ሐሙስ ነሐሴ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የቀረቡ ክሶችን፣ የተለመደ የኮንግረስ አባል ምንም ለውጥ ሊያመጡ የማይችሉ ክሶች ናቸው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጣጣለ፡፡
የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታና አጠቃላይ አስተዳደር ከአሜሪካ ጋር ለመቃኘት ያለመ ረቂቅ ሕግ፣ በሕግ አርቃቂው (ኮንግረስ) የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ፊት በኒው ጀርሲው ኮንግረስ አባል ክሪስ ስሚዝ ቀርቦ ድምፅ እንዲሰጥበት በዕለቱ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡
ረቂቅ ሕጉ የኢትዮጵያ መንግሥት የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው ነው ያላቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ያስቀመጠ ሲሆን፣ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ እንዲጣልበት ሐሳብ አቅርቧል፡፡
ይኼንኑ ረቂቅ ሕግ አስመልክቶ ሪፖርተር ያናገራቸው የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በሰጡት ምላሽ፣ የኮንግረስ አባሉ ያቀረቡት ረቂቅ የአንድ የኮንግረስ አባል የዕለት ተዕለት ሥራ ዓይነት ነው ብለዋል፡፡ ሰውየው ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ያቀረቡትና ምንም ውጤት ያላመጣ ዓይነት ክስ እንደሆነ ገልጸው፣ በመንግሥት ላይም የተለየ ጫና ያመጣል ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶችን ይዞታና አጠቃላይ አስተዳደር ከአሜሪካ ፖሊሲ ጋር ለመቃኘት ያለመ ረቂቅ ሕግ፣ ባለፈው ሐሙስ በሕግ አርቃቂው የኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ፊት ቀርቦ ድምፅ እንዲሰጥበት መታሰቡን የኮንግረስ አባሉ ገልጸዋል፡፡
ለኮሚቴው ከቀረቡት ዘጠኝ የሕግ ረቂቆች አንዱ የሆነው ውሳኔ 128 የኒው ጀርሲው እንደራሴ ክሪስ ስሚዝና ከሃምሣ በላይ የኮንግረስ አባላት እንደደገፉት፣ ከአሜሪካ የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ነገር ግን ኮንግረሱ ያሉት አባላት 47 መሆኑን በመጥቀስ አቶ መለሰ ረቂቅ ሕጉን አጣጥለውታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ኮሚቴው የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስ ስሚዝ፣ “ኢትዮጵያ ጠቃሚ ወዳጅና ለዓለም አቀፍ ሰላም አጋር ብትሆንም፣ እየቀጠሉ ያሉት የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም፤” ብለዋል።
“በፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ የዘፈቀደ እስራቶች፣ ግድያዎችና የማሰቃየት አድራጎቶች፣ በመናገርና በመደራጀት ነፃነቶች ላይ እየተጣሉ ያሉ ዕገዳዎች፣ በተቃዋሚዎችና በጋዜጠኞች ላይ የሚካሄዱ በፖለቲካ የሚመሩ የፍርድ ሒደቶች፣ የማዋከብና የማሸማቀቅ ድርጊቶችና ተመሳሳይ ጉዳዮችን በሪፖርቱ ስታነቡ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የቀረቡ ክሶቹ ናቸው፤” ብለዋል የኮንግረስ አባሉ።
‹‹ከዚህ በፊትም ፀረ መንግሥት አቋም ሲያራምዱ እንደነበር ይታወቃል፤›› ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ እስካሁን ረቂቅ ሕጉ የአንድ አባል (የኮንግረስ) ድጋፍ እንዳገኘ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ኮንግረሱ ፊት ረቂቅ ሕጉ ቢቀርብ እንኳ ውድቅ እንደሚደረግና ‹‹ከመደርደሪያ እንደማያልፍ›› አክለዋል፡፡
በቅርቡ የአሜሪካ ኮንግረስ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎችና የፀጥታ ጉዳይ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ውይይት መደረጉን ቃል አቀባዩ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡
‹‹ውይይቱ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ እንደሚገኝ የተረጋጠበት ነው፤›› በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) መሳተፋቸውን በመጥቀስ፣ የኮንግረስ አባሉ ክሶችን አጣጥለዋል፡፡