Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኦሮሚያ ክልል ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ የግብር መክፈያ ቀኑ ተራመዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል ከሳምንት በፊት ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ፣ ግብር ለመክፈል ተቀምጦ የነበረው የመጨረሻ ቀን መራዘሙን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር ተያይዞ በክልሉ በተነሳው ተቃውሞ የግብር መክፈያ የመጨረሻ ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ መራዘሙን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የመጨረሻ የግብር መክፈያ ቀን ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፣ በክልሉ ውስጥ የቀን ገቢ ግምት ሥራ በሚሠራበት ወቅት ገማቾች አካባቢ ጉድለት ስለነበረና በነጋዴዎች ዘንድ የፍትሐዊነት ችግር በመነሳቱ፣ ይኼንን ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ ሲባል የአሥራ አምስት ቀናት ጭማሪ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ተመሳሳይ ንግድ ላይ ተሰማርተው ግን ደግሞ በገማች ኮሚቴው ዘንድ ፍትሐዊ ያልሆነ አሠራር እንደነበሩ የክልሉ መንግሥት መገምገሙንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረትም ነጋዴዎች ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ከላይ እስከ ታች የቅሬታ ማቅረቢያ መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡

በነጋዴዎች ዘንድ ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር በተያያዘ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ ይኼንን ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከክልሉ የንግድ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ወሊሶ ከተማና አካባቢ ካሉ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ለማ ከምዕራብ ሸዋና ከወሊሶ አካባቢ ከተወጣጡ 700 ከሚሆኑ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ጋር ውይይት እንዳደረጉ፣ የውይይቱ ዋነኛ ዓላማም ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያይዘው የተነሱ ቅሬታዎች የሚፈቱበትን ዘዴ ለማበጀት እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ይኼ የቀን ገቢ ግምት ዝቅተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል መሠረት ያላደረገ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን የሚጎዳ ከሆነ፣ መታየት እንዳለበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ፍትሐዊነትና ከግምት አንፃር ክፍተቶች ካሉ ማየት አለብን፤›› በማለት የክልሉ መንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጡንም አስረድተዋል፡፡

ለፕሬዚዳንቱ በርካታ ጥያቄዎች እንደቀረቡላቸው የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣  የነጋዴዎችን ጥያቄ ለመመለስ የክልሉ መንግሥት ሌት ተቀን እንደሚሠራ ቃል እንደተገባላቸው ተናግረዋል፡፡

ከተጠየቁ ጥያቄዎች መካከል የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ ወደ ዩኒቨርሲቲ ይሸጋገርልን፣ ሆስፒታል በአፋጣኝ ይገንባልን፣ የተጀመሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ይፋጠኑልን፣ ወሊሶ አካባቢ ያለው ኢንቨስትመንት ፍትሐዊ አይደለም የመሳሰሉ ጥያቄዎች እንደሚገኙበት አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ወሊሶንና አካባቢውን በሚችለው አቅም ለማልማትና እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ቃል እንደተገባ ጠቅሰዋል፡፡

ከጥልቅ ተሃድሶው ጋር በተያያዘ በወሊሶ ማኅበረሰብ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እየሠሩ እንዳልሆኑ፣ ሌሎች አመራሮች እንዲሾሙ ጥያቄ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርም በሕዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሥራ እንደሚከናወን፣ አቅም የሌላቸውንና የሕዝብን ጥያቄ በተገቢው መንገድ ተቀብለው ምላሽ የማይሰጡ አካላትን የማንሳት ሥራ እንደሚሠራ ቃል የገቡላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በወሊሶ፣ በአምቦ፣ በጊንጪ፣ በጀልዱ ወረዳ፣ በግንደበረት፣ በነጆና በቡራዩ ከተሞች የሚኖሩ ነጋዴዎች የንግድ ተቋማቸውን ዘግተው መሰንበታቸውንና በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ መንገድ የመዝጋት አዝማሚያ እንደነበር አቶ አዲሱ አስታውሰዋል፡፡ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ እንደሌለ ገልጸው፣ በአምቦና በጊንጪ ከተሞች በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

በወሊሶ ለሁለት ቀናት፣ በአምቦና በጊንጪ ከተሞች ለሦስት ቀናት የዘለቀ ተቃውሞ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉም ከተሞች ወደ ሰላማዊ የንግድ ሥራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች