Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የሚያገኙ የውጭ ዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ተገደበ

የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የሚያገኙ የውጭ ዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ተገደበ

ቀን:

በኢትዮጵያ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩና አዲስ የወጣውን መመርያ የሚያሟሉ የውጭ ዜጎች፣ ቤተ እስራኤላዊያንና የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ ሊያገኙ ነው፡፡ ሆኖም በአገሪቱ ቁልፍ መሥሪያ ቤቶች እንዳይቀጠሩና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ተገድበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ ከሦስት ትውልድ በላይ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች በመመርያው መሠረት የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በማናቸውም የአገር መከላከያ፣ የአገር ደኅንነት፣ የውጭ ጉዳይና መሰል የመንግሥት ተቋማት በመደበኛነት ተቀጥረው መሥራት አይችሉም፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመሆን ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች፣ መታወቂያ የሚያገኙበት መመርያ መውጣቱን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ መመርያው የወጣው የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችን በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣውን፣ አዋጅ ቁጥር 270/1994 መሠረት በማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

መመርያ የወጣው የቻለው በአገሪቱ መደበኛ ነዋሪ የሆኑና በልዩ ሁኔታ ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የውጭ አገር ዜጎችን ለማበረታታት፣ ለመደገፍና አስተዋጽኦዋቸውን ለማጎልበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ቤተ  እስራኤላዊያን ከኢትዮጵያ ነቅለው የወጡ በመሆናቸው፣ የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያና ማስረጃ ለማግኘት የነበረውን ችግር ለመቅረፍ የአሠራር ሥርዓት በማስፈልጉ ነው፡፡ ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ የኖሩ የራስ ተፈሪያን ማኅበረሰብ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በመሆናቸው፣ ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተሰጡ መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትስስር በሕግና ሥርዓት ዕውቅና መስጠት በማስፈለጉ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተወልደው ወደ እስራኤል የተመለሱ ቤተ እስራኤላዊያን ቁጥር 150 ሺሕ እንደ ደረሱ የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹በእስራኤልና በኢትዮጵያ ግንኙነት ውስጥ እንደ ድልደይ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከኢትዮጵያ ጋር ላላቸው ትስስር የሕግ ማዕቀፍ በማስቀመጥ፣ ቁርኝቱ ቀጣይ እንዲሆን በማስፈለጉ መመርያው እንደወጣ አቶ መለስ አብራርተዋል፡፡

የራስ ተፈሪያን ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የፀረ ፋሽስት ትግል ወቅት ብዙ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የተጠቆመ ሲሆን፣ ‹‹እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ራሳቸውን የኢትዮጵያ አካል አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ መለስ ጠቁመው፣ ይህ መብት እንዲሰጣቸው ለብዙ ጊዜ ሲጠይቁ እንደነበርና ለዚህ ዕውቅና መስጠት ግድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህን ዕድል መስጠት መቻሏም ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝላት፣ ከእነዚህ መካከል የፓን አፍሪካዊ አስተሳሰብ እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

መመርያው የመኖሪያ ፈቃድ፣ የሥራ ፈቃድ፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማፍራት የግንባታ ፈቃድ፣ የኢትዮጵያ ዜግነት ከሌላቸው ራስ ተፈሪያን ማኅበረሰብ ለሚወለዱ ሕፃናት ምዝገባ፣ የሌሎች አገሮችን ፓስፖርት የያዙ የማኅበረሰብ አባላት በሕገወጥ መንገድ የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ቪዛ ሳይኖራቸው መኖር፣ የፀና ሰነድ ኖሯቸው ነገር ግን የጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ዕድሳት ሁኔታ ከክፍያ መጠን መብዛት ጋር፣ ወዘተ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

እነዚህ የውጭ ዜጎች በዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ ገብተው ለመቆየት የመግቢያ ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲኖራቸው እንደማይጠየቁና እንደ አገር ውስጥ ባለሀብት በመቆጠር ለአገር ውስጥ ባለሀብት በተፈቀዱ መብቶች እንደሚሳተፉም ቃል አቀባዩ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...