በኢትዮጵያ ከሚዘወተሩና የተመልካችን ቀልብ መሳብ ከሚችሉ ስፖርቶች አንዱ የእጅ ኳስ ነው፡፡ ከእግር ኳስና አትሌቲክስ ባሻገር በኅብረተሰቡ የሚዘወተረው የእጅ ኳስ የራሱን ፌዴሬሽን በማቋቋም የተለያዩ ውድድሮች ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ በአገርና በአህጉር ደረጃ ተሳትፎ የሚያደርገው ስፖርቱ በኢትዮጵያ የማጣሪያና የዞን ውድድሮች በማሰናዳት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የሚዘጋጁት አህጉር አቀፍ የእጅ ኳስ ሻምፒዮናዎች ተቀባይነት እያገኘ እንደመጣና የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያን ሁለተኛ አገራቸው አድርገው እንዲያስቡ ፌዴሬሽኑ ድርሻውን መወጣት ችሏል፡፡ እጅ ኳስ እንደአብዛኞቹ ስፖርቶች አስፈላጊውን ትኩረት ማግኘት ያልቻለ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን በክልሎች ቅስቀሳ በማድረግና ለመጀመርያ ጊዜም የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ መጀመሩ ስፖርቱ ትኩረት እንዲያገኝ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚመሩት አቶ ፍትህ መኖሪያቸው በሐዋሳ ከተማ ሲሆን፣ የሴንትራል ሐዋሳ ሆቴል ባለቤት ናቸው፡፡ በወቅታዊው የእጅ ኳስና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ዳዊት ቶሎሳ ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ማወዳደር ጀምሯችኋል፤ እንዴት ጀመራችሁት?
አቶ ፍትህ፡- የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሊጀምር የቻለው በ2008 ዓ.ም. ለውድድሩ ቅድመ ቅስቀሳ ለማድረግ በጠቅላላ ጉባዔ ከተወሰነ በኋላ ነበር፡፡ ከዛም የነበሩትን ሦስት ክለቦች ወደ አምስት ማሳደግ እንዳለብን በመወሰንና ክልሎች ላይ በመዘዋወር ቅስቀሳ በማድረግ ውድድሮችን አካሄድን፡፡ ቀድሞ የነበሩትን ክለቦች በመያዝ ድሬዳዋ፣ አላማጣ፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ ላይ የዙር ውድድሮችን አከናወንን፡፡ ቅስቀሳውን ስናደርግ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊሲና ፌዴራል ማረሚያ ቤት አብረውን ሲጓዙ የነበሩ የቀድሞ ክለቦች ናቸው፡፡ በዚህ የቅስቀሳ ውድድር 14 ክለቦች ማግኘት ቻልን፡፡ ከዛም 11 ክለቦችን በማሳተፍ በ2009 ዓ.ም. ፕሪሚየር ሊጉን ጀመርን፡፡
ሪፖርተር፡- የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ተሳታፊ ክለቦችን ግንዛቤ ከማስጨበጭ አንፃር ምን ዓይነት መንገድ ነበር የተከተላችሁት?
አቶ ፍትህ፡- በክልል ቅስቀሳ በምናደርግበት ወቅት 14 ክለቦችን ማግኘት ችለን ነበር፡፡ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ 11 ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ለመሳተፍ ምዝገባ አካሄዱ፡፡ ከሦስቱ ነባር ክለበች በስተቀር ቀሪዎቹ አዲስ ነበሩ፡፡ ስለዚህ በውድድሩ ለሚሳተፉ ክለቦች የክለብ ማኔጅመንት ሥልጠናና የውድድር ሕግ አወሳሰን ላይ ባለሙያ በመጋበዝ ሥልጠና እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በተጨማሪም ክለቦቹ የራሳቸውን የገንዘብ ምንጭ እንዴት መፍጠር እንዳለባቸው ሥልጠና እንዲወስዱ አደረግን፡፡ ከዛም የውድድሩ ደንብ፣ በፀደቀበት ወቅት ውድድሩ በደርሶ መልስ መሆን እንዳለበት ውሳኔ ላይ በመድረስ በ2009 ዓ.ም. ከ200 በላይ ጨዋታዎችን በማድረግ የመጀመርያውን ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አከናውነናል፡፡
ሪፖርተር፡- ውድድሩ በሚከናወንበት ወቅት የታዩ ክፍተቶችን ከመቅረፍ አኳያ ምን አከናወናችሁ?
