Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ በ680 ሚሊዮን ብር የጨረታ ዋጋ የገዛውን ሕንፃ ተረከበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲሸጥ የተወሰነውን ባለሰባት ወለል ሕንፃ የጨረታ ሒደቱን በ680 ሚሊዮን ብር በማሸነፍ የገዛው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የሚጠበቅበትን ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ በማድረግ ሕንፃውን እንደተረከበ አስታወቀ፡፡

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በጨረታ ያሸነፈበትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ገቢ በማድረግ ሕንፃውን ለመረከብ የበቃው ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡

ንብ ባንክ በጨረታ የገዛው ሕንፃ ከስምንት ዓመታት በፊት ለግንባታ በሰጠው ብድር የተገነባ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህ ሕንፃ ግንባታ ከባንኩ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ የተበደሩትና በአራጣ አበዳሪነት ተከሰው የተፈረደባቸው አቶ ከበደ ተሠራ፣ ንብረታቸው እንዲወረስ በፍርድ ቤት መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሠረት ባንኩ ያበደረውን ገንዘብ ለማስመለስ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር ለዓመታት የዘለቀ የይገባኛል ክርክር ሲያካሒድ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም ሕንፃው በሐራጅ እንዲሸጥ ሲወሰን፣ ባንኩ ከሌሎች ተጫራቾች ጋር ተወዳዳሮ በከፍተኛ ገንዘብ ሊገዛው ችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለዋና መሥሪያ ቤትነት እያስገነባው የሚገኘው ከ30 ወለል በላይ የሆነው ሕንፃ እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኘውን ይህንን ሕንፃ በጊዜያዊነት ለዋና መሥሪያ ቤትነት ሊጠቀምበት አቅዷል፡፡ በመሆኑም በጨረታ የገዛው ሕንፃ የማጠናቀቂያ ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል ተብሏል፡፡

 የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሕጋዊ ባልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ አማካይነት የተገኘ ንብረት በመሆኑ ንብ ባንክ ሕንፃውን መሸጥ እንደማይችል በማመልከቱ፣ ባለሥልጣኑና ባንኩ በዚህ ጭብጥ ላይ ከስድስት ዓመታት በላይ የፈጀ የፍርድ ቤት ክርክር ሲያካሔዱ ቆይተዋል፡፡

ንብ ባንክ ለሕንፃው ግንባታ እንዲውል ያበደረው 55 ሚሊዮን ብር፣ በአሁኑ ወቅት እስከነወለዱ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ ሕንፃውን ከገዛ በኋላ ባንኩ፣ የሰጠውን ብድር ከነወለዱ በመጠየቅ እንደሚቀበል ይጠበቃል፡፡

አራት ኪሎ አካባቢ፣ ከቱሪስት ሆቴል አጠገብ በሚገኝ ቦታ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ግንባታው ተጀምሮ በማጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ፣ መከታ ሪል ስቴት ሲያስገነባው የነበረ ነው፡፡ ይሁንና መከታ ሪል ስቴት ለሕንፃው ግንባታ የተበደረውን ገንዘብ በወቅቱ መመለስ ባለመቻሉ፣ ባንኩ በሕጉ መሠረት ሕንፃውን በሐራጅ ለመሸጥ ማስታወቂያ አውጥቶ ወደ ዕርምጃ ለመግባት መንቀሳቀስ ሲጀምር፣ የሪል ስቴት ኩባንያው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ፣ ሕንፃውን ሽጦ ገንዘቡን ለማስመለስ ሳይችል ይቀራል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታም ንብረቱ ወይ ሕንፃው በአራጣ የተያዘ፣ ሕጋዊ ባልሆነ የገንዘብ ልውውጥ የተገኘና ይወረስ የሚል ጥያቄ የቀረበበት በመሆኑ ንብ ባንክ ሊሸጠው አይችልም በማለቱ ነው፡፡ ይህ አቤቱታ የቀረበው በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ በገቢዎችና በጉምሩክ ባለሥልጣንና በባንኩ መካከል ለዓመታት ለዘለቀው ክርክርም መነሻ ሆኖ መቆየቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በባለሥልጣኑ አቤቱታ መሠረት፣ ባንኩ ንብረቱን ለመሸጥ ያደረገው እንቅስቃሴ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ይታገዳል፡፡ የዕግድ ትዕዛዝ ሲወጣም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ባንኩ በበኩሉ ዕግዱን በመቃወም ንብረቱን ለመሸጥ መብት እንዳለው በመከራከር በመጨረሻም በተካሔደው ጨረታ መሠረት ሕንፃውን በ680 ሚሊዮን ብር በመግዛት የገዛ ንብረቱ ለማድረግ በቅቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች