Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበቻይና ቱሪዝም ሁሉም ይሸጣል

በቻይና ቱሪዝም ሁሉም ይሸጣል

ቀን:

ሲኤንኤን ትራቭል ባለፈው ሳምንት በድረ ገጹ ቻይና ውስጥ መጎብኘት ያለባቸው 40 ቦታዎችን ዝርዝር አስነብቦ ነበር፡፡ በግንባር ቀደምነት ያሰፈረው 900 ዓመታት ያስቆጠረውን የቻይና ጥንታዊ መንደር ሆንቹዋን ሲሆን፣ በቀጣይ ጥንታዊ የቻይና ቤተ መቅደሶችና ተፈጥሯዊ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በቻይና 23 ግዛቶች ከሚገኙ ቱሪስት ሳቢ ሥፍራዎች መካከል የአገሪቷን ጥንታዊ ሥልጣኔ የሚያንፀባርቁ መንደሮችና ዘመኑ የደረሰበት የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ኪነ ሕንፃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቀደመ ታሪካቸውና በነባራዊ ማንነታቸው መካከል ድልድይ ዘርግተው፣ አገራቸውን ለመጎብኘት ለወደዱ ሁለቱንም ገጽታ ያስቃኛሉ፡፡

በቻይና ቆይታችን በመዲናዋ ቤጂንግና ከአገሪቱ ግዛቶች በአንዷ ኒንሻ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተናል፡፡ በእርግጥ የትኛውም አገር የሚኩራራበት ታሪክ መገለጫ የሆኑ አካባቢዎችን ወይም ባህሉን የሚያንፀባርቁ ክንውኖችን ለቱሪስቶች ክፍት ያደርጋል፡፡ ቻይና ውስጥ ያስተዋልነው የተለየ ነገር ቢኖር፣ ማንኛውንም ነገር ወደ መስህብነት ለመቀየር የሚያደርጉትን ጥረት ነው፡፡ ቤጂንግ ውስጥ ግሬት ዋል ኦፍ ቻይና፣ ቴምፕል ኦፍ ሔቨን፣ ፎርቢን ሲቲ እና ቲናመን ስኩዌርን መጎብኘት እንግዳ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ከነዚህ ታሪካዊ ሥፍራዎች ባሻገር የሆሊውድና የቻይና ፊልሞች የተቀረፁባቸው አካባቢዎች እንዲጎበኙ ያደርጋሉ፡፡

ተፈጥሮ ካደለቻቸው አካባቢዎች በተጨማሪ ሰው ሠራሽ መስህቦችን መፍጠርንም ተያይዘውታል፡፡ ሲኤንኤን ትራቭል በምርጥ 40 ዝርዝሩ ካካተታቸው እንደ ማውንት ውይ ያሉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ካሰፈራቸው ተራሮች በተጨማሪ ሰው ሠራሽ ሐይቆች አሏቸው፡፡ ኩንሚንግ ሐይቅን የመሰሉ ሰው ሠራሽ ሐይቆች ከተፈጥሯዊ ሀብቶቻቸው ባልተናነሰ ከሚጎበኙት መካከል ይጠቀሳል፡፡ አገሪቷ ውስጥ በርካታ የአበባ ፓርኮች ያሉ ሲሆን፣ በመገንባት ላይ የሚገኙም አሉ፡፡ በተለይም ጥንዶች የማይዘነጋ የፍቅር ጊዜ እንዲያጣጥሙባቸው ታስበው የተሠሩ ግዙፍ የአበባ ፓርኮቻቸው ይማርካሉ፡፡

ኒንሻ ውስጥ አሸዋማ በረሃዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸዋል፡፡ ብዙዎች ይጎበኛል ብለው የማይገምቱት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በቻይና እንደ መዳረሻ ይቆጠራል፡፡ የማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት የሚንፀባረቅበት ግዙፍ የፊልም ስቱዲዮም አላቸው፡፡ ወይን ሲጨመቅ፣ ብረታ ብረት ሲሠራ፣ አልባሳት ሲዘጋጁና ሌሎችም የመደበኛው ኅብረተሰብ የዘወትር እንቅስቃሴዎች ይጎበኛሉ፡፡ የወይን ፋብሪካዎች፣ የዓመታት ጉዟቸውን በፋብሪካቸው መጋዘን አስጎብኝተው ነጭና ቀይ ወይናቸውን ጎራ ላለ ሁሉ ያስቀምሳሉ፡፡

