Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኤርፖርት ባለቤትነት ጉዳይ አይመለከተኝም አለ

የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኤርፖርት ባለቤትነት ጉዳይ አይመለከተኝም አለ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኤርፖርት ባለቤትነት ጉዳይ እንደማይመለከተው አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማኔጅመንትና ሠራተኞች ዓመታዊ የሠራተኞች ቀን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲያከብሩ፣ የድርጅቱን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ግልጽ ውይይት ባካሄዱበት መድረክ፣ በቅርቡ የተነገረው ኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ውህደት ጉዳይ ተነስቷል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ አቪዬሽን ቡድን ሥር እንዲተዳደሩ ከሁለት ሳምንት በፊት መወሰኑ ይታወሳል፡፡   

የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማኔጅመንትና ሠራተኞች ባካሄዱት ውይይት፣ በሠራተኞች ባለሥልጣኑ በዚህ ውሳኔ ላይ የነበረው ሚና ምን እንደነበረና ከአቪዬሽን ደኅንነት አንፃር ውህደቱን እንዴት ይመለከተዋል የሚል ጥያቄ ተሰንዝሯል፡፡

ከሠራተኛው ለቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኰሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው፣ የኤርፖርት ባለቤትነት ጉዳይ ባለሥልጣኑን እንደማይመለከት ተናግረዋል፡፡

‹‹የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባለቤት አያይም፡፡ ባለቤቱ ማንም ይሁን የተቀመጡ ደረጃዎችን ጠብቆ እየሠራ መሆኑን ነው የሚመለከተው፤›› ያሉት ኰሎኔል ወሰንየለህ፣ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅትም ቢሆን የባለቤትነት ጥያቄ እንደማያይ አስረድተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሚመለከተው አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ፣ ለሁሉም አየር መንገዶች እኩል አገልግሎት መስጠቱን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹በውሳኔው ላይ ማን ምን ሚና ነበረው የሚለው ከእኛ አቅም በላይ ነው፡፡ መንግሥት ከፈለገ ያሳትፈናል ካልፈለገ አያሳትፈንም፡፡ ይህ በበላይ አካል የተወሰነ ውሳኔ ነው፤›› ያሉት ኰሎኔል ወሰንየለህ፣ ባለሥልጣኑ ከሚያካሂደው ቁጥጥር ሥራ አንፃር የባለቤትነት ለውጥ የሚፈጥረው ችግር እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ውህደቱ ከተገለጸ በኋላ በኤርፖርት ላይ ዕርምጃ ወስደናል፡፡ ለእኛ ከበፊቱ የተለየ ምንም ነገር የለም፡፡ ወደፊትም እንቀጥላለን፡፡ ባለቤትነት ስለማናይ የቁጥጥር ሥራችንን እንደበፊቱ እንቀጥላለን፡፡ አገልግሎት ላይ መቀነስ መጨመር ካለ በሒደት የምናየው ጉዳይ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የመቆጣጠር አቅሙ ምን ያህል ነው? የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ አንድ የድርጅቱ ባለሙያ፣ ‹‹ብሔራዊ አየር መንገዱን ምን ያህል እየተቆጣጠረ ነው? የግል ኦፕሬተሮችን ምን ያህል እየመረመርናቸው ነው? ብሔራዊ አየር መንገዱ እየጠነከረ በመምጣቱ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡

ኰሎኔል ወሰንየለህ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከመቼውም በበለጠ የተሻለ የመቆጣጠር አቅም እንደገነባ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ አየር መንገዱን፣ የውጭ አየር መንገዶችንም ሆነ የግል አየር መንገዶችን በሚገባ የመቆጣጠርና የመርመር ብቃት ያላቸው ኢንስፔክተሮች መኖራቸውን ገልጸው፣ ብሔራዊ አየር መንገዱን በአግባቡ እንደሚቆጣጠሩ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ አየር መንገዱ የተቀመጡ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ደረጃዎችን ጠብቆ ካልሠራ ባለሥልጣኑ ቅጣት ጭምር እንደሚጥልበት አስረድተዋል፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የመቆጣጠር ብቃታችንን መርምሮ የብቃት ማረጋገጫ ሰጥቶናል፡፡ ምርመራውን ያለፍነው ያሉን ባለሙያዎችና አሠራራችን በሚገባ ተፈትሾ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነት ያገናዘበ የደመወዝ እርከን ማሻሻያ ተጠንቶ ተግባራዊ አለመደረጉና የተረቀቀው የአቪዬሽን ፖሊሲ ፀድቆ ሥራ ላይ አለመዋሉ እንደ ድክመት ተነስተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙ የግል አየር መንገዶች ተወካዮችም አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የኢስት አፍሪካ አቪዬሽን ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካፒቴን ሙላት ለምለምአየሁ፣ ኩባንያቸው የቻርተር በረራና አየር አምቡላንስ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ወደ ታላላቅ የአገር ልማት ፕሮጀክቶች እንደሚበሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወደ ካሉብና ሒላላ የጋዝ ፍለጋ ፕሮጀክቶች፣ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንበራለን፡፡ ለእነዚህ የቻርተር በረራዎችና የአየር አምቡላንስ በረራዎች የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ለሚሰጡን አገልግሎት ምሥጋና እናቀርባለን፡፡ በተለይ ለአየር አምቡላንስ በረራ ቅድሚያ ይሰጡናል፤›› ያሉት ካፒቴን ሙላት፣ የበረራ ትምህርት ቤታቸውን ግን ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ ኤርፖርት ተማሪዎቻችን ለማስተማር ከማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ በመንደርደሪያው ላይ ጠብቁ ተብለን ለረዥም ሰዓት ነዳጅ ለማቃጠል እንገደዳለን፡፡ ትምህርት መስጠታችን ለማቋረጥ የምንገደድበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤›› ብለዋል፡፡

በባለሥልጣኑ የአየር ናቪጌሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረአብ በአዲስ አበባ ኤርፖርት አንድ ማኮብኮብያ ብቻ መኖሩን ገልጸው፣ ሁሉም በረራዎች በዚሁ ለማስተናገድ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ አየር መንገዱ በርካታ አውሮፕላኖች ገዝቶ በማስገባት እንቅስቃሴውን በማስፋቱ ማኮብኮቢያው እንደተጨናነቀ አቶ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡ ‹‹መደበኛ የሆኑና መደበኛ ያልሆኑ በረራዎች፣ የጄኔራል አቪዬሽን በረራዎች፣ እንዲሁም ሦስት የበረራ ትምህርት ቤቶች በረራዎች የምናስተናግደው በአንድ ማኮብኮቢያ ነው፡፡ ይህን ሁሉ አቻችለን እየሠራን ነው እንጂ እናንተን ወደ ክልል ሂዱ አላልንም፤›› ያሉት አቶ ሽመልሽ፣ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ያላግባብ አንድን አውሮፕላን ያቆየ እንደሆነ በድምፅና በቪዲዮ መረጃ የተደገፈ ምርመራ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ኤርፖርት ተጨማሪ መንደርደሪያ ለመገንባትና ለጄኔራል አቪዬሽን የተለየ ኤርፖርት ለመሥራት ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሆነ፣ በባለሥልጣኑ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...