Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ግልጽነት በሌለበት ተዓማኒነት አይገኝም!

ግልጽነት የሌለው መንግሥት የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት አይችልም፡፡ በማንኛውም አገር የሚገኝ መንግሥት መረጃን ለሕዝብ በአግባቡ የማድረስ ግዴታ አለበት፡፡ አሠራሩ በይፋ የሚታወቅ፣ ተጠያቂነት ያለበትና አመኔታ የሚጣልበት መንግሥት ግልጽ ነው ይባላል፡፡ ግልጽነት የአንድ አገር ሕዝብ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ማድረግ የሚችልበት መርህ ነው፡፡ በእርግጥም አንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ናት የሚባለው አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽ የሆነና ተጠያቂነት ያለበት መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ መንግሥትም እንደ ተቋም የሚኖረው ሕዝብን ለማገልገል ነው፡፡ ይህ በየትም አገር የተለመደ ቋሚ ሕግ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ግን ግልጽነት የሌለው መንግሥትና በመንግሥት ላይ አመኔታ የሌለው ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውም ይህንን ይመስላል፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ የሚወሰዱት ዕርምጃዎች ደግሞ ሕዝቡን ያወዛግቡታል፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥት ሰሞኑን በሙስና የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሲያውል፣ ማንነታቸው የታወቀው ዘግይቶ ነው፡፡ ከባለሥልጣናቱ መካከል የተወሰኑትን በአምባሳደርነት ሲመድብ ምክንያቱ አይታወቅም፡፡ የሚሄዱባቸው አገሮች አልተገለጹም፡፡ በ40/60 ቤቶች ግንባታ ላይ ከመመርያው ውጪ የድፍረት ተግባር ሲፈጸም ግልጽነት ባለመኖሩ የታወቀው በመጨረሻ ነው፡፡ መመርያ ሲጣስ ተጠያቂነት የለም፡፡ ሕግ አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕግ ተጥሶ ሕዝብ እያለቀሰ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሚስጥር እየሆነ ግልጽነት ይጠፋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ ደግሞ አመኔታ ይነጥፋል፡፡

ግልጽነት የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚረዳ አሠራር ሲሆን፣ ተጠያቂነት እንደሚኖርም ማረጋገጫ ነው፡፡ በአገር ሀብት ላይ ዝርፊያ የፈጸሙም ሆኑ ሥልጣናቸውን ያላግባብ የተገለገሉ ተጠርጣሪዎች ካሉ በቁጥጥር ሥር መዋል ይኖርባቸዋል፡፡ ዕርምጃው ለምን ዘገየ ተብሎ ይጠየቅ ይሆናል እንጂ ለምን ተጠያቂነት ይኖራል መባልም የለበትም፡፡ ነገር ግን ሕዝብ በበኩሉ እነ እከሌ በቁጥጥር ሥር ዋሉ ሲባል እነ እከሌስ ብሎ ሲጠይቅ፣ ግልጽነትን የተላበሰ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው ሲባል እኮ ተጠያቂነቱም እኩል ነው ማለት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ማንም የሚገነዘበው ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነትም እንዳለ ተደንግጓል፡፡ ሥራ ላይ መዋል ሲያቅተው ግን ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህን ጊዜ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ይጠፋል፡፡ ሕዝብ ማን ምን እንደሚሠራ፣ ምን እንዳለውና ምን ዓይነት ኑሮ እንደሚመራ በደንብ ያውቃል፡፡ የተጀመረው ዕርምጃ የሚቀጥል ከሆነ በተስፋ ይጠባበቃል፡፡ መረጃም ሆነ ማስረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን የመንግሥት አሠራር በግልጽነት ላይ ይመሠረታል ማለት ነው፡፡ የተለመደው ዓይነት የዘመቻ ሥራ ውስጥ ተገብቶ ከሆነ ደግሞ ውጤቱ ተቃራኒ ይሆናል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ይኼማ ትኩረት ለማስቀየር የተጀመረ ዘመቻ ነው ተብሎ በስፋት ይወራል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ለየቅል ይነጉዳሉ፡፡

መንግሥት አሠራሩ ግልጽ መሆን ያለበት ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት፣ ሙስናን ከሥር መሠረቱ መንግሎ ለመጣል፣ አገር በጠንካራ መሠረት ላይ እንድትቆም ፣ የአገር ሰላምና መረጋጋት ዘለቄታዊ እንዲሆን፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መደላድል ለመፍጠርና ፍትሕ ለማንገሥ ነው፡፡ ግልጽነት ከሌለ ግን ከሕጋዊነት ይልቅ ሕገወጥነት ይስፋፋል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት የሙሰኞች መፈንጫ ስለሚሆኑ ሕግና ሥርዓት ማስከበር አይቻልም፡፡ በሥልጣን የሚባልጉ ሕገወጦች ሲፈነጩ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አምጥቶ የሕዝብ ኑሮን ለማሻሻል አይቻልም፡፡ ይልቁንም የአገርን ህልውና ሥጋት ውስጥ የሚከት ፈተና ያጋጥማል፡፡ ይህ ደግሞ አገርን ቀውስ ውስጥ ይከታል፡፡ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ እያደረጉ አገርን ለችግር የሚዳርጉ ክስተቶች የሚፈጠሩት፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት ሲያጣ ነው፡፡ መንግሥት አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት ኖሮት፣ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ሊያተርፉ ይገባል፡፡ በተግባር አልታይ እያለ አስቸገረ እንጂ የሥልጣኑ ባለቤት እኮ ሕዝብ ነበር፡፡ ሕዝብ መከበር ያለበት ለዚህ ነው፡፡