አቶ ፍትህ፡- ውድድሩ የመጀመርያ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ክፍተቶች ሲስተዋሉ ነበር፡፡ በተለይ ያሉን ባለሙያዎች ጥቂት ናቸው፡፡ በተጨማሪም ስፖርቱ ንክኪ የሚበዛበት ስለሆነ በዳኝነቱ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህም አንፃር የተጨዋቾቹ ትዕግስትና የዳኞች ችሎታ ወሳኝነት ነበረው፡፡ ስለዚህም በውድድሩ አጋማሽ ወቅት ግምገማ በማድረግ ቀሪውን የ2009 የውድድር ጊዜ በተቻለን መጠን ተጠንቅቀን በማለፍ ለ2010 የውድድር ዘመን የነበሩትን ክፍተቶች ላለመድገም በግምገማ ላይ ተወያይተናል፡፡ በውድድሩ መጠናቀቂያ ላይ ሁለት ጨዋታ ተከናውኗል፡፡ አንደኛው ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ከማረሚያ ቤት ያከናወኑት ነው፡፡ ለዋንጫ የደረሱት ፌዴራል ማረሚያ ቤት መከላከያ ናቸው፡፡ በውድድሩም ከነጥብ ባሻገር በጨዋታ ላይ የሚቆጠሩ ጎሎችን ታሳቢ ስለሚያደርጉ በፍጻሜ ጨዋታው ማረሚያ ቤት ማሸነፍ ቢችልም፣ በነበረበት 8 የጎል ዕዳ የውድድሩ አሸናፊ መከላከያ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል፡፡
ሪፖርተር፡- ፕሪሜየር ሊጉ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በክልል ላይ ስታከናወኑት የነበረው ቅስቀሳ ለዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ያደረገው አስተዋፅኦ ምንድነው?
አቶ ፍትህ፡- በክልሎች ተዘዋውረን ያደረግነው የቅስቀሳ ውድድር በአገሪቱ ያለውን የእጅ ኳስ ደረጃ መመልከት እንድንችልና ከዛም ባሻገር ስፖርቱ የበለጠ ማሳደግ እንድንችል ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም በየክልሉ ብዙ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን ማግኘት ችለናል፡፡ በተጨማሪም የክለብ ቁጥርን መጨመር አስችሎናል፡፡ ታዳጊዎችም መዳረሻቸውን ማግኘት ችለዋል፡፡ ቀደም ብሎ ታዳጊዎቹ መጫወት ቢችሉም ክለብ ስለሌለ የስፖርት ዓይነት ይቀይራሉ ወይም ወደ ሌላ መስክ ይሰማሩ ነበር፡፡ ከውድድር በኋላ ግን ክለቦች በፕሪሚየር ሊግ በመኖሩ ወደዛ ደረጃ ከፍ ለማለት ዕድላቸውን ይሞክራሉ ማለት ነው፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለውድድር ወደ ተለያዩ አገሮች ሲያመራ ተጫዋቾችን ለማግኘት ይቸገር ነበር፡፡ አሁን ግን በቀላሉ ከክለቦች መምረጥ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ለማሳተፍ በየቤቱ መሯሯጥ የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው የውድድር ወቅት እንደ ችግር የሚነሳ ጉዳይ ካለ ቢያብራሩልን?
አቶ ፍትህ፡- በአጠቃላይ የውድድር ወቅት ትልቅ ችግር አድርገን የምናነሳው የፋይናንስ ችግር ነው፡፡ ያንንም ችግር ለመፍታት ፕሪሚየር ሊጉ ከመጀመሩ በፊት የውድድሩን ስም እንኳን ሸጠን የገንዘብ አቅማችንን ለማጠናከር ብንሞክርም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ በእርግጥ ስፖርቱ ባልታወቀበት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማስተናገድ ለባለሀብቱ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ስፖርቱን ለማሳደግ በሚል የውድድሩን ወጪ ሙሉ በሙሉ ፌዴሬሽኑ ነው የቻለው፡፡ ሁለተኛው ችግር የነበረው ከዳኝነት አንፃርና ከስፖርተኞች ሥነ ምግባርና ትዕግስት ማጣት አንፃር ነበር፡፡ ግን በውድድሩ ግማሽ ላይ ችግሮችን በመቅረፍ ውድድሮችን ማከናወን ችለናል፡፡ የፋይናንስ እጥረቱን በተመለከተ በሌሎች ስፖርቶች ሁሉንም ወጪ ክለቦች ነበሩ የሚሽፍኑት፤ በዚህ ፕሪሚየር ሊግ ላይ በየጨዋታው ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ብር ድረስ ስለሚጠይቀን ተቸግረን ነበረ፡፡ ግን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተወሰነ ድጋፍ አድርገውልን ውድድሩን ማጠናቀቅ ችለናል፡፡
ሪፖርተር፡- በሴኔጋል ከሐምሌ 25 እስከ 29 2009 ዓ.ም. በሚከናወነው የአፍሪካ የእጅ ኳስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ተሳታፊ መሆን ችላለች፡፡ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
አቶ ፍትህ፡- ብሔራዊ ቡድናችን ሴኔጋል ላይ የሚካሄደው የእጅ ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ቀደም ብሎ ጂቡቲ ላይ በተደረገው የምሥራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና የሜዳሊያና ዋንጫ ተሸላሚ በመሆኑ ተሳታፊ መሆን ችሏል፡፡ በውድድሩ ላይ ስንሳተፍ ሙሉ ወጪውን ዓለም አቀፉ እጅ ኳስ ማኅበር ቢሸፍነውም፣ አቅማችን ደካማ ስለሆነ ብሔራዊ ቡድንኑን ወደ ሆቴል ማስገባት አልቻልንም፡፡ ሆኖም ግን ወንዶቹ ውድድር ላይ መቆየታቸውን ተከትሎ በቀሩት ጊዜ በቂ ዝግጅት አድርገን፣ ቡድኑን እንልካለን ሴቶቹንም ቢሆን ባለው ጊዜ ልምምድ አድርገው እንዲሳተፉ እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድሮችን ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ውድድሮች ማሰናዳት መቻልዋ ጠቀሜታው ምንድነው?
አቶ ፍትህ፡- ስፖርቱ ትልቅ ለውጥ እያሳየ መጥቷል፡፡ ለዚህም ደግሞ በወንበር ደረጃ ስንወያይበት አህጉር አቀፍ ውድድሮች ማዘጋጀት ስፖርቱን ከማሳደግና ገቢን ከማሳደግ አኳያ፣ እጅ ኳስን ለሕዝብ በሚዲያው በማሳወቅ ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረግ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የምሥራቅ አፍሪካ የዞን ውድድር አዲስ አበባ ላይ ተደርጓል፡፡ በወድድሩም በወንዶችና በሴቶች ዋንጫ ማንሳት ቻልን፡፡ ከዛም በመቀጠል የመላው አፍሪካን ጨዋታዎችን የብሔራዊ ቡድኑ ማጣሪያ ውድድርም እንድታዘጋጅ ተደረገ፡፡ እነዚህ ውድድሮች በኢትዮጵያ ላይ መከናወናቸው በአገሪቱ ያለው የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታና እንግዳ ተቀባይነት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ካለው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ሪፖርተር፡- እጅ ኳስ አንዱ የኦሊምፒክ ስፖርት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያለበትን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ምን ዓይነት መንገድ መከተል ይኖርበታል ይላሉ?
አቶ ፍትህ፡- ቀድሞ በሚዘጋጁ አህጉር አቀፍ ውድድሮችን በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እንሸሸው ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተቻለን አቅም መሳተፍ ጀምረናል፡፡ በአንፃሩ ብዙ የኦሊምፒክ ውድድሮች በየዓመቱ ይዘጋጃሉ፡፡ በነዚህ ውድድሮች ላይ ያለምንም የፋይናንስ ችግር ለመሳተፍና የገንዘብ ምንጫቸውን ለማገዝ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ካለው ተሰሚነትና ስም አንፃር ስፖንሰር አድራጊዎችን ፈልጎ፣ የኦሊምፒክ ስፖርት ናቸው የተባሉትን ስፖርቶች ያለምንም ጉድለት የውጭ ውድድር እንዲያገኙና ልምድ እንዲቀስሙ የአገር ውስጥ ውድድሮችን እንዲያዘጋጁ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ስፖንሰር መጠየቅና እንደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መጠየቅ ሰፊ ልዩነት አለው፡፡ በተጨማሪም ስፖርቱን ወደ ታችም ወርዶ ለመሥራት ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የፋይናንስ ችግሩን ለመፍታት ምን ዓይነት ጥረት አድርጓል?
አቶ ፍትህ፡- እንደ ፌዴሬሽን የፋይናንስ ችግሩን ለመፍታት ብዙ ሥራ አልሠራንም ብዬ አላስብም፡፡ ክለቦች የውድድር ዓመቱን ሙሉ በደርሶ መልስ ጨዋታ እንዲያከናውኑ፣ ክለቦችም እንዲመሠረቱ ታች ድረስ መውረድ ትልቅ ጥረት አድርጓል፡፡ ከፋይናንስ ባሻገር ተገቢ በሆኑ ባለሙያዎች ውድድሮችን ማከናወን መቻላችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የገንዘብ አቅም ቢኖር እንኳን ውድድርን በአግባቡ ማከናወን ካልተቻለ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሥራዎችም እጅ ኳስ የኦሊምፒክ ስፖርት ለማድረግ እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀጣይ ዕቅድ ምንድነው?
አቶ ፍትህ፡- የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መጀመራችን አንድ እርምጃ ወደፊት መሄዳችንን ያሳያል፡፡ በቀጣይ ግን ከአምስት በላይ ክለቦች በወድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ስለዚህ በ2010 ዓ.ም. የሚመጡትን ክለቦችን በመሉ በመያዝ ውድድሩን የበለጠ ማሳደግ በሚቀጥለው ዓመት ለሚያደርገው ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች ቁጥር ቢጨምርም ውድድሮችን ወደ ዞን በማውጣት የመጨረሻ ጨዋታን በአዲስ አበባ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ እንከተላለን፡፡ የክለቦች ቁጥር አናሳ ከሆነ ግን በደርሶ መልስ እናካሂዳለን፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራር ምርጫ መከናወኑ ይታወሳል፡፡ በምርጫውም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እርስዎ እንደ ዕጩ አቅርቦ ነበር፡፡ ምርጫውን እንዴት አገኙት?
አቶ ፍትህ፡- ፌዴሬሽናችን ካለው ጥሩ እንቅስቃሴ በኦሊምፒክም ኮሚቴ አመራርነት ውስጥ ቢካተት የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላል በሚል ሐሳብ አዲስ ተዋቅሮ በነበረ ኮሚቴ ውስጥ እንደ ዕጩነት መቅረብ ችዬ ነበር፡፡ በአጋጣሚ በነበረብኝ የግል ጉዳይ ከአገር ውጭ ስለነበርኩኝ በምርጫው መገኘት አልቻልኩም፡፡ ግን ሁሌም ምርጫ ላይ ሰው ሳይሆን ሥራን መሠረት ያደረግ ምርጫ ቢደረግ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ያው ከምርጫው በኋላም በተጠባባቂነት መመረጥ ችያለሁ፡፡ ግን ከምርጫ በኋላ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አንዳንድ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን በምርጫ ወቅት ሥራዎች ታይተውና አስፈላጊ መስፈርት ቢቀመጥ መልካም ነበር እላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ለውድደር ሲቀርቡ በስፖርት ውስጥ ምን ዓይነት አገልግሎት ወይም አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ ብለው ነው?
