መከላከያ ሠራዊት ለአገር ያለው ጠቀሜታና አስፈላጊነት በምንም ሁኔታ ለጥያቄ አይቀርብም፡፡ የመንግሥትና የአገር ሕልውና፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎችና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ደኅንነት ያለ መከላከያ ሠራዊት ከለላ ሕልውናቸው አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ግን ስንቶቻችን ነን ስለመከላከያ ወይም ስለውትድርና ሕይወት፣ ስለኑሮው፣ ስለችግሩ እንዲሁም ካለበት የሥራ ኃላፊነት አንፃር ለሠራዊቱ የምናስበውና ክብር የምንሰጠው?
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለጦርነት ብቻ የተሰለፈ ኃይል ሳይሆን፣ ለልማትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ዕገዛ በማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ሰፊ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ የራሱን ዩኒቨርሲቲ በማቋቋም ሠራዊቱ ብቃቱንና ዕውቀቱን እንዲያስፋፋና እንዲበቃ ተቋሙ በርካታ ጥረት አድርጓል፡፡ አሁንም እያደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህ ተግባሩም አድናቆቴንና ምሥጋናዬንም አቀርባለሁ፡፡
ይሁን እንጂ ልክ እንደ ሌላ የአገሪቱ ዜጋ ማለትም በሲቪል ማኅበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደሚከሰቱት ሁሉ በመከላከያም ውስጥ ይከሰታሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የመኖሪያ ቤት ችግር፣ ከተመረቁ በኋላ የትምህርት ማስረጃዎን አለማግኘት፣ ከሚሰጠው የሙያ አገልግሎትና ዕውቀት አኳያ ተመጣጣኝ ክፍያ አለማግኘት፣ ከኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ወደ ላይ አለማደግና በዚያው አግባብ ክፍያ አለማግኘት ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
ለማንኛውም ሠራዊቱ የኅብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ መጠን እንደማንኛውም ኅብረተሰብ ሕይወት አለው፡፡ ራሱን መለወጥና ማሳደግም ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጥያቄውንና ስሜቱን በቅርብ እየተከታተሉ የሚመልስና የሚፈታለት አካልና መሪ ይፈልጋል፡፡ ሙያውም ተገቢውን ክብር እንዲሰጠው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
(ተከስተ በርኄ፣ ከአዲስ አበባ)
* * *
ለጋሾች በሚገነቧቸው ፓርኮች ስደተኞችን 30 በመቶ ብቻ ሥራ ያገኛሉ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በታተመው የሪፖርተር ጋዜጣ፣ በፊት ገጹ ‹‹መንግሥት ለአንድ መቶ ሺሕ ስደተኞች የሥራ ዕድል ሊሰጥ ነው፤›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ዜና ሀተታ ዙሪያ መስተካከል የሚገባቸው ሐሳቦች ከዚህ በታች በተጠቀሱት ነጥቦች መሠረት እንዲታረሙ እየጠየቅን፣ ዜናው ከመታተሙ በፊት መረጃውን ለማጠናከር ወይም እውነታውን ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የስደተኞችን ጉዳይ ከሚመለከተው መሥሪያ ቤታችን ማረጋገጥ ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ መጠየቅ አስፈላጊ እንደነበር ለማስታወስ እንወዳለን፡፡
መንግሥት የስደተኞችንና የዜጎችን በተለይ ስደተኞችን የሚያስተናግደው ማኅበረሰብ ሕይወት ለማሻሻል በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2016 ሲካሄድ መንግሥት ለመፈጸም ቃል ከገባባቸው ዘጠኝ ጉዳዮች መካከል፣ ስደተኞችና ስደተኞችን የሚያስተናግዱ ማኅበረሰቦች በተለይ ከውጭ በዕርዳታ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ በሚቋቋሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚመሠረቱ ፋብሪካዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል፡፡
ሆኖም የዚህ ዕቅድ ተግባራዊነት ወደፊት በሚወሰኑ የሕግ ማሻሻያዎችና ሌሎች ድጋፎች ላይ የሚመሠረት ሆኖ፣ ቃል የተገባባቸው ጉዳዮች አፈጻጸም በየደረጃው እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡
አሁን ባለንበት ደረጃ መንግሥት ቃል የገባባቸው ዘጠኙ ነጥቦች የፖሊሲ ቁርጠኝነቱን በማሳየትና ለመፈጸም የሚያስችሉ መደላድሎችንና አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር ወደ ተግባር ለመቀየር በሒደት ላይ የምንገኝ መሆናችንን መገንዘብ ያሻል፡፡
ለመግቢያነት ይህን ከገለጽን፣ በዜናው ይዘት ወይም ቃላት አጠቃቀም ላይ መስተካከል ያለባቸውን ሐሳቦች ከዚህ በታች ለማሳየት እንፈልጋለን፡፡
ከዜናው ርዕስ ስንጀምር በዜናው እንደተጠቀሰው መንግሥት ለአንድ መቶ ሺሕ ስደተኞች ሳይሆን፣ በተገባው ቃል መሠረት ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ከለጋሾች በሚገኝ ድጋፍ የሚገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚፈጥሯቸው የሥራ ዕድሎች ውስጥ 70 በመቶው ለዜጎቻችን፣ ቀሪው 30 በመቶ ድርሻ ስደተኞች ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ የሚመቻችበት የወደፊት አካሄድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሚኖሩ የኤርትራ ስደተኞች ግፋ ቢል በአንድ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ ቆይተው ወደ አውሮፓ ይሰደዳሉ የሚለው የዜናው ሐሳብ የተጋነነ መስሎ ይሰማናል፡፡ እርግጥ ነው ስደተኞች በሕገወጥ የስደት አዘዋዋሪዎች ተታለው ከኢትዮጵያ እንደሚወጡ ይታወቃል፡፡ ሆኖም የኤርትራ ስደተኞች ኢትዮጵያ መጠለያ ጣቢያዎች ያላቸው ቆይታ ግፋ ቢል ለአንድ ዓመት ብቻ ነው ብሎ ለመደምደም አያስችልም፡፡ በትግራይና በአፋር ክልሎች በተቋቋሙ ስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች አሁንም ድረስ በካምፖች ውስጥ መኖራቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡
የደቡብ ሱዳንና የሶማሊያ ስደተኞች በሚኖሩባቸው መጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ የሚኖረው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ፣ ከስደተኞቹ ጋር ሥጋዊ ዝምድና ያለው መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ የመጡት ስደተኞችም በኢትዮጵያ ከሚገኘው ማኅበረሰብ ጋር የቆየ የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ትስስር ስላላቸው፣ ወደፊት ከአገራችን ሕዝብ ጋር ተዋህደው ለመኖር ያላቸው ዕድል የሰፋ እንጂ ጠባብ አይደለም፡፡
ዕቅዱ ከመጀመርያውም በሚገባ ጥናት የተደረገበት፣ ለአገራችን የሚሰጠው ፋይዳ የተለየበት፣ በሁሉም የመንግሥት አስተዳደር እርከን በቂ ግንዛቤ የተያዘበት በመሆኑ ተግባራዊነቱ አያስቸግርም፡፡ በዜናው እንደተጠቀሰው 10 ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት መከፋፈል ተብሎ ሳይሆን፣ ሊጠቀስ ይገባው የነበረው አገላለጽ በሶማሌ ክልል በዶሎ አዶ ወረዳ አካባቢ፣ የገናሌ ወንዝን በመጠቀም እስከ 100,000 የሚደርሱ ስደተኞችንና የአካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መኖሩ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተወሰነ ሔክታር መሬት ላይም ጅምር ሥራዎች መኖራቸው ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው የስደተኛ ቁጥር ከ850 ሺሕ በላይ መሆኑ፣ መንግሥት የስደተኞችን ሕይወት ለማሻሻል የገባቸው የፖሊሲ ቁርጠኝነቶች፣ ስደተኞች በአገራችን በሚኖራቸው ቆይታ ወቅት ራሳቸውን ጠቅመው ወደፊት በየአገራቸው የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ውስጥ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ፣ ምርታማ የዓለም ዜጋ እንዲሆኑና በጎረቤት ሕዝቦች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር፣ ለአገራችን ብሎም ለቀጠናው ዘለቄታዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
(ከብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር)
* * *