Monday, February 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አዲሱ ገበያ አካባቢ የሚኖር ጓደኛዬ የነገረኝ አስገራሚ ነገር ለሳምንቱ ገጠመኝ ዓምድ ጽሑፌ መነሻ ይሆን ዘንድ አቅርቤዋለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ሠፈራቸው ውስጥ የተተከለ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ሥር አንድ መኪና ቆሟል፡፡ ከመኪናው ውስጥ ሁለት ሰዎች ይወርዱና ከትራንስፎርመሩ ላይ የሆነ ነገር ፈትተው ሲወስዱ፣ የአካባቢው ሰዎች ተረባርበው ይይዟቸዋል፡፡ ሰዎቹን በቦክስና በእርግጫ እያዋከቡ በአካባቢው ለነበሩ ፖሊሶች ያስረክቡዋቸዋል፡፡

ፖሊሶቹ ሰዎቹን በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ የቆመው መኪና መስተዋቶች መሰባበራቸውን ያያሉ፡፡ መኪናው የመንግሥት ንብረት በመሆኑ፣ የመንግሥት መኪና ይዘው መጥተው ዘረፋ ያካሂዱ ከነበሩ ሰዎች ጋር ግብግብ የገጠሙ ሰዎችንም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዳሉ፡፡ ሕገወጦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ተገቢነት ቢኖረውም፣ የመንግሥት ንብረት ማውደም ግን ሕገወጥነት ነው በማለት ነው ሰዎቹን ከዘራፊዎቹ ጋር ቀላቅለው የወሰዷቸው፡፡

ጓደኛዬ እንደነገረኝ በበርካታ ቦታዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት ተሽከርካሪዎችን የያዙ አንዳንድ ግለሰቦች ከትራንስፎርመሮች ላይ ፊዩዞችን እየፈቱ ወደ ሌላ ቦታ ይወስዳሉ፡፡ እነኚህ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ግለሰቦች አንዱን አካባቢ በጨለማ እንዲዋጥ እያደረጉ ጉቦ የሚቀበሉበትን ሥፍራ በተሰረቁ ፊዩዞች ብርሃን እንዲያገኝ ያደርጋሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ በአምስትና በአሥር ሜትር ልዩነት ውስጥ ጉቦ የሚከፍሉ የኤሌክትሪክ ብርሃን ሲያገኙ፣ አቅም የሌላቸው ጨለማ ይውጣቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ አዲሱ ገበያ አካባቢ የተፈጠረው ችግርም በዚህ ዓይነቱ ሕገወጥ ተግባር ምክንያት ነው፡፡

እኔና የአካባቢያችን ነዋሪዎች ኤሌክትሪክ በየቀኑ ይጠፋብናል፡፡ መሀል ከተማ ውስጥ ይኼንን በየቀኑ ኤሌክትሪክ ጠፋ ሲባል ላይታመን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቀበና አካባቢ የሚመጣ ማንም ሰው ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ በሠፈራችን ታዋቂ የሆኑት እናት በ80 ዓመታቸው፣ ‹‹ተመስገን ቴክኖሎጂ ተራቀቀ በተባለበት ዘመን ጨለማ ይጨፍርብናል፤›› በማለት ለወረዳ ኃላፊዎች አቤት ቢሉም ማንም አልሰማቸውም፡፡ ‹‹በዚህ ክረምት ጨለማ ተጨምሮበት ኑሮ እንዴት ይገፋል?›› እያሉ ያጉረመርማሉ፡፡

በዚያን ሰሞን መኖሪያ ግቢያችን ውስጥ ተከራይ የሆነች አንዲት ሴት አራስ ልጇ ታሞባት ነበር፡፡ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ኃይለኛ ዶፍ እየወረደ ሳለ ከእመጫቱዋ ቤት ኃይለኛ እሪታ እንሰማለን፡፡ ጎረቤቶች ደንግጠን ስንነሳ እናት እሪ ትላለች፣ የአራት ወር ሕፃን ያለማቋረጥ ይጮሃል፡፡ እኔና ባለቤቴ በዶፉ ውስጥ በጨለማ እየተደናበርን ደርሰን በር አስከፈትናት፡፡ ሕፃኑ ልጅ ትኩሳቱ ያስደነግጣል፡፡ ሠፈራችን ውስጥ የማውቀውን ባለላዳ ታክሲ ለመጥራት ስልኬን ሳወጣ ‹‹No Service›› ይላል፡፡ የእኔም፣ የባለቤቴም፣ የአራሷም ስልክ ማንንም ሊያገናኘን አልቻለም፡፡

በዚያ በዶፍ ጭልጭል የሚል ባትሪ ይዘን እየተመራራን ሆስፒታል በመከራ ደርሰን የሕፃኑን ሕይወት አተረፍን፡፡ ባለቤቴ ግን ከዚያን ቀን ጀምሮ ውጋት ይዟት እየተሰቃየች ነው፡፡ እንዲህ ባለው ጊዜ በኃላፊነት የሚጠየቀው ማን ነው? ወቅቱ ክረምት፣ በዚህ ላይ ኤሌክትሪክ የለም፡፡ በዚህ ላይ የሞባይል ኔትወርክ አይሠራም፡፡ ፈጣሪ ከሰማይ ዝናብ እየለቀቀልን የቧንቧ ውኃ ይጠፋል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ አይታወቅም፡፡ ምላሽ አለን የሚሉት ያልተጠናቀቀውን ተጠናቀቀ እያሉ ያደነቁሩናል፡፡ እኔ ግን በአንድ ምሽት ምክንያት ሁሉንም ታዝቤ በቃኝ ብያለሁ፡፡

አዛውንቷ እናት በዚያ ውድቅት የደረሰብንን ፈተና ሰምተው ሊጠይቁን ይመጣሉ፡፡ የደረሰብንን ነገር ሁሉ ዘርዝሬ ሳስረዳቸው፣ ‹‹ምን ይደረግ? በሬዲዮና በቴሌቪዥን የምንሰማውንና በዓይናችን የምናየውን ረጋ ብለን ማመዛዘን አለብን፡፡ በቀደም ዕለት የገበያ ዋጋ በሬዲዮ ሰምቼ ሾላ ነጭ ሽንኩርት ልገዛ ሄድኩ፡፡ የተነገረው ዋጋ ጥሩ ስለነበር ቶሎ ብዬ ለመሸመት ነበር ሐሳቤ፡፡ እዚያ ስደርስ ግን እንኳን ነጭ ሽንኩርት የብዙ ነገሮች ዋጋ ተሰቅሎ ጠበቀኝ…›› እያሉ መተከዝ ያዙ፡፡ ‹‹አያችሁ ይኼንን ያህል ጊዜ መብራት ጠፍቶብን አቤት ስንል የሚሰማን የለም፡፡ የውሸት የገበያ መረጃ ተነግሮን ስንሄድ የሚነገረን ዋጋ ይገርማል፡፡ ሌላው ቀርቶ ውኃ በክረምት እንዴት ይጠፋል ብዬ ስጠይቅ ገንዳ እየታጠበ ነው ብለው ያሾፋሉ፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ያለው ሬዲዮና ቲቪ ውስጥ ነው እንዴ?›› ብለው ፈገግ አሰኙን፡፡

ይኼንና የመሳሰሉትን ችግሮች እያወራን ቡናችንን ስንጠጣ ከወዲያ ሠፈር በኩል የፍንዳታ ድምፅ ተሰማ፡፡ አንዳንዶች የከባድ መኪና ሳይሆን አይቀርም ስንል፣ ሌሎች ኧረ የመሣሪያ ድምፅ ይሆናል አሉ፡፡ እማማ ግን ከት ብለው ሳቁ፡፡ አሳሳቃቸው አስገርሞን ስናያቸው፣ ‹‹አይ እናንተ የዋሆች፣ እውነት ይኼ ድምፅ ጠፍቷችሁ ነው?›› አሉን፡፡ ሁላችንም ምን ሊሉ ነው በማለት ጠበቅናቸው፡፡ ‹‹ይኼውላችሁ የተሰማው ድምፅ የሙስና ፈንዲሻ ነው፤›› ብለው ሲስቁ፣ ‹‹ማለት?›› በማለት አንድ ላይ ጠየቅናቸው፡፡ ‹‹የሙስና ፈንዲሻ እኮ ይኼ ትራንስፎርመር የምትሉት በየቦታው የሚንጣጣው ጉድ ነው…›› እያሉ ሲስቁ እኛም አጀብናቸው፡፡ አይ እማማ? ዕድሜ ይስጥዎት! ከማንም ዘላባጅ ወሬ የእርስዎ ምልከታ ከበቂ በላይ ነው፡፡

ሰሞኑን በሙስና ምክንያት ሰዎች ታሰሩ ሲባል እንሰማለን፡፡ የሆነስ ሆነና የእስር ዘመቻው ዋናዎቹን ያካትታል? ወይስ አሁንም እታች ያሉትን ብቻ ነው የሚያግበሰብሰው? እነ ደረጃ ‹‹ሐ›› የሚባሉትን ማለቴ ነው?

(መክብብ ደበበ፣ ከቀበና)      

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...