አቶ ፍትህ፡- እንደራሴ ሁለት ነገሮችን ሠርቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ አንደኛ ወደ እጅ ኳስ አመራርነት ከመጣሁ በኋላ ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ማድረግ ችያለሁ፡ ከዛ በተጨማሪም ደግሞ ለአፍሪካም እንድታልፍ ማድረግ ችያለሁ፡፡ ለመላው አፍሪካ ውድድርም ተፎካካሪ በመሆን በወንዶች አራተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለናል፡፡ ሌላው ደግሞ በክልል ላይ ቅስቀሳ በማድረግ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በአምስት የክልልና የከተማ አስተዳደር ከተሞች ላይ ውድድሩ እንዲከናወን ፌዴሬሽኑ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ለዕጩነት ያበቁኛል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በክረምቱ በሐዋሳ ከተማ የሴንትራል መለስ የእግር ኳስ ዋንጫ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፤ ስለ ውድድሩ ቢገልጹልን?
አቶ ፍትህ፡- የሴንትራል መለስ የእግር ኳስ ዋንጫ ክረምት ላይ የሚከናወን ውድድር ነው፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታትም ጨዋታውን ስናካሂድ ቆይተናል፡፡ በውድድሩም ከትምህርት ገበታቸው ለዕረፍት የተመለሱትን ታዳጊዎች አልባሌ ቦታ ከሚውሉና ለክለቦች ግብዓት ይሆኑ ዘንድ በማሰብ በየዓመቱ የሚዘጋጅ ውድድር ነው፡፡ በሐዋሳ ሴንትራል ሆቴል ወጪ የሚከናወን ሲሆን፣ 50 ክለቦች በ13፣15፣17፣19 ዓመት የዕድሜ እርከን ውስጥ ያሉትን ያሳትፋል፡፡ በዚህ ውድደር ላይ በየዓመቱ የከተማው እንዲሁም ሌሎች ክለቦች ታዳጊ ተጨዋቾችን ይወስዳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ ውድድር ላይ ያለፉ ተጫዋቾች ለወጣት ብሔራዊ ቡድን መድረስ የቻሉ ታዳጊዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃና እንቅስቃሴውን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ፍትህ፡- የእግር ኳሱን ወቅታዊ እንቅስቃሴ ስንመለከት ፋይናንሱ በጣም አድጓል፤ ስፖርቱ ግን እየተሻሻለ መምጣት አልቻለም፡፡ ከፍተኛ ወጪ እየወጣበት እግር ኳሱ ማደግ ስላልቻለ ግን ቆም ተብሎ መታሰብ አለበት ባይ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራርነት ዕጩ ሆነው የመቅረብ ፍላጎት እንዳልዎት እየተነገረ ይገኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ ፍትህ፡- እንደዚህ ዓይነት አስተያየት ከሰዎች እየተሰጠኝ ነው፡፡ እኔ ግን እስካሁን ምንም የወሰንኩት ነገር የለም፡፡ ምኞት ግን ይኖራል፤ በቂ ፋይናንስ በሌለበት እጅ ኳሱን የተወሰነ ደረጃ እንዲደርስ ካደረግን፣ በእግር ኳሱም ብንመጣ ይከብደናል ብዬ አላስብም፡፡ ውድድር ማድረግ ስኬት ማሳያ መድረክ እንጂ መሳተፍ ስኬት ነው ብዬ አላስብም፡፡ ስለዚህ በጊዜ ሒደት የምንመለከተው ይሆናል፡፡