- በተያዘው ሳምንት የማዳበሪያ ግዥ ጨረታ ይወጣል
የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ለቀጣዩ ምርት ዘመን 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ አስታወቀ፡፡ የኢትየጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገውን ማዳበሪያ ለመግዛት፣ በዚህ ሳምንት ጨረታ ለማውጣት እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡
መንግሥት በቀጣዩ 2010/11 ምርት ዘመን ጨረታ ማውጣት ሳያስፈልግ ከአምራቾች ጋር ብቻ ድርድር በማድረግ የማዳበሪያ ግዥ መፈጸም የሚፈቅድ ረቂቅ መመርያ አዘጋጅቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ነገር ግን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መመርያውን እስካሁን ባለማፅደቁ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በዚህ ዓመት የተከተለውን የግዥ ሒደት በድጋሚ ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃን አወቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተያዘው ሳምንት የመጀመርያውን ዙር ግዥ ለመፈጸም ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
‹‹የሚወጣው ጨረታ ማዳበሪያ ለሚያመርቱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ብቻ ነው፤›› በማለት፣ ኮርፖሬሽኑ በዚህ ዓመት ያለፈበትን አሠራር እንደማይደግም አቶ ብርሃን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የማዳበሪያ ግዥ የሚፈጸመው ከገዥው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ባላቸው ኢንዶውመንት ትሬዲንግ ኩባንያዎች አማካይነት በመሆኑ፣ የንግድ ሰንሰለቱም ረዥምና መንግሥትን ከፍተኛ ወጪ ሲያስወጣ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ይህንን አሠራር በማስቀረት ለአምራቾች ብቻ ጨረታ በማውጣት፣ በ2009 በጀት ዓመት 882 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ኩንታል ማዳበሪያ በዘጠኝ ቢሊዮን ብር ግዥ ፈጽሟል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ይህንን አሠራር ተከትሎ ግዥ በመፈጸም 2.6 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን አቶ ብርሃን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዓመት የክልሎች የማዳበሪያ ፍላጎት ስለጨመረ 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ እንዲፈጸም በመወሰኑ፣ ኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸሙን በማሻሻል የበለጠ ገንዘብ ለማዳን አቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን የግዥ መመርያው በወቅቱ ባለመውጣቱና ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገው ማዳበሪያ ደግሞ በወቅቱ መግባት ስላለበት ወደ ግዥ መገባቱ ተመልክቷል፡፡
በ2008/2009 ዓ.ም. በግዥ አሠራሩ ላይ ማሻሻያ በመደረጉ የተለያዩ ወጪዎች በመቀነሳቸው፣ በአንድ ኩንታል እስከ 500 ብር ድረስ ቅናሽ ተደርጎ ለአርሶ አደሩ መቅረቡ ተገልጿል፡፡
‹‹በርካታ አርሶ አደሮችን ተዘዋውሬ አነጋግሬአቸዋለሁ፡፡ በማዳበሪያ ዋጋ ላይ ቅናሽ በመደረጉ ደስተኛ መሆናቸውንና በብዛት ገዝተው መጠቀማቸውን ገልጸውልኛል፤›› ሲሉ በዓመቱ የተከናወነው የግዥ ሒደት ውጤታማ እንደነበር አቶ ብርሃን አስታውቀዋል፡፡