Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለምርት ያልበቁ ምርምሮች

ለምርት ያልበቁ ምርምሮች

ቀን:

ለተለያዩ በሽታዎች የሚታዘዝ አንድ ዓይነት ሕክምና ሆኖ ለዘመናት አገልግሏል፡፡ በሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ የሚገኙ ፈሳሾች ሳይመጣጠኑ ሲቀሩ ለበሽታ እንደሚዳርጉ ይታመን ስለነበር ለምንም ዓይነት ሕመም የሚታዘዘው ሕክምና እነዚህን ፈሳሾች ማመጣጠን ነው፡፡ ይህም የሚሆነው የታማሚውን ገላ በተለያዩ ቦታዎች በስለት በመቁረጥ ደሙ እንዲፈስ በማድረግ ነው፡፡

ከ3000 ዓመታት በፊት በሰፊው የአውሮፓ ሕዝብ የተለመደውን ይህን ሕክምና የሚሠራው በፀጉር ቆራጮች ነበር፡፡ የዚህ ሕክምና መሠረት የቀደምት ሥልጣኔ መነሻዋ ግብፅ እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲህ ያለው የሕክምና ጥበብ ለኢትዮጵያም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች በተለያዩ መንገዶች ሲያከናወኑት ይታያል፡፡ ለምሳሌ ለዓይን ሕክምና ቅንድብን መብጣት የተለመደ ነው፡፡

የሕክምናውን ዘርፍ የሕክምና ሀ፣ ሁ . . . የነበሩ ጥንታዊ ሕክምናና የወቅቱ ሳይንስ የተራቀቀበትን ዘመናዊ ሕክምና በሚል ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በእነዚህ የሕክምና ጥበቦች ያለደም የሚደረግ ሕክምና የለም ማለት በሚያስደፍር መልኩ ደም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ፈውስን ለመስጠት ደም በማፍሰስ የተጀመረው ሕክምና ደም በመስጠት ሕይወት ማዳን ወደ ሚቻልበት ዘመን ተሻግሯል፡፡

በእነዚህ ሁለት ተቃርኖ ባላቸው የፈውስ አሰጣጥ ሒደቶች ሳይንሱ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ማየት ይቻላል፡፡ በድንገት የሚከሰቱ ወረርሽኞች እንደ እግዜር ቁጣ ሳይሆኑ አዲስ ምርምር የሚሹ የሕክምና ዘርፍ ተደርገው ይታሰቡ የጀመረው በዘመናዊ ሕክምና ነው፡፡ ውስብስብ የአንጎል ቀዶ ሕክምናዎች ይሠራሉ፡፡ በሞትና በሕይወት መካከል የሆኑ በከባድ የሕክምና ሒደት አልፈው ፈውስ ሲያገኙ ይታያሉ፡፡ ተጣብቀው የተወለዱ መንትያዎች ሳይቀሩ በቀዶ ሕክምና ሲለያዩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የኩላሊት፣ የልብ ንቅለ ተከላና የመሳሰሉት ሰውን ከሞት የመመለስ ያህል ክብደት ያላቸው የዘመኑ ሕክምና ትሩፋቶች ናቸው፡፡

የሕክምና ሳይንስ በተራቀቀበት በዚህ ዘመን ወረርሽኞችን እንደ ጦር መሣሪያ መገልገል (ባዮሎጂካል ዌፐን) አድርገው ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ወረርሽኞችን ፈጥሮ በማሠራጨት ለሚፈበረኩ መድኃኒቶች ገበያ ማጧጧፊያ የሚያደርጉ አካላት አሉ የሚሉ ሐሜቶችም ይሰማሉ፡፡ በሕክምና  ፈጠራ ሥራዎች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰችን መሠረት ያደረጉ በርካታ ክሶች በየዓመቱ ይስተናገዳሉ፡፡ በዚህ የሕክምና ወርቃማ ዘመን ትልቅ እመርታ አሳይተዋል ከሚባሉ ዘርፎች መካከል የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም ነው፡፡

