Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአማራ ክልል የኃይል አቅርቦት ባለማግኘታቸው 197 ፕሮጀክቶች ለዓመታት ሥራ አለመጀመራቸው ተጠቆመ

በአማራ ክልል የኃይል አቅርቦት ባለማግኘታቸው 197 ፕሮጀክቶች ለዓመታት ሥራ አለመጀመራቸው ተጠቆመ

ቀን:

  • የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በክልሉ በኃይል ልማት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብሏል

በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራ በመግባት የግንባታና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ሙሉ በሙሉ አሟልተው የኃይል አቅርቦት ብቻ ባለማግኘታቸው፣ 197 ፕሮጀክቶች ለረዥም ዓመታት ያለ ሥራ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡

የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮሞሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይኼነው ዓለም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ18 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉና ከ6.9 ቢሊዮን ብር በላይ ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ 197 ፕሮጀክቶች፣ በክልሉ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በኃይል እጥረት ሳቢያ ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም፡፡

እንደ አቶ ይኼነው ገለጻ፣ በክልሉ ያለው የኃይል አቅርቦት የክልሉን ልማት ወደኋላ እያስቀረው ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ ሐሙስ ሐምሌ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአማራ ክልል ውስጥ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት እንደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ሁሉ በኃይል ልማቱ ዘርፍ በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ አስታውቋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በኃይል አቅርቦት ዙሪያ ሥር የሰደደ ችግር እንዳለ ቢገልጽም፣ ለኃይል አቅርቦት ሥርጭቱ ወሳኝ ሚና ያላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መከፋፈያ ጣቢያዎች በክልሉ ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጠቁሟል፡፡ በክልሉ ነባር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግም ትኩረት ተሰጥቶት የተሠራ መሆኑን በማስረዳት፣ ፍትሐዊ  የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ለማሳደግ፣ ብሎም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን በእጅጉ ለመቀነስ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ለአብነትም ባለ 400 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው የባህር ዳር ሁለትና ደብረ ማርቆስ፣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸውን የንፋስ መውጫ፣ ሞጣ፣ መተማ፣ ጋሸና፣ አዘዞ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ባህር ዳርና ኮምቦልቻ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መግለጫ  አብራርቷል፡፡

ባለ 130 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው የአኮስታ፣ ዓለም ከተማ ኮምቦልቻ አንድ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ከሚሴና ደብረ ብርሃን፣ እንዲሁም 66 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው የቢቸና፣ ዳባት፣ ፍኖተ ሰላም፣ ዳንግላ፣ ወረታ፣ ጎንደር አንድ፣ ደሴ፣ ወልዲያና ሰቆጣ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ባለፉት 26 ዓመታት ተገንብተው ለክልሉ ኅብረተሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡ 

ቀደም ብለው የተገነቡ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ከማሳደግ አኳያም የጎንደር አዘዞ፣ የኮምቦልቻና የባህር ዳር ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በአሁኑ ወቅት የአቅም ማሳደግ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን፣ በወልዲያና በቆቦ አዲስ ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም አንድ አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በመገንባት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስረድቷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በ2009 በጀት ዓመት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ባሉት አሥራ አንድ ወራት ውስጥ፣ በአማራ ክልል 36.3 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን አቶ ይኼነው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚወስዱ ባለሀብቶች 29.2 ቢሊዮን ብር እንዲያስመዘግቡ የታቀደ ቢሆንም፣ በአሥራ አንድ ወራት ብቻ 36.6 ቢሊዮን ብር ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ 1,903 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያወጡ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ከዕቅዱ በላይ የሰኔ ወርን ሳይጨምር 1,976 ባለሀብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት 184,225 ለሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ውስጥ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ፣ በገጠርና በከተማ ግብርና፣ በአበባ ልማት፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩና ክልሉን ወደ ኢንዱስትሪ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ከዚህ በፊት ባለሀብቶች በተለያዩ ዓመታት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ቢሆንም፣ የተለያዩ ችግሮች እንደሚስተዋሉባቸው አቶ ይኼነው አክለዋል፡፡

ከእነዚህ ችግሮች መካከልም መሬት ከመንግሥት ካገኙ በኋላ አጥሮ በመያዝ መሸጥ፣ አዋጭ ፕሮጀክቶችን ይዘው አለመቅረብ፣ የካፒታልና የፕሮጀክት ማኔጅመንት ዕውቀት ማነስ፣ የመሬት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ብቻ የተጋነነ ፕሮፖዛል ማቅረብ፣ ወዘተ የሚሉት ችግሮች በጉልህ ሲታዩ የነበሩና አሁንም እየታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ መንግሥት በኩልም ውስንነቶች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ይኼነው በቂ መሬት አለማዘጋጀት፣ የሚሰጡ የብድር አገልግሎቶች በቂና ቀልጣፋ አለመሆን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የድጋፍና የክትትል ሥራዎች አነስተኛ መሆን፣ ወዘተ ተጠቃሽ ችግሮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

በአማራ ክልል ለኢንቨስትመንት የሚሆን ምቹ መሬትና የአየር ሁኔታ ያለ ቢሆንም፣ ብዙ ኢንቨስተሮች በክልሉ ኢንቨስት እያደረጉ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በክልሉ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው የሚፈልጉ ወጣቶች ቢኖሩም ወደ፣ ክልሉ በመሄድ ኢንቨስት በማድረግ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ከዓመት በፊት በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ ለነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ አንዱ ምክንያት ከወጣቶቹ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዘ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በክልሉ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተመርቆ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃንና አረርቲ የኢንዲስትሪ ፓርኮች እንደሚገኙበት አቶ ይኼነው አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...