Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየተቦረቦረው የአንድ አገር ልጅነት በአግባቡ መታነፅ የሚችለው ዴሞክራሲን መገንባት ከሰመረልን ብቻ ነው

የተቦረቦረው የአንድ አገር ልጅነት በአግባቡ መታነፅ የሚችለው ዴሞክራሲን መገንባት ከሰመረልን ብቻ ነው

ቀን:

 በታደሰ ሻንቆ

እህል በወፍጮ እንደሚከካ፣ እንጨት በመላጊያ እንደሚላግና እንደሚፈቀፈቅ የሰው ልጅም እንደዚህ ሊደረግ ይችላል፡፡ የሰሜን ኮሪያ አገዛዝ ዜጎቹን ሳይመካከሩ ተመሳሳይ ኦፊሴላዊ ባህርይ እንዲይዙ (ሳይስቁ የሚስቁ፣ ሳያለቅሱ እንባ የሚያወጡ) አድርጎ ፈቅፍቋቸዋል፣ ከክቷቸዋል፡፡ ምንተፍረት የለሽ ማናለብኝነትና ብልጣብልጥነት፣ የተበለጠለትን ወገን የኩርፊያ – የብግነት – የጥላቻ – የቂም ማናፈሪያ አድርጎ ይፈቀፍቀዋል፣ አመል ያስቀይራል፣ የግንባር እጥፋት ያበዛል፡፡ አጋጣሚ ጠብቆ ወፈፍ እያደረገና አዕምሮን ሚዛን እያሳተ ያላሰቡትን ያሠራል፡፡

በተለያዩ አባል ድርጅቶቹ አማካይነት መግዛትን የሞት ሽረት፣ በሌሎች ቡድኖች መተካትን የልማትና የጥፋት ጉዳይ አድርጎ 26 ዓመታት የቀጠለው የኢሕአዴግ ገዥነት ብዙ ነገር ያለማውን ያህል አገሪቱን ወደ መበታተንና ወደ መባላት እያስጠጉ ያሉ የግንኙነትና የአመለካከት ብልሽቶች እየበረቱና እየሰፉ እንዲሄዱ አነሰ ቢባል ሰበብ ሆኗል፡፡ ጥቂት ነገሮችን እንጥቀስ፡፡ ሕወሓትን የሁሉ ነገር ማመካኛ አድርጎ የማየትና የመፍረድ ሚዛን የለሽነት ለመስፋፋት ችሏል፡፡ ብአዴን በሚገዛው አማራ ክልል ውስጥ ተፈጽሟል ለተባለ የማኅበራዊ አስተዳደር ጥፋት ብአዴንን ተጠያቂ ማድረግ ሲገባ፣ ሕወሓትንና ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ተጠያቂ ለማድረግ ሲለፋ የሰማንበት አጋጣሚ (ዶክተሩ ለዓለም ጤና ድርጀት መሪነት በተወዳደረበት ወቅት) አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የ26 ዓመታት ገዢነት በሁሉም ሥፍራ ዜጎች እኩል የሚከበሩበትና ባለመብት የሆኑበት ግንኙነት ሊረጋገጥ ባለመቻሉ፣ እንዲያውም “የአማራ ትምክህት”ን እንደ ዳዊት መድገም፣ ጎሰኛ የሹም ሌቦችና በዳዮች ሕዝብን እያደናገሩ የሚያመልጡበት ዘዴ ተደርጎ ሲሠራበት መቆየቱ፣ እስከ ዛሬ የአገር አንድነት ጠበቃ አድርጎ ራሱን የሚቆጥር ይባል በነበረው አማራነት ውስጥ፣ አማራ የብሔረሰቦች በዳይ ሆኖ ባልተንፈራጠጠበት ሁኔታ ውስጥ እንደ ማሪያም ጠላት መነዝነዙ በምን ምክንያት ነው የሚል መመረርና ከዚህ ሁሉ ለብቻ መሆንስ አለ አይደል የሚል ማቅማማት ተፈጥሯል፡፡ ይህንኑ የሚያትቱ መጻሕፍት ለማየትም በቅተናል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እነዚህ ሊወሱ ከሚችሉት ችግሮች ሁሉ በላይ የኢትዮጵያን መቀጠል ወይም በማያባራ የእርስ በርስ ፍጅት የመጥፋት ዕጣን የሚወስን ትልቅ ጣጣ የሚመጣው ደግሞ ከኦሮሚያ ውስጥ ነው፡፡ ይህም የኦሮሚያ ካርታ ትልቅ ስለሆነ ወይም የኦሮሞ ሕዝብ በቁጥር ቀዳሚ ስለሆነ አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ ኦሕዴድ የ26 ዓመታት ገዢነት ከነፍጠኛ የእጅ አዙር ገዢነት ተላቀናል የሚል እምነት ማስፈን ስላልተሳካለት፣ ጭራሽ ወደ ደጅ ማየት ከጭፍን ጥላቻ ጋር አገርሽቶ ወጣቱን እየመዘመዘ ያለበት ሁኔታ ስላለ ነው፡፡ እዚህም እዚያም በተበራከቱት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚደረገው አካባቢ ዘለል ምደባ እንኳ ትርጉም ያለው ማኅበራዊ መላላስ አላስገኘም፡፡ ከተለያየ ብሔረሰብ በመጡ ተማሪዎች መሀል ያለው ግንኙነት በቅዝቃዜና በመፈራራት የተቆራመደ መሆኑ፣ በትንሽ ሰበብ አምባጓሮ ሊነሳ መቻሉና በየመፀዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ የሚታየው ፖለቲካ ተብዬ መዘላለፍ የዚሁ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የአገዛዙ የድክመት ፍሬ ብቻ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከቀረው ሕዝብ ትግል ጋር እንዳይዋሀድ ሲያወላክፍ የኖረው የኦነጋዊ ፅንፈኛ ብሔረተኝነትም ፍሬ ነው፣ የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ትግል ሰንካላነትና ለፈስፋሳነትም ድርሻ አበርክቷል፡፡

ይህን ችግር በማስወገድና የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም በማሳካት ረገድ ወደ አዳማ ዞሮ የነበረው ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ መመለስ አንዲት ቅንጣት እንዳላዋጣ ሁሉ ዛሬም ከ2008 እና 2009 ዓ.ም. አስደንጋጭ ቅዋሜ ወዲህ፣ ከአዲስ አበባ አቀማመጥ ጋር ለተያያዘ የኦሮሚያ “ልዩ ጥቅም” መልስ መስጠትን ተመርኩዞ በኢንተርኔት ተረጭቶ የነበረው “የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለው ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የጥናት ሰነድ መጋቢት 2009 ዓ.ም.” የሚል ጽሑፍም ችግር ለመፍታት የሚበጅ አይደለም፡፡ የጥናት ሰነድ ተብዬው ከመንግሥት በኩል ከወጣው ረቂቅ ጋር የተወሰነ ተገናዛቢነት ስላለው፣ በኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ ውስጥ ዛሬም ችግር ፈጣሪ የሆነውን ኦነጋዊ የአዕምሮ ሙሽት “ሰነዱ” የሚጋራ እንዲያውም በኦነጋዊነት ኦነግን ለማስናቅ የለፋ በመሆኑ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅሜ ብሎ ሊታገልላቸው መንግሥትም ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮችን አንጋግቼ ለኦሮሞ ሕዝብ ተብከንካኝነቴን አስመሰክራለሁ ሲል ጭራሽ የኦሮሞን ሕዝብ በምን ልዘባነን ባይ ያስመሰለ፣ ችግር ከማቅለል ይልቅ ይብስ መከፋፈልና ግጭት የሚጣራ፣ በዚህም ለፀረ ዴሞክራሲ ገዢነት ዕድሜ የሚቀጥል ወይም ተባልቶ መጥፋትን የሚለማመን በመሆኑ እሱው ላይ እናተኩራለን፡፡

