ፓን አፍሪካዊነትን የሚያቀነቅነው ታዋቂው ኒው አፍሪካ መጽሔት እ.ኤ.አ. በየካቲት 2004 ዕትሙ “Solving The Great Conundrum…How African Can Own Its Natural Resources” በሚል ርዕስ በሰጠው የሽፋን ዘገባው የአፍሪካ ታላቁ እንቆቅልሽ፣ አፍሪካውያን እንዴት የተፈጥሮ ሀብቶቻቸው ባለቤት ይሆናሉ ብሎ ይሞግታል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች አምስት በመቶ የሮያሊቲና ታክስ ብቻ፣ ከ90 እስከ 95 በመቶ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶች ሲመዘብሩ ዓመታትን ያስቆጥራሉ የሚለው መጽሔቱ፣ ኩባንያዎቹ ለማዕድን ፍለጋ ሥራ የሚያወጡትን ወጪ በማጋነን የአኅጉሪቱ ሕዝብ በደኅንነት ሲማቅቅ ይቆያል ይለናል፡፡
የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ቻርልስ ቴለር ወደ ሥልጣን በወጡ በሁለተኛው ዓመት እ.ኤ.አ. በ1997 የበላይቤሪያ አጠቃላይ የማዕድን ሀብቶች ክምችቶች በአየር ላይ እንዲነሱና ጥናት እንዲካሄድ አዘዙ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በአገሪቱ መንግሥት የማዕድን ሀብቶቹን ክምችት ለማወቅ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተገኙበት ነበር፡፡ ምክንያቱም መንግሥት አገሪቱ ምን ዓይነት ማዕድኖች እንዳላት፣ በተጨባጭ የት የት እንደሚገኙና በምን ያህል መጠን እንደሚገኙ ማወቅ ተችሎ ነበር፡፡ ቻርስ ቴለር ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው ጥቂት ዓመታት በፊት በጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚደገፍ አንድ የአሜሪካ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ፣ በላይቤሪያ የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ ተሰማርቶ ነበር፡፡ ኩባንያው ከላይቤሪያ ለሚያወጣው የነዳጅ ሀብት ከእያንዳንዷ ዶላር አምስት ሳንቲም ለአገሪቱ ለመስጠት ፍላጎት ነበረው፡፡ ቻርልስ ቴለር ግን ስምምነቱን ማድረግ አልፈለጉም፡፡ ያ ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያ ስምምነቱን እንዲያደርጉ ደጋግሞ ግፊት ቢያደርግም በእንቢተኛነታቸው በመፅናታቸው፣ በእጅ አዙር እ.ኤ.አ. በ2004 በሴራሊዮን ልዩ ፍርድ ቤት የሴራሊዮን አማፂያንን በመርዳት የሚል ክስ እንዲቀርብባቸው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
የቴለር ክስን ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው ግፊት ይፈጥሩ የነበሩት ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታኒያ ነበሩ፡፡ ይኼ ግዙፍ የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ “የላይቤሪያን ነዳጅ ዘይት እኛ እንድናወጣ ከፈቀዱልን ለፍርድ እንዳይቀርቡ እናደርጋለን ….” የሚል መደለያ አቅርቦላቸው ነበር ይባላል፡፡ ከአገሪቱ የነዳጅ ዘይት ሀብት ገቢ ውስጥ ከያንዳንዷ ዶላር አምስት ሳንቲም ብቻ ማግኘት ፍትሐዊ አይደለም ብለው የሞገቱት ቴለር በኋላ ከመከሰስ አልዳኑም፡፡ ኩባንያው “ክቡር ፕሬዚዳንት ልንረዳዎት አንችልም፣ ልንከላከልሎት አንችልም …” ነበር ያለው
ቴለር ከማዕድን ኩባንያዎች የሚገኘውን የማዕድን ትርፍ ለማሳደግ ያደረጉትን ቁርጠኛ ዕርምጃ የተቃወማቸው አንድ የውጭ ኩባንያ ከሥልጣን ለመወገዳቸው፣ ከሴራሊዮን ልዩ ፍርድ ቤት ወደ ሔጉ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከተላለፉ በኋላ ችሎት ላይ ቆመው ለምን ለእስር እንደተዳረጉ ይኼንን ታሪክ አቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱ በፀጥታ ተዋጠ፡፡ ታሪኩ በአጭሩ ቻርልስ ቴለር የሴራሊዮን አማፂያንን “በመርዳትና በሌሎች ወንጀሎች” ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ በማለት ለ50 ዓመታት በብሪታኒያ እስር ቤት እንዲማቅቁ ፈርዶባቸዋል፡፡
አንድ ዓይነት ባይሆንም እ.ኤ.አ. በ1997 የኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሊዙባ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት ሊዙባ፣ የኮንጎ ብራዛቪል ሕዝብ በምርጫ የጣለባቸውን ኃላፊነት በመጠቀም የቀድሞ ወታደራዊ አስተዳደር ከምዕራባውያን ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች ጋር የገባውን ድርሻ ክፍፍል ምጣኔ በተመለከተ ለመደራደር ሐሳብ አቀረቡ፡፡ አገሪቱ ከነዳጅ ሀብቷ 15 በመቶ ብቻ ታገኝ ስለነበር ፕሬዚዳንት ሊዝቡ ይኼ ዝቅተኛ ድርሻ ወደ 33 በመቶ እንዲያድግ ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ፡፡ ከአንድ የፈረንሣይ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ በስተቀር ሁሉም የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች ደስተኛ ነበሩ፡፡ የፈረንሣይ የነዳጅ ዘይት ኩባንያው ወዲያው ወደ ፈረንሣይ ፓሪስ በማቅናት ለወቅቱ ለፕሬዚዳንት ጃክ ሺራክ መራሹ መንግሥት ድርጊቱ እንዲቆምና ፕሬዚዳንት ሊዝቡ እንዲንበረከኩ ፈረንሣይ እንድታደርግ ተማፀነ፡፡