የቤጂንግ ብሔራዊ ስቴዲየም (በርድስ ኔስት በመባል የሚተወቀውና እ.ኤ.አ. 2008 ለሰመር ኦሊምፒክና ፓራሊምፒክስ) የተሠራው ስቴዲየም ከበርካቶች የጉብኝት ዝርዝር ውስጥ ይካተታል፡፡ አንዳንድ ነገር መሸመት ለሚፈልጉ እንደ ፐርል ማርኬትና ስልክ ማርኬት ያሉ መገበያያ ሕንፃዎች ክፍት ሲሆኑ፣ ከመገበያያነት ጎን ለጎን የቻይና ባህላዊ ጌጣ ጌጦችና ቁሳቁሶችን መጎብኘትም ይቻላል፡፡ መገበያያ ማዕከሎችን ከመዝናኛዎች ጋር አዋህዶ የሚያቀርበው ዋን ፍንጂንግ ጎዳና በቻይና ቆይታችን ከጎበኘናቸው አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡

በደማቅ መብራት ያሸበረቁ ሕንፃዎችና ግዙፍ ስክሪኖች ከሚጎበኙባቸው ጎዳናዎች በአንፃሩ በጥሞና የእግር ጉዞ የሚደረግባቸው መንገደችም ይገኛሉ፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደተተከሉ የሚያሳብቁ ዛፎች ሞቃታማዋን ቻይና ቀዝቀዝ ስለሚያደርጓት ጎዳናዎቹን አንዴ የጎበኘ ደጋግሞ መሄድ ይመኛል፡፡ ቻይና በየትኛውም ዕድሜ ክልል ለሚገኝና ማንኛውም ዓይነት ፍላጎት ላለው ሰው የሚመጥኑ ቦታዎች አሰናድታለች ማለት ይቻላል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ የሚገጎበኙ ሥፍራዎች መፍጠራቸው አገሪቱ ዓለም ላይ ከሚጎበኙ አገሮች ሦስተኛ ከሆነችበት ምክንያት አንዱ ነው፡፡

ወርልድ ቱሪዝም ኦርጋናይዜሽን (ደብሊውቲኦ) ቻይና እ.ኤ.አ. በ2020 ከመላው ዓለም በቀዳሚነት የምትጎበኝ አገር እንደምትሆን ተንብዩዋል፡፡ ከቢዝነስ ነክ ጉዞዎች በመቀጠል ቱሪዝም ለአገሪቱ ዓመታዊ ገቢ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በቀላሉ አይታይም፡፡

በተዘዋወርንባቸው ሥፍራዎች ቻይናውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ብዙ ሺሕ ጎብኝዎች ገጥመውናል፡፡ የጎብኚዎች ቁጥር በርካታ ከመሆኑ የተነሳ አስጎብኚዎች በረዥም እንጨት ላይ ከሩቅ የሚታይ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ለማስጎብኘት ይገደዳሉ፡፡ በቡድን የሚጎበኙ ሰዎች ከሌሎች ጎብኚዎች ጋር ድንገት ቢቀላቀሉ አስጎብኚያቸው የያዘውን ሰንደቅ ዓላማ አፈላልገው ወደ ቡድናቸው ይመለሳሉ፡፡

በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ ያለው ንግድም የተጧጧፈ ነው፡፡ ወቅት ተኮር ከሆነው የኮፍያና የአይስ ክሬም ሽያጭ በተጨማሪ፣ የሚጎበኘውን አካባቢ የሚገልጹ ምስሎች፣ ቅርፃ ቅርፆችና የቤት ውስጥ መገልገያዎች ይቸበቸባሉ፡፡ ከሻጮቹ ጋር በቋንቋ ለመግባባት ቢያስቸግርም ጉግል ትራንዝሌትን እያመሠገኑ መገበያያት ይቻላል፡፡ በእርግጥ አፕልኬሽኑ ቃላትን እንደ አገባባቸው ሳይሆን በቀጥታ ስለሚተረጉም አንዳንዴ ተናጋሪው ለማለት ካሰበው ዐውድ ውጪ ያለ ፍቺ ሊሰጥ ይችላል፡፡ አፕልኬሽኑ ተናጋሪው ማለት ከፈለገው የተለየ ነገር እንደተረጎመ ማወቅ የሚቻለው በቻይናውያኑ ፊት ግራ መጋባት ሲነበብ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ጎብኚዎች ሰላምታ ከመስጠት (ኒ ሀው) እና ከማመስገን (ሼሼ) በዘለለ ማንዳሪን ለመማር የሚገደዱትም ለዚሁ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1949 እስከ 1974 በሯን ለዓለም ሕዝብ ዝግ አድርጋ የቆየችው ቻይና፣ በተለይ ባለፉት ሁለት አሠርታት ራሷን ከዓለም ሕዝብ ጋር ማስተሳሰር ጀምራለች፡፡ በእርግጥ አሁንም ሕዝቡ ቻይናን ካማከሉ እንቅስቃሴዎች ውጪ ላሉ ነገሮች የሚያሳየው ፍላጎት የተገደበ ሲሆን፣ ቻይና በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች እያስተናገደች ነው፡፡ አምና ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ጎብኚዎች ከደቡብ ኮሪያና ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ የቬትናም ቱሪስቶች ቻይናን ጎብኝተዋል፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ የቻይና መስህቦች በተለያየ መለዮ ሲተዋወቁ ይደመጣል፡፡ ዓመታዊ ፌስቲቫሎችና ሌሎችም ክንውኖችን በመጠቀም አገሪቱን የሚያስተዋውቁ እነዚህ መለዮዎች በየዓመቱ ለዓለም ይለቀቃሉ፡፡ በጎበኘናቸው መዳረሻዎች ፀሐይ የምትጠልቅ እስከማይመስል ድረስ በቀንም በማታም ቱሪስቶች ይጎርፋሉ፡፡ እኩለ ሌሊት ገደማ ሰብዌይ ስለሚዘጋ የምሽት ጎብኚዎች በታክሲ ወይም በአውቶብስ ይጠቀማሉ፡፡

በምሽት ከጎበኘናቸው ታሪካዊ ሥፍራዎች መካከል ቲናመን ስኩዌር ይጠቀሳል፡፡ የአደባባዩ ቅጥር ግቢ ምሽት ላይ ተዘግቶ በከፍተኛ ሁኔታ በወታደሮች ቢጠበቅም ጎብኚዎች ወደ አካባቢው ይተማሉ፡፡ በአደባባዩ ዙሪያ ባለው ሰፊ የእግረኛ መንገድ በዝግታ የሚንሸራሸሩ፣ ፎቶግራፍ የሚነሱ ሰዎች አካባቢውን ሰዋዊ ውበት ያላብሱታል፡፡ ከውጪ ጎብኚዎች ባሻገር ቻይናውያንንም በቦታው ያስተዋለ፣ ምን ያህል ለታሪካቸው ዋጋ እንደሚሰጡ ይገነዘባል፡፡

ቲናመን ስኩዌር እ.ኤ.አ. በ1989 ቤጂንግ ውስጥ የተቀሰቀሰውን የተማሪዎች አብዮት በታሪክ ወደ ኋላ የሚያስታውስ ሥፍራ ነው፡፡ አብዮቱን ማፈን የፈለገው የወቅቱ መንግሥት በከባድ የጦር መሣሪያ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ በተማሪዎችና በፖለቲከኞች መካከል የነበረው ሽኩቻ የተጧጧፈው ተማሪዎች የረሃብ አድማ አድርገው፣ ተቃውሞው ወደ 400 ገደማ ወደ ሚሆኑ የቻይና ከተሞች ሲሰራጭ ነበር፡፡ ተቃውሞውን ለማፈን ወደ 300 ሺሕ ወታደሮች በቤጂንግ ያሰማራው የቻይና መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰላ ትችት ደርሶበትም ነበር፡፡ በዛሬዋ ቻይና ታሪክ የማይዘነጋው ወቅት ቅሪት የሆነውን አደባባይ ቤጂንግ ደርሶ የማይጎበኘው አይገኝም፡፡

በአብዮቱ ወቅት ከተስተጋቡ ተቃውሞዎች መካከል የአገሪቱ አምባገነን አመራርና የፕሬስ ነፃነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከአብዮቱ በኋላ ቻይና ውስጥ ለውጥ ቢመጣም፣ ዛሬም በአገሪቷ ፖለቲካዊ አካሄድ ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አለመኖር እንዲሁም የአገሪቱ ሚዲያዎች ባጠቃላይ የመንግሥት መሆናቸው ያስተቻቸዋል፡፡

እንደ ቲናመን ስኩዌር ፖለቲካዊ አንድምታ ባይኖራቸውም ፎርቢድን ሲቲና ቴምፕል ኦፍ ሔቨን የመሰሉ ቤተ መቅደሶችና ቤተ መንግሥቶች በታሪክ ወዳድ ቱሪስቶች ዘንድ ይመረጣሉ፡፡ ፎርቢድን ሲቲ ከሚንግ ሥርወ መንግሥት አንስቶ እስከ ክዊንግ ሥርወ መንግሥት ያገለገለ ቤተ መንግሥት ነው፡፡ ለ50 ዓመታት የመንግሥታት መቀመጫ የነበረው ፎርቢድን ሲቲ፣ 780 ሕንፃዎች የያዘ ሲሆን፣ ጥንታዊ የቻይና ኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይበት ነው፡፡ ከሚንግና ክዊንግ ሥርወ መንግሥት የተሰበሰቡ በርካታ ጥንታዊ መገልገያዎች የሚገኙበት ቅጥር ግቢው፣ የዓለም ቅርስ ሆኖ ከተመዘገበ 50 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ፎቢድን ሲቲን ለመገንባት 14 ዓመታት ወስዷል፡፡ ቅጥር ግቢውን ሙሉ በሙሉ ተዘዋውረን ለመመልከት ጊዜ ባይኖረንም፣ በግቢው ውስጥ እንደ ቤተ መቅደስ የተሠሩ ሕንፃዎች ጎብኝተናል፡፡ ግቢው አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት የቡዲዝም ሃይማኖት ይከናወንባቸው የነበሩትን በአርምሞ ያስተዋለ ሰው በየሕንፃዎቹ የተቀረፁ ምስሎችን ተቀራራቢነት ይገነዘባል፡፡

በአስጎብኚያችን ገለጻ በየሕንፃው የሚስተዋለው ደማቅ ቢጫ ቀለም ነገሥታቱን ሲወክል፣ በግቢው ውስጥ ምድርና ገነትን የሚወክሉ ቦታዎችም ይስተዋላሉ፡፡ በፎቢድን ሲቲ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገሪቱ ታሪካዊ ሥፍራዎች ድራጎኖችን መመልከት አያስገርምም፡፡ ለጥንታዊ ፍልስፍና እምነት ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ቻይኖች በዘመናዊ ሕንፃዎቻቸው ሳይቀር የድራጎን ቅርፅ ያሰፍራሉ፡፡

ፎርቢድን ሲቲ በተገነባበት አካባቢ የተሠራው ቴምፕል ኦፍ ሔቨን ሃይማኖታዊ ይዘቱ ይጎላል፡፡ ፀሎት የሚደረግባቸው ቤተ መቅደሶች ትልልቅና ሰፊ ሲሆኑ፣ መልካም ምርት እንዲሰበሰብ የሚለማመኑበት ክፍል ከሁሉም የገዘፈ ነው፡፡ በቅርብ ርቀት የሚገኙት ላማ ቴምፕልና ሌሎችም ቤተ መቅደሶች ከተቀረው ቻይና የተለየ ፀጥታ የሰፈነባቸው ናቸው፡፡ በታቀደ ሁኔታ የተተከሉት ዛፎች ዮጋ ለመሥራት ወይም ሜዲቴት ለማድረግ ይጋብዛሉ፡፡

በቤጂንግ ነዋሪዎች ከሚስተዋለው ግለኝነት በተቃራኒው በነዚህ ቦታዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ይታያል፡፡ በእግር የሚጓዙ አዛውንት፣ ኩንግፉ የሚሠሩ ጎልማሶች፣ ዱብ ዱብ የሚሉ ወጣቶች፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚዝናኑ ልጆች ማየት መንፈስን ዘና ያደርጋል፡፡ ጎብኚዎች ላይም ስሜቱ ስለሚጋባ በነዚህ አካባቢዎች መሆን ያስደስታቸዋል፡፡

የቻይና የአበባ ፓርኮችም በተመሳሳይ ሁኔታ መንፈስ ዘና ያደርጋሉ፡፡ ለአበባ ብቻ ከተዘጋጁ ፓርኮች ባሻገር በየመንገዱ የአበባ ተክል መገኘቱን በተመለከተ ለአስጎብኚያችን ያቀረብነውን ጥያቄ የመለሰልን፣ ቻይኖች አበባን ከፍቅርና መልካም ስሜት ጋር እንደሚያያይዙት ነበር፡፡ ያስጎበኙን ግዙፍ የአበባ ፓርኮች ለጥንዶች የተመቹ ድልድዮች፣ ፏፏቴዎችና ሠርግ ማከናወኛም አላቸው፡፡ በተለይም ፀሐይ ለመጥለቅ ስትቃረብ ያለው ወጋገን ፓርኮቹን ውበት ይጨምርላቸዋል፡፡ በዓለም ላይ ካሉ ዕውቅ የአበባ ፓርኮች መካከል ተጠቃሽ የሆነው የቤጂንጉ ብሉስ ድሪም ላንድ 20 ሔክታር ይሸፍናል፡፡ በፍቅረኞች ቀን ፓርኩ በጥንዶች እንደሚጨናነቅም ይነገርለታል፡፡

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ቻይና የሚሄዱ ቱሪስቶች ከሚያዘወትሯቸው አካባቢዎች መካከል ኒንሻ ውስጥ የሚገኙ በረሀዎች ይገኙበታል፡፡ በእርግጥ ሰሀራ በረሀ በሚገኝበት አኅጉር ለተፈጠረ ሰው ቻይናውያን በረሀ ብለው የሚያስጎበኙት አካባቢ ባይዋጥለትም፣ ያላቸውን ለቱሪስት ማፍሪያነት መጠቀማቸውን ሳያደንቅ አያልፍም፡፡

ሻቹቱ በተባለው በረሀ ጎብኚዎች ለረዥም ሰዓት እንዲቆዩ በሚል በርካታ የመዝናኛ አማራጮች ቀርበዋል፡፡ በሽቦ ተንጠላጥሎ በረሀውን ከማቋረጥ አንስቶ ከበረሀው ከፍተኛ ቦታ ወደ ታች እስከ መንሸራተት ድረስ እንደየሰው ፍላጎት የሚሆን አማራጭ አለ፡፡ የበረሀውን ከፍታና ዝቅታ በአስገራሚ ፍጥነት በሚጓዙ የወታደር መኪናዎች ተሳፍሮ መጎብኘትም ይቻላል፡፡ በዕድሜ ለገፉ፣ የጀርባና የልብ ሕመም ላለባቸው ሰዎች የተከለከሉት እነዚህ የበረሀ ተሞክሮዎች እችላለሁ ብሎ የሚሞክራቸውን ሰውም መፈተናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም በሽቦ በመታገዝ በአየር ላይ የሚደረጉ ጉዞዎች የልብ ትርታ የሚጨምሩና ሀሞትን የሚፈትሹ ናቸው፡፡

ከሻፑቱ በተጨማሪ፣ ባዲያን ጃራን፣ ታክሊማከንና ጉዳባንቱጉት በቻይና ከሚገኙ በረሀዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከበረሀ ቆይታ አረፍ ለማለት ደግሞ ወደ ሔለን ማውንቴን ኢስተርን ፉት ሒልስ የወይን ፋብሪካ ማቅናት ይቻላል፡፡ ከቻይና ግዛቶች በብዛት ወይን የሚመረተው በሻንዶንግ ቢሆንም ኒንሻም ቻይና ለዓለም የምታበረክተው የወይን ምርት ምንጭ ናት፡፡ በዓለም የወይን ገበያ ስፔንና ጣሊያን ኤክስፖርት በማድረግ ግንባር ቀደምትነቱን ይይዛሉ፡፡

የኒንሻን የወይን ፋብሪካዎች ለየት የሚያደርጋቸው ታሪካዊ ዳራቸው ነው፡፡ ኒንሻ ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ138 ወይን ይጠመቅባቸው የነበሩ ቁሳቁሶች ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2001 ከሰባት ሺሕ እስከ ዘጠኝ ሺሕ ዓመታት ያስቆጠሩ የወይን ዘሮች በአርኪዮሎጂካል ሳይቶች ተገኝተዋል፡፡

ቤጂንግ ውስጥ ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን በርድስ ኔስት ስታድየምና የጥንታዊ ሥልጣኔ አሻራ ግሬት ዋል ኦፍ ቻይና በየአንጻሩ ይገኛሉ፡፡ 80 ሺሕ ሰው የሚያስተናግደው የቻይና ብሔራዊ ስታዲየም እ.ኤ.አ. በ2008 አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ ወደ 428 ሚሊዮን ዶላር ፈሶበታል፡፡ ዕውቁ የቻይና አርቲስት አይ ዌዌን ጨምሮ የአገሪቱ ታዋቂ አርክቴክቶችን ያሳተፈው ስታዲየሙ፣ እ.ኤ.አ. በ2022 የዊንተር ኦሊምፒክና ፓራሊምፒክስ ይካሄድበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለግንባታ በተመረጠው ግብዓት፣ በቅርጹና በሚሰጠው አገልግሎትም ዝናን ያተረፈውን ስታዲየም ስንጎበኝ፣ በተገነባበት ወቅት በተካሄዱ ውድድሮች የተሳተፉ አገሮች የሰፈሩበትን የክብር ግርግዳም ተመልክተናል፡፡ ለጎብኚዎች ምቹ ከሆነው ስታዲየም ጀርባ መጠነኛ ፓርክ ይገኛል፡፡ የስታዲየሙን ግንባታ ጥበብ አድንቀው በተፈጥሮው መንፈስ ማደስ ይቻላል፡፡

የጥንታዊ ቻይና መገለጫ ወደ ሆነው ግሬት ዋል ኦፍ ቻይና የሚሄዱ ጎብኚዎች በርካታ ስለሆኑ በዝግታ በቅደም ተከተል መሄድ ግድ ይላል፡፡ ቻይናን ከወራሪዎች ለመከላከል በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሠራው ግንብ፣ በበለጠ ገናና የሆነው በሚንግ ስርወ መንግሥት በነበረው ግንባታ ነው፡፡ በሚንግ ስርወ መንግሥት የተሠራው የግንቡ ክፍል 359 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ አጠቃላይ ግንቡ 21,196 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡

ሙሉ ግንቡን ለመጓዝ ቀናት ቢወስድም፣ ተጓዥ አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ የግንቡን ደረጃዎች መውጣት ይችላል፡፡ ስለ ግንቡ በመጠኑም ቢሆን የማያውቅ ባይኖርም፣ በዕውን ቦታው ላይ መገኘት ታሪኩን ከማወቅ በዘለለ ሐሴት ይሰጣል፡፡ ከአንዱ ደረጃ ወደ ቀጣዩ ሲሸጋገሩ ቤጂንግ ወለል ብላ ትታያለች፡፡ የግንቡን ዙሪያ መቃኘት የሚችሉበት ነጥብ ላይ ሲደርሱ ምንም እንኳን ሰውነት ቢዝልም በግንቡ የአሠራር ጥበብ ይደመማሉ፡፡ ከመላው ዓለም ለማለት በሚያስችል ደረጃ ብዙ ሺዎች ግንቡን ለማየት ሲሉ ብዙ ማይሎች አቆራርጠው ቻይና ይገኛሉ፡፡ ሕፃናትና አዛውንት አቅማቸው እስከቻለ ድረስ ደረጃውን ሲወጡ ተመልክተናል፡፡

ፈታኙን ደረጃ ለመወጣት ኃይል ማሰባሰቢያ የሚሆኑ ማረፊያ ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ምግብና መጠጥም ይሸጣል፡፡ ጎብኚዎች እርስ በርስ ባይተዋወቁም ውኃ ሲቀባበሉና ሲደጋገፉ ማየት በመካከላቸው ያለውን በቃላት የማይገለጽ አንድነት ያሳብቃል፡፡ በተለይም ከትውልድ አገራቸው የመጣ ሰው ሲያገኙ የሚደሰቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ተጓዦች ግንቡን ወጥተው ሲመለሱ በስማቸው ሜዳሊያ ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል፡፡ ግሬት ዋልና ሌሎችም የቻይና መስህቦችን ትውስታ ወደየአገራቸው ይዘው የሚመለሱበት መንገድ ነው፡፡

ቻይና በየፈርጁ እንግዶቿ ሊደሰቱባቸው የሚችሉ መስህቦቿን አቅርባለች፡፡ መዳረሻዎቹ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ የአገሪቱ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየአካባቢው የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ቻይና የተፈጥሮ ሀብት፣ ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ ቴክኖሎጂና ባህል በቂ አይደለም በሚል ዛሬም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ከመወጠን ወደኋላ አትልም፡፡ በቻይና ቱሪዝም የማይሸጥ ነገር የለም ያስብላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...