  1. በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) የተቀመጠው አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሀል ከመገኘቱ ጋር በተያያዘ “ያለው ልዩ ጥቅም” የተባለለት የአገልግሎት አቅርቦትን ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን፣ እንዲሁም ኦሮሚያንና አዲስ አበባን “የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን” በደፈናው የሚመለከት ነው፡፡ የኦሮሚያ ሕዝብ ጥቅም መሐንዲስነት አይቅረኝ ባለው “ሰነድ” ውስጥ ግን በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በኢኮኖሚና በአስተዳደር ልዩ ጥቅም ሊባል የሚችል ነገር በመብራት እየተፈለገ የተደቀደቀበት ነው፡፡ ኦሮሚኛ የፌዴራል ቋንቋ እንዲደረግ፣ በፊንፊኔ ምክር ቤቶች ውስጥ በየደረጃው 30 በመቶ መቀመጫ ለኦሮሞ እንዲሆን፣ ከንቲባ በኦሮሞ ተወላጆች ጉባዔ አቅራቢነት ከኦሮሞ እንዲመረጥ፣ በአዲስ አበባ የሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ ኦሮሚያ የተወሰነ መብት እንዲኖረው፣ ኦሮሚያ ውስጥ ወንጀል የሠሩ ሰዎችን ከአዲስ አበባ በመያዝ ረገድ የኦሮሚያ አስተዳደር ሃይ ባይ እንዳይኖርበት፣ ፊንፊኔ “ኦሮሞዎች ይኖሩባት የነበረች ጥንታዊ መሬታቸው እንደነበረችና በወረራና በኃይል ተገፍተው ወደ ዳር በመገፋታቸው ቁጥራቸው እየተመናመነ መሄዱንና ወደ አናሳነት መቀየራቸውን  ሕዝቡ እንዲያውቅና ዕውቅና እንዲሰጥ”፣ ይኸውም በመጻሕፍትና በከተማው ላይ እንዲንፀባረቅ፣ ወዘተ ወዘተ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ሁሉ በአንቀጽ 49(5) ውስጥ በሠፈረው የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና “የሚያስተሳስሩ የአስተዳደር ጉዳዮች” ውስጥ ምን ያህልና እንደምን እንደሚካተት መፍረድ አይከብድም፡፡

በአንቀጽ 49(5) ሥር የሚመጡ ተብለው ሊታሰቡ የሚችሉት ጥቅሞችም ቢሆኑ የግድ ከሌሎች የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ጋር መጣጣምን ይሻሉ፡፡ ኢትዮጵያን የአገሮች ፌዴራላዊ ኅብረት አድርጎ ለመምታታትና ለማምታታት የሚመቹ ሐረጎች ሕገ መንግሥቱ ከመግቢያ ጀምሮ የያዘ ቢሆንም፣ ክልሎች ፌዴራላዊ የአስተዳደር አካላት መሆናቸውና የአገሪቱ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶች ሁሉ የመላ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ሀብት መሆናቸውን የተለያዩ አንቀጾች በድምር ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ አበባ ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ለፌዴራሉ መንግሥት ተጠሪና ርዕሰ-ከተማ ከመሆን ጋር ተጎዳኝቶ በአንቀጽ 49 ውስጥ መቀመጡም፣ ከተማዋ የአዲስ አበባ ሕዝብ የራስ በራስ መተዳደሪያ ሥፍራ ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፌዴራላዊ የሥልጣን ማዕከል ስለሆነችም ነው፡፡ ከዚህና ከሕገ መንግሥቱ ተገናዛቢ አንቀጾች አኳያ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ተራክቧዊ ጥቅሞች የሁለት ወገን ናቸው፡፡ የፌዴራል ዋና ከተማዋ የሕዝብ ብዛት የሚፈጥረው የገበያ ዕድል፣ ከኢትዮጵያም የአፍሪካ መዲና ለመሆን የሚደረገው የልማት ግስጋሴ የሚያመጣው ከአዲስ አበባ እንደ ጮራ የሚሠራጭ መሠረተ ልማት፣ የሙያና የጥበብ ክምችት ለኦሮሚያ የቅርብ ጥቅም ነው፡፡ የዙሪያው ኦሮሚያም የተፈጥሮ፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ልማት የአዲስ አበባ የቅርብ ጥቅም ነው፡፡

አንቀጽ 49 ባይኖርም ኖሮ ኢኮኖሚያዊና ፀጥታ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ የአንዱ በሌላው መገፋትና መጎዳት ሳይከተል፣ የአስተዳደር መደበላለቅና ግጭትም ሳይፈጠር አስማምቶ ማከናወን የማይቀር ነበር፡፡ ከአገራዊ ህልውና የሚመነጨውና በሕገ መንግሥቱ የታወቀው የጋራ ባለሀብትነት፣ ዕድገትም የሚሻው ተደጋጋፊነት እያንዳንዱን ክልል ደሴት ለመሆን አይፈቅድለትም፡፡ አንዱ ክልል ከክልሉ የሚመነጩና የሚሻገሩ ወንዞችን አግዶ የራሱ ብቻ ማድረግ እንደማይችል ሁሉ አዲስ አበባም አትችልም፡፡ ወንዞችን ባታግድም በደረቅና በፍሳሽ ቆሻሻዎች እየመረዙ መላክም ለማንም መብት አይደለም፡፡ በክልላዊ አስተዳደር ውስጥ ያለ ተፈጥሯዊ ፀጋን አልምቶ መሠረታዊ ፍላጎትን ለማሟላት ሳይጣጣሩ፣ በአጎራባች ክልል ላይ ሐሳብን መጣል (ለምሳሌ ወንዞችንና የከርሰ ምድር ውኃን ለብከላ ትቶ ንፁህ የመጠጥ ውኃን ከወሰንተኛ አስተዳደር መሻት) መብት አይደለም፡፡

አንዱ ክልል ተጣጥሮም ያነሰውን “ተፈጥሯዊ” ሀብት ሌላው የተረፈው ወሰንተኛ ክልል በዘፈቀደ ሊነፍገው አይችልም፡፡ በአንድ አገር ልጅነት የተሳሰረ ህልውናቸው በጋራ አልምቶ ለጋራ ጥቅም ወደ ማዋል ይወስዳቸዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 96 እስከ 98 ድረስ እንደሚነግረንም እያንዳንዱ ክልል በየፊናው የሚያለማቸው/የሚያስለማቸውና ገቢ የሚሰበስብባቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የፌዴራል መንሥትም የሚያለማቸውና ገቢ የሚሰበስብባቸው (ሰብስቦም ለአገራዊ የጋራ ሥራዎች/ጥቅሞች ክልሎችን ለማገዝ የሚያውልባቸው) ነገሮች አሉ፡፡ የክልልና የፌዴራል መንግሥታትም በአንድ ላይ የሚያለሟቸውና ገቢ የሚሰበስቡባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የእነዚህ ሁሉ መፍቺያና ማግባቢያ ደግሞ ፍትሐዊነትና ተገቢነት ነው፡፡ ስለአጠቃላይ ነገሮች ይህን ያህል ካልን ወደ አነሳነው “ሰነድ” እንመለስና በዝርዝር ቀጭ ቀጭ ማድረግ ውስጥ ሳንገባ ዋና ዋናዎቹን እንነካካ፡፡

2. ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የኦሮሞዎች ጥንታዊ መሬታቸው ባይነት ታሪካዊ እውነትን ይናገራል? “ጥንታዊ መሬታቸው” ሲባል መቼውንም ለማለት ከሆነ ሐሰት ነው፡፡ መገፋት በኦሮሞ ላይ የተካሄደ የአንድ ወገን “ተጠቂነት” ተደርጎ ከታየም ይህም ሐሰት ነው፡፡ የ16ኛው ክፍለ ዘመን ኦሮሞ አጥለቅላቂ እንቅስቃሴ በድፍኑ ሁለቱንም አስተሳሰቦች ፉርሽ ያደርጋቸዋል፡፡ የዚያን ዘመኑ እንቅስቃሴ ውጦሽና መገፋት ስላለማስከተሉ ማሳመን የሚቻለው በኦሮሞ የተጥለቀለቁት ሥፍራዎች ሁሉ ባዶ የነበሩ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ ይህ መከራከሪያ የተመዘዘው ከ16ኛው ክፍለ ዘመን የአሮሞ እንቅስቃሴ በፊት በመካከለኛው ኢትዮጵያ ኦሮሞ አልነበረም ብሎ በማሰብ አይደለም፡፡ እንኳን በመካከለኛው ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያም ውስጥ የኦሮሞን ጥንታዊ ነዋሪነት ማንም ቢሆን የፈለገውን ያህል “ማስረጃ” ቢደረድር ፉርሽ ማድረግ አይችልም፡፡ ይህንን ደፍሮ ለመናገር ሥነ ልሳናዊ ማስረጃዎች ብቻቸውን ያበቁናል፡፡ ከግዕዝ በስተቀር በኢትዮጵያ ሴም ቋንቋዎች ውስጥ የምናገኛቸው የኩሽ ቋንቋ ባህርያት፣ ዛሬ ሴም በምንላቸው ቋንቋዎች የጀርባ ታሪክ ውስጥ ቢያንስ የኩሽና የሴም ቋንቋዎች ተራክቦ እንደነበር ያረጋግጡልናልና፡፡

በአገራችን የብሔረሰብ ምንነት ግንዛቤ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ብሔረሰብነትን ‹ዘርነት› አድርጎ የመረዳት ነው፡፡ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ ጉራጌነት፣ ወዘተ ወዘተ ማኅበረሰቦች እንጂ ዘሮች አይደሉም፡፡ በመወለድ (በደም) አይተላለፍም፡፡ በማኅበራዊ ማህፀን ውስጥ በየቋንቋዎቹና በየባህሎቹ በመቀረፅ የሚገኙ ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ማህፀኖች ውስጥ ሁሌም መጠኑ የተለያየ የጥንቅር መረበሽ (የ‹ባዕድ› አባል መታከል የነባር አባል ወደ ሌላ መሄድ) አያጣቸውም፡፡ ይህ ደግሞ እስከ መገፋፋት እስከ መዋዋጥ ድረስ ሊበረታ ይችላል፡፡ መደባለቅ ለየትኞቹም ብሔረሰቦች ባዕድ ያልሆነና ማስቀረት የማይችሉት ባህርይና ሒደት ነው፡፡ ብሔረሰቦች የሚሸመኑት በዚሁ ሒደት አማካይነት ነው፣ ማለትም የሚመነምኑት ወደ ሌሎች እየተመነዘሩ እንደሆነ ሁሉ፣ የሚገዝፉትም በቋንቋና በባህላቸው የሚቀርፁትን እያባዙና ሌላውን እየዋጡ ነው፡፡ እነዚህን ሒደቶች ማሠልጠን (የኃይልና የበደል ገጽታቸውን መቀነስ) እንችል እንደሆነ እንጂ፣ ሒደቶቹን ማስቆም አንችልም፣ ዛሬም ነገም ይቀጥላሉ፡፡ በአገራችን ኢንዱስትሪያዊ – ከተሜ ኅብረተሰብ እየጎለበተ በሄደ መጠን የብሔረሰቦቻችን “ንፁህነት”ና “ቁጥር” እየሳሳ ውጥንቅጥነትና ኅብርነት እየበዛ መሄዱ በአዲስ አበባም በየትም የማይቀር ነው፡፡

የዚህን ዝንባሌ እውነትነት ከተረዳን መዛነቅና መገፋፋት ለኦሮሞ ብሔረሰብ ባዕድ እንዳልሆነ፣ በአንድ ሥፍራ መኖርም ዘለዓለማዊ እንዳልሆነ ከመስማማት ጋር በአንድ የታሪክ ወቅት ዛሬ አዲስ አበባ በተባለው ሥፍራ የአሮሞ ማኅበረሰብ ተንጣሎ እንደነበር መቀበል ከቻልን፣ በሌላ የታሪክ ሁኔታ ደግሞ እዚሁ ሥፍራ ላይ የተፈጠረውንና እየተፈጠረ ያለውን የውጥንቅጥ ሕዝብ ባለመብትነት ስለምን መቀበል ይቸግረናል? ኦሮሞ ሌሎችን እየጨፈለቀ ዳብሮና ጎልብቶ ግዙፍ ነዋሪ ለመሆን የበቃበትን ዘመን ለአዲስ አበባ ባለቤትነት የመብት መብለጫ፣ ለዛሬው ውጥንቅጥ የከተማው ሕዝብ ደግሞ መብት ማሳነሻ (በታሪክ ዕዳነት መቆጠሪያ) ማድረግ እንደምን ተገቢ ይሆናል? ከምኒልክ በፊት የነበረው ታሪክ ምንም ሆነ ምን፣ ከዚያ በኋላ የተፈጠረውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባ ሕዝብ ህልውና አይደመስስም፡፡

  1. በአዲስ አበባ ሕዝብ ጥንቅር ጉዞ ውስጥ የታየውን የኦሮሞ ቁጥር መሳሳት “በወረራና በኃይል ወደ ዳር የተገፋና የተመናመነ” የሚል ቀላል ማጠቃለያ እውነተኛውን ሒደት ለመግለጽ አይመጥንም፡፡ በወረራም በሰላምም አካባቢዎችን እየሰለቀጡ ሰፊ አገር የመፍጠር የረዥም ዘመን ጉዞ ውስጥ አንድ የመደምደሚያ ምዕራፍ የሆነው የምኒልክ ጠቅላይነት እጅግ መራራ ነበር፡፡ ኦሮሞንም ሆነ ሌሎች ደቡባዊ ሕዝቦችን ወደ ጭሰኝነት ቀይሯል፣ በባርነት ነድቷል፡፡ ይህንን ሲያስተውሉ ክንዋኔውን ባሳካውና በየደረጃው ተጠቃሚም በነበረው “በአማራነት” ስም በተለበጠው ጦረኛ ኃይል ጥንቅር ውስጥ የተበላለጠም ቢሆን ብሔረሰባዊ ቅይጥነት እንደነበር፣ በዚህ ቅይጥ ውስጥ ከመኳንንትነት/ከጦር መሪነት እስከ ተራ ወታደርነት ድረስ ኦሮሞ እንደነበር ለማየት አለመፍቀድ ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ የጠቀስነው ሰነድ በአዲስ አበባ ውስጥ የደረሰውን የኦሮሞ መመናመን በአሜሪካና በአውስትራሊያ ከታየው የአውሮፓ መጤዎች ቀደምት ሕዝብን እያበረሩ፣ እያጋዙና በመጠለያ ሠፈር እያጎሩ በሰቆቃ አራግፈው የሠፋሪ አገር ከፈጠሩበት ሒደት ጋር ሲያሳክርና በዚሁና በመሰል ሒደት ደብዛቸው ላመል ለቀረ ቀደምቶች የሚደረግ (የማትረፍ) ጥበቃን ለኦሮሞ ሲያቀርብ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ቁጥርና ሰፊ ሥፍራ የያዘ ሕዝብ ኦሮሞ መሆኑ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ ሐሳባዊ ወሰን ወዲህና ወዲያ ያለው ኦሮሞነት አንድ ወጥ መሆኑና እየከሰመ ስላለ ሕዝብ ለማውራት አለመመቸቱ ያሳጣኛል ብሎ እንኳ አላሰበም፡፡

