በውብሸት ሙላት
የግብር ነገር ሕዝባዊ መነጋገሪያ ከሆነ እየሰነበተ ነው፡፡ ስለምን መነጋገሪያ እንደሆነ ለሚጠይቅ በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ የመጀመርያውና ዋናው አዲሶቹ የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆች ሥራ ላይ መዋል ሲጀምሩ ይዘውት የመጡትን ለውጦች መጥቀስ ይቻላል፡፡
የግብር ከፋዮች ደረጃ መሻሻል፣ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የግብር አሰላል ከቀድሞው መለየት፣ አዲስ አበባ ላይ የገቢ ግመታ ከተካሔደ ስድስት ዓመታት መሆኑ (በየሦስት ዓመቱ አለመገመቱ)፣ አዋጆቹን ለማስፈጸም የሚረዱት ደንቦችና መመርያዎች በወቅቱ አለመውጣታቸው፣ የመንግሥት ከወትሮው በተለየ ከፍ ያለ ገቢ ከግብር ከፋዩ ለመሰብሰብ ማቀዱ እንዲሁም የተለመደው የግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት የግብር አስተዳደር ድክመትና የፖለቲካ ድባቡን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በቅድሚያ ለተያዘው የበጀት ዓመት የመንግሥትን የገቢ ፍላጎት እንመልከት፡፡ የዓመቱ በጀት ከመጽደቁ አስቀድሞ በተለምዶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ የበጀት ንግግር ያደርጋል፡፡ በዚህም ዓመት ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ንግግር አድርገዋል፡፡ ከግብር ጋር የተያያዙት በተለይም የመንግሥትን ፍላጎትና ሥጋት ብቻ እንመልከት፡፡
መንግሥት ለ2010 የበጀት ዓመት ከያዘው 320 ቢሊዮን ገደማ የሚሆን ብር ውስጥ ከታክስ የሚጠበቀው ገቢ ብር 196.4 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ለ2009 ታቅዶ ከነበረው የታክስ ገቢ የ15.1 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደው 170.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ እንደሚኒስትሩ ገለጻ፣ በ2009 ዓ.ም. ገቢ ይደረጋል ተብሎ ታቅዶ ከነበረው በዘጠኝ ወራት ውስጥ መሰብሰብ የተቻለው 98.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በበጀት ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ 57.4 በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከ42 በመቶ በላይ የሚሆነው በሦስት ወራት እንዲሰበሰብ ይጠበቃል፡፡
ይሁንና የታክስ ገቢ ግምቱ የታክስ አስተዳደሩ እመርታዊ ለውጥ እስካላመጣ ድረስ የገቢ አሰባሰቡ አሁን ካለበት ዝቅተኛ አፈጻጸም በበጀት የተያዘውን ገቢ መሰብሰብ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
እንግዲህ ይኼ ግብርን በተመለከተ የመንግሥት ፍላጎትና ሥጋት ነው፡፡ ከሚኒስትሩ ንግግር መረዳት የሚቻለው ሌላው ቁምነገር ደግሞ ከውጭ የሚገኘው የልማት ዕርዳታ እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ በተጨማሪም ከውጭ የሚደረግ ብድርም ቢሆን የአገሮች የመክፈል አቅም እየተመዘነ ስለሚፈጸምና በዚህ ረገድ የነበራት ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ ከግምቱ መግባት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
እንግዲህ እነዚህ የበጀት ዓመቱ የመንግሥት የገቢ ፍላጎትና ዋና ዋና ሥጋቶች ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሚዳሰሰው ግን በዋናነት ከግብር ሕጎቹ ጋር በተያያዘ የመንግሥት የግብር አስተዳደር ድክምት ምንጮችንና የግብር ፍትሑን እየተፈታተኑት ያሉትን ነጥቦች አጠር በማድረግ መዳሰስ ነው፡፡
የግብር ፍትሕ (Tax Justice)
የግብር ፍትሕን ለመተርጎም የሞከሩ ጸሐፍት ቁርጥ ያለ ትርጉም መስጠት ቢሳናቸው “የግብር ፍትሕ እንደ ዝሆን ነው” ይላሉ፤ የሚታወቅ ነገር ግን የማይተረጎም ለማለት ሲፈልጉ ነው፡፡ የግብር ፍትሕን አንድ ወጥ ብያኔ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ ግብርን በተመለከተ ግዴታና መብት (ሥልጣን) ያላቸውን አካላት በመለየት ከሚኖራቸው መስተጋብር አንፃር መመልከቱ ነገሩን ያቀለዋል፡፡
ስለሆነም፣ የግብር ፍትሕ በዋናነት የግብር ከፋይና የመንግሥት እንዲሁም የአንድ አገር ከሌላ አገር ጋር በግብር ጉዳይ የሚኖራቸው የግንኙነት ሁኔታን ወይንም የእርስ በርስ ግዴታዎችና ኃላፊነትን ይመለከታል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “ግብር” የሚለው ቃል ግብር፣ ታክስና ቀረጥንም ያካትታል፡፡ ግብር ከፋይ ሲባልም እንዲሁ እነዚህን የመክፈል ግዴታ ያለበትን ማንኛውንም አካል ያጠቃልላል፡፡ ግብር ከፋዩን በተመለከተ በቅድሚያ በማቅረብ የመንግሥትን ግን ወረድ ብለን እንመለስበታለን፡፡ የአገሮች የእርስ በርስ ግንኙነት ግን የዚህ ጽሑፍ አካል አይደለም፡፡
ለግብር ከፋዩ የግብር ፍትሕ ማለት መንግሥት በሕግ መሠረት ማንኛውም ሰው ባለንብረት በመሆኑ፣ በመነገዱ፣ ገቢ በማግኘቱ፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን ከመንግሥት በማግኘቱ ወዘተ ለመንግሥት ግብር የመክፈል ግዴታ ጋር ይያያዛል፡፡ ሳያጭበረብሩ፣ ሳይሰውሩ፣ ሳይደብቁ ትክክለኛውን መጠን ሕግ በሚያዘው መሠረት መክፈልን ይጠይቃል፡፡ ይህ ከግብር ከፋዩ የሚጠበቀው ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የግድ የግብር ሕግ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ያለ ሕግ ግብር አይጣልም፡፡ ግብር የሚከፈልበት ማንኛውም ነገር ማለትም የግብር መሠረት እንዲሁም ምጣኔውም ቢሆን አስቀድሞ በሕግ የተለየና የታወቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በመሆኑም፣ የግብር የሕጋዊነት መርሕን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ በአገራችን የሕጋዊነት መርሕ በሰፊው የሚታወቀው ከወንጀል ሕግ በተያያዘ ቢሆንም፣ በሌሎች አገሮች ግን ግብርንም ይጨምራል፡፡ ለግብር ሕግ ሲሆን ጽንሰ ሐሳቡ በተወሰነ መንገድ በወንጀል ሕግ ከሚታወቀው ልዩነት አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ግብር ከፋዩን ለመጠበቅ የሚረዳ መርሕ ነው፡፡
የግብር ሕጋዊነት መርሕ (Principle of Tax Legality)
የግብር ፍትሕ ሲነሳ አብሮ መነሳት ካለባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ የግብር ሕጋዊነት መርሕ ነው፡፡ መርሑ የሚጠይቀው የግብር ሕግጋት በሚወጡበት ጊዜ በማናቸውም መልኩ መተላለፍ የሌለባቸውን ዝቅተኛ መስፈርቶችን ማሳየት ነው፡፡
የግብር ሕጋዊነት መርሕ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያትና አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አገሮች ‹‹ሳይወከሉ ግብር መክፈል የለም!›› የሚለውን ሐሳብ ያካትታል፡፡ ነገሩ ግብር ከፋይ የሆነ ማኅበረሰብ በመንግሥት ዘንድ ወኪል እንዲኖረው የሚጠይቅ ነው፡፡ ከፋይ ሌላ፣ ገዥው ደግሞ ሌላ ሊሆን አይገባም፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የማይችሉ ስለነበር፣ ለሕዝብ ተወካዮችም ይሁን ለሴኔት አባላት ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚችሉበት ሥርዓት ስላልነበር ‘’እንደራሴ ሳይኖረን ግብር መክፈል የለብንም፤’’ ይሉ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ሥልጣን ላይ ካለ መንግሥት የተለየ፣ ሰፋ ያለ ማኅበራዊ መሠረትና መዋቅር ያለው ኅብረተሰብም ሲያነሳው ይስተዋላል፡፡ በተለይም የፖለቲካና የምርጫ ሥርዓቱ አግላይ በሆነባቸው ሁኔታዎች ይዘወተራል፡፡ ስለሆነም ግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ የበኩሉን ግዴታ ሲወጣ የሚፈልገውን ፖሊሲ ለማስፈጸም የሚረዱትን እንደራሴዎች የሚወክልበት የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስፈኛ ሲሆን ይታያል፡፡ ይህ በሚጠፋበት ጊዜ ማጉረምረምም፣ ማጭበርበርም እንደሚበራከት ሲበዛ ደግሞ ማመጽም እንደሚኖር አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ዋናው የግብር ሕጋዊነት መርሕ የሚያርፈው ግን ‘’ያለ ሕግ ግብር የለም’’ የሚለው ላይ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ “ሕግ ሳይኖር ወንጀል የለም!” እንደሚለው ለግብርም መሠረቱ እንዲሁ ሕግ ነው፡፡ ‘ያለ ሕግ ግብር የለም’ ነው ነገሩ፡፡ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ያለው አካል አስቀድሞ በሕግ ግብሩን ለይቶ ሳይጥል ግብር ከፋዩ እንዲከፍል ሊጠየቀው የሚገባ ክፍያ መኖር የለበትም፡፡ ሕግ የግብርንም ጨምሮ ወደፊት የሚሆነውን እንጂ ቀድሞ የተከናወነን ሊመለከት አይገባም፡፡
ይሁን እንጂ፣ ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የወጡት የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆች ወደኋላ ተመልሰው ተፈጻሚ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ በዚህ ዓመት የሰኔ ወር መገባደጃ ላይ የወጣው የገቢ ግብር ደንብ ወደኋላ ተመልሶ ከ2008 ዓ.ም. ሐምሌ ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን የደንቡ የመጨረሻ አንቀጽ ይናገራል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም በተለይም የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችን ግብር የገመተው ባልጸደቀ ደንብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰነው የትርፍ ምጣኔ ሰንጠረዥ የጸደቀው ከደንቡ ጋር ስለነበር ማለት ነው፡፡
ስለሆነም ሕጉ አስቀድሞ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ግብር ከፋዮቹም አስቀድመው መከፈል ያለባቸውን መጠን የሚያውቁበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ባለሥልጣኑም በኦፊሴል ድረ ገጹ እንዴት እንደሚሰላ ያሳየው የግብር መጠኑን ለከፋዮች ይፋ ካደረገ በኋላ ነው፡፡ አስቀድሞ መገለጽ እንደነበረበት ለየባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እስከሚያወጣ ድረስ የመሸጋገሪያ ሕግ ማውጣት እንደሚችል የግብር አዋጁ ላይ ቢገለጽም የወጣ ደንብ የለም፡፡ ስለዚህ ባለሥልጣኑ እንደሚጸድቅ በማመን ነገር ግን ባልጸደቀ ደንብ ወስኗል ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ላይ ደንብና መመርያ እንዲያወጡ ውክልና የተሰጣቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሌሎች አካላት በሦስት ወራት ውስጥ የማውጣት ግዴታ እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ላይ መደንገጉን ነው፡፡
ሌላው የግብር ሕጋዊነት መርሕ የግብር ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለአስፈጻሚው በውክልና አይሰጥም የሚለው ነው፡፡ በተለይም የግብር መሠረት፣ ምጣኔና ግብር የማይከፈልባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ አስፈጻሚው የመወሰን ሥልጣን ሊኖረው አይገባም፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ መርሕ በተቃራኒው የሚኒስትሮች ምክር ቤትና የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር አዳዲስ የግብር መሠረቶችን መወሰን (ለምሳሌ ንፋስ አመጣሽ ግብር አዲሱ የገቢ ግብር ከመውጣቱ በፊት)፣ ከግብር ነፃ የማድረግ ተግባር ውስጥ በሰፊው ተሰማርተዋል፡፡ በተለይ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉት በዝርዝር ላጤነው የተጨማሪ እሴት ታክስ አጽሙ ብቻ መቅረቱን ይረዳል፡፡
ለነገሩ ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ያደረጉት የዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም (International Monetary Fund) ኃላፊዎችም በተለይ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ በሚል ሰበብ የተደረጉ የግብር እፎይታዎች መነሳት እንዳለባቸው አስተያየት ስጥተዋል፡፡ እነዚህ እፎይታዎች ወይንም በተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የማድረግ ሥራ የተፈጸሙት በአስፈጻሚው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በበርካታ አገሮች እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ለአስፈጻሚው በውክልና አይሰጡም፡፡ በእኛ አገር የሚከለክል ሕግ የለም፡፡
በአንዳንድ አገሮች (ለምሳሌ አውስትራሊያ) የግብር ሕጋዊነት መርሕ የግብር ሕግጋት ግልጽነት ጋርም ይያያዛል፡፡ ‘ግልጽ ያልሆነ ሕግ አውጥቶ ግብር አይጠየቅም’ ማለት ነው፡፡
ከላይ የተነሳው ከግብር ከፋዩ አንፃርና የግብር ሕጋዊነት መርሕ በተጨማሪ ግብር ከፋዩ ያለቡትን ግዴታዎች በትክክል ካልተወጣ ግብር የመሰብሰብ ኃላፊነት የተጣለበት አካል ግብር ሰብሳቢው የግብር ሕጉ የሚጠይቀውን በሙሉ ማስፈጸም ይጠበቅበታል፡፡ በአገራችን ያለውን ላጤነ ሰው ግብር ከፋዩ ለግብር መሠረት የሆነውን ወይንም ግብር የሚከፈልበትን ነገር ይወቀውም አይወቀውም በትክክለኛው መጠን የመክፈል ፍላጎትና አዝማማያ ስለመኖሩ የሚያረጋግጡ ጥናቶች የሉም፡፡ ይልቁንስ የተቃራኒውን እውነት የሚደግፉ በርካታ ናቸው፡፡ ምክንያቶቹ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ከግብር ሰብሳቢው ጋር የሚያያዙም አሉ፡፡
ድክመት መላቀቅ የተሳነው የግብር አስተዳደር
የግብር ፍትሕን በተመለከተ ሁለተኛው ግብር ሰብሳቢው ወይንም መንግሥት ያሉበት ተነፃፃሪ ግዴታዎችን የሚመለከት ነው፡፡ መንግሥት ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን የግብር ክፍያ መክፈል የሚችልበት ምቹ ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ ክፍያው የግብር ሕጉ የሚጠይቀውን ለመወጣት አላስፈላጊ የሆኑ ተጨማሪ ወጪዎችን የማያስወጣ መሆን አለበት፡፡ በተቻለ መጠን ምን ያህል መክፈል እንደሚጠበቅባቸው በእርግጠኝነት ቀድመው የሚያውቁት መሆን አለበት፡፡ መንግሥት ግብር ለመሰወር ምቹ ሁኔታዎችን ማጥፋት አለበት፡፡ አንዱ በትክክል ሌላው ደግሞ እንዳሻው የሚከፍልበት ሁኔታ መሆን የለበትም፡፡
የግብር ሕግጋትና ሕጉን ተከትለው የሚዘጋጁ ሌሎች የሒሳብ መግለጫዎች፣ ማስታወቂዎች፣ ቅጾች የተቻለውን ያህል ግልጽና እጥር ምጥን ሊሉ ይገባቸዋል፡፡ ግልጽ ባለሆኑበት ጊዜ ደግሞ በቀላሉ ማብራሪያ የሚገኝበት ዘዴ መዘርጋት አለበት፡፡ በከፋዩና በአስከፋዩ መካከል አለመግባባት ሊፈጠር ስለሚችልም ቀልጣፋና ተደራሽ የግጭት መፍቻ ሊኖር ግድ ነው፡፡ የግብር አስተዳደሩም ከሙስና የፀዳ፣ በሕጉ መንፈስ የሚፈጸምበት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ የገቢ ምንጭ የሆኑ ሥራዎችን የሚያበረታታ እንጂ የማያጠፋ መሆንም አለበት፡፡ ተመሳሳይ ገቢ፣ ንብረትና ንግድን በተለያየ መጠን ከመቀረጥም መራቅ አለበት፡፡
እነዚህ ጥቅል የመንግሥት ኃላፊነቶች ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ ለግብር ፍትሕ ሲባል ከመንግሥት የሚጠበቁና መከናወን ያለባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች አኳያም ይሁን በሌላ መለኪያ፣ የአገሪቱ የግብር አስተዳደር ውጤታማ የሚባል አይደለም፡፡ ለደካማነቱ ደግሞ ብዙም ዋቢ መጥቀስ ሳያስፈልግ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩን የበጀት ንግግርና ሪፖርት ያደረጉትን መውሰዱ ብቻውን በቂ ነው፡፡ መጨመር ካስፈለገ ደግሞ ሰሞኑን የግብር ከፋዮች ሁኔታ መውሰድ ይቻላል፡፡ “ግብር ሰብሳቢ ልክ አበባ አንደምትቀስም ንብ ተክሉን ሳትጎዳ ለማር የሚሆናትን እንደምመጠው ሁሉ ግብሩ ከፋዩን ሳያመውና ሳይጎዳ መሰብስብ አለበት፤” ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡ የግብር ከፋዩ ቅሬታ ምናልባትም የግብሩ አገማመትና አሰባሰብ አሳምሞት እንዳይሆን ማጣራት ይገባል፡፡ ስለሆነም እጅግ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡
ከሚቀሩት ሥራዎቹ ውስጥ የሕጎቹን ራሳቸውን እንመልከታቸው፡፡ የጥሩ የግብር ሕግ ባሕርይ ውስብስብ አለመሆን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ቀላልና ማንኛውም ግብር ከፋይ የሚረዳው መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሕጎቹ ግልጽነት፣ ማንም ግብር ከፋይ የሚኖርበትን የግብር ዕዳ ቀድሞ ማወቅ እንዲችል እንዲሁም ግዴታውን በአግባቡ መወጣት ይረዳዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተመልሶ ለግብር ሰብሳቢው ውጤታማነት ያግዘዋል ማለት ነው፡፡
ውስብስቦቹ የግብር ሕግጋት
የግብር ሕጎቹ፣ ውስብስብ መሆናቸው የግብር አስተዳደሩን ውጤታማ እንዳይሆን እንደሚደርገው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የውስብስብነቱ መነሻም ሆነ መገለጫዎች ብዙ ናቸው፡፡
በመጀመርያ ከሕጉ አረቃቀምና አቀራረጽ ጋር ይያያዛል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ነው፡፡ የአዋጁ አንቀጽ አራትን አቀራረጽ እንመለክት፡፡ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 1 ፊደል ሀ ቁጥር 1 በሚል አኳኋን ተቀርጿል፡፡ ይኼ ዓይነት የሕግ አቀራረጽ መርሑን ከልዩ ሁኔታው ለይቶ ለማወቅ አይደለም ለግብር ከፋይ ለሕግ ባለሙያም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አንቀጾችን መቀነስና ማስተካከል አንዱ ነው፡፡
ሌላው የግብር ሕጎቹን ውስብስብ የሚያደርጋቸው የማሻሻያዎቹ መብዛት ነው፡፡ ይኼንን ለመቀነስና በሌሎችም ምክንያት የገቢ ግብር አዋጁ ተሻሽሏል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁም ቢሆን የተሻሻለውን ካልተሻሻለው መለየት እንዲሁ አስቸጋሪ ነው፡፡
ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ደግሞ የግብር ኮድ (መጽሐፍ) አለመኖር ነው፡፡ የግብር ሕጎቹ በተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች ወጥተዋል፡፡ የግብር ዓይነቶቹ እየበዙ በሔዱ ቁጥር ሕጎቹም ይበዛሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሌላ አገር እንደተለመደው ሁሉንም የግብር ሕግጋት በአንድ አጠቃልሎ፣ የሚሻሻሉትንም ጭምር ማሳተም ይገባል፡፡ ቢያንስ ኅተመቱን በኤሌክትሮኒክ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ የተሻረውን ካልተሻረው፣ የተሻሻለውን ካልተሻሻለው ለመለየት ይረዳል፡፡ የአሜሪካ የግብር ሕግ መጽሐፍ (ኮድ) ከሰባ ሺሕ በላይ ገጽ እንዳለው ልብ ይሏል፡፡ ይህ በአንድ በመጠቃለላቸው ነው፡፡
የግብርን ጉዳይ ከሚያወሳስቡት ሁኔታዎች አንዱ የመመርያዎች አለመታተም ነው፡፡ አለመታተም ብቻ ሳይሆን በድረ ገጹ ላይ እንኳን የማይቀመጡት ብዙ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የተጨማሪ እሴት ታክስ የተነሳላቸው ግብይቶች ወይንም አገልግሎቶች በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በደብዳቤ ከመገለጽ በዘለለ ይፋ አልተደረጉም፡፡
በጣም ቴክኒካልና ከሌሎች ሕጎች ጋር የተለዩ ቃላትን ወይንም ጽንሰ ሐሳብ መጠቀምንም ሌላው ሳንካ ነው፡፡ በግብር ሕጎቹና በንግድ ሕጎቹ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ማንሳት ይቻላል፡፡
የግብር ሕጎቹ ሲወጡ የሚዘጋጁት የግብር ማብራያዎችን ለሕዝብ እንዲደርሱ አለማድረግም ነገሩን ያባብሰዋል፡፡ ሕግ ሲወጣ አርቃቂው አካል ከረቂቁ ጋር አብሮ ማብራሪያ የማዘጋጀት ግዴታ አለበት፡፡ እነዚህ ማብራሪያዎች ምናልባት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቤተ መጽሐፍ ውስጥ ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ በምክር ቤቱም ይሁን በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ድረ ገጽ ላይ እንኳን አይቀመጡም፡፡ የፈለገ ሰው ሊያገኛቸውና የሕጎቹን መንፈስ ለማግኘት ይረዳው ነበር፡፡
ለነገሩ ውስብስብ ያልሆኑትን የግብር ሕጎች እንኳንስ ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ይቅርና የገቢዎችና ጉምሩክ ሠራተኞቹም ይሁኑ የሕግና የ’አካውንቲንግ’ ባለሙያዎችም ዘንድ በአግባቡ አይታወቁም፡፡ ለእዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡
የግብር ሕጎች በትምህርት ሥርዓቱ የተሰጣቸው ቦታ ዝቅተኛ ነው፡፡ የአካውንቲንግ ተማሪዎች በዲግሪ ደረጃ ሲማሩ የታክስ አካውንቲንግ አንድ ትምህርት ብቻ ይማራሉ፡፡ በሕግ ትምህርት ቤትም ቢሆን አንድ ትምህርት ብቻ ሆኖ ነው የሚሰጠው፡፡ ቀደም ሲል ሁለት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን አንድ ነው፡፡ ለዚሁም በየዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው የገቢ ግብር ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመጠኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉትን የግብር ሕጎች ማስተማር አልተለመደም፤ ለነገሩ በቂ ጊዜም የለም፡፡ ስለሆነም በሕግ ትምህርት ቤት የተዘነጉ ወይንም የተካዱ ሕጎች ናቸው፡፡
በዩኒቨርሲቲ ትኩረት መነፈጋቸው በጥናትና ምርምርም ትኩረት እንዳይደረግባቸው ያደርጋል፡፡ እንደ ሕጎቹ መብዛትና መቀያየር፣ በዘርፉ ላይ ነጥረው የወጡ የሚታወቁ ምሑራን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም ይሁን የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የጥናትና ምርምር እንዲሁም የሥልጠና ክፍሎቻቸው የግብር ሕጎቹን ሕዝባዊ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ማብራሪያዎችን በማዘጋጀትና በድረ ገጻቸው ለሚፈልግ ከማስቀመጥ አኳያ ክልሎች የሚሻሉ ይመስላል፡፡ ይኼንን ችግር በመረዳት፣ በተወሰኑ አገሮች ግብርን ግልጽ ለማድረግ ሲባል ብቻ የተቋቋሙ ቢሮዎች አሉ፡፡
የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ከሰላሳ አምስት በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ያላት አገር፣ ይባስ ብሎም ግብርና ኢንቨስትመንትን በሁለተኛ ድግሪ የሚያስተምሩ ባሉበት ሁኔታ አሁን የግብር አስተዳደሩን እንዲሻሻል ማገዝ የሚችል ባለሙያ ባለማፍራታቸው ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የውጭ አማካሪ ሊቀጠር ነው፡፡
ማጠቃለያ
በአንድ የግብር አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ሁለት ተዋናዩች /ግብር ከፋይና ግብር አስከፋይ/ እንደመኖራቸው መጠን ስለግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ከመወሳቱ በፊት አንዱ ስለሌላው ያሉበትን መብትና ያሉባቸውን ግዴታዎች ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ ቀልጣፋና ፍትሐዊ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት እንዲኖር ከተፈለገ የግብር አስተዳደሩ የመጀመርያ ተግባር ሊሆን የሚገባው እያንዳንዱን ግብር ከፋይ በሚገባ ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቀደም ሲል የነበረው የግብር አስተዳደር ሥርዓት ይህን ተግባር ለማከናወን የሚያስችል ዘመናዊ አደረጃጀት ስሌለው ግብር ከፋዩ በውል ተለይቶ መያዝ አልቻለም፡፡ ክትትልም እያደረገ አይደለም፡፡
ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የሚሰበሰበው ግብር አናሳ መሆን፣ ግብር ወቅቱን ጠብቆ ያለመሰብሰብ፣ የአወሳሰኑ ፍትሐዊ አለመሆን አሁንም ተግዳሮት መሆናቸው እንደቀጠለ ነው፡፡
ለእነዚህ ችግሮች መንስዔዎች ደግሞ ከግብር ሕጎች ጋር በተያያዘ ግልጽ አለመሆን፣ የተበታተኑ መሆንንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሰብሳቢው ደግሞ፣ የማስፈጸም አቅሙ ደካማ መሆን፣ ግብር ከፋዩችን በሚገባ ለይቶ አለማወቅ ብሎም በዚህ ዓመት እንደሆነው ዘግይቶ በርካታ ከፋዮችን መለየት፣ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ተከታትሎ ማስገበር አለመቻል፣ ከአንዳንድ ሠራተኞች ጋር በተያያዘ የሥነ ምግባር ብቃት ማነስ፣ ዘመናዊ አሠራርን አለመከተል አሁንም ያልተሻገራቸው እንከኖች ናቸው፡፡ ከግብር ከፋዩ በኩልም አንዳንድ ግብር ከፋዩች ግብርን ጭራሽ ላለመክፈል ወይም አሳንሶ ለመክፈል ከመፈለግ የተነሳ፣ ገቢን በትክክልና በጊዜው አለማስታወቅ፣ ተገቢ የሒሳብ መዝገብን ለግብር አወሳሰን አለማቅረብ፣ የግብር ክፍያን አዘግይቶ ለመክፈል መሞከር፣ አልፎ አልፎም መከሰስን የሚመርጡ እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ በላይ የተመለከቱት የግብር ፖሊሲና የግብር አስተዳደር ድክመቶች ከመሠረታቸው መፈታት ያለባቸው ችግሮች ሲሆኑ፣ መንግሥትም ሁልጊዜ በዘመቻ መልክ መሥራቱን በማቆም፣ ወጥና ተቋማዊ መሠረት መዘርጋት መቻል አለበት፡፡ እነዚህ የግብር አስተዳደር ድክመቶች መቅረፍ ወይንም መቀነስ እስካልተቻለ ድረስ መልሰው ዙረው የግብር ፍትሕን ማዛባታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
አዘጋጁ፡– ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