Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአንድነት ተምሳሌቱ የሠራተኞች ስፖርታዊ ውድድር በወንጂ

የአንድነት ተምሳሌቱ የሠራተኞች ስፖርታዊ ውድድር በወንጂ

ቀን:

የስፖርቱ አደባባይ የጅረት መቧደኛ እየሆነ መምጣቱ ሳያንስ መቃቃርን የሚፈጥር የኳስ ሜዳ እንኪያ ሰላንቲያ ማስተናገጃ የመሆኑ ነገር አሳሳቢ መሆኑ ብቻም ሳይሆን፣ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ አመራሩና የመንግሥት አካል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

የስፖርት ክንውኖች ከስፖርታዊ ጨዋነት፣ ከባህልና ወግ ልማድ አኳያም ብሽሽቅና ሙገሳ፣ መተራረብና ያሸነፈው በተሸነፈው ላይ መሳቅና መቀለድ የተለመደ ያለና የነበረ መሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም፡፡ አሁን አሁን ግን የስፖርት ሜዳዎች ዘር መቁጠሪያና ማናቆሪያ እየሆኑ በመምጣታቸው ቡድኖች በሌሎች ሜዳዎች እየሄዱ መርሐ ግብሮቻቸውን አከናውነው እንደአመጣጣቸው የሚመለሱበት ዕድል እየጠበበ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር እየሆነ መጥቷል፡፡

ይህን አጋጣሚ የጉዳዩ ቀጥተኛ ተዋንያን የሆኑት የስፖርት አመራሮችና ባለሙያተኞች በውጤቱ እንዳይጠቁ ምክንያትም እያደረጉት ይገኛል፡፡ ከእነአካቴው የስፖርት ውድድሮች አሳሳቢ መድረኮች የመሆናቸውን ነገር የአገሪቱ ባለሥልጣናት እየተናገሩ ባለበት በዚህ ወቅት ነገርየው ግን ሥር እየሰደደ ለመሆኑ ማሳያው በማኅበራዊ ድረ ገጽ ያለው ድርጊት ነው፡፡

ይሁን እንጂ በሌላ መድረክ ዕድሜ ጠገብ የስፖርት ማኅበራት የሚያዘጋጇቸው ውድድሮች ግን የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት መሆናቸውን እያሳዩ ነው፡፡

ከተመሠረተ ከአምስት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በየዓመቱ የሚያካሂደው የክረምት ወራት አገር አቀፍ የስፖርት ውድድር ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይኼው አገር አቀፍ የሠራተኞች ውድድር አሁን ያለውን መዋቅራዊ ቁመና ከያዘ በኋላ 22ኛውን ዓመታዊ ስፖርታዊ ውድድሮችን በወንጂ ስታዲየም እያከናወነ ይገኛል፡፡

የኢሠማኮ ኃላፊ አቶ ፍሥሐ ጽዮን ቢያድግልኝ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ እየተከናወነ የሚገኘው የሠራተኞች የቤተሰብ ውድድር፣ ሠራተኛው ጤንነቱን የጠበቀ አምራች ዜጋ እንዲሆን፣ እርስ በርስ የአብሮነትንና የውንድማማችነትን ትስስር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጭምር ያስረዳሉ፡፡ ይኼው ስፖርታዊ ውድድር እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርቶች ካለፈው ሳምንት ከሐምሌ 9 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ በወንጂ ስታዲየም የሚቀጥል እንደሚሆንም ያስረዳሉ፡፡

እንደ ኃላፊው፣ ስፖርት በቢሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ እያንቀሳቀሰ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ በሆነበት በዚህ ዘመን ተቋማዊና አገራዊ መልካም ገፅታን በመገንባት ረገድም ተወዳዳሪ የሌለው መድረክ ነው፡፡ ይህንኑ መነሻ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ቀደም ባሉት ዓመታት እንደነ ትግል ፍሬ፣ ዕርምጃችንና ወደፊት የተሰኙ ጠንካራ የእግር ክለቦችን እስከማቋቋም የደረሰ ከመሆኑም በላይ ከእነዚህ ክለቦች በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድን ሲያስመርጥ የነበረ ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡  

በዚህ እየተከናወነ ባለው የሠራተኛው አገር አቀፍ ውድድር የተመዘገቡ ማኅበራት በእግር ኳስ 26፣ በመረብ ኳስ ወንዶች 15፣ በመረብ ኳስ ሴቶች 5፣ ጠረጴዛ ቴኒስ ወንዶች 15፣ ጠረጴዛ ኳስ ሴቶች 6፣ ዳማ ወንዶች 7፣ ከረንቡላ ወንዶች 13፣ ቼዝ ወንዶች 15፣ ገበጣ ባለ 12 ጉድጓድ 10፣ ዳርት ወንዶች 9፣ ሴቶች 3፣ አትሌቲክስ ወንዶች 13፣ ሴቶች 10፣ ገመድ ጉተታ ወንዶች 5፣ ሴቶች 2 ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ወንዶች 1,400፣ ሴቶች ደግሞ 250 በድምሩ 1,650 ተወዳዳሪዎች ከተለያዩ ተቋማት ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡

በስፖርት የሠራተኛው ተሳትፎ ከ30 ዓመታት በፊት ደርሶበት ከነበረው ከፍተኛ ዕድገት አኳያ አሁን ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ያስረዱት ኃላፊው፣ የሠራተኛው ማኅበረሰብ ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ ማዘውተሪያ ይኖረው ዘንድም የግንባታ ቦታ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡

ስፖርታዊ ውድድሩ ከተጀመረ ጀምሮ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከእግር ኳሱ ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ያለው የ‹‹ወንዜነት›› ችግር እንዳላጋጠመው የሚናገሩት ተሳታፊ ቡድኖች በተለይ ለሪፖርተር እንደሚገልጹት ከሆነ፣ ስፖርት በመርሑ የአንድ አገር ማኅበረሰብን አይደለም የዓለም ሕዝቦች በአንድ ቋንቋ የሚናገሩበት መድረክ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...