናጅቶ የመሥራት ልምድ፣ በመደበኛ ሥራቸውም እንደሚቀጥሉበት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሲሆኑ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን አስመልክቶ ለፓርላማው ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓም. ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ባቀረቡት ረፖርትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶ ቀሪ ሥራዎች በመደበኛ የሕግ አግባብ እንዲፈጸሙ መወሰኑን ገልጸው፣ ይህንኑም ምክር ቤቱ እንዲያወቀው ብለዋል፡፡
ቀሪ ሥራዎችን የክልል መስተዳድር የፀጥታ አካላት ሊፈጽሟቸው እንደሚችሉ፣ ከእነሱ አቅም በላይ የሆነውን ለፌዴራል መንግሥት እንዲያሳውቁ መግባባት ላይ መደረሱን አቶ ሲራጅ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የቆይታ ጊዜ የክልልና የፌዴራል የፀጥታ አካላት ያዳበሩት ተቀናጅቶ የመሥራትን ልምድ፣ በመደበኛው ፀጥታ የማስከብር ሥራ ለመናበብና ለመቀናጀት የጋራ ዕቅድ አውጥተው ማፅደቃቸውን አስረድተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን የደገፉ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በቅርቡ ሲታዩ የነበሩ አለመረጋጋቶች የፈጠሩባቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡ አንድ የምክር ቤት አባል በክልሎች ከአቅም በላይ የሆነ የፀጥታ ችግር በሚገጥምበት ጊዜ ለፌዴራል ባያሳውቁ፣ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ጠይቀዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ በቅርቡ ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የታዩት ችግሮችን መፍታት የተቻለው በክልሎች ፀጥታ ኃይል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት አራት ወራት አብዛኞቹ ሥራዎች የተከናወኑት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
‹‹ክልሎች ከአቅም በላይ ችግር ቢገጥማቸው ለፌዴራል አያሳውቁም ብለን አንገምትም፡፡ ምክንያቱም ክልሎችም ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነት ነው ያለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
በዕለቱ የፓርላማ ውሎ በቅርቡ በአምባሳደርነት በተሾሙት የትምህርት ሚኒስትርና የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚነስትር የታጩ ተተኪዎች ሹመት አግኝተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የትምህርት ሚኒስትር በነበሩት ሽፈራው ተክለ ማርያም (ዶ/ር) ምትክ የእርሳቸው ምክትል ሆነው ሲሠሩ የነበሩት ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) በትምህርት ሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡
በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር በነበሩት አቶ ካሳ ተክለብርሃን ምትክ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ ከበደ ጫኔ ተሹመዋል፡፡ በእርሳቸው ምትክ ደግሞ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የጉምሩክ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሞገስ ባልቻ በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡ አቶ ሞገስ የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