Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በቀን ገቢ ግብር ግመታ ያጋጠሙ ችግሮችን በውይይትና በመግባባት እንፈታቸዋለን የሚል እምነት አለኝ››

አቶ ከበደ ጫኔ፣ በሚኒስትር ማዕረግ

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

ከ18 ዓመታቸው ጀምሮ በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ የደርግ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ ደግሞ ለ15 ዓመታት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉ የካቢኔ ጉዳዮችና የአቅም ግንባታ ሞቢላይዜሽን ኃላፊ፣ የክልሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ አቶ ከበደ ጫኔ፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሰላምና ፀጥታ (Peace and Security) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ አቶ ከበደ ወደ ፌዴራል መንግሥት ተዛውረው ለአራት ዓመታት የንግድ ሚኒስትር ሆነው ከሠሩ በኋላ በ2009 ዓ.ም. ለተወሰኑ ወራት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ከበደ፣ በአሁኑ ጊዜ በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. መጀመሪያ ጀምሮ ተግባራዊ ከተደረገው የቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ቅሬታውን እያሰማና ብሶቱን እየገለጸ ይገኛል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ የቀን ገቢ ግምቱ ፍትሐዊ አይደለም በማለት በክልሎች ሥራ ማቆምና ግጭቶችም ታይተዋል፡፡ በንግድ ማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረውን የቀን ገቢ ግምትና ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት ታምሩ ጽጌ አቶ ከበደን አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከሚያዝያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ መረጃ መሰብሰቡን በመግለጽ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ተግባራዊ እያደረገው የሚገኘው የቀን ገቢ ግምት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል፡፡ ተገቢ የሆነ መረጃ ሰብስቦ ወደ ሥራ የገባ ከሆነ ተቃውሞ የገጠመው ለምንድነው?

አቶ ከበደ፡- የቀን ገቢ ጥናት የተደረገው በአገር አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ ክልሎችን በሚመለከት ጥናቱን በየሦስት ዓመቱ ያካሂዱ ስለነበር ያን ያህል የተፈጠረ ችግር የለም፡፡ በአዲስ አበባ ግን ላለፉት ስድስት ዓመታት ጥናቱ ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ኢኮኖሚው ደግሞ ባለፉት ስድስት ዓመታት ይብዛም ይነስም እያደገ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ያመጣው የንግድ ሥርዓቱ ሽግሽግም አለ፡፡ በፊት ደረጃ ‹‹ሐ›› የነበረ ሰው፣ ባደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ወደ ላይ ያደገ አለ፡፡ በንግድ እንቅስቃሴ ብቃት ማጣትም ወደ ታች የወረደም አለ፡፡ ሁለቱም ገጽታዎች የተፈራረቁበት ነው፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት የግብር ከፋዮችን የቀን ገቢ ግምት ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን አመላከተን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በ2008 ዓ.ም. ግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ በሚያሳትፍ አኳኋን መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ በሙሉ ውይይት ተደርጎባቸው ግብዓቶች የተሰባሰቡበት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ እነዚያ ግብዓቶች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ከታዩ በኋላ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆች ፀድቀው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ በአዋጆቹ የግብር ከፋዩ ደረጃዎች ተሸጋሽገዋል፡፡ የደረጃ ‹‹ሐ›› የመጨረሻ ጣሪያው 100,000 ብር ነበር፡፡ አዲስ በወጡት አዋጆች ይህ ደረጃ ተሻሽሎ እስከ 500,000 ብር ሆኗል፡፡ ደረጃ ‹‹ለ›› ደግሞ እስከ 100,000 ብር የነበረው ከ500,000 ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ደረጃ ‹‹ሀ›› ደግሞ ከ500,000 ብር በላይ የነበረው አሁን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ አዋጁ የደረጃ መሠረቱን ስለቀየረው፣ የንግዱ ማኅበረሰብ የት ላይ እንዳለና የት እንደደረሰ ማጥናት ያስፈልግ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የሒሳብ መዝገብ የማይዙት የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮችንና የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮችን ማጥናት የግድ ይላል፡፡ የደረጃ ‹‹ለ›› እና ‹‹ሀ››ን በሚመለከት የቀን ገቢ ግብር አያስፈልጋቸውም፡፡ ምክንያቱም በሒሳብ መዝገባቸው ይዳኛሉ፡፡ ሕጉም ያስገድዳቸዋል፡፡ የሒሳብ መዝገብና ካሽ ሬጅስተር ማሽን ስላላቸው ጥናት ይካሄድ ቢባል እንኳን መነሻ አላቸው ማለት ነው፡፡ ሐሰተኛ ሰነድ ያሳትማሉ ተብሎ የሚጠረጠሩ ከሆነና ወይም ካሽ ሬጅስተር ማሽን በአግባቡ አይጠቀሙም የሚባል ከሆነ፣ ወይም ታክስ ወይም ግብር ያጭበረብራሉ ከተባለ፣ ግምቱ እነሱም ላይ ሊሠራ ይችላል፡፡ ዋናው ግን የደረጃ ‹‹ሐ›› በመሆኑ ያደገውንና የወረደውን ለመለየት ጥናት በማስፈለጉ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ ለጥናቱም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ መመርያዎች እንዲቀረፁ አድርገናል፡፡ መሥፈርቶች እንዲለዩ አድርገናል፡፡ በጥናቱ ደንበኞች ሳያውቁ መረጃዎች እንዲሰበሰቡና የማጥራት ሥራዎች እንዲከናወኑ ተደርጓል፡፡ የቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ ምን መሆን አለበት የሚለውንም ዓይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ያሰባሰባችሁት መረጃ ቅሬታ እንደሚያስነሳ አስቀድማችሁ ታውቁ ነበር ማለት ነው?

አቶ ከበደ፡- የግምት ሥራ ስለሆነ የምንሠራው ቢጋነን ወይም ቢያንስ ቅሬታ ሊነሳ እንደሚችል እናውቅ ነበር፡፡ ይህንን ለመፍታት የሚያስችል የቅሬታ አፈታት ሥርዓት ከላይ እስከ ታች ማደራጀት ያስፈልግ ነበር፡፡ የገማች ኮሚቴዎች፣ የሱፐርቪዥን ኮሚቴዎች የኢንስፔክሽን ኮሚቴዎች እንዲደራጁ አድርገን ከ2,300 በላይ የሰው ኃይል ከየሴክተሩ በማደራጀት፣ ሥልጠና ሰጥተን አሰማርተናል፡፡ ይህ የሚያሳየው ብዙ ድካም እንደነበረ ነው፡፡ ይህንን ሥራ ካከናወን በኋላ በተቻለን መጠን በመንግሥት ደረጃና በእኛም ተቋም ዋናው ግብር የሚሰበስበው የተሻለ ሀብት ካለው መሆኑ ይታመናል፡፡ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ የተሰማራው በዝቅተኛው ደረጃ ‹‹ሐ›› ነው፡፡ እስከ 500,000 ብር ገቢ ያለው ቢሆንም፣ በአብዛኛው 100,000 ብር ገቢ ያለው ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል የምንሰበስባቸው ገቢዎች ይህንን ያህል ትልቅ ናቸው የሚባሉ አይደሉም፡፡ ምናልባት በድምር ሲወሰድ ከአዲስ አበባ ገቢ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍኑ ናቸው፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው ገቢ የሚሰበስበው የሒሳብ መዝገብ ከሚይዙትና ካሽ ሬጅስተር ማሽን ከሚጠቀሙት ደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› የንግዱ ማኅበረሰብ ነው፡፡ በደረጃ ‹‹ሐ›› ያለው የገቢ ግብር ትንሽ ቢሆንም፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ግብር ሥርዓቱ መግባት አለበት፡፡ አንዱ ሕገወጥ ሌላው ሕግ አክባሪ የሚሆንበት ሥርዓት መኖር የለበትም፡፡ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ ‹‹ግብር መክፈል አለብኝ›› ብሎ ከሚያገኛት የቀን ገቢ መክፈል የሚገባውን መክፈል አለበት የሚል አስተሳሰብ ነው እንጂ፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ኅብረተሰብ ላይ ግብር በመጫን ገቢ ይገኛል ተብሎ አይደለም፡፡ ወደ መሠረታዊ የግብር ሥርዓት ማስገባት ግን መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ሥራው ግምት በመሆኑ፣ በግምት ሥራ ላይ ስህተቶች ያጋጥማሉ፡፡ አንዱ አጋኖ ሊገምት ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ አሳንሶ ሊገምት ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ያሳነሰውንም ሆነ የተጋነነውን በማስተካከል፣ ትክክለኛና የተቀራረበ ግምት በመገመት እንዲከፍሉ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሚደረገው ደግሞ ከግብር ከፋዩ ጋር በመቀራረብና በመወያየት ነው፡፡ እዚህ ላይ የነበረው ችግር፣ መጀመሪያ የግብር ጥናት ይካሄዳል ሲባል የመበርገግ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ሱቅ ዘግቶ መጥፋት፣ ኃላፊነት የማይወስዱ ሕፃናትን ጠባቂ አድርጎ መጥፋት፣ የሉም ብሎ ዕቃዎችን ማሸሽ ዓይነት ዝንባሌዎች ነበሩ፡፡ ይህ ለግብር ከፋዩ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ጥሩ ይሆን የነበረው ‹‹ዕለታዊ ሽያጬ ይህንን ያህል ነው፡፡ ሱቄም እንደምታዩት ነው፡፡ በራሴ ሒሳብ የምይዘው ይህ ነው፡፡ አማካይ ገቢዬ ይህ ነው፤›› ብሎ ተከራክሮ በግልጽ ማሳወቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ግብር ከፋዩ የመደበቅ አቅጣጫ ሲከተል፣ ገማች ኮሚቴውም አልፎ አልፎ ሱቅ ዘግተው በተገኙት ላይ እንደ ጎረቤቶቻቸው ገምተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የተሳሳተና የተራራቀ ግምት ሊሆን ይችላል፡፡ በሌሉበት የቀን ግምቱ ከተገለጸላቸው በኋላ በርካታ ቅሬታዎች መጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ቅሬታዎች ቀረቡ?

አቶ ከበደ፡- ጠቅላላ በአዲስ አበባ ከተማ የተጠኑት 148,000 አካባቢ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቅሬታ ያቀረቡት 47,000 አካባቢ ናቸው፡፡ ከ100,000 በላይ የሚሆኑት ቅሬታ ቢኖርም እንኳን የቀረበላቸው ግምት ተቀራራቢ መሆኑን በመረዳት ግምቱን ተቀብለውታል፡፡ ቅሬታ ካቀረቡት 47,000 ሰዎች ውስጥ እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የተስተናገዱት 18,000 አካባቢ ናቸው፡፡ ቅሬታቸው ከታየላቸው ውስጥ 5,000 የሚሆኑት ግብር ከፋዮች የተሰጣቸው ግምት ተሻሽሎላቸዋል፡፡ ከቀሪዎቹ ጋር በመነጋገር የቀረበባቸው ግምት ትክክል መሆኑን መተማመን ላይ ተደርሶ ፀንቶባቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ የደረጃ ‹‹ሐ››› ካጠናቀቅን በኋላ፣ የደረጃ ‹‹ለ›› እና ‹‹ሀ›› ይስተናገዳሉ፡፡ በአድልዎ የተፈጸመ ነገር ካለም ይስተካከላል፡፡

ሪፖርተር፡- ቅሬታዎቹ ሲቀርቡ በገማቾቹ ላይ የወሰዳችሁት ዕርምጃ ወይም የአሠራር ማስተካከያ አለ?

አቶ ከበደ፡- ከቅሬታዎቹ በኋላ ያስቀመጥናቸው አራት አቅጣጫዎች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኅብረተሰቡ በብዛት ቅሬታውን እያቀረበባቸው ያሉ በዝቅተኛና በአነስተኛ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ላይ የተወሰደው ግምት ከፍተኛ ጫጫታ አስነስቷል፡፡ ‹‹እነሱ ራሳቸው በልተው ካደሩ በቂ አይሆንም ወይ? ለምንድነው እነሱ ላይ ይህንን ያህል ግምት ሚጫነው?›› የሚሉ ተደጋጋሚ ስሞታዎች ከኅብረተሰቡ ሰምተናል፡፡ ከዚህ አኳያ በዝቅተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩት ዘርፋቸው ተለይቶ በተለይ የጀበና ቡና፣ የጉልት ንግድ፣ ትናንሽ የችርቻሮ ንግድ፣ የፀጉር ሥራ፣ የልብስ ስፌት፣ ፑል ቤትና በሌሎች ጥቃቅን የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እነሱ ያመኑበትን እንዲከፍሉ የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡ ያላግባብ የተጫነባቸው ካሉ እንዲነሳላቸው አቅጠጫ አስቀምጠን እየታየ ነው ያለው፡፡ ይህ የተደረገውም እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ችለው በልተው ካደሩ፣ የመንግሥትንም ሸክም ማቃለል የሚችሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ትንሽም ቢሆን ከሚያገኙት ገቢ በራሳቸው እምነት በመክፈል ወደ ታክስ ሥርዓቱ መግባት አለባቸው፡፡ ይህንን አቅጣጫ ይዘን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የያዝነው የደረጃ ለውጥ ያደረጉ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ከ‹‹ሐ›› ወደ ‹‹ለ›› እና ከ‹‹ለ›› ወደ ‹‹ሀ›› የተሸጋገሩ አሉ፡፡ በተለይ ደረሰኝ የማይገኝላቸው የንግድ መስኮች ላይ አስቸጋሪ የሆኑ፣ ሲገመትላቸውም ባልተሟላ ማስረጃ የተጋነነ ግምት እንደተጣለባቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች የደረጃ ‹‹ሐ›› የመጨረሻ ጣሪያ ላይ ሆነው የሚታዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ ደረጃ ‹‹ለ›› ሆኖ 600,000 ብር የነበረ ከሆነና በጣም የተጋነነ ከሆነ፣ ወይም ባልተሟላ መረጃ የተገመተ ከሆነ በደረጃ ‹‹ሐ›› የመጨረሻ ጣሪያ ከ400,000 ብር እስከ 500,000 ብር ባለው እንዲስተናገድ በማድረግ ቅሬታውን መፍታት እንዳለብን አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በፊትም በደረጃ ‹‹ሐ›› እና ደረጃ ‹‹ለ›› የነበሩ ሆነው ጥናት የተካሄደባቸው አሉ፡፡ ጥናቱ እንዲካሄድ የተደረገው ‹‹ሥወራ አለ፣ ማጭበርበር አለ›› ተብሎ ነው፡፡ እኛ መረጃዎች አሉን፡፡ ግን በሒደት የሚጠራ ሆኖ፣ ለጊዜው ራሳቸው በያዙት የሒሳብ መዝገብ የሚዳኙበት አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ በአራተኛ ደረጃ የተገመተላቸው ግምት የተቀራረበ የሆኑትን ደግሞ በመቀራረብና በመወያየት መተማመን ላይ መድረስ እንዳለብን ያስቀመጥናቸው አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ ከጠቅላላ ዓመታዊ ሽያጭ የሚቀነስና ተቀናንሶ በዓመት የሚከፈለው ቁርጥ ግብር ይህ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለወራት ሲካፈል ይህንን ያህል ነው በማለት ተማምነን የሚከፈልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በአገራችን ትልቁ ግብር ከፋይ በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት ተቀጥሮ የሚሠራው የሰው ኃይል ነው፡፡ የንግዱን ማኅበረሰብ ከዚህ ጋር ስታነፃፅረው የሚከፍለው የገቢ ግብር በጣም በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ 1,000 ብር የቀን ገቢ ሽያጭ አለህ ተብሎ የተገመተለት አንድ አነስተኛ የንግድ ድርጅት፣ ዓመታዊ ሽያጩ ሲደመር ወደ 300,000 ብር ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ መታወቅ ያለበት ግን 300,000 ብር ሲባል፣ 300,000 ብር ይከፍላል ማለት አይደለም፡፡ የሚቀናነሰው ተቀናንሶ በትርፍ መተመኛው ሥሌት ተሰልቶ ሲከፍል አሥር በመቶ ይያዝለታል፡፡ 90 በመቶው የሚያዘው በወጪ ነው፡፡ ለተከራየው ቤት፣ ለቀጠረው ሠራተኛ፣ ለተለያዩ ወጪዎች የሚያዝ ነው፡፡ ስለዚህ ግብር የሚከፍለው ከአሥር በመቶ ላይ ብቻ ነው፡፡ ከአሥር በመቶውም ላይ የሚቀናነስ አለ፡፡ ድርጅቱ ሁሉም ነገር ተቀናንሶ የሚከፍለው በዓመት ከ2,500 ብር አይበልጥም፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት እንጂ የጠቀስኩት ቁጥር ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ግን መሠራት ያለበት እንደዚህ ነው ለማለት ነው፡፡ 2,500 ብር ለ12 ወራት ሲካፈል፣ በወር የሚመጣው ምን ያህል ትንሽ መሆኑን መገመት ቀላል ነው፡፡ አመለካከቱን ለተቀበለ ወገን የግብር ጫናው ያን ያህል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተ በኩል አፈጻጸም ላይ ችግር የለም እያሉኝ ነው?

አቶ ከበደ፡- አይደለም፡፡ እኛ ጋ አፈጻጸም ላይ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ በትክክል እንዲገነዘበው ለማድረግ የሠራነው ሥራ ላይ የቀን ገቢ ግምቱንና ዓመታዊ ሽያጩን ነው ያሳወቅነው፡፡ ከዓመታዊ ሽያጩ ጎን ለጎን በዓመት የምትከፍለው ቁርጥ ግብር ይህንን ያህል ነው ብለን አብረን መለጠፍና ማሳየት ነበረብን፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ መምጣቱን መንግሥት እየገለጸ ቢሆንም፣ በተለይ የንግዱ ማኅበረሰብ እንዴት ወደ ታክስ ሥርዓት መግባት እንዳለበት አልተገለጸም፡፡ ይህ ባልሆነበትና የቀን ገቢ ግብር ምን ማለት እንደሆነ እንዲረዳ ሳይደረግ፣ በድብቅ በተሰበሰበ መረጃ ‹‹ይህን ያህል የቀን ገቢ ስላለህ ይህንን ያህል ትከፍላለህ›› መባሉ ተገቢ ነው ይላሉ?

አቶ ከበደ፡- እዚህ ላይ በእኛ በኩል የአፈጻጸም ክፍተት ነበር፡፡ የነበረው አረዳድ ገቢ ግምት ላይ መግባባት ከተደረሰ በኋላ፣ የሒሳብ ሥሌቱ ቴክኒካል ስለሆነ ቀጥለን ዓመታዊ ሥሌቱን እናሳውቃለን የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ሰው በቀን ገቢ ግምቱ ላይ መረዳት አይፈልግም፡፡ ‹‹በዓመት ቁርጥ ግብር ስንት ክፈል ልትሉኝ ነው?›› የሚል ጥያቄ ነው የሚያቀርበው፡፡ ይህንን ስንገመግም የቀን ገቢ ግምትና ዓመታዊ ሽያጩን ስናሳውቅ፣ ጎን ለጎን ሁሉም ነገር ተሠልቶ የምትከፍለው ቁርጥ ግብር ይህንን ያህል ነው ብለን መናገር ነበረብን፡፡ መጀመሪያ ማድረግ የነበረብንን መጨረሻ ላይ ማድረጋችን የአፈጻጸም ክፍተት ፈጥሮብናል፡፡ መጀመሪያ አድርገነው ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ብዥታ አይፈጠርም ነበር፡፡ አስረጅ ኮሚቴዎች አሠራሩን ሲያስረዱ ‹‹ይህማ ቀላል ነው›› እያለ ብዙ ሰው በቀላሉ እየተረዳ ተመልሷል፡፡ ሰው የመሰለው ዓመታዊ ሽያጩ ሲነገረው በአንድ ጊዜ ወዲያው ክፈል የሚባል ስለመሰለው ነው ቅሬታ ማሰማት የጀመረው፡፡ መጀመሪያውኑ ብዥታውን በሚቀርፍ መንገድ ማስረዳት ነበረብን፡፡ አሁን ግን እየተስተካከለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከንግድ፣ ከፋይናንስና ከገቢው ዘርፍ የተውጣጡ 471 ገማች ኮሚቴዎች ተቋቁመው በሰው ኃይል እንዲደራጁ መደረጉ የተገለጸ ቢሆንም፣ በቀን ገቢ ግምትና በታክስ ሥርዓቱ ላይ ዕውቀት የሌላቸውና የሥነ ምግባር ችግርም ያለባቸው መሆናቸውን ቅሬታ አቅራቢ ነጋዴዎች እየተናገሩ ነው፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ከበደ፡- መጀመሪያ የገማች ኮሚቴ አባላት በጥንቃቄ ነው የተመለመሉት፡፡ እንግዲህ የምትመለምለው ካለህ ሰው ነው፡፡ ከፋይናንስ ዘርፍ የተሻሉትን፣ ከእኛም ከገቢው ዘርፍ የተሻሉትን አውጣጥተን ነው ወደ ቀን ገቢ ግምት ያስገባናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ገቢዎችና ጉምሩክ ብቻውን ነበር የሚሠራው፡፡ አሁን ግን የዘመቻ ባህሪ ስለነበረበትና ቶሎ መድረስም ስላለበት ከንግዱም፣ ከፋይናንስና ከገቢው ዘርፍ የተውጣጣ ተመለመለ፡፡ በዚህ ላይ በየደረጃው የሚገኝ የካቢኔ መዋቅር ግንዛቤ በመፍጠር እገዛ እንዲያደርግ ተደርጎ፣ ሁሉም የመስተዳድር አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጎ ነው የገማች ኮሚቴው የተዘጋጀው፡፡ ነገር ግን ደህና ነው ብለህ መልምለኸው፣ ወደ ተግባር ሲገባ የሥነ ምግባር ግድፈት የሚፈጽም ይኖራል፡፡ አንዳንድ ቦታዎችም ላይ ‹‹እንደዚህ እናደርግላችኋለን፡፡ ይህንን አድርጉልን፤›› በማለት የሚጠይቁና የሥነ ምግባር የጎደላቸው እንዳሉ ተጠቁመን ያስተካከልንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል አስቀድመን አስበን ስለነበር፣ የሱፐርቪዥንና የኢንስፔክሽን ኮሚቴ አቋቁመን እግር በግር እየተከታተሉ ማስተካከያ እንዲኖር አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ኮሚቴው አሠራሩ ከመታወጁ በፊት ከ10,000 በላይ የግብር ከፋዮች ጉዳይ ማስተካከያ ሠርቷል፡፡ የሚሰማራው ኮሚቴ ሰው ስለሆነ ፍፁም አይደለም፡፡ በሥምሪቱ ሒደት ሊሳሳት ይችላል፡፡ ስለዚህ ስህተቱን ሊያርም የሚችል የኢንስፔክሽን ኮሚቴ አደራጅተን እግር በግር እየተከታተለ እንዲያስተካክል አድርገናል፡፡ በመጨረሻም በአመራሩ መስተካከል ያለባቸው ካሉም ሪፖርት እየተደረገ በየጊዜው እያረምናቸው እንድንሄድ እየተደረገ ነው፡፡ ገማች ኮሚቴዎቹ የብቃት ጉድለት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የሙያ አቅሙ የላቸውም፡፡ በቅንነት ከታየ ግን ሥራው የተወሳሰበ አይደለም፡፡ ቀና ሆነህ፣ ፍትሐዊ ሆነህ ገቢውን በማየት ለህሊናህ ንፁህ በሆነ አዕምሮ የመገመት ጉዳይ ነው፡፡ በንግድ የተሰማራው ሰው ‹‹ሰደበኝ፣ ተቆጣኝና አመናጨቀኝ›› ብለህ ያልተገባ የቀን ገቢ ግምት የምትጭንበት ከሆነ፣ ወይም ‹‹መክፈል አለበት›› ብለህ ያላግባብ የተጋነነ ግምት የምችጭንበት ከሆነ ግብር ከፋዩ መማረሩ አይቀርም፡፡ የዚህ ዓይነት ነገርም ተከስቶ ዓይተናል፡፡

ግን ብዙ ሽፋን አላቸው ብለን አናምንም፡፡ ከተሰማሩት ኮሚቴዎች ውስጥ በአብዛኛው ጥሩ ሠርተዋል፡፡ ሥራው በባህሪው የግምት ስለሆነ አንድ ሱቅ ላይ ጥሩ ሠርቶ ሌላኛው ላይ ጥሩ ያልሆነ የሚሠራ ያጋጥማል፡፡ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመሥርተህ ስለማትሠራ ለክፍተቱ ያጋልጥሃል፡፡ ዋናው ነገር ግን ስህተቶች ሲያጋጥሙ ለማረም ዝግጁ መሆን ነው፡፡ ስህተቱ ሊያጋጥም እንደሚችል ገምተን ባደራጀናቸው ኮሚቴዎች እንዲፈቱ ማድረግ፡፡ ከዚያ ካለፈ በቅርንጫፍ ደረጃ ቅሬታዎቹ እንዲፈታ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ካልተፈታ እስከ ዋናው መሥሪያ ቤት ድረስ መጥተው ችግሮቻቸውን በማስረዳት ችግሮቹ ሊፈቱበት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት በሚል ያስቀመጥነው ነገር ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ከጠበቅነው ውጪ የመጣ ነገር የለም፡፡ ጫናው ቢጠነክርብንም ባስቀመጥነው መንገድ እየፈታነው ነው፡፡ እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የደረጃ ‹‹ሐ››ን እናጠናቅቃለን ብለናል፡፡ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ደግሞ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ››ን ፈትተን ሁሉም ወደ ግብርና ሥርዓቱ ይገባል ብለን እናስባለን፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው በዝቅተኛ የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩትን ችግር ሙሉ በሙሉ እንፈታዋለን፡፡ ሕጉም የሚለው እያንዳንዱ ነጋዴ ያመነበትን የገቢ ግብር መክፈል አለበት ነው፡፡ እኛም የምንለው ይህንኑ ነው፡፡ እኛ የምንጠላው ከግብር ክፍያ ሥርዓት ውጪ በሕገወጥ መንገድ ፈቃድ ሳያወጡ የሚነግዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት በዚህ አገር ውስጥ ሊኖር አይገባም፡፡ ሕገወጦች እየተጠቀሙ ሕጋዊ ነጋዴዎች ተጎጂ የሚሆኑበት አሠራር ሊቀጥል አይችልም፡፡ ተገቢም አይደለም፡፡ ይህንን ማስተካከል ካልተቻለ አገር ማልማት አይቻልም፡፡ ኢኮኖሚም ሊያድግ ስለማይችል በድህነት መቀጠል ነው የሚሆነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ መፈቀድ የለበትም፡፡ ይህንን ሁሉም ኅብረተሰብ ሊታገለው የሚገባ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግምት አሠራር ቀርቶ ወቅቱን የጠበቀና ሳይንሳዊ አሠራርን የተከተለ መደበኛ አሠራር የማይተገበረው ለምንድነው?

አቶ ከበደ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ የእኛ ኅብረተሰብ ገና ከእርሻ ያልተላቀቀ ነው፡፡ ከአርሶ አደርነት ነው ወደ ዘመናዊ ንግድና ሌላ ሥራ ውስጥ የገባነው፡፡ በታክስ ሥርዓት ውስጥ ‹ሲክታክስ› የሚባል ሲስተም አለ፡፡ ይህ ሲስተም በሁሉም ቦታ የተዘረጋ አይደለም፡፡ ገና ይቀረዋል፡፡ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ ነው የጀመርነው፡፡ 70 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን ግብር የሚከፍሉት እነሱ በመሆናቸው ነው፡፡ አሁን ‹ኢ-ፋይል ፕሮግራም› ጀምረናል፡፡ ከባንክም ጋር አብረን በመሥራት ሰዎች በቤታቸው ሆነው ግብር የሚከፍሉበትን ፕሮግራም እየጀመርን ነው፡፡ ሶፍትዌር ተሠርቶ የሙከራ ፕሮግራምም ተዘጋጅቷል፡፡ ከጥንቃቄው አንፃርም ተረጋግጧል፡፡ ይኼኛው ፕሮግራም በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ቀጥለን በመካከለኛ ግብር ከፋዮችም ላይ እንተገብረዋለን፡፡ እየቀጠለ በዝቅተኛ ግብር ከፋዮችም ላይ ይተገበራል፡፡ በ2010 ዓ.ም. በከፍተኛና በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዘን እየሠራን ነው፡፡ ሥራው ወደ ክልሎችም ተዳርሶ፣ ሲስተሙ ጠቅላላ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታቀፈ የግብር ከፋይ ሥርዓት ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት በተለይ በግብር መክፈያ ወቅት የሚያጋጥመንን የመጨናነቅ ችግር ይቀርፍልናል፡፡ ግብር ከፋዩንም ከመጉላላት ያድናል፡፡ ካሽ ሬጅስተር ማሽኖቻችንም ችግር እንዳለባቸው ስለተረዳን ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በዘመናዊ መንገድ ችግሮችን ሊቀርፍ የሚችል የካሽ ሬጅስተር ማሽን መዘርጋት አለብን ብለን፣ ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር ስምምነት እያደረግን ነው፡፡ ምናልባት በ2010 ዓ.ም. ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ እንቀርፋለን ብለን እየሠራን ነው፡፡ ያለው ሲስተም ከአሥር ዓመት በፊት የተሠራ ስለሆነ መሻሻል አለበት፡፡ ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት ሊያሠራ የሚችል ዘመናዊ የታክስ መረጃ ሥርዓት መዘርጋት አለብን ብለን ሥራው ተጀምሯል፡፡ በውጭ ኩባንያዎች አስጠንተን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሊኖረን ይገባል በማለት እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአንድ መስኮት አገልግሎት ጀምረናል፡፡ አርባ መሥሪያ ቤቶችን የሚያስተሳስርና ደንበኞች በማዕከል አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ተቀይሶ ከኮሪያ አንድ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርመን ሥራው እየተከናወነ ነው፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከገቢና ከጉምሩክ ጋር ቅሬታ ያላቸው 20 መሥሪያ ቤቶችን በኔትወርክ እናስተሳስራለን፡፡ ቀሪዎቹን 20 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ይቀጥላል፡፡ አሠራሩ በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት በማለት ሰው የሚያነሳው ጥያቄ ትክክል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሰኔ ወር በተጣለ የቀን ገቢ ግምት በሐምሌ ወር ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ፣ ነጋዴው እያደረገ ያለው ንግዱ ከተጣለበት ግምት አንፃር አዋጭ መሆን አለመሆኑ ወስኖ አንድ አቋም እንዳይዝ የሚያደርገው አሠራር ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

አቶ ከበደ፡- ትክክል ነው፡፡ ይህ ጥናት በእኛ በኩል መጠናቀቅ የነበረበት በሚያዝያ ወር ነበር፡፡ በሚያዝያ ወር አጠናቀን በሐምሌ ወር ሰው ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ነበረብን፡፡ ነገር ግን ሌሎች ተደራራቢ ሥራዎች ከገቢ ማሰባሰብ ሥራ ጋር ተደማምሮ ሊደርስልን አልቻለም፡፡ ክልሎች ቀድመው ጨርሰዋል፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ክልል ሁሉንም ግብር ከፋይ አጥንቶ፣ ጨርሶና ተማምኖ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ግብር እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡ የልማት ሠራዊቱን አሠልፎ የጨረሰበት ሁኔታ አለ፡፡ እኛ ጋ ግን የመፈጸምም ውስንነትና የሌሎች ሥራዎች መደራረብም እየተገፋ መጥቶ እዚህ ላይ ደርሷል፡፡ እንዳንዘለው አዲሱን የግብር አዋጅ መተግበር አለብን፡፡ አዋጁ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር አለበት ይላል፡፡ ብናልፈው ደግሞ በአዲሱ አዋጅ እንጂ በነበረው አዋጅ ልናስከፍል አንችልም፡፡ ስለዚህ ጥናቱን አጣድፈን ወደ ክፍያ ሥርዓቱ እንዲገባ ነው ያደረግነው፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮች እንደሚኖሩ ብናውቅም ጎን ለጎን እንፈታቸዋለን ብለን ነው የጀመርነው፡፡ ተንጠባጥቦ ቢገፋ እንኳን እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ሁሉንም ነገር እናጠናቅቃለን ብለን ነው ወደ ሥራው የገባነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀን ገቢ ግምት የተጣለባቸውን ክፍያ መፈጸም በማይችሉት ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ አለ?

አቶ ከበደ፡- ይኖራል፡፡ ለአንድ አገር ግብር ካልተከፈለ ልማቱንም፣ ሥራውንም ማስቀጠል አይቻልም፡፡ ግብር መክፈል የአገር ኩራት ነው፡፡ መብትም ነው፡፡ ግዴታም ነው፡፡ ግብር ከፋዮች ቅሬታ ካላቸው የሚጠበቅባቸውን 50 በመቶ ከፍለው መከራከር ይችላሉ፡፡ ምንም ሳይከፍሉ ‹‹መጀመሪያ ቅሬታዬ ይፈታ›› ብሎ መቀመጥ ግን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የአገር ጉዳይ ነው፡፡ አገር ደግሞ ያለ ፋይናንስ ሊንቀሳቀስ አይችልም፡፡ እላፊ ከፍሎ ከሆነ ለቀጣይ የግብር ወቅት ይተላለፍለታል፡፡ ትክክለኛ ግምት ከሆነ ደግሞ ቀሪውን 50 በመቶ ይከፍላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ቅሬታ አለኝ በማለት አልከፍልም ካለ ሌላ ችግር ነው፡፡ ትልልቅ ፕሮጀክቶችና ልማቶች አሉ፡፡ ኅብረተሰቡም የሚጠይቃቸው ሰፋፊ ጥያቄዎች ያለ ፋይናንስ ሊፈቱ ስለማይችሉ ግብር መክፈል ግዴታ ነው፡፡ እየከፈሉ ቅሬታን ማቅረብ ግን ተገቢ አካሄድ ነው፡፡ እኛም የቀረበውን ቅሬታ በአግባቡ እየፈታን መቀጠል ተገቢና ትክክለኛው አካሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ከግምቱ የሚያገኘው ጥቅም ቢኖርም የታክሱን አሰባሰብ ተከትሎ ሊከሰት የሚችል የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነትና የንግድ እንቅስቃሴ አለመረጋጋት ሊኖር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይኼ እንዳይሆን መንግሥት ምን ያዘጋጀው ነገር አለ?

አቶ ከበደ፡- በእኛ በኩል ይኼ ሥጋት ባዶ ሥጋት ነው፡፡ ምክንያቱም የተጨመረ ግብር የለም፡፡ እያደረግን ያለነው ደረጃ ማስተካከል ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት ሰው የገቢ ደረጃው የቱ ጋ እንዳለ የማወቅ ሥራ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ የዕለት ገቢው ከፍ ያለ ደረጃው ወደ ደረጃ ‹‹ለ›› ወይም ወደ ‹‹ሀ›› ሊሸጋገር ይችላል፡፡ እንዲሸጋገር እያደረገው ያለው የኢኮኖሚ አቅም ነው፡፡ ስለዚህ የደረጃ ሽግሽግ ተደረገ እንጂ የግብር ጭማሪ እንዳልተደረገ መታወቅ አለበት፡፡ ሌላው ደግሞ ግብር የማይከፍሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ ነው የተደረገው፡፡ ለምሳሌ ከ8,600 በላይ ንግድ ፈቃድ ያልነበራቸውና ግብር ከፍለው የማያውቁ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በዚህ ጥናት አግኝተናል፡፡ እነዚህን ሰዎች ወደ ሥርዓቱ አስገባን እንጂ ምንም የተጨመረ ነገር የለም፡፡ ከሚያመነጩት ገቢ ለመንግሥት ግብር እንዲከፍሉ ተደርገዋል፡፡ በደረጃ ሽግሽጉ የሚመጣ ጭማሪ ይኖራል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ወደታች የሚወርድ ይቀነስለታል፡፡ በነበረው ሁኔታ የሚቀጥል እንጂ አዲስ ጭማሪ የተደረገ የለም፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ በድምሩ ስናየው በዚህ የገቢ ሽግሽግ ጥናት ማግኘት ከነበረበት የተለመደ ገቢ ውስጥ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የቀነሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይኼ ጭማሪን አያሳይም፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ግብር ተጫነብኝ ብሎ ለመጨመር ባለው ፍላጎት በተጠቃሚው ኅብረተሰብ ላይ ሊጨምር ይችል ይሆናል፡፡ ግን የኢኮኖሚው ሁኔታ ግን ይህንን አያሳይም፡፡ በመሆኑም መጨመር ሳይስፈልግ ባለው ተረጋግቶ ነው መቀጠል ያለበት፡፡ በእኔ እምነት የኑሮውን ውድነት የሚወስነው የንግዱ ማኅበረሰብ አይደለም፡፡ የአምራች ኅብረተሰብ የማምረት አቅም ነው፡፡ አርሶ አደሩ ጋ ጥሩ ምርት ካለና ወደ ገበያ የሚወጣ ከሆነ ዋጋ የሚጨምርበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውና በገጠር የሚኖረው አርሶ አደሩ ምርት ነው የሚወስነው፡፡ የምርት እጥረት ካለ የኑሮ ውድነቱ ሊጨምር ይችላል፡፡ ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በሚመለከት የሚወስነው የዓለም ገበያ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መርካቶ ላይም ሆነ የትም ቦታ ‹‹መንግሥት ግብር ጨምሯል፡፡ እኔም እጨምራለሁ›› የሚለው የኢኮኖሚ መነሻ መሠረት ስለማይኖረው፣ የተሳሳተ መረጃ ይዞ የሚደረግ ጭማሪ ስለሚሆን እሱን ደግሞ መታገል ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀን ገቢ ግምት የማያካትታቸው በየትኛው የንግድ የተሰማሩትን ነው?

አቶ ከበደ፡- በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉት ግብር ከፋዮች ከ334,000 በላይ ናቸው፡፡ አሁን እያጠናን ያለነው 45 በመቶ በሚሆኑት ላይ ነው፡፡ 55 በመቶው በዚህ ጥናት አልተካተቱም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሒሳብ መዝገባቸው የሚዳኙ በመሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አስመጭና ላኪ፣ አከራይና ተከራይ፣ ትራንስፖርት ድርጅቶችና ሌሎችም በውላቸው መሠረት ነው የሚስተናግዱት፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ ከ31,000 በላይ ግብር ከፋዮች አሉ፡፡ የሚከፍሉት በተሽከርካሪዎቻቸው ወንበር ቁጥርና በሚጭኑት የጭነት መጠን ተሠልቶ ነው፡፡ የአከራይ ተከራይም በሚፈራረሙት ውል መሠረት ግብር ይከፍላሉ፡፡ በድምሩ ወደ 192,000 የሚሆኑት ግብር ከፋዮች በራሳቸው በውል ሥርዓት ግብር የሚከፍሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይኼ ጥናት እነሱን አይመለከታቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- በዝቅተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ በበረንዳ ላይ ቡና የሚሸጡ የቀን ገቢ ግምት 3,000 ብር፣ ጠላ የሚሸጡ እናቶች 1,400 ብርና የጉልት ቸርቻሪዎችም ተመሳሳይ ግምት ተጥሎባቸዋል፡፡ ይኼ ግምት የተሠራው ምንን ግምት አድርጎ ነው? ጥናቱ የተጠናው እንዴት ነው?

አቶ ከበደ፡- እነዚህን የመሳሰሉ በአነስተኛ የንግድ መስክ ክፍሎች ላይ እንደ መንግሥትና እንደ ተቋም ያለን አቋም፣ በመጀመሪያ ደረጃ የራሳቸውን የዕለት ምግብ ችለው ካደሩ ለመንግሥትም ድጋፍ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሰዎች የአገሪቱ ዜጎች ናቸውና ከሚያገኙት ትንሽ የቀን ገቢ ‹‹ግብር መክፈል አለብኝ›› የሚል ቁርጠኝነት ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ ነገር ግን እንደዚህ በተጋነነ ግምት ውስጥ ሊገቡ አይገባም፡፡ ያመኑበትንና አቅማቸውን የሚመጥን ክፍያ ነው መክፈል ያለባቸው፡፡ ለምሳሌ ቡና የምታፈላና ሸጣ ራሷን ማስተዳደር መቻሏ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ‹‹ከማገኛት ላይ የአቅሜን ለአገሬ ማበርከት ግብር መክፈል አለብኝ›› ብላ መክፈል አለባት፡፡ ይኼ ለራሷም ኩራት ነው፡፡ ‹‹እኔ በምከፍለው ግብር ነው መንገድ የሚገነባው፣ የኤሌክትሪክ ግድብ የሚሠራው፣ ማኅበራዊ ልማትና መሠረተ ልማት የሚሠራው›› ብላ በኩራት እንድትናገር ያደርጋታል፡፡ የዕለት ገቢዋ 300 ብርና 500 ብር ሆኖ እያለ 3,000 ብር ተገምቶባት ከሆነ ትክክል አይደለም ማለት ነው፡፡ ይኼንን ማስተካከል አለብን፡፡ ይኼንን ነው የቅሬታ ሰሚ አካላት በጥሞናና በቅን ልቦና ሰምተው ማስተካከል ያለባቸው፡፡ በተለይ መንግሥታችን ደሃ ተኮር በመሆኑ ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ አቅፎ አቅም እንዲፈጥሩ ማድረግ ስለሆነ፣ በግብር ጫና በማንኮታኮት እንዳይነግዱ አድርጎ ከሥርዓቱ እንዲወጡ ማድረግ የለብንም፡፡ ራሳቸው ያመኑበትን ‹‹የቀን ገቢዬ ይኼ ነው፡፡ መክፈል ያለብኝ ይኼንን ያህል ነው›› ብለው ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ይኼንን ለማስተካከል አቅጣጫ ሰጥተን እያስተካከልን ነው፡፡ ውጤቱን በጋራ እናየዋለን፡፡ እናንተም ተዘዋውራችሁ በማየት እውነታውን ለሕዝብ ማሳወቅ አለባችሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በወረዳዎችና በክፍላተ ከተማ የተቀመጡ ቅሬታ ሰሚዎች የቅሬታ አቅራቢውን ችግር አዳምጠውና በሚገባው መንገድ አስረድተው ስምምነት ላይ ከመድረስ ይልቅ፣ በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ቅሬታ አቅራቢውን በማሸማቀቀና በማስፈራራት እየመለሱት በመሆኑ፣ ከፍተኛ ግምት የተጫነበት የንግዱ ማኅበረሰብ በጭንቀት ውስጥ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ እናንተ ይኼን አሠራር እንዴት ነው የምትከታተሉት?

አቶ ከበደ፡- ክትትል እያደረግን ነው፡፡ በየቀኑ የሱፐርቪዥን  ቡድን እናሰማራለን፡፡ ቅሬታ በሚስተናገድበት ወረዳና ክፍለ ከተማ በድንገት በመሄድ አሠራሩን የሚከታተል ግብረ ኃይል አደራጅተናል፡፡ በሌላ በኩል የመስተዳድር አካላት በተለይም ደግሞ የወረዳው መዋቅር በጠቅላላ ይኼንን ሥራ እንደ ራሱ ሥራ አድርጎ የሕዝቡ ቅሬታ በትክክል እየተፈታ መሆኑን፣ ከታች ያሉት ቅሬታ ሰሚዎች በአግባቡ እያስተናገዱ መሆን አለመሆናቸውን እንዲያረጋግጡ አድርገናል፡፡ በየቀኑም ሥራው እየተገመገመ አመራር እንዲሰጥበት አድርገናል፡፡ እያደረግን ነው፡፡  በቅርቡም ከአስተዳደሩ ከንቲባ ጋር ሆነን፣ ሁሉም የወረዳና የክፍላተ ከተሞች፣ እንዲሁም የክልል አመራሮች ባሉበት የግማሽ ቀን ውይይት አድርገን ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብን ከተረዳን በኃላ ይዘን ወደ ታች ወርደናል፡፡ እስካሁን ባደረግነው ግምገማ አራዳና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ላይ በጣም ጥሩ መስተንግዶ መኖሩን አረጋግጠናል፡፡ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ስንሄድ ደግሞ፣ ‹‹ማሻሻያ ካደረግሁ ሁሉም ይመጣብኛል፡፡ ሁሉም ከመጣ ደግሞ ጫናውን አልችለውም›› ብሎ ግምቱን የማፅናት ባህሪ ይዞ ነበር፡፡ ይኼ ትክክል አለመሆኑን ገምግመናል፡፡ ሁሉም ይመጣብኛል በሚል ሥጋት መተው የለብህም፡፡ እውነታውን በማየት የተሰጠው ግምት በዝቶበታል ወይስ አልበዛበትም የሚለውን ግምገማ በማካሄድ መፍትሔ መስጠት ነው፡፡ የሚያጣራ ቡድን ልኮ በማጣራት፣ በሚገኘው ውጤት መሠረት ማስተናገድ አለብህ፡፡ አሁንም ቢሆን በገማቹና በቅሬታ ሰሚው ቡድን ‹‹ትክክል ነው›› ተብሎ በማንጓጠጥ የተወሰነበት ካለ መታረም አለበት፡፡ ይኼም ሆኖ መታረም ካልቻለ በቅርንጫፍ ደረጃ የተዘጋጀ ቅሬታ ሰሚ አካል ስላለ ወደዚያ መሄድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ያላግባብ ግምት ተጭኖብኛል የሚል ካለ የግምቱን 50 በመቶ ማስያዝ አለበት፡፡ ይኼንን ካደረገ ደግሞ በግምቱ እንዳመነበት ስለሚቆጠር ቢከራከርም ውጤት ሊያመጣ አይችልም የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ከበደ፡- እሱ እስከ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ድረስ ነፃ ነው፡፡ ከቅርንጫፍ በላይ የሚሄድ ከሆነ ወደ መደበኛ ሥርዓቱ ይገባል፡፡ በመደበኛ አካሄድ ቅሬታውን የሚያቀርብ ከሆነ የፍሬ ግብሩን 50 በመቶ ማስያዝ አለበት፡፡ ይኼ ለሁሉም ይሠራል፡፡ ሃምሳ በመቶውን አስይዞ ይከራከራል፡፡ ወይ ያሸንፋል አለበለዚያ ቀሪውን እንዲከፍል ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀን ገቢ ግምት ላይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጥናት እያጠና ነበር፡፡ ግምቱንም በመረጃ ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርፆ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ፣ የንግዱን ማኅበረሰብ የሚያስቆጣ የግምት ሥራ መጀመር ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ከበደ፡- ይኼንን ሥራ የሠራነው ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር ነው፡፡ የሠራነውም የብዙ ግብር ከፋዮችም ግብዓት እንዲሰባሰብ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን የግብር መተመኛ ዘዴዎቹ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ግብር የሚወሰነው በግብር መክፈያ መቶኛዎች ነው፡፡ አሥር በመቶ የሚከፍል አለ፡፡ 15 በመቶና 16 በመቶ የሚከፍል አለ፡፡ ከአሥር በመቶ እስከ 35 በመቶ ድረስ ተቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆ ባወጣው ደንብ ላይም የሚመሠረት ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ከአጠቃላይ ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር፣ ከግሽበት መጠንና በአጠቃላይ የግብር ሥርዓቱን ከመሠረቱ ለመቀጠል የሚያስችል አጠቃላይ ጥናት ነው የሚያካሂደው፡፡ እኛ ውስጥ በሆነውና ላለፉት ስድስት ዓመታት ባልተጠናው ደረጃ ‹‹ሐ›› ላይ ነው ጥናት ያደረግነው፡፡ ስለዚህ ጥናቱ የሚቃረን አይደለም፡፡ በጋራ የተወሰነ ስለሆነ የተለየ ነገር የለውም፡፡ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሚያጠናቸው ጥናቶች ለእኛ ግብዓት ስለሚሆኑ ተባብረን ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀን ገቢ ግምት በየሦስት ዓመቱ እየተጠና ለንግዱ ማኅበረሰብ ይፋ መደረግ እንዳለበት በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሳይጠና የከረመው ለምንድነው?

አቶ ከበደ፡- በወቅቱ የነበረው አመራር ለምን ጥናቱን እንዳላሠራው አላወቅሁም፡፡ በእውነት ለመናገር ግን በወቅቱ ጥናቱ መካሄድ ነበረበት፡፡ በየሦስት ዓመቱ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ የተወሳሰበና ቅሬታ የሚያስነሳ አይሆንም ነበር፡፡ ምክንያቱም ነጋዴው በየጊዜው ያለበትን ደረጃ እያወቀ ይሄድ ነበር፡፡ እያመነበት ስለሚሄድ አዲስ ነገር አይሆንበትም ነበር፡፡ ያ ባለመደረጉ በአሁኑ ሥራችን ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል፡፡ በንፅፅር የክልሎችን ስናይ ግን የተሻለ ነው፡፡ እነሱ በየሦስት ዓመቱ ጥናት ስላደረጉ ምንም የገጠማቸው ችግር የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ያለፈው አይደገምም፡፡ በሥራ ዘርፉ የተሰማራ ሰው በየሦስት ዓመቱ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ የቀን ገቢ ግምት ጥናት መደረግ አለበት፡፡ አዋጁም የሚለውም ይኼንን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በክልሎች አለመግባባት በመፈጠሩ ወደ ግጭት ያመራበት አጋጣሚ ታይቷል፡፡ በዚህ ላይ የመንግሥት ሐሳብ ምንድነው?

አቶ ከበደ፡- በግብር ግምት ትመና ምክንያት ግጭት ይቀሰቅሳል የሚል ግምት የለኝም፡፡ በውይይት ሊፈታ የሚችል በመሆኑ፡፡ ሕገ መንግሥታችንም አለመግባባቶች በውይይት የሚፈጡበትን መንገድ ነው ያስቀመጠው፡፡ ግብር በዝቶብኛል ብሎ እንዲስተካከል መጠየቅ ነው እንጂ ድንጋይ መወርወርና የመኪና መስታወት በመስበር መፍትሔ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ የዚህ ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ሊያራግቡት ይችላሉ፡፡ ባለፈው ጊዜም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተነስተው የነበሩና የመከኑ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ያንን የመከነ ግጭት እንደ አዲስ መጀመር የሚፈልግ፣ የግብር ሥርዓቱን ‹‹ኢፍትሐዊ ነው፣ ትክክል አይደለም፤›› ብሎ እንደ መሣሪያ በማድረግ ሊቀሰቅስበት ይችላል፡፡ ይኼ አካሄድ ግን ብዙ ስንዝር የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ የኅብረተሰቡ ፍላጎት ሰላም፣ ልማትና በዴሞክራሲ አካሄድ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ነው፡፡ ይኼ ሥርዓት በተዘረጋበት ኅበረተሰብ ውስጥ የአመፅ መንገድ አዋጭ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሰላም ሲደፈርስ ተጎጂ የሚሆነው ራሱ የንግዱ ማኅበረሰብ ስለሆነ፣ ከትናንትና ተሞክሮ ትምህርት ይወስዳል ብዬ አስባለሁ፡፡ በቀን ገቢ ግብር ትመና ያጋጠሙ ችግሮችን በውይይትና በመግባባት እንፈታቸዋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ወደ አመፅና ወደ ጦርነት የሚያስገባ ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ ኃይሎችም ቢሆኑ በዴሞክራሲ አካሄድ በምርጫ ተወዳድረው ለማሸነፍ መሥራት አለባቸው እንጂ፣ ድንጋይ በመወርወርና በማስወርወር ያሸንፋሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ላለፉት ስድስት ዓመታት ጥናት ሳይደረግበት ቆይቶ በድንገትና በችኮላ የቀን ገቢ ግምት ጥናት የተካሄደውና የተጋነነ ግምት የተጣለው፣ መንግሥት የገንዘብ እጥረት ስላጋጠመው ነው የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

አቶ ከበደ፡- መንግሥት ገንዘብ ስላጣ ነው የሚለው የሚያጠግብ ክርክር አይደለም፡፡ መንግሥት ግብር የሚሰበስበው አንደኛ ከባለሀብቶች ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በገጠር ከሚገኘውና 80 በመቶ ከሚሆነው አርሶ አደር ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ዝቅተኛ ገቢ ካለው የኀብረተሰብ ክፍል አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ 20 በመቶ የሚሆነው አዲስ አበባ ከሚገኘው ከደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይ ላይ የሚሰበሰብ ነው፡፡ የሌሎቹ በሒሳብ ደብተራቸው የሚሰበሰብ በመሆኑ የተጨመረ ግብር የለም፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት ገቢ ቢፈልግ በዚህ መንገድ ሳይሆን፣ በተለያዩ መንገዶች ግብር የሚጨምርበት ዕድል አለው፡፡ ኢኮኖሚው 11 በመቶ እያደገ በመሆኑ የገቢ አቅማችን ከዓመት ዓመት እያደገ ነው ያለው፡፡ የዛሬ 15 ዓመታት አጠቃላይ የአገሪቱ ገቢ ግብር 12 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ዛሬ ግን በዓመት 140 ቢሊዮን ብር እየሰበሰብን ነው፡፡ ኢኮኖሚው ባደገ ቁጥር የሚያመነጨው ገቢ በዚያው ልክ ነው፡፡ በእርግጥ የሕዝቡ ፍላጎትም በዚያው ልክ ሰፊ ነው፡፡ ይኼንን የምናደርገው ግን በደሃው ላይ ግብር በመጫን አይደለም፡፡ የአርሶ አደሩ ምርታማነት እንዲጨምርና ምርቱን ኤክስፖርት በማድረግ የተሻለ ዶላር እንድናገኝ በምናደርገው ሥራ ነው እንጂ ገቢ የምናገኘው፣ በጉልት ቸርቻሪዎችና በዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ተጨማሪ ግብር በመጫን አይደለም፡፡ እንደ መንግሥት ግብር የመጨመር ፍላጎት የለንም፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው ባገኘው ልክ ግብር ሊከፍል ይገባል፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...