ለአዲስ አበባ ምሥረታ መነሻው ፊንፊኔ (ፍልውኃ) መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ አዲስ አበባ የአካባቢውን ነባር መጠሪያ ለማሸነፍ ጊዜ እንደወሰደበትም የሚናገሩ ጽሑፎች አሉ፡፡ ፊንፊኔ ከተማ ቀደም ብሎ ተመሥርቷል የተባለው እነ ጣይቱ-ምኒልክ ከእነሱ በፊት የተመሠረተን ከተማ ስሙን ጥለው ነው አዲስ አበባ ያሉት ለማለት ከሆነ፣ ወይም ከተማ ሲጀምር ከመንደር ጀምሮ ነውና ፊንፊኔም ከተማ ነበር ብሎ ለመከራከር ተፈልጎ ከሆነ አያዋጣም፡፡ በምኒልክ ደረጃ ይቅርና በአንድ መስፍን/ራስ ደረጃም የነበረው ተዋረዳዊ የጓዝ ግትልትል (ከመስፍን/መኳንንት እስከ ሠራዊት፣ ሥራ ቤት፣ ነጋዴ፣ መሸታ መሻች፣ የኔብጤ ድረስ) በአንድ ጊዜ አንድ “ከተማ” መሥራት የሚችል ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የዚህ ዓይነቱ አከታተም በአንድ ጊዜ ከድንኳን ወደ ቋሚ ቤቶች መለወጥ የቻለ አልነበረም፡፡ ከተማው እንጦጦ በመቆየትና ወደታች (ወደ ፍልውኃ ራስጌ) በመውረድ መሀል የዋለለበት ጊዜ ነበር፡፡ ለይቶለት ወደታች ከወረደም በኋላ ቢሆን በማገዶ እጥረት እንደገና ሌላ ቦታ የመዛወር ፈተና ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡ የ“አዲስ ዓለም” ታሪክ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ አዲስ አበባን በዋና ከተማነት ለመዝለቅ ያበቃት የባህር ዛፍ መምጣትና መላጣዋ ከተማና ዙሪያዋ ዛፍ በዛፍ ለመሆን መቻሏ ነበር፡፡ መሬትን ጠቅሎ ያዢነት የአፄው እንደነበረ ሁሉ የአዲስ አበባና አካባቢዋ መሬት በጥቂቶች እጅ የመያዙ ታሪክ የጀመረው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ በ1880ዎች ውስጥ ንጉሠ ነገሥቱ ለእቴጌ ጣይቱ፣ ለራስ መኮንን፣ ለንጉሥ ሚካኤል፣ ለሌሎች መሳፍንትና መኳንንቱ መሬት ሰጥተዋል፡፡ በ1900 ዓ.ም. ደግሞ ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዋነኛ መሬት ሰጪነት፣ ሻጪነትና አከራይነት ባሻገር ግለሰቦች ርስታቸውን በመሐንዲስ እያስለኩና ሥዕል እያስነሱ ምስክር ወረቀት የሚቀበሉበት፣ እንዲሸጡና እንዲያከራዩ የተፈቀደበት ደንብ ወጥቷል፡፡

ከቁርቆራ አንስቶም አዲስ አበባ ውጥንቅጥ ጥንቅር አልተለያትም፡፡ የመሳፍንትና የመኳንንት አባላት፣ ፈረንጆች፣ ህንዶች፣ ዓረቦችና ከልዩ ልዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ሥራ ፍለጋ የመጡ/በመንግሥት ለሥራ የተመለመሉ ሰዎች፣ በጦርነት ምርኮና በአደን ለባርነት የተዳረጉ ሁሉ ተገማሽረውባታል፡፡ በግንባታዋ ውስጥም ከፈረንጅና ከህንድ አንስቶ እስከ ባሮች ድረስ ተሳትፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሃያኛ ክፍለ ዘመን ከመግባቱ በፊት የነበረውን የአዲስ አበባ የሕዝብ ብዛት ልዩ ልዩ የውጭ ጸሐፊዎች ከ40 እስከ 50 ሺሕ አካባቢ ገምተውታል፡፡ በ1902 ዓ.ም. ግድም ሜራብ የሚባል ሰው ወደ 65 ሺሕ አድርሶታል፡፡ በዝርዝሩም ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ከፋ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል፣ ወዘተ እየተባለ መጠቀሱ ሳይዘነጋ ኦሮሞ ሲሶ (20 ሺሕ) ያህል፣ ትግርኛና አማርኛ ተናጋሪ ሲሶ፣ አሽከርና ባሪያም ሃያ ሺሕ ግድም ሆኖ ሠፍሯል፡፡ በተለያየ ምክንያት ከየአካባቢው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ገዢዎች ከ30 እስከ 50 ሺሕ የሚደርስ ሰው አስከትለው የሚሰነብቱበት ሁኔታም ስለነበር፣ የከተማዋ የሰው ብዛት እስከ መቶ ሺሕ የሚወጣና የሚወርድ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ በቋንቋ ተነጋሪነት ረገድም ገዢዎቹ የሚናገሩት አማርኛ ዋና መግባቢያ እንደነበር፣ በሁለተኛ ደረጃ ኦሮሚኛ (ኦሮሞ ያልሆኑም በሚረዱት ደረጃ) ይነገር እንደነበር ተጽፏል፡፡ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ከፈረንጅ አፍ ወደ ፈረንሣይኛ ያዘነበሉ እንደነበር፣ በጣሊያኖችና በኤርትራውያን አካባቢ ጣሊያንኛ፣ በንግዱ አካባቢ ደግሞ ዓረብኛ ይደምቅ እንደ ነበር ተወስቷል፡፡

ከፋሺስት ጣሊያን በፊትም ሆነ በኋላ የአዲስ አበባ መሬት በጥቂቶች እጅ ተግበስብሶ መያዙ ያልተለወጠ እንደመሆኑ፣ መሬት የመግዛት አቅም የነበረውም ጥቂት እንደመሆኑ እስከ ደርግ ድረስ የከተማዋ ዋና መስፋፊያና የነዋሪዎቿ መባዣ መንገዶች የጭሰኛ/ወለድ አግድ ምሪትና የቤት ኪራይ ነበር፡፡ ከኦሮሞ፣ ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከጉራጌ፣ ከሲዳማ፣ ወዘተ ወዘተ የተገኙ ሰዎች በአዲስ አበባ ከኪራይ ቤት፣ ኪራይ ቤት የሚንከራተቱ ነዋሪዎች ሆነዋል፡፡ ጥርስ ነክሰው ጥሪት እየቋጠሩም ከባለርስት መሬት በጭሰኝነት እየተመሩ ቤት ቀልሰዋል፡፡ በጋብቻም እየተወራረሱና በአማርኛ ተናጋሪነት እየተለበጡ የአዲስ አበባን ሕዝብ ዝንቅ ማንነት ፈጥረዋል፡፡

ከደርግ አንስቶ እስካሁን በመሬት ላይ አዛዡ መንግሥት እንደመሆኑ ከገጠሩ ክፍል እየቀነሱ ከተማ የማልማቱ ተግባር ይበልጡን በመንግሥት መዳፍ ውስጥ ቆይቷል፡፡ መንግሥት መሬትን አንቆ የቤት እጥረት ችግርን እያከማቸው ሲመጣና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር በፍልሰት እየጋሸበ ሲሄድ፣ ገጠራማ ሥፍራን ወደ ከተማ የመቀየሩ ሥራ በዋናነት መውደቂያ በሚፈልጉ ሰዎችና ሥውር የመሬት ንግድን በሚያባርሩ ጩሉፋቶች አማካይነት ሲከናውን ቆቷል፡፡ ኦሮሞ በወረራና በኃይል ወደ ዳር ተገፍቶ በአዲስ አበባ ውስጥ ወደ አናሳነት ሊቀየር ችሏልና የዛሬው ሕዝብ የተፈጸመውን አውቆ “ዕውቅና እንዲሰጥ” የሚባለው ይህንን ሒደት እንዳልነበር በማድረግ ነው፡፡ በግለሰቦች መሬት ግዢም ሆነ በመንግሥት መሬት ምደባ አማካይነት ከተማ ተስፋፋ ማለት ያው የገጠሬ ወደ ዳር መገፋት ማለት ነው የሚል ተከራካሪ ካለ፣ ገጠራማ መሬትን ሳይነካ ከተማ እንዴት ሊለማ እንደሚችል በራሱ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚካሄድ የከተማ ልማት ምሳሌ ጠቅሶ እያሳየ ሊያሳውቀን ይገባል፡፡

ለመሆኑስ ጥናት ተብዬው ሰነድ የአዲስ አበባ (ኦሮሞን የጨመረ) የጥርቅምቅም ሕዝብ አፈጣጠርን ደፈጣጦ በወረራና በኃይል ኦሮሞን ወደ ዳር የመግፋትና ቁጥሩን የማመናመን ታሪክ አድርጎ መሣል ለምን አስፈለገው? የዚህ ዓይነት ሥዕልስ የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ነው? ታሪክን ቆልምሞና በሰፊው የተዘረጋውን ኦሮሞን አዲስ አበባ ላይ ቆርጦ እንደ አሜሪካ ህንዶች የተመናመነ ቀደምት ባለቤት አድርጎ ማቅረብስ ለምን? ወይስ በኦሮሞ ውስጥ የታዩና የተራረፉ ጎሳዎችን ሁሉ ገትሮ ለማቆየት/ከቅልቅል ለማትረፍም ታስቧል? የኦሮሞን ወደ ዳር መገፋት ለማስተማመን መሞከር፣ የቀድሞ ስሞች እንደገና እንዲመለሱ መጠየቅ፣ ፊንፊኔ ከአዲስ አበባ ጋር የከተማው መጠሪያ እንዲሆን መጠየቅ፣ የዴሞክራሲን ጉዳይ ከንብሎ የከንቲባን ምርጫ በቋሚነት ከኦሮሞ ይሁን ማለት፣ እነዚህን የመሳሰሉት የ‹‹ጥናት ሰነዱ›› ጉዳዮችና የኦሮሚያ አስተዳደር ዋና መቀመጫ ከማያስተዳድራት አዲስ አበባ ጋር መጣበቅ ሁሉ አንድ ፈትል ይሠራሉ፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ነች ባይነትን የማረጋገጥና እንዳትረሳሳ የመጠበቅ ፈትል፡፡

ነገሩ ብሔረሰባዊ የመሬት ባለቤትነትን ከማስተማመንም ያለፈ ፍላጎት አለበት፡፡ ከምኒልክ ወዲህ አዲስ አበባ ላይ ከተጠረቃቀመው ሕዝብ ይልቅ ኦሮሞ ቀዳሚ ነዋሪ መሆኑ የበለጠ ባለመብት ያደርገዋል የሚል ማማ ላይ ቆሞ ዋና ባለመብትነትን የማሳየት፡፡ ለመሆኑ የኦሮሞ ተቆርቋሪዎቹ በጥናታቸው ሒደት ቀዳሚነት በራሱ የመብት ብልጫን እንደማያቀዳጅ ከሚያሳዩ ታሪካዊ መረጃዎች ጋር አልተገናኙም? የኢትዮጵያ ኦሮሞስ ተጎድቶ የኖረው ብልጫ መብት በመነፈጉ እንዳልሆነና ጥያቄውም ያ እንዳልሆነ አጥተውት ይሆን? ወይስ የተሳሳትኩት እኔ ነኝ? ኦሮሞ ይናገር!

4. ከያዝነው ሰነድ ወጣ ካልን፣ ከአዲስ አበባ የዘለለና እነ ድሬዳዋና ሐረር ሁሉ ከአሮሚያ የተቀነሱ ናቸውና ይመለሱ የሚል ጩኸትም እናገኛለን፡፡ “ይህን ያህል መሬት የማሰባሰብን ነገር ምን አመጣው? ለመሆኑ አንዲት አገርን በመገንባት ዕይታ ውስጥ ነው እያሰብን ያለነው?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ ደግሞ እነዚሁ ሰዎች፣ “ለኢትዮጵያ ግንድና የአገር ባለቤት ከኦሮሞ በላይ ማን ሆኖ ነው የኦሮሞ ኢትዮጵያዊነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባው?!!” በሚል ዓይነት አካሄድ፣ የጥያቄውን መነሳት የበደል ያህል አድርገው (ለጥርጣሬ በር የከፈተና እስከ ዛሬም ያልጠፋ ወጣቱን እየቆረጠመ ያለ ፅንፈኛ ዝንባሌ የሌለ አስመስለው) ቀልብ ይገፋሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጩኸት ፅንፈኝነትና መቃቃር በተባበረ ትግል ላይ እየፈጠረ ያለውን አደናቃፊነት ለማምከን እስካላገለገለና መሬት ቆጠራን ትርታው እስካደረገ ድረስ፣ ለማንኛውም ሒሳብን ተሳስቦ በመቆየት ሥሌት ላይ የተሳካ ከመሆን አያመልጥም፡፡ ካልተወሻሸን በቀርም በዚህ ችግር ያልተጠመደ አንድም አካባቢ (ከላይ ከትግራይ አንስቶ እስከ ታች ድረስ) የለም፡፡ እንዲያውም “የብሔር ብሔረሰብ መብት” የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ላይ እስካሁን አቋቁሞ የምናየው ራስን በራስ ከማስተዳደር በበለጠ የመሬት ቅርጫን፣ በዚሁ መሬት በማሳደድና በመሰሰት አባዜ ተጠምዶ መብት ረገጣ ውስጥ መዘፈቅን፣ የእኩልነት፣ የመተሳሰብና የዴሞክራሲ አመለካከትን ከማንፀባረቅ ይልቅ በጎሰኛነት መማቀቅን ነው፡፡ ቅይጥና ዲቃላ ገጽታዎችን ረብሾ ወደ ሴመኛ ገጽታ ለመቀየር መሥራትና ማፈናቀል የእነዚሁ ችግሮች መገለጫ ናቸው፡፡

በእነዚህ ችግሮች ያልተቀፈደድን ወይም እነዚህን ችግሮች ለማራገፍ የተነሳሳን ካለን፣ በብዙ ጥያቄዎች አስተሳሰባችንን መፈተሸ አለብን፡፡ “ኦሮሞ ማለት ኢትዮጵያ/ግንድ” የሚለው አመለካከከት እውነተኛ ከሆነ፣ (ታክቲካዊነት ካልሆነ) የኦሮሞ መሬት እያሉ ከአዲስ አበባ አንስቶ መቁጠር ለምን ያስፈልጋል? መሬቱ እግር አውጥቶ ወዲህም ወዲያም የማይሄድ እንደመሆኑ ዋናው ጉዳይና ሁሌም መፈተሽ ያለበት ክልላዊ አከፋፈሉ የሕዝቦችን የተመጣጠነ ዕድገትና ተጣጥሞ መኖር ማሳካት መቻሉ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አስተዳደራዊ መምታታትና ግጭት በማይኖርበት ሁኔታ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፌዴራላዊ ዋና ከተማ ሆና፣ የኦሮሚያ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ውጪ ቢሆን ኦሮሞና ኦሮሚያ ምን ይጎድልባቸዋል? አንዳንዶቹ እንደሚሹት አሁን ባለው የኦሮሞ ስፋት ላይ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሌላም “የእኔ የተባለ” የተጨመረበት ከበፊቱ የባሰ ግዙፍ ክልልን ፈጥሮ ከእነ ቤንሻንጉል ጋር ማሠለፍ የተመጣጠነ ዕድገትን ከማግባባት አኳያ ፍትሐዊና ጠቃሚ ይሆናል? ከመብት አኳያስ በሚሊዮኖች የሚቆጠረውንና ከአራቱም ማዕዘናት የመጣውን ጥርቅምቅም የአዲስ አበባን ሕዝብ አንድ ብሔርነትንና አንድ ቋንቋ ተናጋሪነትን መሠረት አድርጎ በተዋቀረ ክልል ውስጥ ገብቶ እንዲተዳደር መሻት እንደምን ፍትሐዊ ይሆናል? መደረግስ የሚገባው ይህ ሥፍራ የእዚህ ክልል አካል መሆን አለበት ብሎ ፍላጎትን መጫን? ወይስ የአወቃቀር ሚዛናዊነት ባልተረሳበት አኳኋን ሕዝብ እንዲወሰን መተው?

“ኦሮሞ እንደ ወርዱና እንደ ቁመቱ የሚመጥን ሥልጣን ይሰጠው” እየተባለ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ብልጫ ሥልጣን ይሰጠው ለማለት ነው? ከዚህ ይልቅ የሁሉንም ሒሳብ በዴሞክራሲ ማስተካከል እንደሚቻል አምኖ እውነተኛ የሕዝቦች (የዴሞክራሲ) አስተዳደር መረጋገጥን ጥያቄ ከፍ ማድረግ አይሻልም? ሚጢጢነትንና ግዙፍነትን ያዳበለው አወቃቀር በጅቶናል? ብሔረሰባዊ መፈላለግን ሳያናጉ ብሔረሰብ ዘለል የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ መናኸሪያዎችን መፍጠር ይቻለን ይሆን? እስከ ዛሬ ጎሰኝነትን አሸንፎ እኩልነትንና የሕዝቦችን መግባባት በሁሉም ሥፍራ ማሳካት ለምን ተሳነን? በዴሞክራሲ ጉድለት ምክንያት? አወቃቀሩ ለጎሰኝነት ተመችቶ? ወይስ ከዴሞክራሲ መጓደል ጋር ብሔረተኛ አዕምሮና ፖለቲከኛነት አላራምድ ብሎ? ራስን በራስ ማስተዳደር የግድ ብሔረሰባዊ ይዞታን ለይቶ ማደራጀት ይሻል? ብሔረ ብዙ ቅንብርንና ብሔረሰባዊ መብትን ማስላት አይቻልም? እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች የ26 ዓመታት ስኬትና ውድቀት ላይ ተመሥርቶ የወደፊቱን ለማቃናት የሚጠቅሙ ይመስለኛል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ሊመረምራቸው የሚገቡ ሌሎች ጥያቄዎችም አሉ፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ የኦሮሞ መሬት እዚህና እዚያ ቀረ እያሉ የሚቆጥሩና ንብረት አስተማምነው ለማቆየት የሚሹ ብሔረተኞች ዕውን መሬት በማስገኘት ኦሮሞን ይጠቅሙታል? ወይስ አናክሰው ወደ ጠብ ይወስዱታል? አዲስ አበባን ምሳሌ አድርገን ነገሩን ከሁለት አቅጣጫ እንመልከተው፡፡ የአሁኑ ብሔረሰባዊ አወቃቀር እስከ ቀጠለ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ መገናኛ ተብሎ የሚታሰበው ፌዴራላዊ አስተዳደር ለአገሪቱ እምብርት ከሆነውና በውጥንቅጥነቱ ብሔረሰቦችን ከሚያንፀባርቀው ከአዲስ አበባ የበለጠ የሚስማማ አያገኝምና የአስተዳደር ማዕከሉ አዲስ አበባ ሆኖ መቀጠሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

የኦሮሚያ ሕዝብ ፍላጎቱን በውሳኔ-ሕዝብ ይግለጽ የሚለው አፈር ደፈር ባይ ጥያቄስ መሬት ለማሰባሰብ ይበጅ ይሆን? አደፋፋሪ ሁኔታ አግኝቶ ጥያቄው ገጦ ቢመጣ ወዲያውኑ በኦሮሞና በሌሎች መካከል የሚከፈተው መከፋፈልና መወዛገብ ውሳኔ-ሕዝብ ለማካሄድ እንኳ የሚያስችል አይሆንም፡፡ የሚፈለፈለው ጣጣ ወለል አድርጎ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ሰፊና ሀብታም ክልል ስላለኝ እንደ አገር ራሴን ችዬ መቆም እችላለሁ የሚለው ተመኪነት ሐሳዊ ግንዛቤ መሆኑን ነው፡፡ በተዓምር መስማማት ተችሎ ውሳኔ-ሕዝብ ቢካሄድና የመነጠል ውሳኔ ቢያሸንፍ ውዝግብና ግጭት መሰስ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ ትልቁ የውዝግብ አውሎ ንፋስ የሚነሳው ደግሞ የአዲስ አበባ ጥርቅምቅም ሕዝብ ለአንድ ብሔረሰብ ውሳኔ ከማጎንበስና ካለማጎንበሱ ዘንድ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ የፖለቲካ ዕጣዬን ከራሴ ውጪ ማንም አይወስንልኝም ብሎ ቢያፈነግጥ ጦር ይመዘዛል? ወይስ ሕዝቡን ወደ ሌላ ደፍቶ መሬት ይወሰዳል? የትኛውም ወገን መሬትንም፣ ሰላምንም፣ ህልውናንም የሚያጣበት የፍጅት እሳት የሚጀመረው እንደዚህ ነው፡፡

 5. ከዚህ በተቃራኒ ኦሮሞ እውነተኛ ጥቅሜ፣ ኦሮሞ ማለት ኢትዮጵያ መሆኑን የአመለካከቴም የተግባሬም ሐዲድ ማድረግ ነው ቢልስ? ይህንን አቋም ማጥበቅ የአጋጣሚ ብልጥ የመሆን ጉዳይ ሳይሆን አመለካከትንና ታሪካዊ እውነታን ማስማማት ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደሚባለው ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ የሆነው ወይም ኦሮሞ ማለት ኢትዮጵያ ማለት የሆነው ሰዎች ስለደጋገሙት ወይም ኦሮሞ ሰፊ ቦታ ላይ ስለሚኖር ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ማኅበራዊ የመወራረስ ታሪክ ከማንም በላይ ሊሰረዝ እንዳይችል አድርጎ በሕዝቦች ላይ የጻፈው ኦሮሞ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ እውነታ (ሪያሊቲ) መሠረት ሁሉም የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች እየተቦደሱ ኦሮሞነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በሌላ በኩል ኦሮሞ ከማንም በላይ ከአገሪቱ ብሔረሰቦች ጋር ኩታ እየገጠመና ማበጠር በማይቻል ደረጃ ቅልቅል እየፈጠረ ማኅበራዊ መያያዣ ሆኗል፡፡

የኦሮሚኛ ፌዴራል ቋንቋ የመሆን ነገርም ታሪክ የገነባችውን መላላስ ሙሉ የማድረግ ጉዳይ እንጂ፣ ኦሮሞን የመሸንገያና የኦሕዴድን ገዢነት የማደሻ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኦሮሞም ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችም የኦሮሚኛን የፌዴራል ቋንቋ መሆን ከዚህ ማዕዘን ነው ሊያስተናግዱት የሚገባው፡፡ የኦሮሚኛ የፌዴራል ቋንቋነት እንዴት ባለ የተግባር አካሄድ ይምጣ የሚለው ጥያቄም ከዚሁ አኳያ መታየት አለበት፡፡ ማለትም ከላይ ታውጆ የፌዴራል አውታራት ባሉበት ሁሉ ኦሮሞ ባለጉዳዮች ከአማርኛ ጋር መነካካት ሳያስፈልጋቸው ጉዳያቸውን የሚያከናውኑበት፣ የፌዴራል መንግሥቱም በኦሮሚኛ የሚለፍፍበት፣ በእነዚህ ለውጦች አማካይነትም ኦሮሞዎች ጭማሪ የሥራ ገበታ የሚያገኙበት ትንሽ ውጤት ይምጣ? ከዚህ አልፎ ኦሮሚኛ በመላ አገሪቱ በትምህርትነት ይታዘዝና አማርኛ ትምህርት “የነፍጠኛ ቋንቋ/የተጨቆንበት” እየተባለ ማሾፊያ እንደሆነ ሁሉ ኦሮሚኛም ኦሮሞን ለመደለል የተጫነ በሚል ዓይን እየታየ የውሸት ትምህርት ይሁን? ወይስ ከዚህ በተለየ ሕዝባዊ ጎዳና ኩርፊያና መከፋፈል ተሰብሮ የተለዋወስንበት እውነተኛው ታሪክ ተፈልቅቆ ኦሮሞነቴ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች  ዘመድ አድርጎኛል፣ በኦሮሞዎች ውስጥ እኔነቴ ገብቷል፣ በብሔረሰባዊ እኔነቴ ውስጥም ኦሮሟዊ አሻራ አለ የሚለው ንቃተ ህሊና የጠቅላላችን ለመሆን በቅቶ፣ ኦሮሚኛን መማርና ኦሮሚኛን የፌዴራል መግባቢያ ሆኖ ማየት የእኔነትን አንድ ገጽታ ማግኘትና እኛነትን በአርማታ የማጠንከር ተግባር ሆኖ ይምጣ? ለመልሱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይነጋገሩበት፡፡ (በነገራችን ላይ የኦሮሚኛን አጻጻፍ መማር ቢጠቅምም ሌላ ፊደል ያላቸው በዚያው አማካይነት ኦሮሚኛን ከመጻፍ የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ በኦሮሚኛ መነጋገርን እናሳካ እንጂ፣ በቁቤ የተጻፈን ነገር ወደ ሌላ አጻጻፍ፣ በሌላ አጻጻፍ ያለ ነገርን ወደ ቁቤ አዙሮ የመረዳትን ዕድል ፍልሰፋ የማያልቅበት አዲሱ የመረጃ ጥበብ ያቃናዋል፡፡)

በኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነትን፣ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ኦሮሟዊ አሻራን በሚመለከት ግንኙነት ውስጥ ስንኖር የመሬት ቆጠራና ስስት ከሚያመጣው መናቆርና በዚህም አማካይነት ከሚከተል የአምባገነኖችና የከፋፋዮች መጫወቻነት ነፃ ከመውጣት በቀር የሚከፈል ቀረጥ የለም፡፡ ያኔ ፊንፊኔንና አዲስ አበባን ያላንዳች ፖለቲካዊ  አንድምታና መተዛዘብ እንዳፈቀደ መጠቀም ቀላል ይሆናል፡፡ የእኔ እያሉ መሬት ቆጠራም አስቂኝ የዱሮ ታሪክ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን አንዱ ወሰን አስፊ ሌላው አፈግፋጊ፣ አንዱ ውኃ በካይ ሌላው ብክለት ተቀባይ መሆን ይፈቀድለታል ማለት አይደለም፡፡ ተቀናጅቶ የጋራ ልማት ማካሄድም የወሰን ለውጥን ማስከተል አይኖርበትም፡፡ ከጋራ መተሳሰብ ጋር ሸክምነትና ተሸካሚነት፣ ከተምታታ መከፋፈልና መርኮምኮም ዞሮ መጣ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ምግባርና ግንኙነት ከታረመ ልዩ ጥቅም ሰጪነትም ሆነ ተቀባይነት ትርጉመ ቢስ ይሆናሉ፡፡

እግረ መንገዳችንን የተምታቱ ነገሮችን እናጥራ፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ዙሪያውን ያሉ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አባላት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸውና በአዲስ አበባ ምክር ቤት ውስጥ የተወሰነ ውክልና ማግኘታቸው ልዩ ጥቅም ሳይሆን መብት ነው፡፡ የትም ክልል ውስጥ በአናሳነት የሚገኙ ማኅበረሰቦች እንዳይዘነጉና ጥቅማቸው እንዳይጨፈለቅ፣ ምክር ቤታዊ ውክልናቸው የክልሉን የሥራ ቋንቋ ቻሉ አልቻሉም ሳይባል መሟላት ይኖርበታል፡፡ መቃብር የገባ የዱሮ ሠፈር ስም ሁሉ እየተማሰ እንዲወጣና ተመልሶ እንዲለጠፍ መፈለግም ለኦሮሞ ከመቆርቆር ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌለው፣ አለባበስና አነጋገር እንዳይቀየር ገትሮ ከመያዝና አምልጦ ሲቀየር ወደ ነበረበት ለመመለስ ከመታገል የማይሻል ወፈፌ ግብዝነት ነው፡፡ እንደዚያ ከጀመርንማ የምናውቀው ኦሮሟዊ ስም ጋ ስንደርስ ምን ያስቆመናል? መባል ያለበት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፌዴራላዊ መንግሥት ማዕከል እንደ መደረጓ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የሚያንፀባርቁ ገጽታዎች ይኑሯት ነው፡፡

6. ተፍታተው መነጋገሪያ ሊሆኑ የሚገባቸው የምላቸውን ጥቂት ነጥቦች በአጭር በአጭር በማስቀመጥ ላጠቃል፡፡

  • የብሔረተኛነት ህሊና፣ የብሔረኛነት ፖለቲካ (ፓርቲ) እና ገዢነት ምን እንዳተረፈልንና ምን እንደነጠቀን ለመረዳት የ26 ዓመታት ልምዳችንን መገምገም ይኖርብናል፡፡ ብሔረሰባዊ አመጣጥንና እኛነትን ማወቅ፣ በየቋንቋችን መሥራት፣ ባህሎቻችንን ማበልፀግና መንከባከብ መብታችን ነው፡፡ ይህ መብት ከመቼውም በበለጠ በአገራችን ውስጥ ተፈልቅቆ ወጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ክፍልፋይ ብሔረተኝነት (ጎሰኝነት) ብሔረሰባዊ ማንነትን እንደ ጮገጊት አፍኖ ከሌሎች ጋር ማስማማት እንዳይችል አውኮታል፡፡ በብሔረሰብነት ውስጥ ያለ ማኅበራዊ ተዛምዶን ሲያዩ የማኅበራዊ መፐዋወዝ ታሪክ በብሔረሰቦች መሀል የገነባውን መወራረስ ማስተዋል ይገባል፡፡ ከዚህም ጋር የአገር ልጅነትን ማገናዘብ አግባብ ነው፡፡ ምክንያቱም ተባልቶ ከመጥፋት መትረፊያ ነውና፡፡
  • በብሔረሰባዊ ቋንቋና ባህል ውስጥ መኖር የግድ ብሔረሰባዊ አጥር መሥራትን አይጠይቅም፡፡ ቋንቋን እየተከተሉ የአስተዳደር ይዞታን መከለስ ቀላል ሆኖልናል? ብለን ብንጠይቅ መልሳችን አዎ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ሙከራ ታሪክ ከሠራቸው ቅልቅልና ዲቃላ ማኅበራዊ ገጽታ ጋር እንድንላተም ነው ያደረገን፡፡ ብሔረሰባዊ ክልሎች ለማዋቀር ተነስተን ብሔረሰቦች የተጎዳኙባቸውን ክልሎችም ከማደራጀት አላመለጥንም፡፡ እንደዚያም ተደርጎ በየክልል ውስጥ ንዑስ (ውስጣዊ) የብሔረሰብ ግቢዎች የመፍጠር አባዜ የንትርክና የግጭት መፍለቂያ ሆኗል፡፡ ክፍልፋይ ብሔረተኝነት፣ የአንድ ዓይነተኛ ማኅበረሰብ ብጤኞች ልዩ ልዩ ነን እንዲሉ አድርጓል፡፡
  • “አንድነት በልዩነት!”፣ “ልዩነት ውበት ነው!” እንላለን፡፡ በነገራችን ላይ የእንግሊዝኛውን “ዳይቨርሲቲ” ከ“ልዩነት” በተሻለ የሚገልጸው ዥንጉርጉርነት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ እዚያም እዚያም ትንንሽ ግቢዎች እየሠራን፣ መፈክር የምንፈክርለትን የዥንጉርጉርነት አንድነት ተቃርነናል፣ አውከናል፡፡ የግቢ ይዞታን ማስፋትና ቡራቡሬነት ውሎ አድሮ ነገር እንዳያመጣ፣ የተቀላቀለ/የተደባለቀ ገጽታን የማበጠርና የጠራ በሚባለው ማንነት የመሞረድ ሙከራ ብዙ ነገር በጥብጧል፡፡ ብሔረሰባዊ ጥራት እንደይቀየርና እንዳይበረዝ መጣርማ የባሰበት ነው!!
  • በዚህ ላይ ክፍልፋይ ብሔርተኝነት ሌላ አጥፊነትም አለው፡፡ ወዲህም ወዲያ ቢያገላብጡት ወይም “ዴሞክራሲያዊ” የሚል ቅፅል ቢለጥፉበት ክፍልፋይ ብሔርተኝነት በእኩልነት ለመተያየት የማያስችል የአድልዎ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ይህ ወሬ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ጎሰኛ አንጓላይነት ብሔረሰባዊ መብትን ማስከበር እስኪመስል ድረስ ተንሠራፍቶ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ሲያቆስል ቀይቷል፡፡
  • ታዲያ ብሔረሰቦችን ከማቀናጀት ካላመለጥን፣ ተቀናጅተንም ክፍልፋይነት ከበጠበጠን፣ ቅንጅቱን የሚቻለውን ያህል ለማቻቻል ከመሞከር ጋር የትንሹም የትልቁም ማኅበረሰብ አባላት በእኩልነት ለመኗኗር የሚችሉበትን ዥንጉርጉርነት ሳንረብሽ፣ እንዲያውም መሰባጠርንና መላላስን የአንድነት መጠንከሪያ፣ የመጪ ዘመን ማኅበራዊ ገጽታ አድርጎ በሚያይ አዲስ ህሊና ውስጥ መኖርን ብንሞክረው ምን አለ?
  • በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክን ያቦተለኩ ሁለት ፅንፎች ተፈጥረዋል፡፡ የአፄዎችን ገድል አጥብቀው ይዘው አትንኩብን የሚሉና በተቃራኒው የአፄዎቹን ታሪክ ተፀናውተው በወረራ መደፈቃቸውን አጥብቀው የያዙና ማን የደፈረ ተችቶን የሚሉ፡፡ የሁለቱንም ወገንተኛነትና የፖለቲካ ጭጋግ መግፈፍ የተሳካለት የተሟላ ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ገና አላገኙም፡፡ የትኛውንም ታሪክ በጥያቄ መበርበርና መመርመር አስፈላጊያችን መሆኑ፣ እንዲሁም አትንኩብን  የተባለ ታሪክ ወይ ወደ ተረትነት ወይ ወደ ሃይማኖትነት የነጎደ መሆኑ የገባቸው ጥቂት አሳቢዎች ሚዛናዊ በመሆን ዕይታ ውስጥ የተወሰኑ ነገሮች እየወረወሩ ክፍተት ለመሙላት ሲጣጣሩ እናያለን፡፡ የሚያጠግብ የታሪክ ሥራ ቀረበንም ራቀንም፣ ያለፈ የወረራ ታሪክን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ትውስታው መጥፎውንና ግፉን ብቻ እየመረጠ የሚፈትል ከሆነ ትርፉ በደመኝነት መቃቃር ነው፡፡ ወረራው ብዙ ጥፋት አድርሷል፡፡ ያም ሆኖ ከኦሮሟዊው ማኅበራዊ መዘናነቅ ጋር ተጋግዞ ዛሬ ያለነው ሁላችንም ካወቅንበት የሕዝቦች ብልፅግናና ልዕልና መናኸሪያ ልናደርገው የምንችል ትልቅ አገር አስገኝቶልናል፡፡ ከወረራው ጠባሳ በታች ያለው ማኅበራዊ መወራረስ ደብዝዞ የኖረው የተዛባ የአፈና አገዛዝ ለዘመናት በመቆየቱና የአርነት ትግሎችም ክፉ ክፉውን እንደ ጥጥ ያባዝቱ ስለነበር ነው፡፡ አገዛዙ ሳይታረም ለረዥም ጊዜ መቆየቱም ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ የተቦረቦረው የአንድ አገር ልጅነት በአግባቡ መታነፅ የሚችለው ዴሞክራሲን መገንባት ከሰመረልን ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲና ፍትሐዊነት በዘገዩ ቁጥር ፅንፈኛ ፍላጎት እንደሚጨምር፣ በዚያው ልክ ተያይዞ መቀመቅ የመውረድ አደጋ ርቀቱን እየቀነሰ ወደ እኛ እንደሚያመራ ሁላችንም ልብ ልንል ይገባል፡፡ መታወቅ ያለበት ሌላው ነገር፣ ከመከፋፈል ወጥቶ መተባበር አስፈላጊ የሚሆነው ዴሞክራሲ ከተጨበጠ በኋላ አይደለም፡፡ ኅብረትን የምንሻው ከሁሉ በፊት ዴሞክራሲንና እኩልነትን ለመጨበጥ ነው፡፡
  • ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...