Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሚኒስትሮች ምክር ቤት አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲዋሀዱ ወሰነ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲዋሀዱ ወሰነ

ቀን:

  • የኤርፖርቶች ድርጅት ሆቴሎች በአቪዬሽን ቡድን ይታቀፋሉ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አየር መንገድንና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን ለማዋሀድ የቀረበውን ረቂቅ ደንብ ዓርብ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡

የውህደት ሐሳቡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተረቆ በትራንስፖርት ሚኒስቴር አማካይነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ታውቋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አመራሮች ጋር በመሆን፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሠራተኞችን እሑድ ሐምሌ 9 ቀን በድርጅቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሰብስበው ስለውህደቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ አህመድ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው ፉክክር እየጠነከረ መምጣቱን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ተቋቁሞ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ አየር መንገዶች የሚወዳደሩት በሚሰጡት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በኤርፖርቶቻቸውም ጭምር መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም እያስመዘገበ ካለው ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚፈልገው የኤርፖርት መሠረተ ልማትና የኤርፖርት አገልግሎቶች እየሰፉ እንደመጡ ጠቁመዋል፡፡

የአየር መንገዱን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር የኤርፖርት አገልግሎቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳደግ በማስፈለጉ አዲስ አደረጃጀት መተግበር አስፈላጊ እንደሆነ እንደታመነበት ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኤርፖርት መሠረተ ልማቶች በመላ አገሪቱ ለማዳረስ ላደረገው ጥረት መንግሥት ዕውቅና እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ አህመድ፣ ሆኖም በኤርፖርት አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን መንግሥት አዲስ አደረጃጀት ለማዋቀር ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ቡድን በአዋጅ ሲቋቋም በሥሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ይታቀፋሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ ቦርድ የሚተዳደሩ ሲሆን፣ የጋራ መርሐ ግብር ይኖራቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ድርጅቶች የየራሳቸው መለያ ብራንድና የንግድ ምልክት ይዘው ይቀጥላሉ፡፡ ሽግግሩ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ መድረኩን ለጥያቄ ክፍት ሲያደርጉ፣ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሠራተኞች በዋነኛነት የቀረበው ጥያቄ ከሥራ ዋስትና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የሠራተኞች የአገልግሎት ክፍያ እንዴት እንደሚሆን ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የኤርፖርት አገልግሎት ለማሻሻል ሲታሰብ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጀት ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ኤርፖርት ጉምሩክ፣ ኤርፖርት ኢምግሬሽንና ደኅንነት የመሳሰሉ መሥሪያ ቤቶችን አሠራር አብሮ ማዘመን ወሳኝ ስለሆነ በዚህ በኩል ምን የታሰበ ነገር አለ የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ የውህደቱ ዓይነት ግልጽ አይደለም የሚል አስተያየትም ተሰንዝሯል፡፡

ከሠራተኞች ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ አህመድ የሠራተኛ ቅነሳ እንደማይኖር ገልጸው፣ በማኔጅመንት አካባቢ ግን የተወሰነ ሽግሽግ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ አጋር መሥሪያ ቤቶችን አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በኤርፖርት ጉምሩክ አሠራር ላይ ጥናት ተሠርቶ ለሚኒስቴሩ መቅረቡን ገልጸው በቀጣይ በኢምግሬሽንና በደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ላይ በጋራ የተቀናጀና የተቀላጠፈ አሠራር እንዲኖር የሚያስችል ተመሳሳይ ጥናቶች ይሠራሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት የሠራተኛው የሥራ ዋስትና እንደማይነካ ገልጸው፣ ሠራተኞች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ የውህደቱ ዝርዝር ሁኔታ ወደ ተግባር ሲገባ እንደሚገለጽ አቶ ዳዊት አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በበኩላቸው፣ የአየር መንገዱም ሆነ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ህልውና በማኔጅመንቱና በሠራተኛው እጅ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ህልውናችን የሚገኘው በእጃችን ነው፡፡ ሁላችንም ተባብረን ጠንክረን ከሠራን የጀመርነውን የዕድገት ጉዞ ማስቀጠል እንችላለን፡፡ ተባብረን ጠንክረን መሥራት ካልቻልን ሁላችንም ተያይዘን እንጠፋለን፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ተወልደ ለአንድ ኩባንያ ውድቀት ማኔጅመንቱ 80 በመቶ፣ ሠራተኛው 20 በመቶ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ገልጸው ሁሉም ሠራተኛ ተባብሮና ጠንክሮ እንዲሠራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

እንደ አዲስ የሚቋቋመው የአቪዬሽን ቡድን የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ድርጅት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማስገንባት ላይ ያለውን ባለ አራት ኮከብ ሆቴልና ሌሎች የመንግሥት ሆቴሎችን ተረክቦ እንደሚያስተዳድር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2025 የተባለ የ15 ዓመታት የዕድገት መርሐ ግብር ነድፎ ሥራ ላይ ማዋል ከጀመረ እ.ኤ.አ. 2010 ጀምሮ አምስት እጥፍ ማደጉ ይነገራል፡፡ አየር መንገዱ ከአፍሪካ ግዙፍ የሚባሉትን የግብፅና የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶችን በመብለጥ ከአፍሪካ ትልቁና ትርፋማ አየር መንገድ መሆኑን፣ የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማኅበር እ.ኤ.አ. በ2014 ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 86 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤትና 95 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት፡፡ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ብዛት ከ12,000 በላይ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በበኩሉ በ2025 ከአፍሪካ ምርጥ የኤርፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን ግብ አስቀምጦ፣ በርካታ የኤርፖርት ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ በ350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማስፋፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን በክልል በሰመራ፣ በሐዋሳ፣ በሽሬ፣ በባሌ ሮቤ፣ በደምቢዶሎና በነቀምቴ ከተሞች ኤርፖርቶች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ 23 ኤርፖርቶች ሲያስተዳድር፣ አራቱ ዓለም አቀፍ ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...