ፕሬዚዳንት ሊዝቡ እ.ኤ.አ. በ1998 እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ከኒው አፍሪካ መጽሔት ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ፕሬዚዳንት ጃክ ሺራክ ወዲያው ወደ ፓሪስ አስጠርተዋቸው የቀድሞ መንግሥት ወታደራዊ መሪን ምክትል ፕሬዚዳንታቸውና የመከላከያ ዋና አዛዥ እንዲያደርጉ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጧቸው፡፡ ይኼ የፈረንሣይ ጣልቃ ገብነት ከኮንጎ ብራዛቪል ሕገ መንግሥት ጋር የሚጋጭ ቢሆንም፣ ፈረንሣይ የፈለገችው የፈረንሣዩን ግዙፍ ነዳጅ ዘይት ኩባንያ ጥቅም ለማስከበር የሚያስችላት ተቀናቃኝ ኃይል ወደ ሥልጣኑ ቁንጮ ማምጣት ነበር፡፡ ሊዝቡ የኮንጎ ብራዛቪል ሕገ መንግሥት እንደማይፈቅድ ለቀድሞው የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ጃክ ሺራክ ሲነግሯቸው፣ ሕገ መንግሥቱን አንቋሸው ውሳኔውን እንዲተገብሩ አዘዙ፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሊዝቡ መንግሥት አልቆየም፡፡ በትንሽ “የእርስ በእርስ ጦርነት “ሥልጣኑን እንዲያጣ ተዳረገ፡፡ የቀድሞ መንግሥት ወታደራዊ መሪ አማፂ ወታደሮች መንግሥቱን እንዲጥሉ ያ የፈረንሥይ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ጀልባዎቹን እስከ መስጠት የዘለቀ ድጋፍ በማድረግ የፕሬዚዳንት ሊዝቡ መንግሥት እንዲወድቅ አደረገች፡፡ ፈረንሣይ ለኮንጎ ብራዛቪል ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆን ያጨችው የቀድሞ መንግሥት ወታደራዊ አዛዥ ሥልጣኑን ተቆናጠጠ፡፡ ፕሬዚዳንት ሊዝቡ ከኮንጎ ነዳጅ ገቢ አገሪቱ 33 በመቶ ማግኘት አለባት ቢሉም፣ ይኼ ዕርምጃቸው ሥልጣናቸውን እንዲያጡ ዳረጋቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የፈለጉት ድርሻ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ 20 በመቶ ኩባንያው በመክፈል የአገሪቱን ነዳጅ ሀብት መበዝበዙን ቀጠለ፡፡ ጉዳዩ በዚህ ተጠናቀቀ፡፡
ከሃያ አምስት ዓመት በፊት የሊዝቡ መንግሥት መገርሰስ ጋር የሚመሳሰል ድርጊት እ.ኤ.አ. በ1974 በኒጀር ተመሳሳይ ድርጊት ተከስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ኒጀርን ያስተዳድሩ የነበሩት ሀማኒ ዶሪ ልክ እንደ ኮንጎ ብራዚቪሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ በወቅቱ ምዕራባውያን ዘመም በመሆኑ የሚታወቀው የኒጀር መንግሥት የኒጀር ዩራኒም ማዕድን በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማራው የፈረንሣይ ግዙፍ ማዕድን አውጪ ኩባንያ፣ ከዩራኒየም ገቢው ለኒጀር የሚሰጠውን አነስተኛ ምጣኔ እንዲያሻሽል መጠየቁን ተከትሎ ፈረንሣይ ጥርስ ውስጥ ገባ፡፡ “በሙስና ተንሰራፍቷል …” ተብሎ መንግሥት እንዲወገድ ተደረገ፡፡ ታዋቂው አፍሪካዊ ጋዜጠኛ ባፉር አንኮ ሃማ ድርጊቱን ማመን ልክ “አሳማ መብረር ይችላል…” እንደ ማለት ይሆናል በማለት ለኒጀር መንግሥት መውደቅ በምዕራባውያኑ የተሰጠውን ምክንያት ያጣጥለዋል፡፡
ኒጀር የምታወጣውን የዩራኒም ማዕድን የምትሸጠው ለፈረንሣይ ነው፡፡ አገሪቱ ይኼንን ውድ የዓለማችን ማዕድን ሀብት ባለቤት ብትሆንም፣ በአፍሪካ እጅግ በድህነት ከሚታወቁ አገሮች አንዷ ከመሆን አልታደጋትም፡፡ የተትረፈረፈ ሀብት ቢኖራትም ኒጀር ዛሬም ከድሆች ተርታ ተሠልፋ እናገኛታለን፡፡
የጋምቢያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ያያ ጃሜ፣ “ለእኔ አገሮች ሦስት በመቶ ወይም አምስት በመቶ ከማዕድን ሀብታቸው ለማግኘት መደራደር እንደ ስድብ እቆጥረዋለሁ፤ ” በማለት የአፍሪካ አገሮች ከተፍጥሮ ሀብቶቻቸው ብዝበዛ እንዲቆም መጠየቃቸውን ይናገሩ ነበር፡፡ ‹‹ለኳታር ኦሚር ሁልጊዜ የምነግራቸው ነገር ቢኖር ከእሳቸው አገር ጋር አገሬ ጋምቢያ መፎካከር ትችላለች፡፡ ሁለቱም አገሮች ትንንሽ ናቸው፡፡ የኳታር ሕዝብ ኑሮ በእጅጉ የተሻሻለው ከጋምቢያ የበለጠ የተትረፈረፈ ጋዝ ክምችት በአገሪቱ መኖሩን አላውቅም…” በማለት ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሁኔታውን አነፃፅረውት ነበር፡፡
