Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልስምንት መቶ ዓመታት ያስቆጠሩ የጣና ገዳማት ዕድሳት እንደሚያስፈልጋቸው ተገለፀ

ስምንት መቶ ዓመታት ያስቆጠሩ የጣና ገዳማት ዕድሳት እንደሚያስፈልጋቸው ተገለፀ

ቀን:

በጣና ሐይቅ ከ13ኛ ምዕት ዓመት ጀምሮ በየዘመኑ እንደተመሠረቱ የሚነገርላቸው በርካታ ገዳማት ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም ዕድሳት እንደሚያስፈልጋቸው የዑራ ኪዳነ ምሕረት ቁልፍ ያዥ አባ ፍሬ ስብሐት ገልጸዋል፡፡  

በገዳማቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶች፣ ጥንታውያን የ13ኛው ምዕት ዓመት የብራና መጻሕፍት፣ ሥዕል፣ ወዘተ እንዲሁም የቀድሞ ነገሥታት አልባሳትና አፅም የሚገኙ ሲሆን፣ በየገዳማቱ ላይ የተገነቡት አብያተ ክርስቲያናት ከቆይታቸው አንፃር እርጅና ተጭኗቸው ከ13ኛው ምዕት ዓመት ጀምሮ ታሪክን ከዘመን ዘመን እያሸጋገሩ ያለፉት እነዚህ ገዳማት ዕድሳት እንደሚያስፈልጋቸውና በተለይ በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሣሉ የተገለጸው የዑራ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ሥዕሎች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ዕድሳት እንደተደረገላቸው ቢነገርም፣ አሁን ላይ ተጨማሪ ዕድሳት ካልተደረገላቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ ተናግረዋል፡፡

በጥንታዊ ቅብ ሥዕሎች ከሚታወቁት አንዱ የሆነው ዑራ ኪዳነ ምሕረት ተጠቃሽ ነው፡፡ ዑራ ኪዳን ምሕረት በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዐምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት በአቡነ ዘዮሐንስ እንደተመሠረተች ይነገራል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በሥዕል መልክ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ግድግዳው እያረጀ በመምጣቱ አስቸኳይ ዕድሳት እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል፡፡

ለዑራ ኪዳነ ምሕረት ዕድሳት ለማድረግ አንድ ዓመት የፈጀ ጥናት መደረጉንና ይህም ሥዕሎቹን ባሉበት ቦታ ለመመለስ እንደሚያስችል፣ አባ ፍሬ ስብሐት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከባህልና ቱሪዝም ጋር በመወያየትም ሥዕሉ እንዳለ ተነስቶ ዕድሳት እንደሚከናወንለት አክለዋል፡፡

መስከረም 2010 ዓ.ም. የሚጀመረው ዕድሳቱ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ታሪካዊ መስኅቦች በየቦታቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርግ አባ ፍሬ ስብሐት ተናግረዋል፡፡

የቅኔ ማህሌቱ ከሸንበቆ፣ ቅድስቱና መቅደሱ ከመንፈቅ ወራት በላይ ሲቦካ ከቆየ ጭቃና ድንጋይ የተሠሩ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ጣሪያው በሳር ክፍክፍ የተሸፈነ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ባሕር ዳር ከተማ ካሏት የቱሪስት መዳረሻዎች አንፃር ለጎብኚው ምቹ የሆኑ የትራንስፖርትና መሠረተ ልማቶች አለመሟላት እንቅፋት እየሆኑ መምጣታቸው ይነገራል፡፡ የጢስ ዓባይ መንገድም አመቺ አለመሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌላኛው ተፈጥሯዊ መስኅብ ከሆኑት መዳረሻዎች ውስጥ ደሴቶቹን የሚያገናኙ የየብስ መንገዶች ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ደሴቶች የውኃ ትራንስፖርት፣ የየብስ መጓጓዣ ሲኖሩት፣ መንገዶቹን ለመገንባት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ግንባታቸውን አጠናቆ ለመሥራት ከስምምነት መደረሱን የባሕር ዳር አስተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መምሪያ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ቀድሞ በውኃ ትራንስፖርት ወደ ዑራ ኪዳነ ምሕረት ሲደረግ የነበረውን ጉዞ በቀጣይ ከባሕር ዳር ዘጌ ድረስ የሚደርስ መንገድ ፕሮጀክት ተጠንቶና ጨረታ ወጥቶ ግንባታው በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀመር አቶ በሰላም አስረድተዋል፡፡

የመንገዶቹ መገንባት የቱሪዝም ገቢ ከማሳደጉም ባሻገር ለአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ለሚመጡ ቱሪስቶች ተፈጥሯዊ የሆኑ አካባቢዎችን ለመመልከት ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡

ከዑራ ኪዳነ ምሕረት ዕድሳት ጋር ተያይዞም የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ነባራዊ ሁኔታቸው ተጠብቆ እንዲታደሱ ጥናት ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል ተብሏል፡፡

ዓምና በከተማዋ የተከሰተውን ረብሻ ተከትሎ እስካሁን ድረስ የፀጥታ ችግር እንዳለ በማድረግ ያልተገባ ስም እንዲሰጣት የሚያደርጉ ወገኖች እንዳሉ መደረጉ ስህተት እንደሆነና ከተማዋም ሰላማዊ እንደሆነች አቶ በሰላም ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