የቢሊዮኖች መድኅንና ኢንዱስትሪውም ትሪሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2011 ባወጣው መረጃ መሠረት 12420 ዓይነት የተለያዩ በሽታዎች አሉ፡፡ ለእነዚህ በሽታዎች ፈውስ የሚሆኑና የተሻለ ፈዋሽነት ያላቸውን መድኃኒቶችን ለማግኘት በርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎች ቀን ከሌት ደፋ ቀና ይላሉ፡፡

አንድን መድኃኒት ከምርምር ጀምሮ ለኅብረተሰቡ እንዲቀርብ ፈቃድ የሚያገኝበት ደረጃ እስኪደርስ በአማካይ ከ11 እስከ 14 ዓመታት እንደሚፈጅና ቢሊዮኖችን ኢንቨስት ማድረግ እንደሚጠይቅ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 139372 ክሊኒካል ስተዲዎች በ182 አገሮች እንደሚሠሩ U.S. National Institutes of Health’s ClinicalTrials እ.ኤ.አ. በ2013  በድረ ገጹ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡ በየዓመቱ የሚመዘገቡ ክሊኒካል ጥናቶች ቁጥርም እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ በ28 በመቶ እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡

ከፍተኛ የበሽታ ሥርጭት እንዳለባቸው በሚነገረው ታዳጊ አገሮች በተለይም በኢትዮጵያ መሰል የምርምር ሥራዎች እምብዛም አልተለመዱም፡፡ የብልሀርዚያ መድኃኒት ካገኙት ከዶክተር አክሊሉ ለማ ውጪ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ መድኃኒት አገኘ ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች በየዓመቱ በገፍ ከሚያስመርቋቸው ተማሪዎች መካከል በፋርማሲ ሙያ የሚመረቁ ብዙ ሆነው ሳለ የምርምሩ ጉዳይ ኋላ የመቅረቱ ነገርም አሳሳቢ ነው፡፡ አንዳንዶች በየፋርማሲው ተቀጥረው መድኃኒት ከመሸጥ ያለፈ ሚና የላቸውም በሚልም ይተቻሉ፡፡ በየትምህርት ተቋማቱና ሌሎች የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ የሚጀመሩ የምርምር ሥራዎችም በተለያዩ ምክንያቶች በጅምር ይቀራሉ፡፡

‹‹ጠንካራ በጀት በጅቶና በተማከለ ሁኔታ መሥራቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘም ትልቅ ችግር አለ፡፡ የተሟላ ላቦራቶሪ አለመኖርና የሠለጠነ የሰው ኃይል በበቂ አለመኖር ሌላው ፈተና ነው፤›› ያሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ መምህሩ አቶ አብዮት እንዳለ ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ ተመራማሪ መምህር ሆነው ማገልገል ከጀመሩ አምስት ዓመታት እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ፡፡

ፀረ ተህዋስያንን በባህላዊ መንገድ ለመከላከል የሚውሉ ባህላዊ መድኃኒቶች ላይ ሳይንሳዊ ምርምር አድርገዋል፡፡ በተለይም አማራጭ የወባ መድኃኒት ለማግኘት ባደረጉት ምርምር አበረታች ውጤት ማግኘት ችለው ነበር፡፡ ‹‹ብዙ ጥናት ፕሪ ክሊኒካል ደረጃ ደርሶ ነው የሚቋረጠው፤›› የሚሉት አቶ አብዮት፣ ምርምራቸው በአይጥ ላይ ተሞክሮ ጥሩ ውጤት አግኝተው እንደነበር፣ ይሁንና ወደ ቀጣዩ የምርምር ደረጃ ሳይሸጋገር በጅምር መቅረቱን ይናገራሉ፡፡

‹‹ባሉት አስቸጋሪ ነገሮች ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው እዚህ ጋር ብቻ ተወስነን አንቀርም፤›› በማለት ምንም እንኳ ያሉት ችግሮች ምርምሮች ለውጤት እንዳይበቁ ማነቆ ቢሆኑም ከመሥራት ግን እንደማያግዳቸው ይናገራሉ፡፡

በአገሪቱ መሰል የምርምር ሥራዎች የሚሠሩት በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ምርምር፣ በአርማውር ሀንሰን የጥናት ማዕከልና በዩኒቨርሲቲዎች ነው፡፡ የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስፈልጓቸው የተሟላ ላቦራቶሪ፣ ብቃት ያለው የሰው ኃይል፣ እንዲሁም የበጀትና መሰል ችግሮች የምርምር ሥራዎቻቸው የትም እንዳይደርሱ ማነቆ ሆነውባቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፋርማሲ ትምህርት የፋርማሱቲካል ኬሚስትሪና ፋርማኮግኖሲ ትምህርት ክፍል ኃላፊዋ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ማሪያማዊት ዮናታን እንደሚሉት፣ በዲፓርትመንታቸው በባህላዊ ሕክምና ግብዓት በሆኑ ከ150 በላይ ዕፅዋት ላይ የተሠሩ ከ200 የሚበልጡ የታተሙ ጥናቶች አሉ፡፡ በሁለተኛውና በሦስተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የበጀት ዓመት ውስጥ በዘመናዊ የሕክምና ሳይንስ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ቢያንስ አንድ ግብዓት ለማውጣትም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡

‹‹ከዘመናዊ ሕክምና ጋር መስተጋብር እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ሞሪንጋን ብንወስድ ሞሪንጋ ከሌሎች ቅጠሎችና መድኃኒቶች ጋር ሲወሰድ ምን ዓይነት ችግር ያመጣል፣ በምን ያህል መጠንስ ሊወሰድ ይገባዋል የሚሉትን ነገሮች ማጥናት ነው›› በማለት ተቋሙ በኃላፊነት እየሠራ ስላለው ሥራ ይናገራሉ፡፡

አንድ መድኃኒት ሠርቶ ለማውጣት ዓመታት የሚጠይቅ፣ ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈጅና የበርካታ ባለሙያዎች ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡ መድኃኒቱን ለማበልፀግ ከሚደረገው ጥናት ባሻገር ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት የሚችሉ በኬሚስትሪ፣ በሒሳብ፣ በሕግና በሌሎችም የሙያ ዘርፍ ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡

‹‹ኋላ የቀረነው አቅም ስላጣን አይደለም፡፡ ባለን አቅም የተለያዩ ባለሙያዎችን ባካተተ መልኩ ተቀናጅተን መሥራት አልቻልንም፤›› የሚሉት ዶክተር ማሪያማዊት፣ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀናጅቶ የመሥራቱን ነገር ለማበረታት በቅንጅት ለሚሠሩ የምርምር ሥራዎች የተለየ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

አንድ መድኃኒት የምርምር ጊዜውን ጨርሶ የገበያ ፈቃድ እስኪያገኝ የተለያዩ የምርምር ሒደቶች ማለፍ ግድ ይለዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ የሚያስፈልጉ ወጪዎችንና ፈቃድ ከተሰጠው በኋላም አምርቶ ለገበያ በማቅረቡ ረገድ የሚያስፈልገውን ወጪ ሁሉ የሚሸፍኑ ትልልቅ ተቋማት አሉ፡፡ ኢንዱስትሪውም በጣም ሰፊና ዓመታዊ የመድኃኒት ሽያጫቸው እስከ 70 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ እንደ ፒፋይዘር ኢንክ ያሉ ግዙፍ ተቋማት የሚሳተፉበት ነው፡፡

ካደጉት አገሮች ጋር ሲነፃፀር በሌላኛው ፅንፍ ላይ ሆኖ የሚታየው የአገሪቱ የመድኃኒት ምርምር ገና እንደ ጭላንጭል ብርሃን ነው፡፡ ኢንዱስትሪውም አቅም ልፋት የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹‹በባህላዊ ሕክምና እንደ ግብዓት ሆነው ከሚያገለግሉ ዕፅዋት መካከል መድኃኒት ማውጣት አያቅተንም፡፡ ነገር ግን መድኃኒቱን ተቀብሎን የሚያመርት ኢንቨስተር የለንም፤›› በማለት በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ መድኃኒቶች ቢኖሩም በአገሪቱ የፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ ባለማደጉ ምርምሮች ተማሪዎችን ከማስመረቅ ባለፈ ትርጉም ማጣታቸውን ዶክተር ማሪያማዊት ይናገራሉ፡፡

መሰል የምርምር ሥራዎችን እንዲሠራ በአዋጅ በተቋቋመው በአርማውር ሀንሰን የምርምር ተቋም የተለያዩ ክትባቶች፣ ባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒቶች ላይ ምርምር ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም አጠቃላይ ክሊኒካል ትራያል ይሠራል፣ ከተቋሙ ውጪ የተጀመሩ ምርምሮችን በክሊኒካል ትራያልስ የማሠራት፣ የመድኃኒት ልየታ ሥራ የመሥራት ሥልጣንም ተሰጥቶታል፡፡ እስካሁንም በተቋሙ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ለሥጋ ደዌ ታማሚዎች የሚሰጠው መድኃኒት ይጠቀሳል፡፡ ለዘጠኝ ወራት የሚቆየውን የተላመደ የቲቢ ሕክምና ወደ ስድስት ወር መቀነስ የሚያስችል ጥናት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አብዛኛው ሥራዎቹን የሚሠራው ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው፡፡ የተለያዩ በውጭ አገር የተጀመሩ የምርምር ሥራዎች ክሊኒካል ትራያል በተቋሙ ይሠራሉ በመሠራት ላይም ይገኛሉ፡፡

‹‹ሁሉም የራሱን ፍላጎት ይዞ ነው ሚመጣው፡፡ የእነሱን መድኃኒት እዚህ እንሞክራለን፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከዚህ የምትጠቀመው ነገር የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ራሳችንን ችለን የራሳችንን አጀንዳ ቀርፀን መሥራት ነው የምንፈልገው፤›› የሚሉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ቶሌራ፣ የሌሎች አገሮችን መድኃኒት መሞከሪያ ከመሆን ይልቅ እዚሁ ማምረት የሚቻልበት አማራጭ ላይ ማተኮሩ ብልህነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በመድኃኒት ምርምር ረገድ ትልቅ ክፍተት ቢኖርም፣ የብሔራዊ እንስሳት ሕክምና  ምርምር ተቋም በእንስሳት ሕክምና ረገድ ጉልህ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ እስካሁን ከ20 በላይ የሚሆኑ የእንስሳት ክትባቶችን መሥራት ችለዋል፡፡ ‹‹ለእንስሳት ተብሎ ከውጭ የሚመጣ ክትባት የለም፡፡ የእነሱን አርዓያ መከተል እንፈልጋለን፤›› ይላሉ፡፡ ይህም ቢሆን በአገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታና አንድን መድኃኒት ለማውጣት ከሚፈጀው ጊዜ፣ የሰው ኃይልና ገንዘብ አንፃርና የትኛው ምርምር የተሻለ ውጤታማ ይሆናል? የሚለው ጉዳይ በሚገባ ሊጤን ይገባል፡፡

ባህላዊ መድኃኒቶችን ወደ ዘመናዊ መቀየር ያንን ያህል ልፋት እንደማይጠይቅ የሚናገሩት ዶክተር ታዬ፣ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ባህላዊ መድኃኒቶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መሥራት የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ተቋሙም ከተለያዩ ባህላዊ ሐኪሞች ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝና አበረታች ነገሮች መኖራቸውንም ይናገራሉ፡፡ በምርምር ሒደት ላይ ከሚገኙ መድኃኒቶች መካከል በአይጥ ላይ ተሞክረው ይበል የሚያሰኝ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ በቅባት መልክ የተዘጋጁና በሰው ላይ ቢሞከሩ ችግር እንደማይፈጥሩ የሚተማመኑባቸው መድኃኒቶችም አሉ፡፡ የሚዋጡ መድኃኒቶችንም በክኒን መልክ ለማዘጋጀትና በሰዎች ላይ ለመሞከር በሒደት ላይ መሆናቸውን ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

ጥቂት የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ቢኖሩም፣ ሥራዎቻቸውን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ከማሳተም ባለፈ ምርምራቸው ወደ ተግባር ተቀይሮ ፈውስ ሲሰጥ ማየት አልተለመደም፡፡ መሰል ምርምሮችን ማሠራት የሚችል የተሟላ ላቦራቶሪ ማግኘትም ከባድ ነው፡፡ ‹‹እኔም ብዙ ጥናቶች ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትሜያለሁ፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡን የሚጠቅም ነገር ሠርቻለሁ ማለት አልችልም፤›› የሚሉት ዶክተር ታዬ፣ ምርምሮች ምርት ሆነው እንዲወጡ መሠራት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

ይህንን ለማድረግ ግን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት በመኖሩ በምርምር ሥራ ልምድ ያካበቱ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶችን መቅጠር፣ በጊዜ ሒደት ደግሞ ማፍራት ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአርማውር ሀንሰን ሁለት ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች እንደሚገኙ፣ ከስዊድን መንግሥት ባገኙት ዕርዳታም ተጨማሪ ሁለት ሳይንቲስቶችን ለአምስት ዓመታት ያህል መቅጠር እንደሚችሉ ዶክተር ታዬ ተናገረዋል፡፡

ዋናው ምርምር የሚካሄድበትና ባለሙያዎች በብዛት የሚቀጠሩት በፋራማሱቲካል ኢንዱስትሪው እንደሆነ፣ ነገር ግን በአገሪቱ የሚገኙ አምራቾች ከአገሪቱ የመድኃኒት ፍላጎት ከ20 በመቶ የበለጠ ማምረት እንዳልቻሉ፣ 80 በመቶ የሚሆነው የመድኃኒት አቅርቦት ከውጭ የሚመጣ መሆኑን፣ ይህም የሥራ ምኅዳሩን በማጥበብ  ወደ ምርምር ሥራ የሚገቡ ባለሙያዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ እንዲሆን ማድረጉን የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ ገብረእየሱስ ተናግረዋል፡፡

1585 አባላትን ያሉት ማኅበሩ ችግሩን ለማጥበብ የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎችንና አምራቾችን ለማስተሳሰር እየሠራን እንገኛለን፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ጥራት ያለው ትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ እናደርጋለን፤›› ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮግራም ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል እንደሚሉት፣ በጤናው ዘርፍ ያሉ የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የማድረጉን ኃላፊነት ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ለአርማውር ሀንሰን ተሰጥቷል፡፡ የምርምር ሥራዎችን መደገፍ እንደ አቅጣጫ በተቀመጠው መሠረት መንግሥት በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ የሰው ኃይል ከመገንባት አኳያም በየተቋማቱ የሚሠሩ ባለሙያዎች ለከፍተኛ ትምህርት ውጭ አገር ተልከው እንዲማሩ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ በየትምህር ተቋማቱ ለሚሠሩ የምርምር ሥራዎችም የተለያዩ ድጋፎች ይደረጋል፡፡

በአብዛኛው የሙያ መስክ ከምርምር ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ጤና እንዲሉ›› በጤናው በኩል ያለው የበለጠ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ በዓለም ጤና ድርጅትና በሌሎች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጎማ እየተደረገ በየዓመቱ ለመድኃኒት የሚወጣው ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡ የአገሪቱ የመድኃኒት ገበያ ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ በየዓመቱም የ25 በመቶ ዕድገት የሚያሳይ ሲሆን፣ በ2012 ፍሮስት ኤንድ ሱሊቫን የተባለ አጥኚ አካል የአገሪቱ የመድኃኒት ገበያ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው መድኃኒትም ከውጭ የሚገባ ነው፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች በተለያዩ ተቋማት ድጎማ በቅናሽ ዋጋ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ናቸው፡፡ ይህ ድጎማ ግን እስከ መጨረሻው የሚቀጥል ሳይሆን አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስትመደብ የሚቀር ነው፡፡

በተያዘው የዕድገት ዕቅድም አገሪቱ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንደምትገባ ይነገራል፡፡ ‹‹ምን ተይዞ ጉዞ›› እንዳይሆን በሕክምናውና በሌሎችም ዘርፎች ያለው ዝግጅት መፈተሹ ተገቢ ነው፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...