“በተቃራኒው እኛ የአፍሪካ መሪዎች አምላክ የሰጠንን የተፈጥሮ ሀብቶች ተገቢውን ገቢ የማግኘት መብታችንን ተነፍገን፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ለሕዝቦቻችን ጥቅምና ኑሮ መሻሻል እንዳንጠቀም በሚያሳፍሩ ድርድሮች ተተብትበናል፡፡ ችግሩ ይኼ ነው፡፡ ምክንያቱም መጥተው አምስት በመቶ እንደሚሰጡና ፕሬዚዳንቱ ምን ያህል ማግኘት እንደሚፈልግ ቢነግሩን ….እንስማማለን! የነዳጅ ሀብቶቹ ግን የፕሬዚዳንቱ ሳይሆን የጋምቢያ ሕዝብ ሀብቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ በጋምቢያ ሕዝብ ስም አምስት በመቶ ወይም አሥር በመቶ አልቀበልም፡፡ ይኼንን የማይረባ መቶኛ ምጣኔ ብቀበል ለጋምቢያ ሕዝብ ምን እነግረዋለሁ? እኛ አሥር በመቶ እናገኛለን፣ እነሱ ደግሞ 90 በመቶ ያገኛሉ ማለት ነው ብለው፣ በአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች ለአኅጉሪቱ ሕዝቦች ጥቅም እየዋሉ አለመሆናቸውን ሞግተው ነበር፡፡
ጃሜ የአምስት በመቶ ምጣኔው ፍትሐዊ አለመሆኑን ሲሞግቱ እ.ኤ.አ. በ2014 በነበረው መረጃ መሠረት፣ “….ዛሬ ነዳጅን ብንወስድ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 100 ዶላር ነው እንበል፡፡ ጋምቢያ አንድ ቢሊዮን በርሜል ነዳጅ ዘይት በዓመት ታመርታለች፡፡ አንድ ቢሊዮን በርሜልን በ100 ዶላር ብናባዛ የሚሰጠን ቁጥር 100 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡ ድሮም ሆነ ዛሬ የነዳጅ ጉርጓድ ለመቆፈርና ሁሉም የካፒታል ወጪ ቢደመር ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ወጪ ነው፡፡ በዘርፉ የተሰማራ ኩባንያ የወጣው ሁለት ቢሊዮን ዶላር የካፒታል ወጪ ለማካካስ አምስት ዓመት ወይም ስድስት ዓመት በቂ ቢሆንም፡፡ ታዲያ አሥር በመቶ ወይም አምስት በመቶ ምጣኔ ለበርካታ ዓመታት እንድንቀበል ይደረጋል?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ “ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ በታች የሆነ የካፒታል ወጪ ለመሸፈን ሲባል አምስት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ በመቀበል ለ35 ዓመታት አገሪቱ መዝለቅ የለባትም፤›› ይሉናል፡፡ ይህንን ያሉት ከሥልጣን ከመወገዳቸው በፊት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ በየችኞቹ የአፍሪካ አገሮች ባልተጻፈ ሕግ፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸው በውጭ ኩባንያዎች በተጠቀሰው መንገድ በልዩ ልዩ መነሻዎች በሚረቀቁ ብቃት የሌላቸው የማዕድን ሕጎች ሲበዘበዙ ይስተዋላል፡፡ በግዴለሽነት፣ በስንፍና፣ በአቅም ማነስ፣ በሙስና፣ በሕገወጥ ቡድኖች በመዘወር ወይም በተለያዩ ኩባንያዎች ተፅዕኖ በእነዚህ የማዕድን ሕጎች አማካይነት፣ የአፍሪካ አገሮች የማዕድን ሀብቶች ለውጭ ኩባንያዎች ማስረከብ የተለመደ አሠራር ሆኗል፡፡
ፓን አፍሪካዊነትን የሚያቀነቅነው ታዋቂው ኒው አፍሪካ መጽሔት እ.ኤ.አ. በፌቡሩዋሪ 2004 ዕትሙ፣ “Solving The Great Conundrum…How African Can Own Its Natural Resources” በሚል ርዕስ በሰጠው የሽፋን ዘገባው የአፍሪካ ታላቁ እንቆቅልሽ፣ አፍሪካውያን እንዴት የተፈጥሮ ሀብቶቻቸው ባለቤት ይሆናሉ ብሎ ይሞግታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2003 የጋና ፓርላማ የማዕድን ሕግን ለማሻሽል ሲሞክር አስደንጋጭ ነገር ገጠመው፡፡ የማዕድን አምራች ኩባንያዎች ከዘርፉ የሚያገኙትን ገቢ በውጭ አገር በሚከፍቱት ባንክ እንዲቀመጥ መፍቀዱን ጨምሮ፣ የአገሪቱን የማዕድን ሀብቶች ባለሀብቶቹ እንደፈለጉ የሚያባክኑበት ክፍተቶች ያሉበትን ሕግ ማፅደቁ ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል፡፡
የጋና ፓርላማ የመንግሥት ፋይናንስ ኮሚቴ በድንገት አገሪቱ ባለፉት መንግሥታትም ሆነ እስከ እ.ኤ.አ. 2003 ድረስ ጋና የማዕድን ሀብቶቿን በተመለከተ ያወጣቻቸውን ሕጎችና የተፈራረመቻቸውን ስምምነቶች ሲፈትሽ በደረሰበት ግኝት ተደናግጧል፡፡ በጋና የቀድሞ መንግሥታት የተፈረሙ የማዕድናት ሕጎችን በተመለከተ አገሪቱ የተፈራረመቻቸው አብዛኞቹ ስምምነቶች ለውጭ የማዕድን አውጭ ኩባንያዎች እጅግ ያጋደሉ መሆናቸው ተደረሰበት፡፡ በጋና ፕሬዚዳንት የሕፈት ቤት የፖሊሲ ግምገማና ክትትል ኃላፊ ዶ/ር ቶኒ አይዶ፣ እንዲህ ካለ ዘረፋ የጋና የተፈጥሮ ሀብቶች ከመሬት ሳይወጡ ቢቀሩ እንደሚሻል ተናግረው ነበር፡፡ ወደፊት አንድ ቀን አገር በቀል (ባህላዊ) ማዕድን አውጪዎች ምንም ያህል ኋላ ቀር ዘዴ ቢጠቀሙም፣ አቅማቸውን በማሳደግ ለአገር ጥቅም እንጂ ለውጭ ኩባንያዎች እንዳይውሉ ማድረግ እንደሚመርጡ ተናግረው ነበር፡፡ በተነፃፃሪ ጋና ከአፍሪካ አገሮች የማዕድን ሀብቷን ለሕዝቧ ጥቅም በማዋል ረገድ የተሻለች እንደሆነች ይነገራል፡፡
የጋና የመሬትና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የጋናን የማዕድን ዘርፍ የሚከታተልና በማዕድን ፍለጋና ማውጣት ለሚሰማሩ ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን አለው፡፡ በሚኒስቴሩ ሥር የማዕድን ኮሚሽን የተዋቀረ ሲሆን፣ የማዕድን ሕግን የሚከታተልና የማዕድን ፖሊሲ አፈጻጸም የሚከታተል ነው፡፡ ኮሚሽኑ የማዕድን ልማትን ለማስፋፋት መንግሥትን በዘርፉ የሚያማክር እንደሆነ ይነገራል፡፡ የጋና የከበሩ ማዕድናት ገበያ ኮርፖሬሽን መንግሥታዊ ድርጅት ሲሆን፣ አነስተኛና ጥቃቅን እንዲሁም ባህላዊ የማዕድን አውጪዎችን በተለይ የወርቅና የአልማዝ ንግድ ልማት ላይ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ የማዕድን ውጤቶችን በቀጥታ ወይም ፈቃድ ከተሰጣቸው አካላት የመግዛት ኃላፊነትም ተጥሎበታል፡፡ የማዕድን መምርያው የማዕድን የሥራ ደኅንነትና ጥንቃቄ ይከታተላል፡፡ የጋና ጂኦሎጂ ሰርቬይ መምርያ ጂኦሎጂካል ጥናቶችን በማከናወን ዘርፉን ያግዛል፡፡ የጋና ብሔራዊ ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ደግሞ መንግሥታዊ ድርጅት ሲሆን፣ ለአገሪቱ የነዳጅ ፍለጋና ምርት ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው፡፡
የጋና የማዕድን ንግድ ምክር ቤት በማዕድን የተሰማሩ የግል ኩባንያዎች ማኅበር ሲሆን፣ በዘርፉ ጤናማ ንግድ እንዲኖር የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ ምክር ቤቱ ለኅብረተሰቡ ስለጋና የማዕድን ዘርፍ መረጃ በመስጠትና ከዘርፉ የሠራተኞች ማኅበራት ጋር በመደራደር ይሠራል፡፡ በማዕድን ዙርያ የሚደርሱ አደጋዎች ሪፖርት የሚቀርቡት ለጋና ማዕድን ንግድ ምክር ቤት ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ስለማዕድን ሕግ መረጃ መስጠትና ከዘርፉ ሠራተኛ ማኅበራት ጋር አባል ኩባንያዎቹን ወክሎ ይደራደራል፡፡ የጋና ማዕድን ተመጣጣኝ የሮያሊቲ ምጣኔና 45 በመቶ የቀረጥ ሥርዓት ደንግጓል (በአገራችን ሕግ ግን 35 በመቶ መሆኑን ልብ ይበሉ)፡፡
የኢትዮጵያን ማዕድን በጨረፍታ
ፖታሽ በማዕድን መልክ የሚመረት የሟሟ ፖታሽየም የተሰኘ ንጥረ ነገር የያዘ ጨው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለማዳበሪያ በዓለም ዙሪያ በዓመት 30 ሚሊዮን ቶን ይመረታል፡፡ ፖታሽ ጨርቃ ጨርቅ ለማንጣት፣ ለመስታወት ለሳሙና ማምረት፣ ማዳበሪያን ጨምሮ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለማችን በፖታሽ ክምችቷ ቀዳሚዋ መሆኗና ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ መመረት እንደ ጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአፋር ክልል በዳሎል እ.ኤ.አ. ከ1900 ዓ.ም. የመጀመርያው የጣሊያን ኩባንያ የፖታሽ ማዕድን ያመርት ነበር፡፡ በኋላ በ1960ዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፒርሰን ኩባንያ በዳሎል ከተማ የፖታሽ ፋብሪካ በማቋቋም ያመርትበት የነበሩት ቁሳቁሶችና መኪናዎች የጨው ዓምድ ውጧቸው ተቀብረው ይታያሉ፡፡ በአንድ ወቅት ከዳሎል እስከ አስመራ በተዘረጋው ባቡር ሐዲድ የፖታሽ ምርትን ኢትዮጵያ እስከ ህንድና ሌሎች የዓለም ገበያ ታቀርብ ነበር፡፡
ዳሎል በምድራችን በጣም ሞቃታማ ከሚባሉ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ መንገድ ባለመኖሩ የጨው ምርቱ በግመል ይጓጓዝ ነበር፡፡ በኤርትራ ከሚገኘው የመርሳ ወደብ እስከ ዳሎል ድረስ 28 ኪሎ ሜትር የሚዘልቅ የባቡር መስመር ተሠርቶ እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 1918 ተጠናቀቀ፡፡ የባቡር መንገዱ ከተሠራ በኋላ 50,000 ሜትሪክ ቶን ፖታሽ ይመረት የነበረ ሲሆን፣ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ማቋረጡን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በጀርመን፣ በዩናይትድ ስቴትስና የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት በብዛት መመረት መጀመሩ ይጠቀሳል፡፡ የፖታሽ ምርት እ.ኤ.አ. ከ1920 እስከ 1929 በጣሊያን ኩባንያ ማምረቱን ጀምሮ 25,000 ቶን በማምረት ወደ ውጭ የተላከ ሲሆን፣ በዳሎል አስመራ ኩባንያ እ.ኤ.አ. ከ1951 እስከ 1953 የተወሰኑ ፖታሽ ቶን ወደ ህንድ መላክ ችሎ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960ዎች የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ፒርሰን ኩባንያ ጆሎጂካል ሰርቬይ አካሂዶ ወደ ማምረት ገብቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1965 ብቻ 10,000 ጉድጓዶችን በ65 ቦታዎች በዳሎል አካባቢዎች ቆፍሮ ፖታሽን ሲያመርት ከቆየ በኃላ፣ ኩባንያው ባልታወቀ ምክንያት ሥራውን እርግፍ አድርጎ ትቶ ወጣ፡፡
