በበሪሁን ተሻለ
ዘንድሮ በ2009 ዓ.ም. ሰኔ 30 ላይ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የአገሪቱ ሃምሳ ስድስተኛው የበጀት ዓመት ነበር፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ አዲሱን ማለትም 57ኛውን የበጀት ዓመት ጀምረናል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ወዳለው ወደ 60ኛው የአገሪቱ የበጀት ዓመት ውስጥ ትገባለች፡፡ የመንግሥት ፋይናንስ ገንዘብና በጀት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ አገር ሊያከብረው የሚገባ ከወዲሁ ሊዘጋጁበት የሚገድ የአልማዝ ኢዮቤልዩ ነው፡፡ የሚከበር ነገር አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡
የያዝነው የዘንድሮው ባለ 320.8 ቢሊዮን ብሩ ዓመት ሃምሳ ሰባተኛው የበጀት ዓመት ነው ያልኩት፣ ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ ሰላሳ ቀን የሚዘልቀው የአንድ ዓመት ጊዜ አንድ የበጀት ዓመት ብሎ የተቆረጠውና የተወሰነው በአዋጅ ቁጥር 162/1951 ጀምሮ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ትንሽ ላፍታታው፡፡ የበጀት ዓመቱ በልዩ ሕግ የተወሰነው ነሐሴ 21 ቀን 1951 ዓ.ም. በወጣ የበጀት ዓመት አዋጅ ቁጥር 162 ነው፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የበጀት ዓመት ከካሌንደር ዓመት ተለይቶ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ 30 ቀን ድረስ ያለው የአንድ ዓመት ጊዜ የበጀት ዓመት ተባለ፡፡ ሆኖም የበጀት ዓመቱን የወሰነው ሕግ የወጣውና የፀናው ነሐሴ 21 ቀን 1951 ዓ.ም. በመሆኑ፣ የመጀመሪያው የበጀት ዓመት ከመስከረም 1 ቀን 1952 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 1952 ዓ.ም. ድረስ ያለው ሆነ፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 1952 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 1953 ዓ.ም. ድረስ ያለው ሙሉ የበጀት ዓመት ሁለተኛው ሆኖ መቆጠሩ ቀጠለ፡፡
የዛሬ ዓመት በዚህ ወቅት የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ ወር (ሰኔ) ገና እንደተጀመረ በወጣው የእሑድ ሰኔ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ሪፖርተር (ቁጥር 1682) ‹‹የበጀት ዲሲፒሊን አለን?›› በሚል ርዕስ በዚህ ረገድ ያለብንንና የሚጎድለንን ዘርዝሬ ነበር፡፡ በተለይም የበጀት ዲሲፒሊኑ አንድ ማመላከቻ የሆነው የጊዜ ሰሌዳ እንዴት ‹‹እያማረበት›› መጥቶ ዛሬ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ሳይፀድቅ ቢቀር፣ ነውርም ችግርም አለመሆኑን ደጋግመን እየመሰከርን ነው፡፡
የበጀት ሥርዓቱን የማቋቋም የሠለጠነውን ዕርምጃ ከ60 ዓመት አካባቢ በፊት አንድ ብለን ስንጀምር ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት እጅግ ቢዘገይ ከመጋቢት 15 ቀን በፊት ለምክር ቤቱ መቅረብ አለበት፡፡ ምክር ቤቱም በበጀቱ ላይ ድምፅ መስጠቱን እጅግ ቢያንስ አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት መጨረስ አለበት በሚል ሕግ እንገዛለን ብለን ጭምር ነበር፡፡ በዛሬውና እርግፍ አድርገን በተውነው አሠራር መካከል ያለው ልዩነት የጊዜው ሰሌዳ ልልነት ብቻ አይደለም፡፡ የቀድሞውን ጥብቅ የጊዜ ሰሌዳ የሚደነግገው የበጀቱን ሐሳብ አሰናድቶ ከሚያቀርበው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በጀቱን ከሚያስተዳድረው ከገንዘብ ሚኒስቴር በላይ የሆነ አካል ያወጣው ሕግ ነው፡፡ ፓርላማው እጅግ ቢያንስ አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት በበጀቱ ላይ ድምፅ መስጠቱን መጨረስ አለበት የሚለውም ሕገ መንግሥቱ ነበር፡፡ ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት እጅግ ቢዘገይ ከመጋቢት 15 ቀን በፊት ለምክር ቤቱ መቅረብ አለበት የሚለው ሕግ ደግሞ የበጀት ዓመቱን የወሰነው ሕግ ነበር፡፡
