Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የኤክስፖርት ገቢ ሳያድግ ከውጭ መበደር ተቆጥቧል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ብድር ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማሻቀቡና ይህንን ብድር ለመክፈል የሚያስችለው የኤክስፖርት ገቢ በታሰበው መጠን ባለመገኘቱ፣ ብድር ለመክፈልም ሆነ ተጨማሪ ለመበደር እንቅፋት መፍጠሩ ተገለጸ፡፡ በ2010 በጀት ዓመት ግን ከኤክስፖርት ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ተስፋ በመደረጉ፣ የአገሪቱን ዕዳ በማቃለል ተጨማሪ ለመበደር ግን ዕቅድ ተይዟል፡፡

የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. የአገሪቱን የብድር ጫና በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አገሪቱ ከውጭ የተበደረችው የሚከፈለው በውጭ ምንዛሪ እንደሆነ፣ በብድሩ ልክ ግን ኤክስፖርት እንደሚፈለገው ባለመጨመሩ ተጨማሪ ብድሮችን መበደር ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ግንዛቤ መወሰዱን አስረድተዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ኤክስፖርት ማሳደግ ማለት በጣም በጣም ወሳኝ ግብ ነው ብለን እየሠራን ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ጨምረው እንዳስረዱት፣ የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከሌሎች መለኪያዎች አንፃር ሲታይ ግን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

‹‹ይህች አገር የወሰደችው ብድር ከአገር ውስጥ ምርት ዕድገት (GDP) አንፃር ሲታይ፣ ከመንግሥት ገቢ (ታክስና ታክስ ያልሆኑ ገቢዎች) አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ሥጋት የለም፤›› በማለት አገሪቱ በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ አገሮች ጭምር በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ ነው፡፡ ባለበት የቆመ ኢኮኖሚ አይደለም፡፡ የብድር ጫና አደገኛ የሚሆነው ኢኮኖሚ አንድ ቦታ ላይ ሲቆም ነው፤›› በማለት ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ‹‹ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በፍጥነት እንደሚያድግ ተንብየዋል፤›› በማለት አገሪቱ የዕዳ ጫና ሥጋት እንደሌለባት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ብድር ከውጭ ተወስዶ ለምን ዓላማ ዋለ? የሚለው ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚወስዷቸው ብድሮች ናቸው እየጨመሩ የመጡት፡፡ ኢትዮጵያ የተበደረቻቸው የውጭ ብድሮች በሙሉ ለመሠረተ ልማት ግንባታና ኤክስፖርት ለሚደግፉ ኢንቨስትመንቶች የዋሉ ናቸው፡፡ የውጭ ብድሮችን በእነዚህ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ማዋል ብድሩን መልሶ ለመክፈል ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል፡፡ ግንባታዎቹም የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ከፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የመክፈል አቅም በሚያሳድጉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ነው ብድሩ የዋለው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ለ2010 በጀት ዓመት የተመደበው 320.8 ቢሊዮን ብር በጀት ያለበትን የ53 ቢሊዮን ብር ጉድለት ለመሙላት የሚወሰደው ብድር ግን ጫና የሌለበት እንደሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለበጀት ጉድለቱ የምንወስደው ብድር ዝቅተኛ ወለድና በረዥም ጊዜ የሚከፈል (ኮንሴሽናል) ብድር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት በአጠቃላይ 119.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ለግብርና፣ 35.9 ቢሊዮን ዶላር ለኢንዱስትሪ፣ 49.8 ቢሊዮን ዶላር ለአገልግሎት፣ 15.3 ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዢ፣ 7.2 ቢሊዮን ዶላር ለዕዳ ክፍያ፣ 3.8 ቢሊዮን ዶላር  ለውጭ ምንዛሪ ክምችት፣ እንዲሁም 2.8 ቢሊዮን ብር ለሕጋዊ የገንዘብ ዝውውርና ለውጭ ምንዛሪ ሒሳብ ደረሰኝ እንደሚውሉ ድልድል ተሠርቶ ታቃዷል፡፡

ዕቅዱ እንደሚያመለክተው ከወጪ ንግድና ከአገልግሎት ዘርፍ፣ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሚላክ ገንዘብ፣ ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) እና ከውጭ ብድር 115.3 ቢሊዮን ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ ታቅዷል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ቢሆኑም፣ በየዓመቱ ከኤክስፖርት የተገኘው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መድረስ እንዳልቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

መንግሥት በዕቅድ ዘመኑ ከግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ላሉት ግዙፍ ዕቅድ በርካታ መሠረተ ልማቶችና በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት ውጥን ይዟል፡፡ እነዚህን ግንባታዎች ለማካሄድ አገሪቱ ከፍተኛ ብድር የተበደረችና ለመበደርም ዝግጁ የሆነች ብትሆንም፣ የአገሪቱ ኤክስፖርት ይህንን ዕቅድ በሚገባ መደገፍ አለመቻሉ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

በዚህ መሠረትም አበዳሪዎች ለማበደር ያላቸው ፍላጎት እንዲቀንስ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ የፌዴራል መንግሥት ኤክፖርት ሳያሳድግ በተጨማሪ ብድር የዕዳ ጫና ውስጥ መግባት አደጋ ሊያስከትል ይችላል በማለት ጠንከር ያለ ወለድ ካላቸው ብድሮች ራሱን አቅቧል፡፡

ሚኒስትሩ ግን በ2010 ዓ.ም. ይህ እንደሚቀየር ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም የግብርና ምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት የሚገኝበትና በግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ላይ የነበሩ ማነቆዎች የተፈቱ በመሆኑ፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በሰፊው ኤክስፖርት ስለሚጀምር የሚቀጥለው ዓመት የተሻለ እንደሚሆን ምክንያታቸውን አቅርበዋል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ይፋ ባያደርገውም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በአጠቃላይ በሚቀጥለው ዓመት ስምንት ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ታቅዷል፡፡ ይህ በአሁኑ ወቅት እየተገኘ ካለው ከሦስት እጥፍ በላይ ስለሚሆን፣ የተስተጓጎለው የውጭ ብድር እንዲለቀቅ የማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚኖረው እየተገለጸ ነው፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች