–ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት አገሮች ምክክር አካሂደዋል
ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች አገር ሆና በተመሠረተች ማግሥት በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውና ለስደት መዳረጋቸው ከእንግዲህ መቆም አለበት ያሉ የአገሪቱ ወጣቶች፣ ለሰላምና ለመረጋጋት የተደራጀ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀመሩ፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተገኙት የደቡብ ሱዳን ወጣቶች በአገራቸውና ከአገር ውጪ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ፣ በመንግሥታዊ መዋቅሮች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በተለያዩ ሲቪክ ማኅበራት ውስጥ በማገለግል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ሙዚቀኞችና በሌሎች ሙያዎች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የተወከለቡት የደቡብ ሱዳን ወጣት መሪዎች ፎረም የተባለ የሲቪክ ማኅበር በመመሥረት መንቀሳቀስ የጀመሩት በጥር ወር ሲሆን፣ ለአንድ ወር ያህል ድንበር ተሻጋሪ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ ከሚመለከታቸው የቀጣናው አገሮች ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች ጋር ሲነጋገሩ መቆየታቸው ታውቋል፡፡
በኬንያና በኡጋንዳ የነበራቸውን ቆይታ በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ወጣቶቹ፣ አዲስ አበባ ከሚገኙ የውጭ ዲፕሎማቶችና የአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ተወካዮችና እንደ ኦክስፋም ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችም ጋር መክረዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ዕጣ ፈንታ ያሳስበናል ያሉት ወጣቶቹ በአሥር አደራጆች 70 ወጣቶችን በማካተት የጀመሩት የወጣቶች ፎረም፣ ከፖለቲካና ከብሔር ተኮር አመለካከቶች ራሱን በማግለል፣ ሁሉንም ደቡብ ሱዳናዊ ያማከለ የጋራ ስምምነት እንዲፈጠር የሚንቀሳቀስ አካል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የእስካሁኑ ይብቃ፡፡ ከእንግዲህ ዝም አንልም፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ወገን ከአገራችን አይበልጥም፤›› የሚሉ መልዕክቶችን ያስተላለፉት ወጣቶቹ፣ በደቡብ ሱዳን የጦርነት ቁያ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን ሚና ተችተዋል፡፡
ትችት ከቀረበባቸው ተቋማት አንዱም ኢጋድ ሆኗል፡፡ ኢጋድ መንግሥትና ተቃዋሚ ወገኖችን ለማደራደር የተከተላቸው አካሄዶች ችግር እንደነበረባቸው በመግለጽ፣ ከእንግዲህ ቤት አፈራሽ መፍትሔ ያስፈልጋል በማለት በዚሁ አግባብም መላውን የደቡብ ሱዳን ወጣቶች በማስተባበር ጦርነቱን በማስቆም ዕርቅ የማውረድ ዓላማ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
‹‹ደቡብ ሱዳንን ማዳን›› ወይም ‹‹ኪዩር ሳውዝ ሱዳን›› በሚል መርህ መንቀሳቀስ ከጀመሩት ወጣቶች መካከል፣ የደቡብ ሱዳን ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር፣ ጠበቃ እንዲሁም ተሟጋች የሆነው ቤኒ ጌዲዮን ማቦር ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፣ አገሪቱ 830 ፐርሰንት የደረሰ የዋጋ ግሽበት ውስጥ ትገኛለች፡፡
ከአገሪቱ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በጦርነት ጦስ ለስደት ሊዳረግ የሚችልበት ሥጋት መደቀኑን የጠቆመው ማቦር፣ ገበሬዎች ማምረት ባለመቻላቸው ማሳዎች ጦም ማደራቸውን፣ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ከማሻቀቡም በላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልቁል እየተንደረደረ፣ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ወደ መፈራረሱ መቃረቧን አስጠንቅቋል፡፡ ይህ እንዳይሆን የደቡብ ሱዳን ወጣቶች ስለአገራቸው ሰላምና መረጋጋት መምከር እንዲጀምሩ ጠይቋል፡፡ አብረውት አዲስ አበባ የከረሙ የወጣቶች ፎረም አባላትም የጦርነት በቃን ጥሪያቸውን አሰምተዋል፡፡
በኬንያ፣ በኡጋንዳና በኢትዮጵያ ያካሄዷቸውን የምክክር መድረኮች ካጠናቀቁ በኋላ በጁባ ከተማ አገር አቀፍ ስብሰባ በመጥራት ለወመያየት እንዳቀዱ የገለጹት ወጣቶቹ፣ በስብሰባቸው ሁሉንም ወገን ያካተተ ጉባዔ እንደሚጠሩም አስታውቀዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ከምሥረታዋ ማግሥት ጀምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ጎረቤቶቿ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የንግድ ተፈላጊነት ነበራት፡፡ በተለይም ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ እንደምትገባ ስትጠበቅ የነበረችውና ራምሴ የሚል ስያሜ እንደሚሰጣት ሲነገርላት የነበረችው አዲሲቷ የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ፣ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋ የተጣለባት ነበረች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ የተገኘው ነዳጅ ለኢትዮጵያ ሌላኛው የተስፋ ምንጭ ነበር፡፡ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሊዘረጋ የሚችል የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ዕቅድ መውጣት በጀመረበት ወቅት፣ አገሪቱ ማባሪያ ወዳልተገኘለት የእርስ በርስ ጦርነት መግባቷ በርካታ ውጥኖችን በነበር እንዲቀሩ አስገድዷል፡፡