Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ የብረት ማዕድን ምርት ፈቃድ ሰጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሰቆጣ ማይኒንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የከፍተኛ ደረጃ ብረት ማዕድን ምርት ፈቃድ ሰጠ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ተሰብስቦ በማዕድን አዋጅ ቁጥር 678/2002 (እንደተሻሻለው) መሠረት፣ ለ20 ዓመታት ፀንቶ የሚቆይ የከፍተኛ ደረጃ የብረት ማዕድን ምርት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

የብረት ማዕድን ፍለጋውን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የብረት ማዕድን ምርት ፈቃዱን በፊርማቸው አፅድቀዋል፡፡

የኢትዮ-ጣሊያን ኩባንያ የሆነው ሰቆጣ ማይኒንግ በአማራ ክልል ዋግህምራ ዞን በሚገኙት ሰቆጣ፣ ዝቋላና አበርገሌ ወረዳዎች ውስጥ የከፍተኛ ምርት ማዕድን ፍለጋ ለማካሄድ እ.ኤ.አ. ማርች 18 ቀን 2013 ፈቃድ መውሰዱን የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሰቆጣ ማይኒንግ 242 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላለፉት አምስት ዓመታት ያካሄደው የብረት ፍለጋ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ከፈጀ በኋላ በመጨረሻ ውጤት ማስገኘቱ ተገልጿል፡፡

የሰቆጣ ማይኒንግ ኩባንያ ከፍተኛ ባለድርሻና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ሉቺያኖ ፌራቶሊን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ባካሄደው ፍለጋ በድምሩ 79 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብረትና 24 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የብረት ይዘት ያላቸው ማዕድናት ክምችት አግኝቷል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔር ለኩባንያው ድጋፍ ሰጥተው በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹ሰቆጣ ማይኒንግ ሄማታይት የተባለውን የብረት ዓይነት ለማምረት የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. የአዋጭነት ጥናት ሰነድ በማቅረብ የከፍተኛ ደረጃ የምርት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ኩባንያው የምርት ፈቃድ እንዲሰጠው ያቀረበው የአዋጭነት ጥናትና የምርት ማመልከቻ በሚኒስቴሩ የምርት ግምገማ ኮሚቴ ይሁንታ አግኝቷል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ሰቆጣ ማይኒንግ በማዕድን ፍለጋ ሒደት የምርት ጥራቱ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የተለያዩ ናሙናዎችን የቻይና መንግሥታዊ ተቋም ወደሆነው ሲኖ ስቲል ኢንስቲትዩት ልኮ ማስመርመሩን፣ ግኝቱም ከፍተኛ ጥራት ያለው እንደሆነ ማረጋገጡን ሚስተር ፌራቶሊን አስረድተዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ በድጋፍ ደብዳቤያቸው ላይ እንደገለጹት፣ በአዋጭነት ጥናቱ መሠረት እሴት በመጨመር ሒደት እንዲያልፍ በማድረግ 93 በመቶ የብረት ይዘት ያለው 47 ሚሊዮን ቶን ሄማታይት ብረት መኖሩ በጥናቱ መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡  

ሰቆጣ ማይኒንግ የምርት ፈቃድ በማግኘቱ በሦስት ዙሮች ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከማዕድን ብረት ለማምረት ተዘጋጅቷል፡፡

በመጀመርያው ዙር 50 ሺሕ ሜትሪክ ቶን፣ በሁለተኛው ዙር 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብረቶች ለማቅለጥ፣ እንዲሁም በሦስተኛው ዙር ዓመታዊ የማምረት አቅሙን 250 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብረት የማድረስ ዕቅድ አውጥቷል፡፡

በሁለተኛው ዙር ኩባንያው ከማዕድን አቅልጦ የሚያገኘው ብረት ላይ እሴት በመጨመር፣ ለከፍተኛ ግንባታዎች የሚውሉ የተለያዩ የብረት ዓይነቶችን እንደሚያመርት ታውቋል፡፡

ሰቆጣ ማይኒንግ ይህንን ግዙፍና በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሚሆነውን ግንባታ የሚያካሂደው፣ ከቻይናው ግዙፍ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ባለቤት ከሆነው ቤጂንግ ሲቢአርኤፍ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ጋር በሽርክና ነው፡፡ የቻይናው ኩባንያ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅስ ሲሆን፣ በሰቆጣ ማይኒንግ ኩባንያ ላይ አሥር በመቶ ድርሻ አለው፡፡

ሚስተር ፌራቶሊን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሁሉም ዙሮች ለሚካሄደው ግንባታ 410 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዟል፡፡ የፋይናንስ ምንጩም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከቻይና ኤግዚም ባንክ፣ እንዲሁም ከኩባንያዎቹ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ከወርቅና ከተወሰኑ ማዕድናት በስተቀር በከፍተኛ ደረጃ የብረት ማዕድን ፍለጋም ሆነ የምርት ፈቃድ ተሰጥቶ አያውቅም፡፡ ሚኒስቴሩ የመጀመርያውን የፍለጋ፣ የምርት ፈቃድ የሰጠው ለሰቆጣ ማይኒንግ መሆኑ ታውቋል፡፡ የብረት ማዕድን በተለይ ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ላቀደው መንግሥት ወሳኝ ቢሆንም፣ በተለይ ፍለጋው ከፍተኛ ገንዘብ ሊያስወጣ፣ ገንዘቡን ካስወጣም በኋላ ላይገኝ ስለሚችል መንግሥት ወደ ዘርፉ መግባት ሳይችል መቆየቱ ይነገራል፡፡  

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፣ ‹‹ማዕድን ፍለጋ ቁማር ነው፡፡ ሊገኝም ላይገኝም ይችላል፡፡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ እንጂ የመንግሥት መሰማራት ተመራጭ አይደለም፤›› በማለት በዚህ ዘርፍ የመንግሥትን አቋም ግልጽ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች