Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክበወጉ ያልተቆረጠው የቁርጥ ግብር

በወጉ ያልተቆረጠው የቁርጥ ግብር

ቀን:

በውብሸት ሙላት  

ቁርጥ ግብር፣ ለማስገበር አስቸጋሪ የሆኑ ገቢ ላይ ይተገበራል፡፡ በቁርጥ የሚጣል ግብር መጠን በተጠና ግምት ይሰላል፡፡ ግብር ተማኙና ሰብሳቢው ባለሥልጣን ትክክል ነው ብሎ የሚያስበውን ግብር በግምትም ቢሆን ለማወቅ የተለያዩ መረጃዎች ላይ ይመሠረታል፡፡ ይሁን እንጂ ቁርጥ ግብር ሲጣል በባሕርይው ቅሬታ ማስከተሉ እንደማይቀር የታወቀ ነው፡፡ በአገራችንም የግብር ግምት ማስታወቂያ ለከፋዮች ሲሰጥ ብዙ ጊዜ ቅሬታ ማቅረቢያ ቅጽ አብሮ ይሰጣል፡፡ 

ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ይፋ ያደረገውን የግብር ግመታን ተከትሎ የመጣው ቅሬታ አሁን ላይ ሕዝባዊ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ይባስ ብሎም፣ በአንዳንድ ቦታዎች ለግጭትና ለሥራ ማቆምም መነሻ ሆኗል፡፡ በግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን ዘንድ የተለመደው የግብር ግምት ማሳወቂያው ወር ሰኔ ነው፡፡ ከዚያ ከሐምሌ አንድ እስከ ጥቅምት ሠላሳ ደግሞ የግብር መሰብሰቢያ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ወቅት ለግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ‘መኸሩ’ ሲሆን፣ በአንፃሩ ለከፋዩ ‘ክረምቱ’ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የገመተውን፣ ያሰላውን፣ በሰነድ እንዲያዝ ያደረገውን ግብሩን የሚሰበስብበት ‘መኸር’ ወቅቱ ነው፡፡ ለከፋዩ ደግሞ ምንም ይሁን ምን ከገቢው ቀንሶ የሚከፍልበት ጊዜ ስለሆነ ‘ክረምቱ’ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ግብር ለሥልጣኔ የሚከፈል ዋጋ›› ስለሆነ ሊከፈል ግድ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት የሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ የፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከነበሩበት የዕረፍት ጊዜያቸው ላይ ተጠርተው አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ካፀደቋቸው ሕግጋት ውስጥ ‹‹የገቢ ግብር›› እና ‹‹የታክስ አስተዳደር›› አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ አዋጆች ከወጡበት ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምረው ሥራ ላይ መዋል እንዳባቸው በአዋጆቹ ላይ ተገልጿል፡፡

አዋጆቹን ለማስፈጸም እንዲረዳም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ማውጣት እንዳለበት በሕጎቹ ግዴታ ተጥሏል፡፡ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ደግሞ መመርያዎችን በተዋረድ ማውጣት እንደሚጠበቅበትም እንዲሁ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ደንቡ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አርቅቆት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀው 2009 ዓ.ም. ከሰኔ አጋማሽ በኋላ ነው፡፡ ይህ ደንብ ተፈጻሚ የሚሆነው ግን አሁንም ወደ ኋላ ተመልሶ ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆች ላይ እንደተገለጸው ለእነዚህ ሕጎች በትክክል መፈጸም በዋናነት መመርያዎችን የማውጣት ሥልጣኑን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በሕጎቹ መሠረት ማስተዳደሩን ደግሞ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተሰጥቷል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም አዲሶቹን አዋጆቹንና ደንቡን ሥራ ላይ በሚያውልበት ጊዜ ግብር ከፋዩን ቀድሞ ከለመደው አሠራር ለየት ያሉ ሁኔታዎች አጋጥመውታል፡፡ ስለሆነም ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በርካታ ግብር ከፋዮችም ወይም ደግሞ ቀድሞ ግብር ለማይከፍሉ ዜጎች የግብር ‹‹መርዶ›› በመሰማታቸው ቅሬታዎች ተፈጥረዋል፡፡

ይህ ጽሑፍ የሚዳስሰውም የፌዴራሉ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አዲሶቹን አዋጆች መሠረት በማድረግ የፈጸማቸውን ተግባራት የተወሰኑ ጥያቄዎችን ማንሳት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም የቁርጥ ግብር ምንነትን፣ የአገማመት ስልቶችን፣ በቁርጥ ግብር የሚከፍሉትን እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመጠቆም ለመፍትሔነት የሚሆኑ መንገዶችን እግረ መንገዱን ያመለክታል፡፡ በተለይ ደግሞ የሕጎቹ ወደ ኋላ ተመልሰው ተፈጻሚ መሆናቸው ላይ ጥያቄ ያነሳል፡፡

የባለሥልጣኑ ግምትና ውጤታቸው

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም. የነጋዴዎችን የዕለታዊ ገቢ ትመና አከናውኖ ለከፋዮች አሳውቋል። እንዲህ ዓይነት የገቢ ትመና በ2003 ዓ.ም. ከተደረገ በኋላ ላለፉት ስድስት ዓመታት እንዳልተከናወኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የአሁኑ ትመና ዓላማ የሚመስለው ግብር ከፋዩ ነጋዴ በሚያገኘው ገቢ ልክ የገቢ ግብር መክፈል የሚችልበትን መረጃ ለመሰብሰብ ይመስላል። በተጨማሪነትም፣ በግብር መረብ ውስጥ ያልተካተቱን ነጋዴዎችን በመለየት በግብር ከፋይ ማድረግ ነው፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያካሄደውን ዕለታዊ የገቢ ትመና ሥራ አጠናቆ ይፋ ሲያደርግ የግብር ከፋይ ደረጃው የሚመደበው በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ መሠረት እንደሚሆን ግልጽ ነው። ቀድሞ ከነበረው አዋጅ በተለየ ሁኔታ፣ ዓመታዊ አጠቃላይ የሽያጭ ወይም የአገልግሎት ገቢያቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑት ደረጃ ‘ሀ’ ግብር ከፋይ፣ ከአምስት መቶ ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢያላቸው ደረጃ ‘ለ’፣ እንዲሁም አምስት መቶ ሺሕና ከዚያ በታች ገቢ ያላቸው ደረጃ ‘ሐ’ ይሆናሉ፡፡ የግምት ሥራ ከተከናወነ ስድስት ዓመታት በማለፉ፣ የመገመቻ ዘዴውም ስለተቀየረ፣ የደረጃዎቹ መነሻም ስለተለወጠ የደረጃ ለውጥ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ይኖራሉ፡፡ የደረጃ ለውጥ ማድረግ በራሱ የሚያስከትላቸው ተጨማሪ ግዴታዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ግብር ሥርዓቱ እንደአዲስ የገቡት በመቶ ሺሕ ይቆጠራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በአማራ ክልል 50490፣ በኦሮሚያ ደግሞ ከ43 ሺሕ ያላነሱ ወደ ግብር መረብ እንዲገቡ መደረጉ ተዘግቧል፡፡ በአጭሩ ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ያከናወነውን ግምታ ይፋ ሲያደረግ መጠኑ ላይ ከሚመጣው ቅሬታ ባሻገር የግብር ከፋዮች ደረጃ ላይና የማይከፍሉትን ወደ ግብር መረብ የማምጣት ውጤት ይኖረዋል፡፡

የቁርጥ ግብር ምንነቱ ምክንያቱ

ቁርጥ ግብር አንድ የተለየ የግብር ዓይነት ሳይሆን ግብር ከፋዩ ምን ያህል ግብር መክፈል እንዳለበት የመተመኛ ዘዴ ነው፡፡ የአንድን ግብር ከፋይ የግብር ዕዳ በትክክል ለማወቅ ወይም ለመወሰን በመጀመሪያ ደረጃ የግብር ከፋዩ አጠቃላይ መረጃዎች ሊታወቁ ይገባል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ውስጥ የግብር ከፋዩ ስምና አድራሻ፣ የንግድ ዘርፉ፣ ዓመታዊ ገቢው፣ የንግድ ትርፍ ምጣኔው የመሳሰሉትን ግብር ከመወሰኑ በፊት ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡

ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ የግብር ከፋዩን መረጃ ከአሰባሰበ በኋላ ግብሩን በገቢ ግብር አዋጅ መሠረት በተሰጠው ሥልጣን ከግብር ከፋዩ የሚፈለግበትን ግብር ለመሰብሰብ ከሦስት አንድኛውን አማራጭ መንገድ ሊከተል ይችላል፡፡

የመጀመሪያው በሒሳብ መዝገብ ግብርን መወሰን ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ተገቢ የሒሳብ መዝገብ በመያዝ ገቢና ወጪ ያለው ትርፍና ኪሳራ የሚያሳይ የሒሳብ ሪፖርት በሒሳብ ጊዜ ውስጥ ለገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ ያሳውቃል፡፡ እንደ መርሕ፣ የሒሳብ መዝገብ ቀልጣፋ አሠራርን የሚያሰፍን ወጪ ቆጣቢና በተገኘ ገቢ ላይ ግብርን ለመሰብሰብ የሚያስችል ስልት ነው፡፡ 

የገቢ ግብር አዋጁ ላይ እንደተገለጸው ከደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች በስተቀር በማናቸውም የንግድ ሥራ የተሰማሩ፣ በሙሉ ወይም በከፊል የሚከራዩ ሕንፃዎች ባለቤት የሆኑ የሒሳብ መዝገብና ሰነዶችን የመያዝ ግዴታ አለባቸው፡፡ በዚህም መሠረት የቀረቡት መዝገቦች ከሒሳብ አያያዝ መርሖችና ከግብር ሕጐች አንፃር ተመዝነው ተቀባይነት የሚያገኙ ከሆነ ግብሩ በዚሁ መዝገብ መሠረት ይወሰናል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ፣ በመረጃ ግብር የመወሰን ዘዴ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ግብርን መተመን በእርግጥ አድካሚ ከመሆኑ ባሻገር መረጃ ለመሰብሰብም አስቸጋሪ በተጨማሪም ጊዜና ወጪ ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከግብር አወሳሰን አንፃር ሲታይ ግን በጣም ውጤታማና ፍትሐዊ የሆነ ግብርን ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥልት ነው፡፡

ከላይ በተገለጹት መንገዶች ግብርን መተመንና መሰብሰብ ሳይቻል ሲቀር በግምት ግብር መወሰን ይመጣል ማለት ነው፡፡ በግምት ግብር መወሰን  የመጨረሻው አማራጭና ሌሎች አማራጮች ሲጠፋ ሥራ ላይ የሚውል ዘዴ ነው፡፡

በግምት ተመሥርቶ ግብርን ከመወሰን አስቀድሞ የግብር ማሰረጃዎችን ወይም ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚገባ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 88446 ግንቦት 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በውሳኔው ላይ እንደተገለጸው የአመልካቹ ድርጅት ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረቱና የሒሳብ ሰነዶቹ መውደማቸውን ከተረጋገጠ፣ አመልካቹ የሒሳብ መዝገብና ተያያዥነት ያላቸውን የሒሳብ ሰነዶቹ እንዲያቀርብ ታዞ አላቀረበም በሚል ምክንያት ግብሩን በግምት ከመወሰኑ አስቀድሞ ከተቃጠሉት ሰነዶች ሌላ ግብር እንዲከፈል በተጠየቀው ዘመን አመልካች የያዘው የሒሳብ መዝገብና የሒሳብ ሰነዶች መቃጠላቸውን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን አመልካች ካሉት ተቀብሎ በመመርመር እንዲሁም ተጠሪውም ከራሱ በኩል በሚኖረው የማጣሪያ መንገድ በማጣራት ማስረጃዎቹን መዝኖ ግብሩ በግምት ሊወሰን የሚገባ መሆን አለመሆኑን በመለየት የአመልካችን ክርክር የማይቀበልበት በቂ ምክንያት ካለው ግብሩን በግምት መወሰን ሲገባው ግብሩን በግምት መወሰኑ ተገቢነት እንደሌለው ውሳኔው ያስረዳል፡፡

በግምት መወሰን ሲባል በዘፈቀደና ግብር ሰብሳቢው እንደው በነሲብ የመሰለውን ግብር የሚጥልበት ሥርዓት ነው ማለት ግን ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፡፡ በግምት ግብር የሚወሰነው በመደበኛ ቁርጥ ግብር፣ በጥናት መረጃ መሠረት የቀን ገቢ ወይም ዓመታዊ ሽያጭ ወይም አገልግሎት አቅርቦት ተገምቶ ግብሩ ሊሆን ይችላል፡፡

በግምት ግብር ከሚወሰንባቸው ዘዴዎች አንደኛው ቁርጥ ግብር (Presumptive Tax) ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የግብር አወሳሰን ከተወሰነ መጠን በታች ዓመታዊ ገቢ ያላቸው ነጋዴዎች፣ የተወሰነ ዘርፍን ሊያካትት ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት የሒሳብ ሰነድ የሚይዙ ነጋዴዎች ሆነው አመኔታ ባጣባቸው ጊዜ ሊተገብረው ይችላል፡፡ ትኩረቱ ግን አነስተኛ ግብር ከፋዮችና ከንግዳቸው ገቢ ለኑሯቸው የሚጠቀሙት ላይ ነው፡፡ የንግዱ ገቢ ተለይቶ በሒሳብ ሰነድ ሳይያዝ በየዕለቱ ሲጠቀሙበት ለማለት ነው፡፡

በመሆኑም በቁርጥ ግብር የሚከፍሉት ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ በአንፃሩ ገቢያቸውም አነስተኛ ነው፡፡ የሒሳብ ሰነድም አይዙም፡፡ በአነስተኛ መጠንና ዋጋ ስለሚሸጡም ከንግድ አዋጭነትም ሲታይ የሒሳብ ሰነድ እንዲይዙ ማድረግ አዳጋች ይሆናል፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ሁኔታ ገቢውን ለመደበቅና ለመሰወር ይመቻል፡፡ በጣም የታወቁት የቁርጥ ግብር የሚጣለው ግብርና ላይ ነው፡፡ አርሶ አደሮችን አርብቶ አደሮችን በዓመት በቁርጥ ግብር ማስከፈል በብዙ አገሮች የተለመደ ነው፡፡

አገሮች ወደ ቁርጥ ግብር የሚያዘነብሉበት በርካታ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ቀላልነቱ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የቁርጥ ግብር ከፋዮች አነስተኛ ዓመታዊ ሽያጭ ስላላቸው እነዚህ ከፋዮች ላይ ስለሆነ ብዙ የተወሳሰቡ ሒሳብ ሰነዶች የሚያስፈልጉት በመሆኑ ነው፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ የግብር ስወራንና ማጭበርበርን ለመቀነስ ስለሚረዳ ነው፡፡ ግብር እንዲከፍሉ የሚጠበቁት ሰዎች ቢሰውሩም፣ ቢያሸሹም ቢያጭበረብሩም ዞሮ ዞሮ በግምት ተቆርጦ ስለሚጣልባቸው ለእንዚህ አድራጎት የሚያሰጉ አይሆኑም፡፡ ሰነድ መያዝ ሳያስፈልግ ስለሚወሰን ማለት ነው፡፡

ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ መንግሥት ከዜጎች የሚፈልገውን ግብር በፍትሐዊነት ለማከፋፈል ይረዳዋል፡፡ በመሆኑም የግብር ፍትሐዊነትን  ለማስፈን ያግዛል፡፡ በተለይ ደግሞ የገቢ ወይም የግብር መገመቻዎቹ የታወቁ መሥፈርቶች ከሆኑ  ዕዳውን ለማከፋፈል ያግዛል፡፡

በአራተኝነት ሊወሰድ የሚችለው የሒሳብ ሰነዶችን ለመያዝ ማትጊያ መሆኑ ነው፡፡ ቁርጥ ግብር በባሕርይው የሚስተባበል ነው፡፡ ለማስተባበል ግን አስቀድሞ በታወቀና በተፈቀደ ሁኔታ የሒሳብ መዝገብ መያዝን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም፣ በዛብኝ የሚል ቅሬታ ካላ በሰነድ ማስተባበል ስለሚቻል ግብር ከፋዮች ወደ መደበኛ የግብር አከፋፈል ሥርዓት እንዲገቡ ያበረታታል፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ ንግድን በማበረታታትም ይታወቃል፡፡ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ የሚጣለው ግብር ዘርፉን መሠረት አድርጎ እንጂ ነጋዴዎች ወይም ባለሙያዎች የእውነት ባገኙት ገቢ ላይ አይደለም፡፡ ስለሆነም ጠንክረው እንዲሠሩና ገቢያቸውን እንዲጨምሩ ይረዳል፡፡

በመጨረሻም መንግሥት በራሱ ለተለያዩ ግቦች በቀላሉ እንዲጠቀምበት ዕድሉን ያመቻቻል፡፡ ግምቱን በመጨመር የገቢ ፍላጎቱን ያሳካበታል፡፡ ፍትሐዊነትን ለማስፈን ሲፈልግም ቀላል ነው፡፡ ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲያጋጥሙትም ግምቱን በመቀነስና ሌሎች ታክቲኮችንም በመጠቀም ትርፍ ይገኝበታል፡፡ በቂና ጥራት ያለው ባለሙያ የሌለው መንግሥትም ይህንኑ የግብር አስተዳደር ዘዴ ይጠቀማል፡፡

የቁርጥ ግብር ሕጎቹ የጋራ ባሕርያት

የቁርጥ ግብር ሕጎች የሚያመሳስላቸው ጠባያት አሉት፡፡ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ተስተባባይነታቸው ነው፡፡ ግምትን መሠረት አድርጎ የሚሠላ የግብር ስሌት ለቅሬታ የተጋለጠ ነው፡፡ ስለሆነም የተለየ ማስረጃ አለኝ የሚል ሰው ማስተባበል የሚችልበትን ሁኔታ ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ የሚስተባበል ስለመሆኑ በግልጽ ባይደነገግም መስተባበሉ ግን የተለመደ ነው፡፡

የማይስተባበል ሲሆን ግን መገለጽ ያስፈልገዋል፡፡ የአስገዳጅነት ባሕርይ ያላቸው ሕጎች አስገዳጅነታቸው ቀድሞና በግልጽ መታወቅ አለባቸው፡፡ ስለሆነም የቁርጥ ግብር ተስተባባይነቱ ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው፡፡ ይሁን እንጂ በብዙ መልኩ ዘፈቀዳዊነት ያጠቃዋል፡፡ ሰብሳቢው ባለሥልጣን ከከፋዩ በቂ መረጃ ባላገኘ ጊዜ የራሱን መረጃና መሥፈርት ይወስዳል፡፡ ግብር ከፋዩ የተሻለ መረጃ ካለው እንዲያቀርብ ሊፈቀድለት ይገባል፡፡ ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ ትክክለኛ ማስረጃ ቢኖረው ኖሮ መሰብሰብ ይችል የነበረውን ግብር የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይገምታል፡፡

ከዚህ አንፃር ሥራ ላይ የዋለው አዋጆችና እሱን ተከትሎ የወጣው ደንብ እጅግ የዘገየ ስለሆነ ለግብር ከፋዮች ሰነድ እንዲይዙም ወይም የፈለጉትን እንዲመርጡ ዕድል አልሰጠም፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ የገመተውን በሒሳብ ሰነድ ለማስተባበል የሚኖረው ዕድል ጠባብ ነው፡፡

የማይስተባበል በሚሆንበት ጊዜ ግን አንድም ለዘርፉ የሚጣለውን መክፈል ግድ ነው፡፡ ካልሆነም ዝቅተኛውን መጠን መንግሥት ያስቀምጣል፡፡ በተተመነ ዝቅተኛ መጠን ላይ አለበለዚያም ልክ እንደ እርሻ ግብርና መሰሎቹ ላይ በጥቅል ይጣላል፡፡

ቁርጥ ግብር ሲጣል የሚገምተው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከማስፈጸም የዘለለ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ውሳኔ እንዳይወስኑ ሊደረግ ይችላል፡፡ የማስፈጸም ኃላፊነት ብቻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ግን ቢያንስ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች የሽያጭ መጠናቸውን በትክክል የሚያሳይ ደረሰኝ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ የገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ሥልጣን እንዳይኖራቸው ማድረግ ከነባራዊው ዕውነታ መራቅ ነው፡፡ በአንፃሩ፣ ሰፊ የመወሰን ሥልጣን ለመስጠት ደግሞ የሙስና ደረጃው፣ የአስተዳደር ወጪውን ይወስኑታል፡፡

ከሕጉ ከዚህ ጠባይ አኳያ በዚህ ዓመት የተደረገውን ግምታ ስንመለከት፣ በመጀመሪው ነገር የመገመቻ መስፈርቶቹን ነጋዴው አስቀድሞ ሊያውቀው የሚችልበት አጋጣሚ አልተፈጠረም፡፡ ለነገሩ፣ ነጋዴው ይቅርና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለመገመቻ የሚያገለግለው ሠንጠረዥ የፀደቀው ሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ሆኖ ሳለ አስቀድሞ ምን መሠረት አድረጎ ግምት እንደሠራ አይታወቅም፡፡

ሌላው የቁርጥ ግብር መለያው በተፈጥሮው የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄም የማያጣው መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚወሰደው ተመሳሳይ ገቢ ያላቸው ሰዎች የተለያየ ግብር በመጠየቃቸው እኩል ያልሆኑትን እኩል ማድረጉ ነው፡፡ እኩል የሆኑትን ደግሞ የተለያየ ግብር ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ኋላ ላይ ደግሞ ግምት ላይ ተመርኩዞ የተጣለን ግብር መክፈል ያቃታቸውን ከፋዮች ንብረታቸውን መውረስ ያስከትላል፡፡ ስለሆነም እኩልነትን ይገዳደራል፡፡ በግምትም ከንብረት ባለቤትነት መነጠቅን ያስከትላል፡፡ ለቅሬታ መነሻ የሚሆነውም አድሏዊ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ቅሬታዎች ወደ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄነት ሊያድጉ ይችላሉ፡፡

የቁርጥ ግብር አቆራረጥ

ግብር አስገቢው መሥሪያ ቤት በደረጃ ‹‹ሐ›› የሚመደቡትን ወይም የዓመት ገቢያቸው እስከ ብር 500,000  ይደርሳል ብሎ ለሚያምንባቸው ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታ ለመወሰን የቁርጥ ግብር አወሳሰን ዘዴ በሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ የቁርጥ ግብር በንግድ ሥራው ዓይነትና በንግዱ ስፋት፣ የንግድ ሥራው በሚገኝበት ቦታ ያሉትን ልዩነቶች በሚያንፀባርቅ መልኩና ለቁርጥ ግብር አወሳሰን በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚፀድቀው ሠንጠረዥ መሠረት በማድረግ ሲወሰን እንደነበር ይታወቃል፡፡

አዲሱ የገቢ ግብር አዋጁና ደንቡ እንዳመለከቱት የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የንግድ ሥራ ግብር በግምት ላይ ተመሥርቶ እንደሚሰላና ለማስላትም የሚያገለግለውን የየዘርፉን የትርፍ ምጣኔ ከዚሁ ደንብ ጋር ሠንጠረዥ አያይዟል፡፡ በደንቡ በግምት ለሚሰላውም ግብር መነሻው የግብር ከፋዩ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ በሚወድቅበት ቅንፍ ውስጥ ያለውን ዓመታዊ ከፍተኛ ጠቅላላ ገቢ መሠረት በማድረግ እንደሆነ ገልጿል፡፡ በደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የሚከፈል ግብር በዓመታዊ የሽያጭ መጠን ላይ የተመሠረተ የግምት መደበኛ የቁርጥ ግብርና አመልካች ባላቸው የንግድ ሥራ ዘርፎች የቁርጥ ግብር ዘዴዎች ግብር እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች ሊይዙት የሚገባውን የሒሳብ መዝገብ ሊይዙ እንደሚችሉና በዚሁ መሠረት ሊከፍሉ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

የቁርጥ ግብሩ ከግብር መርሖች አኳያ

አንድ ጥሩ ታክስ ሊኖሩት ስለሚገባ ባህርያት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ያራመዷቸው ሐሳቦች አሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ በዕውቁ ምሁር አዳም ስሚዝ የተራመዱና በስፋት በምጣኔ ሀብት ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን አራት ዋና ዋና ባሕርያት እንመለከት፡፡

አንደኛው ባሕርይ ‘ፍትሐዊነት’ ነው፡፡ የግብር ፍትሐዊነት መርሕ የሚያመለክተው እኩል ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እኩል ግብር፣ የተለያየ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ የተለያየ ግብር መክፈል እንዳለባቸው ነው፡፡

ሁለተኛው መርሕ ‘ግልጽነት’ ነው፡፡ አንድ ግብር ከፋይ ስለሚከፍለው ግብር የመክፈያ ጊዜ የአከፋፈል ሁኔታና የክፍያ መጠን ግልጽ ሊሆንለት ይገባዋል፡፡ አንድ ግብር ከፋይ ሊከፍል የሚጠበቅበትን ግብር መቼ? በምን ያህል መጠንና እንዴት መክፈል እንዳለበት በግልጽ የማያውቅ ከሆነ፣ በአንድ በኩል ከግብር አስከፋዩ በኩል ሊያገኝ የሚገባውን ተገቢ አገልግሎት ሊያጣ የሚችልበት (ለሙስና በር የሚከፈትበት አጋጣሚ ጨምሮ) ሁኔታ ይኖራል፡፡ በተጨማሪም ትክክለኛ ግብር የከፈለ ቢሆንም እንኳ የተጭበረበረ ሊመስለው ስለሚችል በግብር ሥርዓቱ ላይ እምነት ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ግብር ከፋዩ ስለሚከፍለው ግብር ግልጽነት ሊኖረው ይገባል፡፡

ሦስተኛው የአዳም ስሚዝ መርሕ ደግሞ ‘አመቺነት’ ነው፡፡ የማንኛውም ግብር አከፋፈል ለከፋዩ አመቺ በሆነበት ጊዜና ሁኔታ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡ የአንድን ተቀጣሪ የደመወዝ ገቢ ግብር በቀጣዩ ወር አጋማሽ ላይ ራሱ መጥቶ እንዲከፍል ከማድረግ ይልቅ ደመወዝ እንደተከፈለው ወዲያውኑ በከፋዩ አማካኝነት ተቀንሶ እንዲቀር ቢደረግ፣ የእርሻ ሥራ ገቢ ግብርን ጎተራ ባዶ በሚሆንበት ጊዜ ከሚሰበሰብ ይልቅ በምርት መሰብሰቢያ ጊዜ ቢሰበሰብ፣ የሽያጭ ታክስን ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ሲገዛ ታክሱን አብሮ የሚከፍልበት ሁኔታ ብናመቻችለት የግብር አሰባሰቡን ውጤታማ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ከፋዩም ጫናው ሳይሰማው ግብሩን ሊከፍል ይችላል፡፡

አራተኛው መርሕ ደግሞ ኢኮኖሚያዊነት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊነት የሚመለክተው ግብሩ በአነስተኛ ወጪ መሰብሰብ መቻሉን ነው፡፡ ማንኛውም ግብር ለመሰብሰብ ወጪ ይወጣል፡፡ ሆኖም ግብር በመሰብሰብና በማስተዳደር ሒደት አማካይነት መኖር እንደሌለበትና የምናወጣው ወጪም በተቻለ መጠን አነስተኛ (ቢበዛ ከሚሰበሰበው ገቢ ያነሰ) መሆን እንዳለበት ያስገነዝበናል፡፡

እነዚህን አራት መርሖች ይዘን ዘንድሮ የተከናወነውን የዕለት ገቢ ግምት ሁኔታና አጠቃላይ የቁርጥ ግብሩን ብንመዝነው በብዙ መልኩ እንደሚወድቅ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የሕጎቹ ወደ ኋላ ተመልሰው ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለረጅም ጊዜ ግምት ባለመሥራቱ ነው፡፡ የሕጉ ወደ ኋላ ተመልሶ እንዲሠራ መወሰኑ የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄም ሊያስነሳ ይችላል፡፡ በተለይ ሕጉ የወንጀል ቅጣትን የሚያስከትል ስለሆነ፡፡ 

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...