Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅኢትዮጵያ የጉዞ ታላቅ መዳረሻ

ኢትዮጵያ የጉዞ ታላቅ መዳረሻ

ቀን:

የአሜሪካው ዜና ማሠራጫ ሲኤንኤን፣ በትራቭል ገጹ ኢትዮጵያ ለጉዞ ታላቅ መዳረሻነት የሚያበቋት 14 ምክንያቶችን በፎቶ አማካይነት ዘርዝሯል፡፡ እነርሱም ጭላዳ ዝንጀሮ (ስሜን ፓርክ)፣ የገረዓልታ መልክዐ ምድር (ምስሉ የሚታየው)፣ ኤርታሌ፣ ቆነጃጅት፣ የቡና ባህላዊ ሥርዓት፣ ፋሲል ግንብ፣ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ፣ ታላቁ ሩጫ፣ ጫሞ ሐይቅ፣ የሙርሲ ባልቴት (ምስሉ የሚታየው)፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ጣና ገዳማት፣ እንጀራና ወጥ፣  የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መኝታ ቤት ናቸው፡፡

ቀብር ድረሱ

      የግዕዝን ተስካር ገና ሳናወጣ

አማርኛ ሞተ ኑ ቀብር እንውጣ

ቅርብ ቀን አግኝቼው ምን አገኘውና

አምሮበት ተስማምቶት አልነበር በደህና?

      ነገሩ ወዲህ ነው አለው ብዙ ሚስጥር  

ግዕዝ ታላቅ ሆኖ በይፋ ሲነገር

አማርኛ ደግሞ ገና ጨቅላ ነበር

እምብዛም ያልወጣ ከነገሥታት መንደር

            ኋላም ሲጎረምስ ሕግን ተላለፈ

አባቱን ናቀና በኩራት ከነፈ

ራሱን ለመሾም ግዕዝን ሊጎዳ

እየገፈተረ ሰደደው በሜዳ

      ግዕዝም ቢጨንቀው በተስኪያን ተጠጋ

      እሷም እቅፍ አድርጋ ያዘችው ሸሽጋ

      ከሚኖሩት አንሶ ከሞቱት ተሽሎ

      እነሆ ይኖራል አልቦ ዘመድ ብሎ

አማርኛ ግና ግፍ አለበትና

ይሰፈር ጀምሯል በሰፈረው ቁና

ጉድጓዱ ሊማስ ነው ዛሬ ቀኑ ደርሶ

ሸጋው የእንግሊዝ አፍ በየቦታው ነግሶ

  • አምደወርቅ ኃይለማርያም

******

የአራት ወር እስራት

ፕራግ ሚሮስላቭ ብሬፕታ የተባለ ሰው በትራም [ቀላል ባቡር] ውስጥ ተቀምጦ ሲሄድ የኮሚኒስትን መንግሥት በማማቱ የአራት ወር እስራት የተፈረደበት መሆኑን ‹‹ቬሴርኒ ፕራሐ›› የተባለው የፕራግ ጋዜጣ አስታውቋል፡፡ ተናገረ የተባለውም ቃል ከዚህ የሚከተለው ነው፡፡

‹‹በገንዘብህ አንዳች ነገር መሥራት በማይቻልበት ጊዜ ዛሬ መሥራት ዋጋ ያለው ነውን? ዕቃዎች የሉም፡፡ ለምሳሌ የአልጋ ልብስ አንሶላ እንኳ የለም፡፡ እንዲሁም ሻማዎች፣ ስፓርታክ አውቶሞቢል፣ የቴሌቪዥን ራዲዮኖች የሉም፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚገርመው ነገር የጥቃቅን ክብሪቶች እንኳ መታጣት ነው ዋናው ነገር የተያዘውን ፕላን በመቶ አርባ ከፍ ማድረግ ስላለብን ይሆናል፡፡  

– የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ (ሐምሌ 2 ቀን 1950 ዓ.ም.)

********

‹‹ኢትዮጵያ ንቂ የልጆችሽንም ጩኸት አድምጪ››

ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጉዳዮች በራሳቸው ይመካሉ፡፡ ከነሱም ሌላ በኢትዮጵያ የሚመኩ አሉ ብዙ ጥቁር ሕዝቦች፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከሰሜን አሜሪካ በስተደቡብ በሚገኙ ደሴቶች ውስጥ የሚኖሩት የዌስት ኢንዲያን ጥቁሮች ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ጃማይካውያን፡፡ እነዚህ በራስ ተፈሪ ስም ራስ ተፈሪያን የሚባል ቡድን አቋቁመው ኢትዮጵያ መመኪያ ሀገራቸው እንደሆነች ይከራከራሉ፡፡ አብርሃም በእግዚአብሔር ጥሪ ከከሃዲዎቹ ሀገር ከካራን ወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ወደ እግዚአብሔር ሀገር ወደ ከነዓን እንደሄደ የነሱም የተስፋ ምድራቸው ሀገር እግዚአብሔር ኢትዮጵያ እንደሆነች ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ነው በሕይወታቸውና የሕይወታቸው መግለጫ በሆነው በሥነ ጽሑፋቸው ውስጥ ኢትዮጵያ ገንና የምትገኘው፡፡

ዌስት ኢንዲያንስ ምንጫቸው አፍሪካ እንደሆነች ያምናሉ፡፡ የማንነታቸው መገኛ እንደምትሆንም ይገምታሉ፡፡ በአ.አርዳቶርኔ መጽሐፍ The scholar Man ውስጥ ያለው የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ አዳም ኩየስተስ የማንነቱን ጉዳይ አንስቶ ሲናገር ‹‹የራሴ ታሪክ ኖሮኝ  እንዳደገ ሰው ስለራሴ ምንም ነገር አላውቅም፡፡ የማውቀው ያልሆንኩትን ብቻ ነው፡፡ እንግሊዛዊ አይደለሁም እንደምገምተው እንዲያውም ዌስት ኢንዲያንም አይደለሁም›› ይላል፡፡ ትግሉ ማን እንደሆነ ለማወቅ ነው፡፡

በዚህ የማንነት ፍለጋ ውስጥ ነው አፍሪካ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ የማንነታቸው ተምሳሌት ሆና በየድርሰቶቻቸው ውስጥ የምትገለፀው፡፡ በሲልቪያ ዋይንተር በተጻፈው ‹‹The Hills of Hebron›› በሚለው ድርሰት ውስጥ ፀጉሩ የተንዠረገገውና ፂማሙ ራስታ ሲታሠር በፖሊስ መኪና ፊት ተንበርክኮ በጥልቅ ስሜት፤

ኢትዮጵያ ንቂ የልጆችሽንም ጩኸት አድምጪ

ኢትዮጵያ ዛሬ ነፃ ናት፤ የኛም ለቅሶ በምድሪቱ ያስተጋባል

ኢትዮጵያ ንቂ፣ ንጋታችን በእጃችን ናትና፡፡ እያለ ይዘምራል፡፡ The Children of Sisyphus በሚለው በኦርላንዶ ፓተርሰን ድርሰት ውጥ ያለው የራስ ተፈሪያውያን መሪ ወንድም ሰሎሞን ደግሞ የኃይለሥላሴ መንፈስ እንዳደረበት ጥቁር ሙሴ ይቆጠራል፡፡ የራስ ተፈሪያውያን ተከታይ ሴቶች ስለኒህ የኢትዮጵያ ንጉሥ እንደሚከተለው ይናገራሉ፡፡

‹‹በነሱ እኩይ መንገድ እኛን ሴቶችን ያረከሱንን ነጫጮቹን ውሾችና ቡናማዎቹን ከሃዲዎች የእኛ ጥቁር አምላክ፣ እውነተኛ የእስራኤል ልጆች፣ የጥቁር ንጉሥ ሰለሞንና የጥቁሯ ንግሥት ሳባ ዘሮች ያቃጥሉልናል፡፡

ይኸው ወንድም ሰለሞን ስለጥቁሮች በደል ‹‹አዎ ወንድሞቼ! ነገር ግን አሁንም ከኛ የደበቁት ከሁሉም በላይ በጣም ጠቃሚ የሆነ ሌላ ነገር አለ፡፡ ይህም ያ ሰው አምላክ ነው፡፡ የራስ ተፈሪ መንፈስ ስለምንፈልገው በሁላችን ላይ አርፏል፡፡ ይህ ይህ ነው ወንድሞቼ ነጮቹ ሰዎች በእሱና በኛ ላይ የፈፀሙት የከፋ ሀጢአት፡፡ ይህንንም ቡናማዎቹ አጋሮቻቸው አሁንም ያስተጋባሉ፡፡ በማለት ብቸኛው መፍትሔያቸው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ መሆኑን ይሰብካል፡፡ በዚሁ ገጽ ላይም ኢምፔሪያሊዝም ነጮችንም ጥቁሮችንም ባርያ እንዳደረጋቸውና እንግሊዝን ያገነናትና ለዚህ ያበቃትም የጥቁሮች ላብ መሆኑን ይዘረዝራል፡፡

  • ገዛኸኝ ጌታቸው ‹‹ኢትዮጵያ በዌስት ኢንዲስ ሥነ ጽሑፍ›› (1992)

*******

‹‹የዛፎች  ምክር››

አንድ ጊዜ ዛፎች ተሰበሰቡና አንድ ምክር መከሩ አሉ፡፡ ይሄ ምሳር የሚባል እየጨፈጨፈ ጨረሰን ምን እናድርግ የሚል አንድ ትልቅ ጉባኤ ተጠራ፡፡ አንድ ዛፍ ተነስቶ ወንዝ እንጣለው አለ …ሁለተኛው ተነሳና ጉድጓድ ቆፍረን እንቅበረው አለ፡፡… ሌላው ደግሞ እሳት ውስጥ እንጨምረው አለ፡፡ ሁሉም በየተራ እየተነሱ ሃሳባቸውን ሰጡ፡፡…. መቼም ሽማግሌ አይጥፋ አንድ ሽማግሌ ዛፍ ተነሱ …አዬ ይኼ ሁሉ መፍትሔ ሊሆን አይችልም አሉ፡፡ ምንድነው መፍትሔው ሲባሉ…. ይሄን መጥረቢያ አኛን እንዲጨፈጭፍ ያደረግነው እኛው እራሳችን ነን፡፡ እኛ እጀታ ባንሆነው ኖሮ በምን ይመታን ነበር አሉ፡፡

  • የወግ ገበታ
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...