Saturday, June 15, 2024

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ተጀምሮ የተጠናቀቀው የአምስተኛው ፓርላማ ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሰኔ ወር ከመገባደዱ ከቀናት በፊት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች፣ ወደ 80 ሺሕ ብር የሚገመት የሕዝብ ገንዘብ በማባከንና ባልተገባ መንገድ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በመባል ተከሰው ክስ ለሕግ መቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሕዝብን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚወሰድ ዕርምጃ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ዕርምጃው ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስተኛው የፓርላማ የሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሊዘጋ ቀናት ሲቀሩት የተወሰደ ነበር፡፡

ክሱ የተመሠረተው በፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት መሠረት በተገኘ ማስረጃ ነው፡፡ ለሕግ አውጭው በሚቀርብለት ሪፖርት መሠረት ሊጠየቁ በሚገባቸው አካላት ላይ ምክር ቤቱ በሚያደርገው ግፊት ወይም ማሳሰቢያ መሠረት ክሱ መቅረቡ ይታመናል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምክር ቤቱ በየዓመቱ ተመሳሳይ የኦዲት ሪፖርቶች መሠረት በአስፈጻሚ አካላት የሚቀርቡ ግድፈቶችን፣ ደካማ አሠራሮችን፣ ከሙስና ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥፋቶችን በተመለከተ ሊጠየቁ የሚገባቸው ተቋማትና አመራሮች ላይ ጥብቅ ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚሉ ማሳሰቢያዎች ሲያስተላልፍ ጎልቶ ይሰማል፡፡

እንዲህ ዓይነት የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎችን (Check and Balance) አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ ተደርጎበት ነበር ከቀናት በፊት የምክር ቤቱ ቆይታ የተጠናቀቀው፡፡ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል፡፡

‹መስከረም ሲጠባ ጥቁሩ አደይ ሲፈነዳ›

አገሪቱ በምትመራበት የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ምክር ቤቱ ስለሚሰበሰብበትና የአገልግሎት ዘመኑን በሚደነግገው አንቀጽ 58፣ በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ዕለት ይከፈታል፡፡ እንዲሁም የርዕሰ ብሔሩን ሥልጣንና ተግባር በሚወሰነው አንቀጽ 71 ለፕሬዚዳንቱ ከተዘረዘሩት ተግባራት የመጀመርያው፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች (የሕሥብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች) አካላት ከ2/3ኛው በላይ ሲገኙ የዓመቱን የሥራ ዘመን ይከፍታሉ፡፡ በዚሁ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና በምክር ቤቶቹ የአባላት አሠራርና ሥነ ምግባር ደንብ፣ ርዕሰ ብሔሩ በሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች መካከል ተሰይመው የመክፈቻ ንግግር በማቅረብ የአዲሱን የፓርላማ የሥራ ዘመን በይፋ ያበሥራሉ፡፡

በዚህ ዕለት የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት በአብዛኛው ከሚከናውነት መደበኛ ስብሰባዎች በተለየ ደማቅ ድባብና በዓላዊ ስሜት አለው፡፡ ያለፈው ዓመት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ ጋር ተያይዞ የምክር ቤቱ አባላት ወደ ተመረጡበት አካባቢ በመሄድ፣ ወይም በሌላ ተልዕኮዎች ለሦስት ወራት ተለያይተው የሚገናኙበት ወቅት በመሆኑ አንዱ ድምቀት ነው፡፡ እንዲሁም አባላቱ ከወትሮዎቹ የመደበኛ ስብሰባዎች በተለየ የሚወክሏቸውን ብሔር ብሔረሰቦች የሚወክሉ ባህላዊ ልብሶች ተላብሰው የምክር ቤቱን የመክፈቻ ስብሰባ ያደምቁታል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ለአባላቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ያደርጉላቸዋል፡፡ የአበባ ዘንጎችንና አዲስ ዘመን የሚያመላክት የአደይ አበባ ምሥል የታተመበት ፖስት ካርድ በመስጠት፣ የመልካም ምኞት መልዕክቶችን ያስተላልፉላቸዋል፡፡ ይኼ ዓይነቱ ሥርዓት ባለፉት ሁለት አሥርት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን መስከረም 30 ቀን የተጀመረው የ2009 ዓ.ም. የሥራ ዘመን መክፈቻ ይኼንን ዓይነት የተለመደ ድባብ አልነበረውም፡፡ ምንም እንኳ አባላት የብሔረሰቦቻቸውን መገለጫ የሆኑ አልባሳትን ለብሰው ቢመጡም፣ እንዲሁም የመነፋፈቅ ስሜታቸው ቢስተዋልም በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ ተከስተው በነበሩ ሁከቶች ስሜታቸው ቀዝቅዞ ነበር የተስተዋለው፡፡

