በደነቀ ፀጋዬ አባይሬ
የ40/60 የመኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም በሕግ ብቻ መመራት ያለበት የመንግሥት ፕሮግራም ነው፡፡ ለዚህ ፕሮግራም ዋነኛው መነሻ ‹‹የ40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ የቤት ፈላጊዎች የምዝገባ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 21/2005 ዓ.ም.›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ሕግ በሌላ ሕግ እስካልተሻረ ድረስ ሁሉም ወገን በአግባቡ ሊገዛበት የግድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በግልጽ ማየት እንደተቻለው ይህ የ40/60 ፕሮግራም ዕርዳታ (Charity) ወይም ደግሞ መጠቃቀሚያ እየሆነ ያለ ይመስላል፡፡ የ40/60 ፕሮግራም እንደተፈለገው በዕርዳታ መልክ የሚታደል አይደለም፡፡ ይልቁንም ከላይ በተመለከተው የፕሮግራሙ መመርያ አንቀጽ 16 እና በሥሩ በተዘረዘሩት ንዑስ አንቀጾች መሠረት የሚፈጸም ነው፡፡ መንግሥት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ፣ ለሁሉም ቤት አልባ ወገኖች እኩል የሆነ ዕድል ሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ በግልጽ ማየት እንደተቻለው ሕጉና መመርያው በእጅጉ እየተጣሰ ነው፡፡ አፈጻጸሙ በሙሉ ግለ ሕግን በተላበሰ መንገድ አንዱን ልጅ አንዱን ደግሞ የእንጀራ ልጅ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ሕግን ባልተላበሰ ውሳኔ መሠረትም የ648 ዕድለኞች (ዜጎች) ሕጋዊ መብት በጠራራ ፀሐይ መነጠቅ ችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህንን የዕድል ነጠቃ ጉዳይ እስከ ወዲያኛው ድረስ አደባብሶ ለማለፍና ለመሸፋፈን፣ የተለያዩ ኃላፊዎች በተለያዩ ሚዲያዎችና መድረኮች እየቀረቡ ፍፁም ያልተገባና ከፕሮግራሙ መመርያ ጋር በእጅጉ የሚጣረስ መግለጫ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን እውነታ በአግባቡ መመልከት ካስፈለገ፡-
- እሑድ ሐምሌ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት በኢቢሲ አንድ የቀረበውን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ የአቶ ይድነቃቸው ዋለልኝን መግለጫና ማብራሪያ ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡
- ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢቢሲ አንድና በኤፍ ኤም 102.1 ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የቀረበውን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የአቶ አባተ ስጦታውን መግለጫ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በመጀመሪያ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በመግለጫ ጋጋታ ሳይሆን፣ ሕጉና መመርያው በሚፈቅደው ብቻ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ መፍትሔው የሚገኘው ነገረ ጉዳዩን አድበስብሶ በማለፍ ሳይሆን፣ መመርያውን በአግባቡ መተርጎም ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለማንሳት የምፈልገው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም በዚህ እውነታ ላይ በሁሉም ወገኖች የሚሰጡት መግለጫዎች በሙሉ ማለት ይቻላል የዕድለኞችን ሕጋዊ መብት ለማስከበር ሳይሆን፣ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት የሁለቱን ባለሥልጣናት (የሥራ አስኪያጁንና የምክትል ከንቲባውን) መግለጫ እንደ ቅደም ተከተሉ መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡
የሥራ አስኪያጁን መግለጫ በተመለከተ በመጀመሪያ ከእሳቸው መግለጫ ውስጥ ቀጥሎ የተመለከቱትን ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች በአግባቡ እንመልከት፡፡
- ‹‹የዲዛይን ስህተት ሊፈጠር ችሏል፡፡ በዚህም መነሻ ምክንያት ከሰንጋ ተራና ከክራውን የ40/60 ሳይቶች ውጪ ባሉ 11 የ40/60 ሳይቶች ላይ ማስተካከያ ተደርጓል. . .›› የሚለውን፣
- የሕንፃው መሠረት ቢሮው ከመቋቋሙ በፊት የተጀመረው ነው፡፡ ቢሮው በወቅቱ አልተቋቋመም ነበር፤›› የተባለውን
ከእነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ በመነሳት ደግሞ የሚከተሉትን አራት የሆኑ ጥያቄዎችን በአግባቡ ማየት ይገባል፡፡
- የዲዛይን ስህተት መኖሩ በአግባቡ ከተረጋገጠ ለባለ ዕድለኞቹ ለምን አስቀድሞ ተገቢ የሆነ መግለጫ መስጠት አልተቻለም?
- የዲዛይን ስህተት መኖሩ በአግባቡ ከታወቀ የሠንጋ ተራና የክራውን የ40/60 ሳይቶች ለምን እንደ 11ዶቹ የ40/60ዎቹ ሳይቶች ማስተካከያ አልተደረገባቸውም?
- እሺ ቤቶቹ በዲዛይን ስህተትም ተገንብተው ተጠናቀዋል ይባል፡፡ ባለ አንድ መኝታ ዕድለኞች ብቻ ተለይተው ለምን እንዲሰረዙ ተደረገ? በምን ዓይነት የሕግ አግባብስ ተወሰነ? ከሁሉም በላይ ደግሞ የሁሉም ዕድለኞች (ባለ አንዱም፣ ባለ ሁለቱና ባለሦስቱም መኝታ ክፍሎች) መጠን ሰፋፊ ተደርገው የተሠሩበት እውነታ ባለበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ በአግባቡ ሊመለስ የሚገባው መሠረታዊ ጥያቄ ቢኖርም ይህና ይህ ነው፡፡
- እነዚህ ከዲዛይን ውጪ ተገነቡ የተባሉት የሰንጋ ተራና የክራውን 40/60 መኖሪያ ሕንፃዎች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምን ዓይነት የሕግ አግባብ ማስረከብ ተቻለ? የሚለውም ሌላው ጥያቄ ነው፡፡
እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሁሉም ዓይነት ዕድለኞች ማለትም የባለ አንድ፣ የባለ ሁለትና የባለሦስት መኝታ የጋራ ጥያቄዎች መሆናቸው በአግባቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እነዚህን እውነታዎች እያድበሰበሱ ማለፍና ያልተገባ መግለጫ መስጠት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ስህተትም ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ የሆነ የተጠያቂነትም ጉዳይ በአግባቡ ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የብዙኃኑን በደል እስከ ወዲያኛው ድረስ ሸፋፍኖ ለማለፍ የሚደረገው ፍፁም ተዓማኒነት የሌለው መግለጫ ሊቆም ይገባል፡፡ የዜጎችን ሥነ ልቦና ‹‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት›› በሚለው ዓይነት ዘይቤ በላይ በላዩ ማቁሰል አይገባም፡፡ መግለጫዎቹ በሙሉ የዕድለኞችን ሕጋዊ መብት የሚያስከብሩ ሳይሆኑ፣ ይልቁንም በጠራራ ፀሐይ የተነጠቁት ዜጎች ዕድል ለመሸፋፈንና ንጥቂያውን ሕጋዊ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው በአግባቡ ሊታይ የሚገባው ቢኖር የሰንጋ ተራውና የክራውኑ የ40/60 መኖሪያ ቤቶች ውስጣዊ ክፍሎች ልክ እንደ ሌሎቹ የ40/60 11 ሳይቶች ማስተካከያ ነገር ተደርጎለት ቢሆን ኖሮ፣ ሊኖር ይችል የነበረውን መሠረታዊ ጠቀሜታ በአግባቡ ማየት ያስፈልጋል የሚለው ነው፡፡ ይህንንም ተጨባጭ በሆነ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ማየት ይቻላል፡፡
በመጀመርያ ለባለ ዕድለኞች ተላልፈዋል ከተባሉት 972 ዕድለኞች በተጨማሪ ለሌሎች 333 ባለሁለትና 111 ባለሦስት መኝታ ዕድለኞች በድምሩ ለ444 ዕድለኞች፣ እንዲሁም ለ204 ባለ አንድ መኝታ ዕድለኞች በጠቅላላው ለ648 ዕድለኞች ሊሰጥ ይችል የነበረ የ40/60 መኖሪያ ቤት የቤት ባለቤትነት ዕድል ሊፈጠር ይችል ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ እንዴት? ማለት ካስፈለገ ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከተውን በአግባቡ መመልከት ይበቃል፡፡ በሰንጋ ተራ አካባቢ ተገንብተው ለዕድለኞች ተላልፈዋል ከሚባሉት ባለ 12 ወለል ሕንፃዎች እንነሳ፡፡ ባለ 12 ወለል ሕንፃ አንድ ወለል ላይ ስድስት ዕድለኞች ብቻ ይገኛሉ፡፡ በሌሎች ተስተካክለዋል በተባሉት 11 የ40/60 ሳይቶች ላይ ባሉ ባለ 12 ወለል ሕንፃ አንድ ወለል ላይ አሥር መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ማረጋገጥ ካስፈለገ በመገናኛ የ40/60 መኖሪያ ቤቶች ሳይት ከተገነቡት ባለ 12 ወለል ሕንፃዎች መካከል አንዱን ሕንፃ ወስደን እንመልከት፡፡ በዚህ የአንድ ሕንፃ አንድ ወለል ላይ አሥር ዕድለኞች (መኖሪያ ቤቶች) ይገኛሉ፡፡ በአሥር ወለሎች ላይ ደግሞ 100 ዕድለኞች አሉ ማለት ነው፡፡
ወደ ሰንጋ ተራው የ40/60 ሳይት ስንመለስ ግን ይህንን ዓይነት ዕድል ፈጽሞ ማግኘት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በሰንጋ ተራ ባለው አንድ ባለ 12 ወለል ሕንፃ ላይ ለመኖሪያ ቤት የሚሆኑ አሥር ወለሎች ቢኖሩም፣ በአንድ ወለል ላይ ያለው የመኖሪያ ቤት (ዕድለኞች) ብዛት ስድስት ብቻ ነው፡፡ በዚህም ሥሌት መሠረት በአሥሩ ወለል ላይ 60 ዕድለኞች ብቻ ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በመገናኛና በሰንጋ ተራ ተመሳሳይ በሆነው ባለ 12 ወለል ሕንፃ ላይ የ40 መኖሪያ ቤቶች (ዕድለኞች) ልዩነት አለ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት በሰንጋ ተራ ባሉ አምስት ባለ 12 ወለል ሕንፃዎችና በክራውን ሳይት ባሉት 14 ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንፃዎች ላይ፣ ተጨማሪ 648 ዕድለኞች የመኖሪያ ቤት ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህንን ሥሌት ለመረዳት ቀጥሎ የተመለከተውን ተጨማሪ ትንታኔ በአግባቡ መመልከት ያስፈልጋል፡፡
በሰንጋ ተራ ሳይት
በአንድ ባለ 12 ወለል ፎቅ ሕንፃ አንድ ወለል ላይ አሥር ዕድለኞች፣ በአሥር ወለሎች ላይ 100 ዕድለኞች፣ በአምስት ሕንፃዎች ላይ ደግሞ 500 ዕድለኞች ሊኖሩ ይችሉ ነበር ማለት ነው፡፡
በክራውን ሳይት
በአንድ ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንፃ አንድ ወለል ላይ አሥር ባለ ዕድለኞች፣ በስምንት ወለሎች ላይ 80 ዕድለኞች፣ በ14 ሕንፃዎች ላይ ደግሞ 1,120 ዕድለኞች ሊኖሩ ይችሉ ነበር ማለት ነው፡፡
በሰንጋ ተራና በክራውን ሳይቶች ርክክባቸው ተፈጽሟል፡፡ የተባሉት ሁለቱ ሳይቶች ልክ እንደ ሌሎቹ 11 ሳይቶች የ40/60 መኖሪያ ቤቶች በአግባቡ ተስተካክለው ተገንብተው ቢሆን ኖሮ፣ በአጠቃላይ 1,620 ዕድለኞች የቤት ባለቤት መሆን የሚችሉበት ዕድል ይኖር ነበር፡፡ አሁን በተጨባጭ የሆነው ግን በግልጽ ማየት እንደተቻለው 972 ዕድለኞች ብቻ መሆን ችለዋል፡፡ በዚህና በመሳሰለው የአሠራር ጉድለትና ችግር ምክንያት፣ ወይም ደግሞ ፍትሕ አልባ በሆነው አሠራርና የኃላፊነት ጉድለት ምክንያት፣ በጠቅላላው የ648 ዜጎች ዕድል በጠራራ ፀሐይ ተነጥቋል ማለት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ 648 ዕድለኞች ለተጨማሪ ያልተገባ የቤት ኪራይና ወጪ፣ እንዲሁም ወደፊት ሊከሰት በሚችለው እነሱን በማይመለከታቸው የዋጋ ልዩነት (ተጨማሪ ዕዳ) እንዲጠቁ ተደርገዋል ማለት ነው፡፡ ቀጣይ ሕይወታቸውም በኪራይ ሕይወት ውስጥ ተዘፍቆ እንዲኖርና ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት እንዲሰቃዩ የተደረገበት አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ የመንግሥት መመርያ፣ የተጠቃሚ ዕድለኛ ወገኖች ጉጉትና ምኞት ግን እንዲህ እንዳልነበረ በአግባቡ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የምክትል ከንቲባውን መግለጫ በተመለከተ
ምክትል ከንቲባው በ40/60 መኖሪያ ቤቶች የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸምና የ2010 ዓ.ም. የሥራ ዕቅድ ላይ ከኮንትራክተሮች፣ ከአማካሪዎችና ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ባደረጉ ጊዜ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱትን መልሶች ሰጥተዋል፡፡ ‹‹. . . ይኼ ነገር ‹ጀስት› የግንባታ ብልሽት የለውም፡፡ የጥራት ችግር የለውም፡፡ ዳሜጅ የለውም፡፡ ቤቶቹ ሰፍተዋል፡፡ ይኼ በዲዛይን የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡ ተገቢውን ትምህርት ወስደን አሁን በቀሪዎቹ በሚሠሩት 38 ሺሕ ቤቶች ላይ ተገቢውን ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ከሚገባው በላይ ሰፍተዋል ማለት ነው ቤቶቹ፡፡ ስለዚህ ፌር አይሆንም፡፡ እነዚህን ባለ አንድና ባለ ሁለት መኝታ ቤት ውስዱ ብለህ ለ55 ካሬ ሜትር የተመዘገቡ ሰዎችን 125 ካሬ ሜትር ውሰዱ ብሎ እንትን ማለት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡ . . . እዚህ ላይ ስህተት የሚያጋጥም ነው፡፡ የሚጠየቅበት ይቅርታ የለም፡፡ ምክንያቱም ዕድሉ አላቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ‹ኦሬዲ› አሉ፡፡ ስለዚህ በዲዛይን የሚያጋጥም ስህተት ነው፡፡ ‹ቴክኒካሊም› የሚያጋጥም ስህተት ነው፡፡ በተገቢው ማስተካከያ ያለፋቸው ሰዎች ተካክሰው በሚቀጥለው ቅድሚያ የሚያገኙበት ሥርዓት ይዘረጋል ማለት ነው፡፡ . . .ቤቶቹ በ18 ወር እንደማያልቁ ከመነሻው ትክክል እንዳልነበረ አረጋግጠናል፡፡ ይስተካከላል አሁን፡፡ ‹ዘ ሆል› ፕሮግራሙ ‹ፕራክቲካሊም› አንድ ሕንፃ ‹ጂ ቱዌልቭ› በ18 ወር በአገራችን ውስጥ ያለቀበት ሁኔታ የለም፡፡ ስህተት ነው ይህ ሁሉ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ የሆነውን ‹ታይም ሴት› አድርገን ለፕሮግራሞቹ ‹አጀስትመንት› ይደረጋል፡፡ ማስተካከያ ይደረግባቸዋል ማለት ነው. . .›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህ የምክትል ከንቲባው መልስ በእጅጉ አስገራሚና አሳዛኝ እንደሆነ በአግባቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህንን የምለው ደግሞ ያለበቂ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ከምክትል ከንቲባው መልሶች መካከል የሚከተሉትን ስድስት አባባሎች ብቻ በአግባቡ ወስዶ መመልከት ይቻላል፡፡
- ‹ጀስት የግንባታ ብልሽት የለውም፡፡ የጥራት ችግር የለውም፡፡ ዳሜጅ የለውም፡፡›
- ‹ይኼን ተገቢውን ትምህርት ወስደን አሁን በቀሪዎቹ 38 ሺሕ ቤቶች ላይ በሚሠሩት ላይ ተገቢውን ማስተካከያ ተደርጓል፡፡›
- ‹እነዚህን ባለ አንድ መኝታ ቤቶች ባለ ሁለት መኝታ ቤት ውስዱ ብለህ ለ55 ካሬ ሜትር የተመዘገቡ ሰዎችን 125 ካሬ ሜትር ውሰዱ ብሎ እንትን ማለት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡›
- ‹ስህተት ነው የሚያጋጥም ነው፡፡ የሚጠየቅበት ይቅርታ የለም፡፡ ምክንያቱም ዕድሉ አላቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ኦሬዲ አለ፡፡ ስለዚህ በዲዛይን የሚያጋጥም ስህተት ነው፡፡ ቴክኒካሊም የሚያጋጥም ስህተት ነው፡፡›
- ‹ያለፋቸው ሰዎች ተካክሰው የሚቀጥለው ቅድሚያ የሚያገኙበት ሥርዓት ይዘረጋል ማለት ነው፡፡›
- ‹ዘ ሆል ፕሮግራሙ ፕራክቲካሊም አንድ ሕንፃ ጂ ቱዌልቭ በ18 ወር በአገራችን ውስጥ ያለቀበት ሁኔታ የለም፡፡› የሚሉትን ነጥቦች አንድ በአንድ ወስደን እንመልከት፡:
በመጀመርያ ዋነኛው ጥያቄ መንግሥት ለዜጎቻችን በሕጋዊ መንገድ (መመርያን መሠረት ያደረገ) የፈቀደው የዕድለኞች ሕጋዊ መብት ተገቢ የሆነ ምላሽ አልተሰጠውም የሚለው ነው፡፡ ምክትል ከንቲባው ግን ይህንን ነባራዊ እውነታ ወደ ጎን ትተው ያልተገባና ከጉዳዩ ጋር ያልተያያዘ መልስ ሰጥተዋል፡፡
እነዚህ በምክትል ከንቲባው የተገለጹት አባባሎች በሙሉ የ40/60 መኖሪያ ቤትን መመርያ የተላበሱ አይደሉም ማለት ይቻላል፡፡ ይልቁንም ደግሞ ግለ ሕግን የተላበሱ ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ የ40/60 ፕሮግራም ዋነኛው ተልዕኮ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤት ባለቤት ማድረግ ሲሆን፣ ይህንንም በተመለከተ በምክትል ከንቲባው አንድም ነገር አልተባለም ማለት ይቻላል፡፡ ምክትል ከንቲባው በሰጡት መልስ ላይ ብዙ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹በዲዛይን የሚያጋጥም ስህተት ነው፡፡ ቴክኒካሊም የሚያጋጥም ስህተት ነው፤›› በማለት የሰጡት መልስ የሚያስገርም ነው፡፡ ለመሆኑ 648 ዕድለኞችን ባዶ ያደረገ ግዙፍ ስህተት ተፈጽሞ ‹ቴክኒካሊ ስህተት ነው› ብሎ መናገር ተገቢ ይሆን? የእዚህን መልስ ለባለ ሙያዎች አስተያየት ትቶ ማለፍ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ እንደኔ እንደኔ አንድ ነገር ብሎ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በምክትል ከንቲባው መልስ ውስጥ ሊጠቀስ የሚችለው አስገራሚ ጉዳይ ‹‹ዳሜጅ የለም›› የሚለው ነው፡፡ በመጀመርያ ‹ዳሜጅ› የሚባለው ጉዳይ ‹ማቴሪያል› ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ይልቁንም የበርካታ ዜጎቻችን ሕጋዊ መብት ቅጥ ባጣ አድሎአዊ አሠራር በመነጠቁ፣ ከፍተኛ የሆነ የህሊና ‹ዳሜጅ› መፈጠሩ በአግባቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የ‹ዳሜጅ› ጉዳይ ከተነሳ በብዙ ዓይነት መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡
ተስተካክለው በተገነቡት 11 የ40/60 ሳይቶች ውስጥ ይደረግ በነበረው የማስተካከል ሥራ ላይ ከፍተኛ የሆነ ‹ዳሜጅ› መኖሩ በአግባቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በወቅቱ የነበረውን ‹ዳሜጅ› እንዲህ ቀላል ነገር ነበር ብሎ መግለጽ አይቻልም፡፡ ይህም ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ሌላው ሊገለጽ የሚገባው ጉዳይ የ40/60 መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም በተቀመጠለት ዕቅድ መሠረት ወቅቱን ጠብቆ ቤቶቹን አጠናቆ ለባለ ዕድለኞች ማስረከብ አለመቻሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በራሱ ጊዜ የጊዜ ‹ዳሜጅ› ነው ማለት ይቻላል፡፡ የ40/60ን ‹ዳሜጅ› በተመለከተ በአግባቡ ለመግለጽ ካስፈለገ የዜጎች የሞራል ‹ዳሜጅ›፣ የዜጎች ገንዘብና ማቴሪያል ‹ዳሜጅ›፣ እንዲሁም እጅግ በጣም የተንዛዛው የጊዜ ‹ዳሜጅ› ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡ የተከበሩ ምክትል ከንቲባ ይህንን ሀቅ በአግባቡ ሊቀበሉት ይገባል፡፡ መቀበልም ብቻ ሳይሆን ዜጎችንም በአግባቡ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፡፡
ሌላው በምክትል ከንቲባው ምላሽ ውስጥ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር፣ ‹‹እነዚህን ባለ አንድና ባለ ሁለት መኝታ ቤት ውሰዱ ብለህ ለ55 ካሬ ሜትር የተመዘገቡ ሰዎችን 125 ካሬ ሜትር ውሰዱ . . . ማለት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፤›› የሚለው ነው፡፡ ይህም አስገራሚ ነው ለመሆኑ አሁን ዕድለኞች ሆነው የቀረቡት የባለ ሁለትና የባለ ሦስት መኝታ ክፍል ተመዝጋቢዎች (100 ካሬ ሜትር የነበረው ባለ ሦስት መኝታ 150 እና 168 ካሜ ተደርጎ 75 ካሬ ሜትር የነበረው ባለ ሁለት መኝታ 124. ካሜ) ተደርጎ የተሰጣቸው በምን ዓይነት የሕግ አግባብ ይሆን? ለመሆኑ ባለ 55 ካሬ ሜትር የሆኑት ባለ አንድ መኝታ ዕድለኞች 107 ካሬ ሜትር የሆነውን ቤት እንዲያገኙ ቢደረግ ኖሮ፣ ለባለ ሁለትና ለባለ ሦስት መኝታ ዕድለኞች ከተሰጠው ዕድል ጋር በምን ዓይነት ሁኔታ ይለይ ይሆን? ለዚያውም ደግሞ ሁሉም ቤቶች መመርያውን ባልጠበቀ መጠነ ስፋት ላይ ተመሥርተው በተገነቡበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ሌላው በአግባቡ ሊታይ የሚገባው ቢኖር ‹‹ዘ ሆል ፕሮግራሙ ፕራክቲካልም አንድ ሕንፃ ጂ ቱዌልቭ በ18 ወር በአገራችን ውስጥ ያለቀበት ሁኔታ የለም፤›› የሚለው ነው፡፡
- ይህንን በተመለከተ ብዙ ማለት አያስፈልግም፡፡ ግን ግን ደግሞ አንድን ጉዳይ በአግባቡ ገልጾ ማለፍ ይገባል፡፡ በመጀመርያ ተገቢ የሆነ የፋይናንስ አቅም እስካለ ድረስ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥም ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማወቅ ይገባል፡፡ 18 ወራት ማለት እጅግ በጣም ሰፊ የሆነ ጊዜ ነው፡፡ በሠለጠኑ አገሮች እንኳ በየብስ (ደረቅ መሬት) ላይ ቀርቶ በውኃማ አካል ላይ እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ ግንባታ ማከናወን ተችሏል፡፡ ሌላው ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ‹‹ዕድሉ ያለፋቸው ሰዎች ተካክሰው በሚቀጥለው ቅድሚያ የሚያገኙበት ሥርዓት ይዘረጋል፤›› የሚለው ነው፡፡ ይህም ግርምት ይፈጥራል፡፡ ለምን ቢባል መመርያው ይህንን ስለማይል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሊታወቅ የሚገባው ዋናውና ሕጋዊ የሆነው መብት በጠራራ ፀሐይ ተቀምቶ፣ በሚቀጥለው ተካክሶ ይሰጣቸዋል ብሎ መናገር ቀልድ ነው፡፡ በማንኛውም ወገን በአግባቡ ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ፣ እነዚህ 648 ዕድለኞች ወሳኝ የሆነውን ሕጋዊ መብት መቀማት የቻሉት ዝም ብሎ አይደለም፡፡
- ይልቁንም 111 የባለ ሦስት መኝታ ዕድለኞች እያንዳንዳቸው 386,400.00 ብር= 42,890,400.00 ብር፣
- 333 የባለ ሁለት መኝታ ዕድለኞች እያንዳንዳቸው 250,000.00 ብር= 83,250,000.00 ብር፣
- 204 የባለ አንድ መኝታ ዕድለኞች እያንዳንዳቸው 162,645.00 ብር= 33,179,580.00 ብር፣
በድምሩ፡- 648 ዕድለኞች በአጠቃላይ= 159,319,980.00 ብር በባንክ መቆጠብ መቻላቸው ነው፡፡
ይህም ገንዘብ በተጨማሪ በባንክ ሊቆጥቡ የሚችሉትና የባንክ ወለድ ሳይታሰብ ማለት ነው፡፡ ይህ የ648 ዕድለኞች ቁጠባ ሲታይ ዕድለኞቹ ከመንግሥት ከሊዝ ነፃ የሆነ መሬት ቢሰጣቸው ኖሮ፣ በትንሹ ከአምስትና ከስድስት የማያንሱ ባለ 12 ወለል ሕንፃዎችን መገንባት ይችሉ ነበር ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ያህል አቅም የፈጠሩትን ዕድለኞች ፍፁም የሆነ አድልኦና መገለል በማድረግ፣ አንዲትም ዕድል እንዳያገኙ ሲደረግ በእጅጉ የሚዘገንን በደል ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ በዜጎች ላይ የተፈጠረው ከፍተኛ የሆነ በደል በአግባቡ መታየት ያለበት ሲሆን፣ የአገሪቱ የበላይ አመራሮችም በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ሊሰጡበት ይገባል፡፡ በአገሪቷ ሕግ መሠረትም ተገቢው የማስተካከያ ዕርምጃ ተወስዶ፣ ውጤቱ ለመላው ሕዝቡ በአግባቡ ሊገለጽ ይገባል እላለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