Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹እስካሁን ባለው ዕድሜዬ በትልልቅ ሆቴሎች ተዝናንቼና ማሳጅ ወስጄ አላውቅም››

‹‹እስካሁን ባለው ዕድሜዬ በትልልቅ ሆቴሎች ተዝናንቼና ማሳጅ ወስጄ አላውቅም››

ቀን:

አቶ መላኩ ፈንታ፣ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

በመዝገብ ቁጥር 141352 ሁለተኛ ክስ ጋር በተያያዘ የተከሳሽነት ቃላቸውን የሰጡት የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ ‹‹እስካሁን ባለው ዕድሜዬ ትልልቅ ሆቴሎች ተዝናንቼና ማሳጅ ወስጄ አላውቅም፤›› ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

አቶ መላኩ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ይህን የተናገሩት፣ ከቀረጥ ነፃ የገቡ የኮንስትራክሽንና የሆቴል ዕቃዎች ላልተፈቀደና ተገቢ ላልሆነ አካል ጥቅም ላይ ውለዋል? ወይስ አልዋሉም? በሚለው ላይ በተለይ ከኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ጋር በተያያዘ በተሰጠ ምስክርነት፣ ‹‹አቶ ስማቸው ከበደ ማሳጅና ጊፍት ካርድ እየሰጧቸው ይዝናኑ ነበር፤›› መባሉን በሚመለከት በሰጡት መልስ ነው፡፡

ከሆቴሉ የተባረሩ ሠራተኞች በእሳቸው ላይ የሰጡት ምስክርነት ሐሰተኛና ትክክል አለመሆኑን የተናገሩት አቶ መላኩ፣ እሳቸው በትልልቅ ሆቴሎች ይገኙ የነበረው ስብሰባ ለመክፈትና ለመዝጋት ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በተቋማቸው ሥራ አስፈጻሚዎች የተገመገሙት ለደኅንነታቸው አሥጊ ሊሆን በሚችል አንድ ቦታ እንደሚያዘወትሩ እንደነበር የተናገሩት አቶ መላኩ፣ እሱም ቅዳሜና እሑድ ዕረፍት በሚኖራቸው ጊዜ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚያዘወትሩበት ሰሜን ሆቴል አካባቢ በሚገኝ ሻንጋሪላ በሚባል አንድ ትንሽ ቤት ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሥራ ቦታቸው እንኳን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ጊዜ አግኝተው ምሣ መብላት ስለማይችሉ ከክበብ እያስመጡ ቢሯቸው ውስጥ ይመገቡ እንደነበር ጠቁመው፣ ምስክሮቹ ግን ሐሰተኛ የሆነ ምስክርነት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም. ከቀረጥ ነፃ መብት ጋር በተገናኝ የተደረገው የማጣራት ሥራ የገቢ ዕቅድን ለማሟላትና የገቡ ዕቃዎች ለታለመላቸው ዓላማ መዋል አለመዋላቸውንም ለማጣራት እንደነበር አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

በተደረገው ማጣራት ከፍተኛ ገንዘብ የተገኘው ለኮንስትራክሽን ከገቡ ብረት፣ ሲሚንቶና የተለያዩ ዕቃዎች እንደነበር የተናገሩት አቶ መላኩ፣ ከቀረጥ ነፃ የገቡት የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ምን ያህሉ ለታለመላቸው ሥራ እንደዋሉና እንዳልዋሉ ለማወቅ የኢንጂነሪንግና ተያያዥ ዕውቀቶች ያላቸው ባለሙያዎች ስለሚያስፈልግ፣ መንግሥታዊ ድርጅት የሆነውን ሕንፃና ዲዛይን ድርጅትን መጠየቃቸውን አስረድተዋል፡፡ ሕንፃና ዲዛይን ድርጅት ሲጠየቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ክፍያ በመጠየቁ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በጀት እንዲመድብላቸው ሲጠየቅ ‹‹በጀት የለኝም›› በማለቱ፣ አቅጣጫቸውን ወደ ሆቴሎች ማዞራቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የባለሥልጣኑ የዳሰሳ ቡድን አባላት ናሙና ሲወስዱ አንዳንዶቹ በነፃ የገቡ የሆቴል ዕቃዎች ተሰባብረው፣ አንዳንዶቹ መጋዘን ውስጥ ተቀምጠውና አንዳንዶቹ በሆቴሎቹ የሌሉ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

የመሥሪያ ቤቱ የዳሰሳ ቡድን ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕዎች 95 በመቶ የሚሆኑት ሆቴሎች በተመሳሳይ ሁኔታ እንደተጠቀሙባቸው፣ በአንድ ላይ (በጥቅል) ዕርምጃ ቢወሰድ በፖለቲካው፣ በኢንቨስትመንቱና በታክስ መሠረቱ (ቤዝ) ላይ መናጋት ስለሚያመጣ መጀመሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመነጋገር ውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ከአሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ ከሆቴሎች ማኅበርና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ኦዲት አስደርገው በፈቃደኝነት እንዲከፍሉ፣ የማይከፍሉ ከሆነ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተስማምተው መለያየታቸውንም አስረድተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሆቴሎች ሲከፍሉ ባልከፈሉት ላይ ምርመራ መጀመራቸውን የጠቆሙት አቶ መላኩ፣ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ከተወሰነበት ላይ አምስት ሚሊዮን ብር ከፍሎ ስለነበር እሱ ላይ ምርምራ አለመጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ምርመራ ቢጀምርም የቀረበለት መዝገብ በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 98 መሠረት ለሦስተኛ ወገን መተላለፉን ወይም ላልታለመለት ዓላማ የዋለ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳልቻለ በመግለጽ መዝገቡን መዝጋቱን አቶ መላኩ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ እሳቸውም የሚያውቁት ይኼንኑ ብቻ መሆኑን አክለዋል፡፡

ነገር ግን በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ላይ ጉዳዩ ለእሳቸው ተመርቶ ‹‹ይታይላቸው›› ብለው እንደመሩ አቶ እሸቱ ወልደ ሰማያት (የቀድሞ የባለሥልጣኑ ዓቃቤ ሕግ ዋና ዳይሬክተር የነበሩ) የተባሉ የዓቃቤ ሕግ ምስክር፣ ሐሰተኛ ምስክርነት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም አድራሻ  ተደርጎ ለእሳቸው የተጻፈላቸው ቢሆንም፣ የመሩት በወቅቱ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮሐንስ መለሰና አቶ ነብዩ ሳሙኤል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እነሱም ቢሆኑ የመሩት ‹‹በሕጉ መሠረት ይታይላቸው›› ብለው መሆኑን አክለዋል፡፡ ‹‹እኔ አልመራሁም፡፡ ግን እኔ እንደ መራሁ ተደርጎ የተሰጠውን የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤቱ ሳያረጋግጥ ብይን ሰጥቶብኛል፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ከኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ጋር በተያያዘ የተሰጠባቸው ብይን ትክክል አለመሆኑንና ሆቴሉም ‹‹የተጣለብኝ ግብር ትክክል አይደለም፤›› ብሎ ለከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር አስታውሰው፣ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የመጀመሪያውም ሆነ ሁለተኛው ቆጠራ (ከቀረጥ ነፃ ገቢ የተባሉት ዕቃዎች ቆጠራ) ትክክል አለመሆኑን ገልጾ ውድቅ እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወንጀል ስላልሆነ በአስተዳደር በኩል ማለቅ ስላለበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ዕቃዎች ጋር የሚገናኙ ነገሮች ወንጀል እንዳልሆኑና በአዋጅም ወንጀልነቱ ቀሪ እንደሆነ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም ውሳኔ እንደሰጠበት አቶ መላኩ ተናግረው፣ የተከሳሽነት ቃላቸውን ሰጥተው ጨርሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...