ታዋቂው የማዳበሪያ አምራች ያራ ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ. በ2018 ፖታሽ ለማምረት ዕቅድ እንዳለውና የተለያዩ ኩባንያዎች የናይጄሪያዊው ቱጃር አሊኮ ዳንጎቴን ጨምሮ፣ በፖታሽ ምርት ዙሪያ ለሚመለከተው መንግሥት አካል ፕሮጀክት ማስገባታቸውን የእንግሊዝኛ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ (በነገራችን ላይ የማዕድን ዜናዎች የሚበዙት በአገራችን በእንግሊዝኛ በሚታተሙ ጋዜጦች ነው፡፡ ምክንያቱም ኩባንያዎቹ መንግሥትንም ሆነ የፋይናንስ ተቋማትን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የሚፈልጉበት አዝማሚያ መረዳት ይቻላል)፡፡
ዳሎልን ጨምሮ የአገራችንን ልዩ ልዩ የማዕድንና የኢነርጂ መገኛ ሥፍራዎችን፣ ካርታዎችንና ጥናቶችን የሚያውቁ ዘርፉን የሚያሽከረክሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አሉ፡፡ በፖታሽ ዘርፍም መሰል ነገር እታየ ይመስላል፡፡ ወደ ኋላ ሄዳችሁ የማዕድን ዘርፉን ዘገባዎች ብትፈትሹ ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡
የማዕድን ፈቃድ በማውጣት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በማዕድን ሕጉ በተቀመጠ አንቀጽ በመጠቀም ድርሻቸውን እያስተላለፉ ቀስ በቀስ እየወጡ፣ ኩባንያውን በሕጋዊ መንገድ በውጭ ዜጎች እጅ በተዘዋዋሪ እንዲወድቅ ማድረግ የተለመደ አሠራር እየሆነ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ በፖታሽ ምርት ቀዳሚ ብትሆንም፣ ኩባንያዎቹ በፍጥነት ወደ ሥራ ገብተው አገራችን ከዘርፉ ተጠቃሚ እየሆነች ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ጣሂር ሻህ “King Solomon’s Mines” መጽሐፉ (የኢትዮጵያ የወርቅ ሚስጥር ከንግሥት ሣባ እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን በሚል ርዕስ የደራሲ ጣሂር ሻህ ጋዜጠኛ ብሩክ መኰንን ተክለየስና አቶ እንቆጳዚዮን ሀብታሙ ጃካሞ ተርጉመውት ነበር)፡፡ ሃይተር በዚህ መጽሐፉ የኢትዮጵያን የወርቅ ማዕድን ሚስጥር፣ “….የማነበው መጽሐፍ የፊት ሽፋን ከላይኛው ከንፈሩ በላይ ያለውን ጺሙን ያሳደገው ኸይተር ሄልሜት ጭንቅላቱ ላይ አድርጎ የሳፋሪ ሸሚዝና ቁምጣ ለብሶ፣ እንዲሁም ረዥም የሲጋራ መሰኪያ ቀፎ ከንፈሩ መሀል ሰክቶ ይታያል፡፡ ከጀርባው ትልቅ የተዠጎረጎረ የነብር ቆዳ ተሰቅሏል፡፡ የመጽሐፉን የመጀመርያው ምዕራፍ ያለማቋረጥ አንብቤ ጨረስኩ፤” ይላል፡፡
ጣሂር ስለ ፍራንክ ኸይተር ሲናገር እ.ኤ.አ. በ1902 በዌልስ የጠረፍ ከተማ ውስጥ ከአንድ በግብርና ከሚተዳደር ቤተሰብ ተወለደ መሆኑን፣ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ታላቅ አዳኝ የመሆንና በጭለማው አኅጉር ጉዞ የማድረግ ህልም ነበረው፡፡ ህልሙን ዕውን ማደረግ የሚችልበት የመጀመርያው አጋጣሚ የተፈጠረው ለንደን ውስጥ በአንድ የዱር እንሰሳት ማሳያ ቦታ፣ የእንሰሳትን ሙሉ አካል የማድረቅ ሥራ ለመሥራት መቀጠሩን የጻፈው ጣሂር፣ በሚሠራው ሥራ ኩራት ይሰማው ነበር ይለናል፡፡ “…በአፍሪካ አንድ ያልተለመደ ጉዞውን የሚያደርገው ወደ አቢሲኒያ ሲሆን፣ የጉዞው ዓላማ ለእንሰሳት ማሳያ ድርጅቱ መቶ ዝንጀሮዎችን ይዞ ለመምጣት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1924 ኸይተር በባቡር ተሳፍሮ ወደ ማርሴይ ከተጓዘ በኃላ ከማርሴይ በሞተር ጀልባ ጅቡቲ ገባ፡፡ ከጂቡቲ በባቡር ወደ ድሬዳዋ ተጓዘ፡፡ በዚያን ጊዜ አሁን ጭር ያለው የባቡር መተላለፊያ ከተማ ግሪኮችና አርመኖች ማንኛውንም የንግድ ሥራ የሚያካሂዱበት፣ ከደንከል በረሃ የሚመጡ ጦረኞች ጋሻቸውን ከፍ አድርገው ይዘውና አንገታቸው ላይ የወንድ ብልት አንጠልጥለው የሚንጎራደዱበትና ወከባ የበዛበት ነበር፡፡ ኸይተር ከሐረር ከተማ ወጣ ባለ ቦታ ድንኳን ተክላ የተቀመጠች ብሩህ አዕምሮ ያላትና በአካባቢው ታዋቂ ከሆነችው ሮዚታ ፎርበት ከምትባል ተጓዥ ሴት ጋር ተዋውቆ ነበር፡፡
‹‹….ኸይተር በሚያስገርም ሁኔታ መቶ ዝንጀሮዎች ይዞ ወደ አገሩ በመመለስ ተልዕኮውን አጠናቀቀ፡፡ ሆኖም እንስሳቱን ይዞ ሲጓዝ ቅዱሶቹን እንስሳት ሰርቀሀል በማለት አንድ መንኩሴ ረግመውት ነበር፡፡ ኸይተር የመነኩሴውን እርግማን ከምንም ባለመቁጠር ዝንጀሮዎችን በመርከብ ጭኖ ወደ ለንደን ወሰዳቸው፡፡ ዝንጀሮዎቹን መርከብ ላይ የጫኑት ምንም ቦታ ክፍተት በሌለው ሳጥን ውስጥ ታሽጎባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሌሊት ላይ የባህር ማዕበል ተነስቶ መርከቡ ላይ የተጫኑት ሳጥኖች ተሰባበሩ፡፡ ሳጥኖቹ ውስጥ የነበሩ ዝንጀሮዎች ረብሻ ሲፈጥሩ የመነኩሴው እርግማን ውጤት ታየ፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታት ኸይተር ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መጥቷል፡፡ በዚች አገር ተለክፎ ነበር፡፡ በኑሮው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ወደ ሩቅ ቦታዎች ሲጓዝ ብዙ መከራ ድርሶበታል፡፡ አይጥና ቢራቢቢሮ አዳኝ ሆኖ ሲሠራ ቢቆይም ስሙ በስፋት የሚነሳው ግን በወርቅ አሳሽነት ሥራው ነው፤” ብሎ በመጽሐፉ ያትታል፡፡
እንደ ጣሂር መጽሐፍ እ.ኤ.አ. በ1920ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ውዥንብር ነግሦ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ዳግማዊ ምንሊክ ግዛታቸውን ለውጭው ዓለም ክፍት በማድረግ ሥልጣኔ ለማስፋፋት ሞክረው የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በገባር የአገዛዝ ሥርዓት ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ በጣት የሚቆጠሩ አውሮፓውያን የአገሪቱን ኋላ ቀርነት በመገንዘብ የቅንጦት ዕቃዎች የመግዛት አቅም ላላቸው ሰዎች በመሸጥ ሀብት ሲያካብቱ፣ ሌሎች አውሮፓውያን ደግሞ የከበሩ ማዕድናት ያሉበትን ቦታ ከመንግሥት በኪራይ እየወሰዱ ወርቅ በማውጣት ሥራ ተሰማርተው ነበር፡፡ ፍራንክ ኸይተር ወንዞችን በመገደብና ያልተነካ የወርቅ ክምችት የሚገኝባቸውን በምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ያሉ ቦታዎችን ብቻውን በመቆፈር ብዙ ዓመታት አሳልፏል፡፡ የአካባቢው ሰዎች “አባ ኩታ” (የእብደት አባት) በሚል ቅጽል ስም ነበር የሚጠሩት፡፡ የአካባቢው ሰዎች ለኸይተር ይኼን ቅጽል ስም የሰጡበት ምክንያት እንደሱ ያለ የማይታክት ወርቅ አሳሽ አይተው ስለማያውቁ ነበር፡፡
ወርቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ከመሬት እየተቆፈረ ስለመውጣቱና በአካባቢው ወርቅ የማውጣት ሥራ ስለመካሄዱ ኸይተር እርግጠኛ ነበር፡፡ በኸይተር አመለካከት ኢትዮጵያ ጠቢቡን ንጉሥ በወርቅ ለማንቆጥቆጥ ወደ እየሩሳሌም ጉዞ ያደረገችው የንግሥት ሳባ ግዛት ነበረች፡፡ በሰሜን ተራሮች ውስጥ ዱካቸው የጠፋ በአንድ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ወርቅ ይወጣባቸው የነበሩ የዋሻ ሰንሰለቶች እንደነበሩ ኸይተር ያምናል፡፡ በዋሻዎች መግቢያ ላይ በተሠሩ ገዳማት ውስጥ የሚኖሩ መነኩሳት የውጭ ዜጎች በወርቅ ወደ ተሞሉት ዋሻዎች እንዳይገቡ እንደሚከላከሉና “የታላቋን …ንግሥት” መመለስ እንደሚጠብቁ ሰምቷል፡፡ በወርቅ ፍለጋ ብቻውን ሲባዝን ቆይቶ ቱሉ ወለል ከሚባል ተራራ ላይ መግቢያቸው በጥርብ ድንጋዮች የተዘጋ ወደ ወርቅ ማውጫ ጉድጓዶች የሚያስገቡ ዋሻዎችን አግኝቶ ነበር ፡፡
በዋሻው ውስጥ ያሉ አውሬዎችን እንዳይረብሽ በመፍራት ኸይተር በአንደኛው መግቢያ በቀስታ ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ከዚያም “አንድ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የተደበቀ ሀብት አገኘሁ፤” ይላል፡፡ ሆኖም ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ማውጣት ከመጀመሩ በፊት… በዋሻው ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት የሚፈስ ደራሽ ጎርፍ ስለመጣበት ከዋሻው ለመውጣት ተገደደ፡፡ አዳዲስ ቁሳቁሶች ይዞ ወደ ዋሻው ተመልሶ ሲመጣ የዋሻዎቹን መግቢያ ለማግኘት የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡
“Search of King Solomon’s Mine” በሚል ርዕስ በተጻፈው የጣሂር ሻህ መጽሐፍ፣ ‹‹ተጨማሪ መረጃ ሊሰጠው የሚችል አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ አውቅ ነበር … አዲስ አበባ ስንደርስ ስለ ፍረንክ ኸይተርና ስለ ቱሉ ወለል የበለጠ ማወቅ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ዶ/ር ፓንክረስት በኢትዮጵያ ኅብረተሰብና ታሪክ ዙሪያ ጥልቅ የምርምር በማካሄድ ይታወቃሉ፤›› በማለት፣ ስለቱሉ ወለል ወይም ፍረንክ ኸይተር ሰምተው ያውቁ እንደሆነ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን ይጠይቃቸዋል፡፡
“…..እንደ ማስታውሰው ከሆነ ቱሉ ወለል ከቤንሻንጉል ብዙም የማይርቅ ቦታ ነው፡፡ አካባቢው ጥራት ያለው ወርቅ የሚገኝበት መሆኑ በታሪክ ይታወቃል፡፡ ምኒልክ ቦታውን በ1886 ዓ.ም. የተቆጣጠሩት፣ በዚያ አካባቢ ያለውን የማዕድን ሀብት ለመጠቀም አስበው ነበር፡፡ የማዕድን ሀብቱን እንዲያወጣም ኢልግ ለሚባል ሰው ፈቃድ ሰጥተው ነበር፡፡ ሰውዬው ነጆ ውስጥ የጥንት ግብፃውያን ወርቅ ያወጡበት እንደነበር የገመተውን ቦታ አገኘ፤” ይላል፡፡ የዚያን ዕለት ፓንክረስት ስለጠቀሱለት ሰዎች የተጻፈ ነገር እንዳለ ለማረጋገጥ ያመጣቸውን መጽሐፎች አንድ ባንድ አሰሳቸው፡፡ ግሪካዊ የሥነ ምድር ባለሙያ አጋታኪደስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ140 ዓ.ም. የጻፈው መጽሐፍ የጦር እስረኞች ወርቅ በቁፋሮ በማውጣት አገልግሎት እንዲሰጡ ስለሚደረግበት ሁኔታ ይናገራል፡፡ “ብዛት ያላቸው የጦር እስረኞች በብረት ሰንሰለት ታስረው ቀንና ሌሊት እንዲሠሩ ይገደዳሉ፡፡ እስረኞቹ የማያውቁትን ቋንቋ በሚያወሩ ይጠበቁ ስለነበር የማምለጥ ተስፋ አልነበራቸውም፤” በማለት ጽፏል፡፡
አጋታኪድስ ከሞተ ከሰባት ምዕተ ዓመታት በኋላ ኮስሞስ የሚባል የግሪክ ቋንቋ የሚናገር ነጋዴ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ምዕራባዊ ጠረፍ አካባቢ ዕጣንና ወርቅ የሚገኝበት ቦታ እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ ኮስሞስ በ524 ዓ.ም. በወቅቱ የአክሱም ግዛት ከነበረችው የአዱሊስ ወደብ ሲደርስ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የአገው ጎሳዎች ወርቅ ማውጣት ሥራ እንደሚሠሩ፣ የሥነ ማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች አዝጋሚ የንግድ ሥርዓት በሚገልጹት ዕቃን በመለዋወጥ ላይ የተመሠረተ ንግድ ያካሂዱ እንደነበር መስማቱን ተናግሯል፡፡ በየዓመቱ የአክሱም ንጉሥ ከአገዎች ጋር የንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ወኪሎችን ይልክ ነበር፡፡ ወኪሎች በብዙ ጠባቂዎች ታጅበው ከብት፣ ብረት፣ ጨውና ሌሎች ሸቀጦችን በማቅረብ በልዋጩ ወርቅ ይገዛሉ፡፡ የንግድ ልውውጥ በሚደረግበት ቦታ ድንኳን በመትከል ዙሪያውን በእሾሃማ እንጨት ያጥራሉ፡፡ የበሬ ሥጋና ሌሎች ሸቀጦች አጥሩ ላይ ይሰቅላሉ፡፡ ምሽት ላይ አገዎች የሚፈልጉትን ዕቃ በመውሰድ በምትኩ የወርቅ እንክብሎች ያስቀምጣሉ፡፡
ኮስሞስ አካባቢውን ከጎበኘ ከአንድ ሺሕ ዓመታት በኋላ ፖርቹጋላዊ ተጓዥና ፓትሪያሪክ ሁዋን ደ ቤርሙዴዝ የዓባይ ወንዝን ተከትሎ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጉዞ አድርጓል፡፡ “የሀብት ጌታ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው ቤርሙዴዝ በስሙ የተሰየመችው በካሪቢያን አካባቢ ያለችውን የቤርሙዳ ደሴት በማግኘቱ ዕውቅና ያገኘ ሰው ነው፡፡ ቤርሙዳ ደሴትን ያገኛት ከቨርጂኒያ ተነስቶ የባህር ጉዞ ሲያደርግ መርከቡ ስለተሰበረችበት ማረፊያ መሬት ሲፈልግ ነው፡፡ ቤርሙዴዝ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተራቆተ፣ ነገር ግን ሁለት እጁ ወርቅና ሲሶው ደግሞ ቀይ አፈር ያለበት ምድር መሆኑን መናገሩን ጣሂር በመጽሐፉ አስፍሯል፡፡ ይኼ የጣሂር ሻህ መጽሐፍ ስለአገራችን የወርቅና ማዕድን ሀብቶቻችን የሚነግረን ብዙ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የተለያዩ የኅትመት ወጤቶች የሚሰጡን መረጃዎች አሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በጁላይ 1998 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ አንድ በየአካባቢው ታሪክ መረጃዎችንና ምንጮችን ማሰባሰብና ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ፕሮጀክት ተጀምሮ ነበር፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በዕርዳታ የሰጠው የኢጣሊያ የትብብር ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት የተሠራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአፍሪካ የዓረብ አገሮች ጥናትና ምርምር ክፍል ኔፕልስ ኦሪያንታል ምርምር ክፍል ትብብር “የወለጋ የታሪክ ሰነዶች እ.ኤ.አ. ከ1880ዎቹ እስከ 1920ዎቹ ” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ በአሌክሳንድሮ ትሪዮልዚና ተሰማ ታዓ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ1997 ዓ.ም. ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡ በዘመኑ የነበሩ ነገሥታት ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች ጋር ያካሄዱትን የደብዳቤ ልውውጦች የያዘ ታሪካዊ ሰነድ ብቻ ሳይሆን፣ የወርቅ ማዕድን በውጭ ኃይሎች እንዴት ይመዘበር እንደነበር ይጠቁማል፡፡
