Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የፍትሕ ሥርዓት እስካለ ድረስ ሁሉም ሰው ፍትሕ እንደሚያገኝ አምናለሁ››

‹‹የፍትሕ ሥርዓት እስካለ ድረስ ሁሉም ሰው ፍትሕ እንደሚያገኝ አምናለሁ››

ቀን:

ያለመከሰስ መብታቸውን ያጡት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በቆዩባቸው ዘጠኝ ዓመታት ሕዝብና መንግሥትን ለመበደል የሠሩትና ህሊናቸውን የሚቆረቁር ድርጊት አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ የፍትሕ ሥርዓት እስካለ ድረስ ፍትሕ እንደሚገኝ  ተናገሩ፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ጉጆ ይህንን የተናገሩት፣ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ያለመያዝና ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጠየቀበት ወቅት ነው፡፡

ሐምሌ 28 ቀን በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ከዕረፍት ተመልሶ የተሰበሰበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአባሉን የአቶ ዓለማየሁ ጉጆ ያለመያዝ መብት እንዲያነሳ የጠየቁት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ናቸው፡፡ የፓርላማ አባሉ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታነታቸው በጥቅም ትስስር ሳቢያ ያለጨረታ ለአንድ ኩባንያ ፕሮጀክቶችን አሳልፈው ሰጥተዋል ተብለው በመጠርጠራቸው፣ ያለመያዝና ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት የተደረገው የግዥ እንቅስቃሴ የግዥ ኤጀንሲን ይሁንታ ያላገኘ፣ ያለምንም ዓይነት ጨረታ ለአንድ የውጭ ኩባንያ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ውል እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡ የተደረገው እንቅስቃሴ ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ የጥቅም ትስስር ያለበት በመሆኑ፣ ምርመራውን ለማጣራት ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ተጠይቋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያለጨረታ መሰጠቱ ብቻ ሳይሆን ሥራውን ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቀ ተደርጎ ሙሉ ክፍያ መከፈሉ፣ በዚህም የጥቅም ግንኙነት (ትስስር) እንዳለ የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ለዚሁ ተቋም ከቀረጥ ነፃ ስምንት ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ተደርጎ ውሉ ከተቋረጠና ካለቀ በኋላ ገና ያልተጠናቀቀ እንደሆነ፣ እንዲሁም ለአሥራ ስምንት ወራት እንደሚራዘም በመግለጽ ከቀረጥ ነፃ የገቡት ተሽከርካሪዎች ለባንክ ብድር መያዣነት እንዲውሉ በመፍቀዳቸው የተነሳ፣ የጥቅም ትስስር መኖሩን እንደሚያሳይ አቶ ጌታቸው ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡

ሥራው ሳይጠናቀቅ 20 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ከተከፈለ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ እንዲሰጠው በማድረግ የሚኒስቴሩን ሰባተኛና ስምንተኛ ፎቅ እንዲያድስ፣ የ2.2 ሚሊዮን ዶላር ውል ለዚህ ተቋም መሰጠቱን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪው በሚያስገነቧቸው የቤት ግንባታዎች እስከ 500 ሺሕ ብር የሚደርስ በጉርሻ ወይም በጉቦ መልክ መቀበላቸውን የሚያስረዱ መረጃዎች በመኖራቸው ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሌላ የአራት ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ለአንድ የአሜሪካ ኩባንያ በመስጠት በኩባንያው መሪ ግለሰብ ጋባዥነት ለአንድ ወር ያህል ከመላ ቤተሰባቸው ጋር አሜሪካን እንዲጎበኙ መደረጉን በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ወጪያቸው ተሸፍኖ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ መደረጉ የጥቅም ትስስር መኖሩን እንደሚያሳይ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

በምክር ቤቱ መቀመጫ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጀርባ የሚቀመጡት አቶ ዓለማየሁ በተነሳባቸው ጉዳይ ምላሽ የመስጠት ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡

‹‹መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት አደንቃለሁ፤›› በማለት የጀመሩት አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹እውነቱ እንዲወጣ የተባለውን ዕርምጃ (ያለመያዝና ያለመከሰስ መብታቸው የመነሳቱን ጉዳይ) እደግፋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ባገለገልኩባቸው ዘጠኝ ዓመታት ሕዝብና መንግሥትን ለመበደል የሠራሁት ሥራ ህሊናዬን የሚቆረቁረኝ የለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የቀረበባቸው ጉዳይ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መድረክ መጀመሪያ ቢታይ ይመርጡ እንደነበር፣ ይህ መሆኑም የተፋጠነ ፍትሕን ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሕግና የፍትሕ ሥርዓት እስካለ ድረስ ሁሉም ሰው ፍትሕ እንደሚያገኝ አምናለሁ፡፡ ሥርዓታችንም ፍትሕ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ግን የእኔ እምነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተጠረጠሩበት ወንጀል ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ፓርላማው ድምፅ በሰጠበት ወቅትም አቶ ዓለማየሁ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