የዛሬውን የበጀት ሰሌዳችንን የወሰነውን የሕግ ዓይነት ያወጣው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የወጣ የሕግ ዓይነት እንዴት አድርጎ ሁሉንም ሊገዛ እንደሚችል ለመገመት የሚያስቸግር ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው መመርያ በራሱ በሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ላይ ግዴታ ያቋቁማል ብሎ ከነጭራሹ ‹‹አደራ››ውን ለእሱ መስጠት እንዴት ይቻላል? በአጠቃላይ መንግሥት የሚከተለውና ሊከተለው የሚገባ አስገዳጅ የሆነ ከእሱ በላይ የሆነ የሥልጣን አካል ያወጣው የበጀት የጊዜ ሰሌዳ ሕግ የለውም፡፡
እንዲያውም የፌዴራል መንግሥትን የፋይናንስ አስተዳደር ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 648/2001 በጀትን ስለማፅደቅና ስለማሳወቅ በሚደነግገው አንቀጹ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ ለተከታዩ የበጀት ዓመት የሚያስፈልገውን በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደግፎ ስለተላከው በጀት ማብራሪያ ይሰጣል፣ የዓመቱ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የክልል መንግሥታት እስከ ሐምሌ 7 ቀን እንዲያውቁት ይደረጋል፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው በጀት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ይወጣል ማለቱ ሲታይ፣ በነባሩና በአሁኑ መካከል ያለውን የጊዜ ሰሌዳ የበጀት ዲሲፒሊን ሥልት ልልነትና ልዩነት መገንዘብ አያዳግትም፡፡
የተጠቀሰው የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ ለመንግሥት በሚለቀውና በሚተወው በዚህ ልቅና ‹‹ነፃ›› ዕርምጃ መሠረት አዲሱ የበጀት ዓመት ከመጀመሩ በፊት፣ አዲሱን በጀት አዘጋጅቶና አደላድሎ የማሳወቅ ግዴታ የለብንም፡፡ ፓርላማው በበጀቱ ላይ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ፣ ሰኔ 30 ቀን ራሱ ላይ ጭምር ድምፅ መስጠት ይችላል፡፡ በዚህ መካከል ምናልባትም ከዚህ በኋላ የፀደቀው በጀት በነጋሪት ጋዜጣ እስኪታተም ድረስ የሚወስደው ጊዜ አለ፡፡ እስከ ሐምሌ 7 ቀን ያለው ሁሉም መሥሪያ ቤቶችና የክልል መንግሥታት በጀቱን የሚያውቁበት ጊዜ ራሱ፣ ከበጀት ዓመቱ ውስጥ የአንድ ሳምንት ‹‹የሥራ ማቆም›› ዕረፍት ይሰጣል፡፡
ይህም ሆኖ ይሁን፣ ወይም በዚህ ምክንያት አገር ድኅረ ሰኔ 30 የመንግሥቱን በጀት በሙሉ አያውቅም፡፡ ሁልጊዜ በሐምሌ ወር እንደምንሰማው፣ በዚህ ዓመትም ደግመን ደጋግመን እንዳረጋገጥነው የክልል መንግሥታት በጀታቸውን የሚያፀድቁት ገና ሐምሌ ወር ውስጥ ዘልቀው ገብተው ነው፡፡ ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በተሰማው በዕለቱ ዜና መሠረት የአማራ ክልል መንግሥት የ37.69 ቢሊዮን ብር፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የ55.8 ቢሊዮን ብር በጀት ማፅደቃቸውን ሰምተናል፡፡ ስለኦሮሚያ በጀት ከዚህ በተጨማሪ የሰማነው የክልሉ ምክር ቤት ማለትም ጨፌው በክልሉ ሥራ አስፈጻሚ የቀረበለትን የ2009 ዓመት የ5.8 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማፅደቁንም ነው፡፡ ‹‹ተጨማሪ በጀቱ ለመምህራንና ለመንግሥት ሠራተኞች በበጀት ዓመቱ ለተደረገው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ የሚሆን እንደሆነም ተገልጿል፤›› ተብለናል፡፡
የኦሮሚያን ክልል የ2009 ዓ.ም. የ5.8 ቢሊዮን ብር የተጨማሪ በጀት ማፅደቅ ጉዳይ ለጊዜው አቆይተን፣ የሁለቱን ክልሎች የ2010 ዓ.ም. የበጀት ጉዳይ መጀመሪያ እንመልከት፡፡ የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የየራሳቸው የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡ በጀት የማፅደቅና በጀት የማስተዳደር ሥልጣናቸውም ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡ በተለይም የክልሎች የበጀት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52/2/ሠ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለክልሉ በተወሰነው የገቢ ምንጭ ክልል ውስጥ ግብርና ታክስ መጣል፣ መሰብሰብ፣ የክልሉን በጀት ማውጣትና ማስፈጸም የክልል ሥልጣን ነው፡፡ ስለዚህም የፌዴራል መንግሥት በጀት ለምሳሌ የ2010 ዓ.ም. በጀት 320 ቢሊዮን ብር አለፈ ሲባል፣ በዚህ ውስጥ ከተካተተው የክልሎች ድጎማ በቀር የተባለው 320 ቢሊዮን ብር የመላውን ኢትዮጵያ የመንግሥት በጀት አያሳይም፡፡
ክልሎች የራሳቸው በጀት አላቸው ማለት ግን ክልሎች ከዚህ እኩል የገዛ ራሳቸውን የበጀት ዓመት ያወጣሉ፣ የተለየ የበጀት ካሌንደርም ይኖራቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህም የፌዴራልም የክልልም የበጀት ካሌንደር አንድ ነው፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሰኔ 30 ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ በዚም ምክንያት ከሰኔ መጨረሻ በኋላ ክልሎች ስለበጀት ማፅደቅ ማውጣት ሲያወሩ መስማት የለብንም፡፡ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብና አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት አገራዊ ተግባር ከዩኒፎርም (ወጥ ከሆነ) የበጀት ካሌንደር በላይ ይጠይቃል፡፡
ክልሎች የበጀት ማፅደቅ ሥራቸውን ሐምሌ ውስጥ ጭምር ገብተው የሚሠሩት የተለየ ካሌንደር ኖሯቸው ወይም አምሯቸው ሳይሆን፣ የፌዴራሉ መንግሥት አሠራር ተፅዕኖ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፌዴራሉ የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ የዓመቱ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ፣ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የክልል መንግሥታት እስከ ሐምሌ 7 ቀን እንዲያውቁት ይደረጋል ይላልና፡፡
በጀት የአንድ መንግሥት ዕቅድ የገንዘብ ተመን ነው፡፡ እንዲህ ያለ ተልዕኮና ግዳጅ ደግሞ ከጊዜ ሰሌዳ የበለጠ ዲሲፒሊን የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ይፈልጋል፡፡ ይጠይቃል፡፡ የኦሮማያ ክልላዊ መንግሥት ከ2010 ዓ.ም. በጀት ጋር የ2009 ዓ.ም. የ5.8 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ ማለትን ያህል ዜና ተሰምቶ መጠየቅና መጠያየቅ አለመኖሩ፣ ለምን አለመባሉ ራሱ የሚገርም ነው፡፡ በጀት ማለት እኮ መንግሥት ሊያከናውናቸው የሚገደድባቸውን መደበኛ ተግባሮቹን፣ ያለበትን የሥራ ድቅን ካለው የገንዘብ የጊዜና የሥራ ችሎታ ጋር አገዳድሮ በዓመት የሥራ ዕቅድ ዘርዝሮ በውሳኔው ይፈቅድለት ዘንድ ለፓርላማው የሚያቀርበው ሐሳብ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. የተፈቀደው በጀት ተጨማሪ የ2009 ዓ.ም. በጀት የራሱን የበጀትን ትርጉም የሚፈታተን ነው፡፡ ሳይታይ የቀረ ወጪ መኖር በራሱ የመንግሥትን የዕቅድ ችሎታ የሚያሳጣና አሳጥቶ የሚያሳይ ነው፡፡
የዛሬ ዓመት በሐምሌ ወር የፌዴራል ፋይናንስ አስተዳደር ሕጉ ተሻሽሏል፡፡ ከተሻሻሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ የ‹‹ተጨማሪ በጀት›› ትርጉም ነው፡፡ ከሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በፊት ተጨማሪ በጀት ማለት፣ ‹‹በበጀት ዓመቱ ለመንግሥት ሥራዎች ማስፈጸሚያ የተፈቀደው የገቢ በጀት በቂ ሳይሆን ሲቀር፣ ወይም በበጀት ዓመቱ የወጪ በጀት ያልተፈቀደለት የመንግሥት ሥራ በማጋጠሙ ወይም የተፈቀደው የወጪ በጀት በቂ ባለመሆኑ ምክንያት የሚፈቀድ በጀት ነው፤›› አሁን ተጨማሪ በጀት ማለት በበጀት ዓመቱ ለመንግሥት ሥራዎት ማስፈጸሚያ ከፀደቀው የገቢ በጀት በላይ ለመሰብሰብ፣ ወይም የወጪ በጀት ያልፀደቀለት የመንግሥት ሥራ በማጋጠሙ ወይም የፀደቀው የወጪ በጀት በቂ ባለመሆኑ ምክንያት የሚፀድቅ ተጨማሪ በጀት ነው ተባለ፡፡
ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ዓመት የሚሞላው የተሻሻለው የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ የበጀት መፅደቅ መዘግየትን የሚመለከተውን ድንጋጌውንም አሻሽሏል፡፡ በነባሩ ሕግ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከ አዲሱ የበጀት ዓመት መጀመሪያ የዓመቱን በጀት ሳያፀድቀው ቢዘገይ ምክር ቤቱ የዓመቱን በጀት እስኪያፀድቀው ድረስ፣ አንደኛ ባለፈው ዓመት የፀደቀው በጀት በየወሩ እየታየ ተፈጻሚ እንዲሆን፣ ሁለተኛ ቀደም ሲል ለተፈቀዱ የካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ በሚኒስትሩ እየተፈቀደ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረግ ነበር፡፡ አዲሱ ማሻሻያ በጀት ቢዘገይ ምክር ቤቱ የዓመቱን በጀት እስከሚያፀድቀው ድረስ፣ ‹‹ቀደም ሲል ለተፈቀዱ ፕሮግራሞች፣ ንዑስ ፕሮግራሞች፣ ፕሮጀክቶችና የመደበኛ ወጪ ዋና ዋና ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ በሚኒስትሩ እየተፈቀደ ጥቅም ላይ ይውላል፤›› ተብሎ ተሻሽሏል፡፡ እነዚህ ሁለት ማሻሻያዎች የሚያሳዩት በአስፈጻሚው አካል ላይ በሕግና ለስም ያህል እንኳን፣ ያለው ነባራዊ አስገዳጅነት የሌለው ክልከላና ልጓም እየቀረ መሄዱን ነው፡፡
በመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጁ ላይ ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል ሌላው የውስጥ ኦዲት ነው፡፡ ማሻሻያው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የውስጥ ኦዲት ኃላፊና ባለሙያዎች ተጠሪነትን ለገንዘብ ሚኒስትር ማድረጉ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የሚኒስትሩም ሥልጣንና ኃላፊነትም ከዚሁ አኳያ ተቃኝቷል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ለየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ በተናጠል ወይም ለተወሰኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጋራ የውስጥ ኦዲትን ተግባር የሚያግዝ ገለልተኛ የኦዲት ኮሚቴ የማቋቋም ሥልጣንም ለሚኒስትሩ ተሰጥቷል፡፡ የውስጥ ኦዲት በነፃነት ውጤታማ፣ ፈጣንና ኢኮናሚያዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን ማረጋገጥም የሚኒስትሩ ተግባር ነው፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የውስጥ ኦዲት የኃላፊዎችና የባለሙያዎች ተጠሪነት ለገንዘብ ሚኒስትሩ ያዛወረው አዲሱ ሕግ ግን ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ እንኳን፣ ከመጥራትና የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ንቃትና ግንዛቤ ከመሆን ይልቅ የጋዜጣ የሹክሹክታ መድረክ የትልቅ ርዕሰ ጉዳይ መነሻ ሆኗል፡፡ ፎርቹን ጋዜጣ በተለይ የሚታወቅበት ያላለቀለትንና አረጋግጬዋለሁ ብሎ የማይወራረድበትን ፍሬ ነገር የሚያቀርብበት ‹የአሉ አሉ›› መድረክ አለው፡፡ ፎርቹን ሳምንታዊው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በዚህ የ‹ፋይንላይን/ጐሲፕ› ጥጉ ያወጣው ወሬ ርዕሰ ጉዳይ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ትብብሩ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከስተና መሥሪያ ቤታቸው ‹‹ያስነሱት አቧራ›› እና ‹‹የቀሰቀሱት የተኛ ሰው›› መኖሩ ነው፡፡ በፎርቹን የሹክሹክታ ዘገባ መሠረት ማኒስትሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎች ማለትም ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ እንዲሁም የሒሳብ ሹሞችን በግል ተጠያቂ የሚያደርግ መመርያ ማውጣታቸውን፣ ከአምስት ያላነሱ የፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተሰማሩበትን የተለየ የሥራ መስክና ባህርይ ገልጸው ከመመርያው ሽፋን ውጪ እንዲሆኑ ጠይቀው ደብዳቤ የጻፋ መሆኑን እናነባለን፡፡
ጉዳዩን በዚህ ደረጃ በሹክሹክታ እንዲነሳ ያደረገው ከሌሎች መካከል በሕግ አወጣጥ ሥርዓታችን ውስጥ የተጣቡን ሁለት ችግሮች ናቸው፡፡ አንደኛው ችግር 13 ክፍሎች፣ 70 አንቀጾች ያሉትን ባለ 31 ገጹን የ2001 ዓ.ም. የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ያሻሻለው የ2008 ዓ.ም. ማሻሻያ አዋጅ ለዚያውም ገና አንድ ጊዜ በተሻሻለው አዋጅ ላይ ሲበዛ የሚለጣጥፍ፣ የሚጣፍና ብዙ እመጫቶች የሚያስገባ ድሪቶ በድሪቶ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በእናት አዋጁ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
ሁለተኛው ችግር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የውስጥ ኦዲትና ባለሙያዎች ተጠሪነት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ይሆናል የሚለው ሕግ ዝርዝር አፈጻጸሙ፣ ይወጣበታል የተባለው መመርያ የሚባለው ‹‹የሕግ›› ዓይነት ችግር ነው፡፡ መለያና የቁጥር አሰጣጥ ሥርዓት የሌለው ማዕከላዊ ባለቤት ያልተበጀለት መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የውስጥ ኦዲትን የሚመለከተው መመርያ እስካሁን የምናውቀው የ2003 ዓ.ም. መመርያ ቁጥር 7/2003 ነው፡፡ በአውጪው ባለሥልጣን ላይ የተጣለ የማሳተምና የማሳወቅ ግዴታ ባለመኖሩ አዲስ መመርያ ስለመውጣት አለመውጣቱ የምናረጋግጥበት አሠራር የለንም፡፡
ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የውስጥ ኦዲት አኳያ የመጣውን ለውጥ ያስከተለው በ2008 ዓ.ም. ሐምሌ የዛሬ ዓመት የወጣው ማሻሻያ አዋጅ ነው፡፡ የውስጥ ኦዲትን ተጠሪነት ከእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ወጪ በግልጽ ለገንዘብ ሚኒስትር አድርጎታል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤት በተሾመ ወይም በተመደበ ማንኛውም ሰው ላይ በእያንዳንዱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ምክንያት ከብር አምስት ሺሕ እስከ አሥር ሺሕ የሚደርስ ሦስት ጊዜ ሊደጋገም የሚችል አስተዳደራዊ ቅጣት የጣለውም ይኸው ማሻሻያ ሕግ ነው፡፡ በገንዘብ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከሦስት ጊዜ በላይ አስተዳደራዊ ቅጣት የተጣለበት ሰው ከኃላፊነት እንዲነሳ ሚኒስትሩ እንደ አግባቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወይም ለፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ልማት ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረብ ላይ ‹‹ዘጭ›› የሚል ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ የሚጣሉ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ጨምሮ ይህን ሁሉ የሚያስፈጽምበት የውስጥ ኦዲት ኃላፊና ባለሙያዎች ተጠሪነት ዝርዝር ጉዳይ የሚወሰንበት በመመርያ ነው መባሉ፣ የሕጉን ግልጽነትና የተፈጻሚነት ልክና መልክ ለአሉባልታና ለሹክሹክታ አጋልጦታል፡፡
መጀመሪያ ነገር በመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ላይ ተፋጻሚ የሚሆን፣ በእነሱም ላይ ግዴታ የሚያቋቁም ሕግ ከእነሱ በላይ በሆነ የሥልጣን አካል መውጣት አለበት፡፡ የተለያየ የሥራ ባህርይ አለን፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ የተሰጠን ሥልጣንና ተግባር የተለየና ባለልዩ ባህርይ አደራ ነው የሚሉ ፎርቹን የጠቆማቸው ዓይነት ደብዳቤዎችና የአቻ ለአቻ ጥያቄዎች፣ አሠራሩን ከአሁኑ መፈታተን የጀመሩት ዝርዝር አፈጻጸሙ ሚኒስትሩ በሚያወጣው መመርያ ይወሰናል በመባሉ ጭምር ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከተጠቀሱት አምስት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ በተለይም የደኅንነቱና የመከላከያው ተቋም በቅርቡ በተቋቋሙበት ሕግ እንኳንስ ከውስጥ ኦዲት ከሌላም ጭምር ‹‹ያልተገባ›› ጣልቃ ገብነት የሚመክት ልዩና ጥብቅ ድንጋጌ አላቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የእነሱ የውስጥ ኦዲት ተጠሪነት ለገንዘብ ሚኒስትር መሆን አሠራራቸውም ሚኒስትሩ በሚያወጣው መመርያ መገዛትና ሌላ ሌላው ሁሉ በአጭሩ ‹‹የሽሮ ድንፋታ›› የሚሉት ዓይነት የማይመስል ነገር ነው፡፡
ምሳሌዎችን እናቅርብ፡፡ የትኛውምና በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤት ከ‹‹የሒሳብ መዛግብት›› ድንጋጌና ግዴታ ነፃ አይደለም፡፡ የተሟሉና ትክክለኛ የሆኑ የሒሳብ መዛግብት ይይዛል፡፡ የሒሳብ መዛግብቱና ገንዘብ ነክ ሰነዶቹ በውስጥ ኦዲተሮች ይመረመራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሒሳብ መዛግብቱና ገንዘብ ነክ ሰነዶቹ በየዓመቱ በዋናው ኦዲተር ወይም እርሱ በሚሰይመው ኦዲተር ይመረመራሉ፡፡ ይህ በእያንዳንዱ ባለበጀትና የመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ የተጣለ የወል ግዴታ ነው፡፡
እነዚህን የወል ግዴታዎች ግን በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ‹‹ቢከፈቱት ተልባ›› የሚያደርጉ ልዩ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የመከላከያ ሚኒስቴር የበጀትና የሒሳብ መዛግብት ግዴታ ቢኖርበትም፣ ‹‹ሚኒስትሩ አገራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን ለመከላከል ሲባል እጅግ ጥብቅ ሚስጥር ብሎ የሰየማቸውን የሰው ኃይል ፕሮፋይል፣ የሒሳብ መዛግብትና ሰነዶች እንዲሁም የክፍያ ማስረጃዎች ለማንም አካል እንይዳገለጹ ሊያደርግ ይችላል›› (የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 71/3) ይላል፡፡
የኢንፎሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 808/2006፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 804/2005 ተመሳሳይና አቻ ድንጋጌዎች አሏቸው፡፡
በእነዚህ ድንጋጌዎች ፊት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የውስጥ ኦዲት ኃላፊና ባለሙያዎች ተጠሪነት የገንዘብ ሚኒስትር ሆነ ወዘተ ማለት የአረፋ ፊኛ ነው፡፡ ህልውናውም ‹‹ፍንዳታ››ውም አቧራ ማስነሳቱ የተኛ ሰው መቀስቀስ አይችልም፡፡
የመንግሥት ገንዘብ አስተዳደር ግን የበጀት ዲሲፒሊን ጨምሮ ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ ለአገር ደኅንነት የሚገባውን ክብርና ጥበቃ ያግኝ ማለት ሥራውና ሥልጣኑ ለቢሻኝ ውሳኔ ይዳረግ፣ ከተጠያቂነት ውጪና በላይ ይሁን ማለት አይደለም፡፡ የበላይ የሌለበት፣ ሕግ የማይገዛው ሰው ወይም ተቋም መኖር የለበትም፡፡
የመንግሥት ሥራ አካሄድ በሕዝብ ዓይንና ጠያቂነት ሥር መውደቁ የሕዝብንና የመንግሥትን መተማመን ያስገኛል፡፡ ግብር ከፋይነትም የሕዝብ ግንዛቤና ንቃት ይሆናል፡፡ ጥፋትን የሚያጋልጥንና ለመብት የሚቆረቆርን፣ ታክስን አለመክፈልን፣ ታክስ አለመክፈልን ማገዝን ጨምሮ ላጥቃ የሚል ቢመጣ ከበላዩ ጌታ የሌለው ሕግ አለሁልህ ይለዋል፡፡ የሕጉ አለሁልህ ባይነት በሕግ አወጣጥም ሆነ በሌላ ምክንያት ቢፈዝና ቢጓደል ደግሞ ሥር የያዘ ዴሞክራሲ ካለን እሱ እየተከታተለ ለሕጉ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡ ለ60ኛው የአልማዝ ኢዮቤልዩ ማለም ያለብን ለእንዲህ ዓይነት የመንግሥት ገንዘብና በጀት አያያዝ ፍጥርጥር ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