ጃንሆይ
….እነዚህ ነጆ ያሉት ፈረንጆች ዘንድሮ በሰኔ ጀመሩ፡፡ እኔ ካዲስ አበባ ሳለሁ እስከ ዛሬ ድረስ ከዚህ ከነጆ ያለውን አገር ዙሪያ ገባውን ሁሉ እየዞሩ በተራራ በተራራው በየጎብታው ሁሉ ባንዲራ ይተክላሉ፡፡ እኔ ደሞ ይኸ ባንዲራ መትከል የወርቅ ሥራ አይደለም ምንድን ነው ነገሩ ብዬ ብጠይቃቸው፣ ያገሩን እሩቅነትና ቅርብነቱን ለማወቅ ነው አሉኝ፡፡ ቅርብነቱና እርቀቱ በባንዲራ አይታወቅም ነበር፡፡ ሐምሌ 28 ቀን 1898 ዓ.ም. (የወለጋ የታሪክ ሰነዶች እ.ኤ.አ. ከ1880ዎቹ እስከ 1920ዎቹ) ጃንሆይ
……ከነጆ ካሉት ከፈረንጆች ጋር ወርቁን ሥራ ተጠባበቁ ያሉኝን የዕለት የለቱን የአንዳንድ ቀኑን አሳዩኝ ብላቸው፣ ከመኪናው ባንድ ወር የተሠራውን አንድ ቀን ይወጣል እንጂ የዕለት የዕለቱን አይወጣም አሉኝ፡፡ ባንድ ወር ተሠራውን ከመኪናው አውጥተው ከነባዚቃው ብንመዝነው ሰባ ስድስት ወቄት ወርቅ ሆነ፡፡ ደግሞም ከነባዚቃው ማለቴ በጣም ተጠምቆ ዕቃ እንደሚቀባ ሆኖ ነው፡፡ ይኼንንም ከነባዚቃው ሰባ ስድስት ወቄት ሆነ፡፡ ዛሬ ዕለት የወጣውን ዕለቱን ይነጠርና ልየው ብላቸው ዛሬ አናነጥረውም አይሆንም ይደር አሉኝ፡፡ ወርቁ ከነሱ እጅ አደረ፡፡ አድሮ ከኛ ፊት አነጠሩት፡፡ ቢነጠር 13 ወቄት ከአላድ ሆነ፡፡ ነገር ግን ዕለት የወጣውን የለቱን ብናነጥረው መልካም ነው፡፡ እነሱ እጅ አድሮ በማግስቱ ብናነጥረው ቢሰርቁስ በምን ይታወቃል?
ነሐሴ 28 ቀን 1898 ተጻፈ (የወለጋ የታሪክ ሰነዶች እ.ኤ.አ. ከ1880ዎቹ እስከ 1920ዎቹ)
የቺካጎ ታይምስ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. በ1928 ዘገባው ጣሊያን ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ የወረረችው በዓድዋ ጦርነት የተከናነበችውን “ውርደት” ለመበቀል እንደሆነ፣ የሚቀርበውን የታሪክ ሀተታ ብቸኛ ምክንያት አለመሆኑን ይጠቅሳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1928 ቺካጎ ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ይዞ በወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት መነሻ በጣሊያንና በእንግሊዝን ፉክክር የተነሳ ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቱ እንደምትወረር ይጠቁም ነበር፡፡ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያንና እንግሊዝ የአገሪቱን ሕዝቦች በጎሳ (Ethinic Group) በመከፋፈልና ቁርሾ በመፍጠር የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት፣ ዛሬም ለእርስ በእርስ ግጭቶች መንስዔ እንደሆኑ የሚከራከሩ አሉ፡፡ ቺካጎ ሰንደይ ታይምስ እ.ኤ.አ. በ1928 ለንባብ ባበቃው ዘገባው ፍራንክ ኸይተር በጻፈው መጽሐፉ፣ የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ኢትዮጵያ ያለውን ወርቅ ሞሶሎኒ አይቆጣጠረውም፣ ያንን ሀብት የሚያገኝ ቢኖር ታላቋ ብሪታኒያ መሆን አለባት ብሎ መናገሩን ጠቁሞ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 52 የፌዴራል የኢኮኖሚ ነክ ዓላማዎች አንቀጽ 89 ንዑስ አንቀጽ 5 “መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን ለሕዝቡ የጋራ ጥቅምና ዕድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፤” በማለት ደንግጓል፡፡ ‹‹ፌዴራል መንግሥት ሥልጣን የመሬት፣ ተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤›› ተብሎም ተቀምጧል፡፡ በአገራችንን በየትኛውም ጥግ የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት የአገሪቱ ሕዝቦች በመሆኑ፣ ለአገሪቱ ሕዝቦች ኑሮ መሻሻልና ዘላቂ ልማት በሚያረጋግጥ ረገድ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እንዲኖር የማዕድን ሕጎቻችን በአግባቡ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን አሁን በአፍሪካ ኅብረት “African Mining Vision” (የአፍሪካ ማዕድን ራዕይ) የሚል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የአፍሪካን ማዕድን ሀብቶች ለዘላቂ ልማት ማዋል ስለሚቻልበት ሁኔታ ብርቱ ክርክር ይደረጋል፡፡ የማዕድን ዘርፍን መቆጣጠር የሚችል ጠንካራ ሕግና አሠራር መዘርጋት የሁሉም አገሮች ፈተና እየሆነ መጥቷል፡፡ አገራችንም ይኼንን ዘርፍ በአግባቡ አይኗን ከፍታ መመልከት ካልቻለች የምናጣው ብዙ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