ሕዝብ ከመንግሥት ከሚፈልጋቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ መረጃ በአግባቡ ማግኘት ነው፡፡ መብቱም ስለሆነ፡፡ መንግሥት እጁ ውስጥ ያሉ መረጃዎችን በሙሉ መዘርገፍ አለበት ለማለት ሳይሆን፣ እንደ ሰሞኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በፍጥነት ማንነታቸውን ማወቅ አለበት፡፡ መንግሥት በቃል አቀባዩ አማካይነት በጥናት ላይ ተመሥርቶ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን እየተናገረ፣ ማንነታቸውን ለሁለት ቀናት መደበቅ ምን አስፈለገው? በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በእርስ በርስ ግንኙነት በግምት ላይ የተመሠረቱ ያልተጣሩ መረጃዎች ሲለቀቁ፣ በብዙዎች ላይ የሥነ ልቦና ጉዳት ይከሰታል፡፡ በተዛቡ መረጃዎች ሳቢያም ንፁኃን ዜጎች ይሳቀቃሉ፡፡ የ40/60 ቤቶች ዕጣ ሲወጣ ከመመርያው ውጪ ለምን ግንባታ ተካሄደ? በየትኛው ሕግ ነው እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ ድርጊት የተፈጸመው ሲባል ደግሞ ምላሹ አስደንጋጭ ነው፡፡ ሕግና ተጠያቂነት የሌለ ይመስል በሕዝብ እንዴት ይቀለዳል? ፍትሕን የሚደረምስ ተግባር ተፈጽሞ የሚያስጠይቅ ነገር የለም ማለት ምን የሚሉት ቀልድ ነው? የአምባሳደሮች ምደባ ሲከናወን የግለሰቦችን ስም ከመስማት በዘለለ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ለምን እንደተመደቡ ግልጽ አይደለም፡፡ የት እንደሚመደቡም አይነገርም፡፡ በብዙ አገሮች ባለሥልጣናት ለምን አምባሳደሮች እንደሚሆኑና ከሚመደቡባቸው አገሮች ጋር በመንግሥት ድረ ገጽ ላይ ይፋ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ለምን ሚስጥር ይሆናል? መንግሥት ምደባውን ግልጽ የማያደርገው በየትኛው ሕግ ነው? አሠራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዳለበት የደነገገው እኮ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ታዲያ ማን ያክብረው? ተግባባን?

ይህ ዘመን ቴክኖሎጂ የተራቀቀበት በመሆኑ መረጃ በብርሃን ፍጥነት ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላው ይተላለፋል፡፡ በአንድ የዓለም ጥግ የሚከናወን ድርጊት በቀጥታ ሥርጭትም ሆነ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሁሉም ቦታ በፍጥነት ይደርሳል፡፡ በዚህ ዘመን አንድ ሰው ከጎረቤቱ አልፎ ራቅ ያሉ ሥፍራዎች ያሉ ሰዎችን አኗኗር ጭምር የማወቅ ዕድሉ በጣም የሰፋ ነው፡፡ በዚህ ዘመን መረጃን ፍሪጅ ውስጥ ደብቆ ለማቀዝቀዝ መሞከር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚብስ የታወቀ ነው፡፡ እዚህ ላይ መሰመር ያለበት የአሁኑ ዘመን ትውልድ በፈጣን የመረጃ ቅብብሎሽ ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ ካሉ መደበኛ ሚዲያዎች በተጨማሪ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ፈጣንና ተከታታይነት ያላቸው መረጃዎች ይደርሱታል፡፡ የመንግሥት መረጃዎች በዘገዩ ቁጥር ለተዛቡ መረጃዎች ይጋለጣል፡፡ በዚህም ምክንያት በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ይጠፋል፡፡ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ፍትሐዊነትም ላይ ጥርጣሬ ይገባዋል፡፡ ጥያቄም ያነሳል፡፡ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሁሉንም ነገር ሚስጥራዊ የማድረግ ባህል በዚህ ዘመን እንደማይሠራ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘመን ያለፈበት ባህል የመንግሥት ሥራ ውስጥ መወሸቅ አይኖርበትም፡፡

መንግሥት አሠራሩን ግልጽ ሲያደርግ ተሿሚዎቹን ለመቆጣጠር ይረዳዋል፡፡ አሠራሩ የተሸፋፈነ ሲሆን ግን ተሿሚዎች በሥልጣን ይባልጋሉ፡፡ የአገር ሀብት ይዘርፋሉ፡፡ የሕግ የበላይነት እየተጋፉ እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ይሆኑና የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ በአለፍ ገደም በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ቢታይም፣ በየቦታው በብልሹ አሠራሮች የተዘፈቁ ሹማምንቶች የመኖራቸው ዋነኛ ምክንያት የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ነው፡፡ ዜጎች በየደረሱበት በሙሰኛ ባለሥልጣናት ሲንገላቱ፣ የአገር ሀብት በየተቋማቱ በተሰገሰጉ ሙሰኞች እየተዘረፈና እየባከነ መሆኑ በግልጽ በአደባባይ ሲቀርብ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚንዱ አሳፋሪ ድርጊቶች በግልጽ መፈጸማቸው እየታወቀና የምሬቱ ገደብ ሲገነፍል እየታየ ማድበስበስ ውስጥ ሲገባ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎ እንዲህ ዓይነት ድንገተኛ የሚባሉ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ መንግሥት የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ የዘየደው ነው ይባላል፡፡ ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር ስለሌለ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችም ሆኑ ሌሎች ተግባራት ጥርጣሬ ይፈጥራሉ፡፡ የጥርጣሬው ምክንያት ራሱ መንግሥት ሆኖ ሌሎች ላይ ማሳበብ አይቻልም፡፡ አሁንም ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ይሁኑ፡፡ ግልጽነት በሌለበት ተዓማኒነት አይገኝምና!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...