ወርኃ መስከረም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቅበት ልዩ ባህሪው የክረምት ጭጋግ ወደ ብርሃን ወቅት መሸጋገሪያ፣ ልምላሜና በአደይ አበባ ያሸበረቀ ብርሃን የሚፈነጥቅበት መሆኑ በተለይ ስሜት ይታያል፡፡ ነገር ግን ቀደም ብሎ በ2008 ዓ.ም. የመጨረሻ ወራት ተቀስቅሶ እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. የዘለቀው ሁከትና ከፀጥታ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ የግጭት ወቅት ነበር የምክር ቤቱ ሥራ የተጀመረው፡፡ በኋላም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እንደተገለጸው፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች 669 ዜጎች የተገደሉበት፣ ከ1,200 በላይ የቆሰሉበት፣ እንዲሁም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የታሰሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይም በአሳዛኙ የኢሬቻ የበርካቶች ሞት፣ በዚህም ሳቢያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ባወጀበት ማግሥት ነበር የፓርላማው መክፈቻ ቀን የነበረው፡፡

በ2009 ዓ.ም. ምክር ቤቱ ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ አስቸኳይ አዋጁን ከርዕሰ ብሔሩ የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ ማፅደቁ ነበር፡፡ በበርካቶች ዘንድ ‹‹ጥቁር መስከረም›› በተባለው ወቅት የፀደቀው አስቸኳይ አዋጅ የመጀመርያው የስድስት ወራት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በድጋሚ ለአራት ወራት የተራዘመውም በዚሁ የምክር  ቤቱ የሥራ ዘመን ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢሕአዴግ የአስተዳደር ዘመን ለመጀመርያ ጊዜ የታወጀ ነው፡፡ በቅርቡ ለተጠናቀቀው ለአምስተኛው ፓርላማ ሁለተኛው የሥራ ዘመንም ታሪካዊ ውሳኔ ያስተላለፈበት ሆኖ አልፏል፡፡ ፓርላማውም የተዘጋው ይኼው አዋጅ ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመበት ቀነ ገደብ ለመጠናቀቅ 43 ቀናት ሲቀሩት ነው፡፡

ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም. ተከስቶ ከነበረው ተቃውሞና ግጭት ጋር በኋላ፣ መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ‹‹የሕዝብን ጥያቄ›› በአግባቡ ለመመለስ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን የመንግሥታቸውን ካቢኔ እንደገና እንዳዋቀሩ ይታወሳል፡፡ የአዲሱንም የካቢኔ አባላት ሹመት ማፅደቅን ምክር ቤቱ በቀዳሚነት ተግባራዊ ካደረጋቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በምክር ቤቱ የአሥር ወራት የሥራ ጊዜ ውስጥ በጉልህ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ሌሎች ተግባራት ውስጥ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ መቋቋም አንዱ ነው፡፡ ሰባት አባላት ያሉት ቦርድ በምክር ቤቱ አባል አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ሰብሳቢነት የተሰየመ ነበር፡፡ ሥራውን በጥቅምት ወር መጨረሻ በይፋ የጀመረው መርማሪ ቦርድ፣ አንድ ጊዜ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁ ምክንያት የሆነው ተቃውሞና የፀጥታ ኃይል የወሰዱትን ዕርምጃ ተመጣጣኝነት በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ የታዘዘበት ጊዜ ነበር፡፡ የኮሚሽኑ የማጣራት ሥራም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከተከሰተው ሁከት በተጨማሪ፣ በተመሳሳይ ወቅት በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን በዲላና በአጎራባች ወረዳዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት አብሮ እንዲያጣራም ነበር ውሳኔ የተላለፈው፡፡ ኮሚሽኑም በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. የምርመራ ውጤቱን ግኝቶች በተጠናቀቀው የፓርላማው የሥራ ዘመን ነበር ያቀረበው፡፡ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘ ኮሚሽኑ በተመሳሳይ ምክር ቤቱ ከመከፈቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ፣ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተቀስቅሶ በነበረውና 23 ታራሚዎች የሞቱበትን ክስተት እንዲያጣራ በታዘዘው መሠረት፣ የምርመራ ግኝቱን ሪፖርት ያቀረበበት ጊዜ ነበር፡፡

ዓመቱ ከፖለቲካውና ከአስተዳደራዊ ግጭቶች በተጨማሪ የተለያዩ አሳዛኝ ክስተቶች የታዩበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ምክር ቤቱ ብዙም ያልተለመዱ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ ለመደረጉ የተለያዩ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ለአብነት በዓመቱ ሁለት ብሔራዊ የሐዘን ቀናትን ማወጁ ይታወሳል፡፡ የመጀመርያው የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከመከፈቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በተከሰተው የኢሬቻ በዓል አደጋ 55 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ100 በላይ በመቁሰላቸው ሳቢያ ነው፡፡ ሁለተኛው አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 130 ሰዎች የቆሻሻ ክምር ተንዶ በመሞታቸው ነበር፡፡

በእርግጥ የዓመቱ ሁለት ብሔራዊ ሐዘኖች ለአምስተኛው የፓርላማ ዘመን የመጀመርያ አይደሉም፡፡ ከዚያ በፊት ተመሳሳይ የሐዘን ቀናት በጋምቤላ ክልል በደቡብ ሱዳናውያን ለተገደሉ ዜጎችና በ2007 ዓ.ም. በሊቢያ አይሲኤስ በተባለው ሽብርተኛ ቡድን ግድያ ለተፈጸመባቸው ዜጎች መታወጃቸውም ይታወሳል፡፡

ፓርላማው በመደበኛ ሥራው በአሥር ወራት ካከናወናቸው ውስጥ ከቀረቡለት ረቂቅ ሕጎች 68 ያህሉን ያፀደቀው ይገኝበታል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን ሪፖርቶች በማዳመጥ፣ የተቋማት ኃላፊዎች ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች የሰጡዋቸውን ምላሾች ሲያደምጥም ከርሟል፡፡

ከተቋማት ሪፖርቶች ውስጥ በዋነኛነት የዋና የኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ምንም እንኳ የዋና ኦዲተር ሪፖርት በአብዛኛው የፓላማ አባላትን ቀልብ እንደሚይዝ ቢታወቅም፣ በዘንድሮው ሪፖርት የምክር ቤት አባላት በተለየ ሁኔታ ምላሻቸው ተሰምቷል፡፡

‹‹አሁንስ የኦዲት ሪፖርትን ባየሁ ቁጥር ተመሳሳይ ጥፋቶችን፣ ተመሳሳይ ጉድለቶችንና ችግሮችን መስማት እያመመኝ ነው፤›› ሲሉ ነበር በግንቦት ወር ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር የተባሉ የምክር ቤት አባል የገለጹት፡፡

‹‹የማይጠየቁ›› ተጠያቂዎች

በዋና ኦዲተሩ የሚቀርቡ ጉድለቶችም ሆኑ ሌሎች ተቋማት የሚነሱ ሊያስጠይቁ የሚችሉ ጉዳዮች በሕዝብም ቢሆን በቀዳሚነት የሚነሱ ናቸው፡፡ ከምክር ቤት የሚመጡ ማሳሰቢያዎችን ተመርኩዘው ሊጠየቁ ሲገባቸው ሳይጠየቁ መቅረታቸው፣ ምክር ቤቱን ጉልበት አልባ አድርጎታል የሚሉ ትችቶች በስፋት የሚነሱት ከዚህ ጋር በተገናኝ ነው፡፡

አፈ ጉባዔው በአንፃሩ ምክር ቤቱ በሥራ አስፈጻሚው ተፅዕኖ ሥር አለመሆኑን በተደጋጋሚ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ተጠያቂነት ለማስፈን ማንኛውንም ተቋም ሆነ አመራሮችን ከዚህ በኋላ እንደማይታገሱ፣ ምክር ቤቱ ግፊት እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ሲገልጹም ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ ይመስላል በዘንድሮው የዋና ኦዲተር ሪፖርት አባላቱ ምሬት በተሞላበት ስሜት ትችታቸውን የሰነዘሩት፡፡

‹‹በየዓመቱ ተመሳሳይ ነገር እየደገምን መሄድ የለብንም፣ ዕርምጃ መውሰድ መጀመር አለብን፤›› ሲሉም ወ/ሮ ሙሉ ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸው ተግባራት በሁሉም ዘርፎች የተሻለና ውጤታማ እንደነበር አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ መግለጻቸው ይታወሳል።

የምክር ቤቱን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ በበጀት ዓመቱ ምክር ቤቱ ያከናወናቸው ተግባራት በሁሉም ዘርፎች የተሻሉና ውጤታማ ነበር፤” ብለዋል። ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የአቅም ግንባታ ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው በዚህም የዕውቀት፣ የክህሎትና የአመለካክት አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ አባላትን ወቅቱ ለሚጠይቀው ተልዕኮ ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል።

እንዲሁም የሕዝብን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በተሻለ ደረጃ ያረጋገጡ ጥራት ያላቸው ሕጎች መውጣታቸው ተመልክቷል።

የ2010 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥትን የበጀት አዋጅን ጨምሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተረቀቁ 68 ልዩ ልዩ፣ የብድርና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና የማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች ውይይት ተደረጎባቸው ፀድቀዋል።

በዓመቱ 46 ያህል ወሳኝ ሕጎች ላይ ውይይት መደረጉን ከምክር ቤቱ መዘጋት በኋላ ተገልጿል፡፡ ኃላፊዎች ይኼንን ይበሉ እንጂ ከኦዲትና ከተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አኳያ የሚነሱ ጥያቄዎች በምክር ቤቱ አሠራር ላይ ጥያቄ ያስነሳሉ፡፡

 የፌዴራል ዋና ኦዲተር በየዓመቱ የሚያወጣው የተጠቃለለ የኦዲት ሪፖርት ላይ የሚስተዋሉት የኦዲት ችግሮች እየተባባሱ እንጂ እየተቃለሉ አልሄዱም መባላቸው ተጠቃሽ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶቹ በተለያዩ ነጥቦች ላይ በተሰጣቸው የኦዲት ሪፖርት መሠረት ማስተካከያ አለማድረጋቸው መሆኑን፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ አስገንዝበዋል።

በኦዲት ግኝቶች ላይ ዕርምጃ መውሰድ የማይፈልጉ መሥሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች ምክር ቤት ቀርበው እንኳን የዋና ኦዲተሩን አስተያየት የማይቀበሉ መሆኑን ነው የተናገሩት።

እነዚህ መሥሪያ ቤቶችና የሥራ ኃላፊዎች ያለበቂ ምክንያት በፌዴራል ዋና ኦዲተሩ በቀረቡ የኦዲት ሪፖርቶች በተሰጡ የማሻሻያ አስተያየቶች ላይ በወቅቱ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው፣ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትልባቸው መሆኑን በአግባቡ ሊገነዘቡት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

ዋና ኦዲተሩ ይኼን ይበሉ እንጂ በየዓመቱ ተደጋጋሚ የኦዲት ችግር የሚጋጥማቸው ተቋማትም ሆኑ የሥራ ኃላፊዎች በሕግ ተጠያቂ ሲሆኑ አይታይም። ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ችግር ካለባቸው ተቋማት ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።

የፌዴራሉ ዋና ኢዲተር መሥሪያ ቤት የተቋማትን የኦዲት ግኝት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከማሳወቅ ባለፈ በራሱ የሚወስደው ዕርምጃ አለመኖሩ ይታወቃል።  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሪፖርቱን ከማዳመጥ ያለፈ ሚና እንዳልነበራቸውም ነው የሚገለጸው።

ከነዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ምናልባትም የፓርላማው ግፊት ለውጥ ማሳየት መጀመሩን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ነገር ግን በተለይ በዋና አባካኝ በሆኑ ትልልቅ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ ስለመወሰዱ አሁንም ጥያቄ ይነሳል፡፡ እንዲሁም መጠየቅ ሲገባቸው ሊጠየቁ ስላልቻሉ ተቋማትና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ ጥያቄዎቹ ደግሞ በምክር ቤቱም ቀደም ብለው ሲነሱ የነበሩ፣ ወደፊትም ሊቀጥሉ የሚችሉ ናቸው፡፡

ዘመነ ታብሌት

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ከሚታወቅባቸው ልማዳዊ አሠራሮች ሁለት አዳዲስ ለውጦችም የተስዋሉበት ነበር፡፡ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጀመርያ ጊዜ በአዳራሹ የመጀመርያ ረድፍ ይቀመጡበት ከነበረው ወንበር በመነሳት ወደ ዋናው መድረክ ከአፈ ጉባዔው ጎን በመቀመጥ ንግግር ማድረጋቸው ነው፡፡  

የወረቀት ሰነዶች ሥርጭትና የኅትመት ወጪን በመቀነስ ዘመናዊ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ ፕሮግራም የቀረፀው የሕዝብ ወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፣ ለምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ታብሌት ኮምፒዩተሮችን ገዝቶ የተከፋፈለው በዚሁ ዓመት ነበር፡፡

‹‹የምክር ቤቱን አሠራር ወደ ወረቀት አልባ እንቀይረው በማለት ነው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት የቀረፅነው፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከረዩ ባናታ በወቅቱ ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡

በምክር ቤቱ ሰፊ የሆነ የወረቀት ሥራ የሚከናወን መሆኑንና ትልቅ ማተሚያ ቤትም እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ከረዩ፣ በተለይ ረቂቅ የበጀት ሰነድ በሚቀርብበት ወቅት ለአንድ የምክር ቤት ተመራጭ ሁለት እሽግ ወረቀት እንደማይበቃ ጠቁመዋል፡፡

ስለዚህም ምክር ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በመዘርጋት አሠራሮቹን ወደ ዲጂታል እንዲቀይር አስፈላጊ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የታብሌት አገልግሎቱ ከመጋቢት ወር ቢጀምርም ፓርላማው እስከተዘጋበት ሰኔ መጨረሻ ድረስ አንዳንድ አባላት ስለአጠቃቀሙ ግራ ሲጋቡና እርስ በርስ ሲረዳዱም ማየት ተችሏል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ሪፖርት በሚቀርብበትና በረቂቅ አዋጁ ውይይት ወቅት የግል ጉዳያቸውን በተሰጣቸው ታብሌት ሲመለከቱና አጠገባቸው ለተቀመጡ የምክር ቤት አባላት ሲያጋሩም ማስተዋል ተችሏል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ ሥራውን የጀመረው ፓርላማ፣ ለመጪው ዓመት 320.8 ቢሊዮን ብር በጀት በማፅደቅ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -