ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እንድትመድብ ከሚያስገድዱ ሸቀጦች ውስጥ ነዳጅን የሚስተካከለው እንደሌለ ይታመናል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ ባሳየበት ወቅት እንኳ፣ አገሪቱ ለውጭ ሸቀጦች ግዥ ካዋለችው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ አብላጫውን የወሰደው ነዳጅ ነው፡፡ የዓለም ነዳጅ ዋጋ መቀነስ ሲወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ ቢያደርግም፣ ትልቁን የገቢ ንግድ ወጪ የሚጠይቅ ሸቀጥ ከመሆን አልገደበውም፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጭንቅ የሆነባት አገራችን ከዛለው የወጪ ንግድ፣ ከብድርና ከዕርዳታ እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች ከሚሰባሰበው ገንዘብ ውስጥ ለነዳጅ የሚከፈለው መጠን፣ ነዳጅ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ሚና ከግዙፍም በላይ ስለሆነ ነው፡፡ አቅመ ደካማ ኢኮኖሚ ኖሮንም እንኳ ለነዳጅ መግዣነት የሚውል ዶላር ይፈለጋል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ሸቀጥ እንደመሆኑ ግብይቱም የተለየ ባህሪይ አለው፡፡
እንደማንኛውም የውጭ ሸቀጥ በቀላሉ የሚገባ አይደለም፡፡ በትንሹ ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ከሻጭ ጋር የግዥ ስምምነት ማሠርን ይጠይቃል፡፡ ከሌሎች የገቢ ምርቶች ይልቅ በልዩ ትኩረት ወደ አገር ውስጥ ቢገባም፣ የሚያስከፍለንን ዋጋ በማይመጥን መልኩ ሥርጭቱ ላይ በርካታ እንከኖች ይታያሉ፡፡
በነዳጅ ሥርጭት ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮችም በርካታ ጉዳዮችን ሲያበለሻሹ እናያለን፡፡ የሚፈጠረው መደነቃቀፍ ለምን መፍትሔ እንዳጣ፣ ደጋግሞ የሚከሰተው የነዳጅ እጥረትም ለምን እንደማይፈታ ግራ ያጋባል፡፡ መንገድ ተደረመሰ፣ ነዳጅ የጫነችው መርከብ ዘገየች እየተባለ ምክንያት ሲደረደር፤ በሌላ ጊዜም እንዲሁ ሌላ ሰበብ እየተፈጠረ የነዳጅ ማደያዎች በተሽከርካሪዎች ተከበው ሲታመሱ ማየት የሰርክ ልማድ እየሆነ ነው፡፡ ተደጋግሞ የሚታየው የዚህ ዓይነቱ እንከንም የሥርጭት ችግሩን በቋሚነት ለመቅረፍ ከልብ እንደማይሠራ ያሳብቃል፡፡
ነዳጅ እጥረት ጭምጭምታው በተሰማ ቅፅበት የጭነት ዋጋ ገበያውን ሲያተረማምስ እናስተውላለን፡፡ የነዳጅ እጥረት ወሬ ሲሰማ፣ ከመሀል አገር ውጭ የሚገኙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ተሽቀዳድመው ታሪፍ በመቀየር ተገልጋዩ ከሚገባው በላይ እንዲከፍል ይጫኑታል፡፡ ይህ ደግሞ ተደጋግሞ ሲከሰት የሚታይ ነው፡፡ ለሰዓታት የነዳጅ አቅርቦት ሲስተጓጎል የሚፈጠረው ችግር በርካታ ነው፡፡
ነዳጅ ጠፋ በተባለ ሰሞን ቁፋሮ የሚያከናውን የኮንስትራክሽን መሣሪያ ይቆማል፡፡ የአርማታ ማቡኪያ ማሽን ድምፁ ይጠፋል፡፡ አንዱ ሲቆም ተያያዥ ሥራዎችን በማጓተት ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በነዳጅ የሚሠሩ ማሽኖች በአቅርቦት መዘግየት ምክንያት ያለ ሥራ የሚያቃጥሉት ጊዜ፣ ግንባታዎች በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት እንዳይጠናቀቁ ምክንያት የሚሆንበት አጋጣሚ ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ ሌሎችም በርካታ ችግሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ የለም በማለታቸው ሳቢያ ጎዳናዎች በተሽከርካሪዎች ተጣበው፣ ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት መሆናቸውም አገር ውስጥ የገባውን ነዳጅ በአግባቡ ካለማሠራጨት የተነሳ ነው፡፡
ነዳጅ አላቸው ወደ ተባሉ ማደያዎች ከየአቅጣጫው የሚመጡ ነዳጅ ፈላጊዎችን በቅጡ ለማስተናገድ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለሰዓታት ወረፋ ጠብቆ ለመገልገል ያለው ፍላጎት ይረብሻል፡፡ ለሰዓታት ወረፋ ይዞ ነዳጅ አለቀ ሲባል ተገልጋዩን ምን ያህል እንደሚያማርር መገመት አያዳግትም፡፡
ከዚህ ቀደም እንዲህ ያሉ ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር የሚደረደሩ ምክንያቶች ባይታጡም፣ ለሰሞኑ ችግር ግን ለየት ያለ ሰበብ ተሰጥቷል፡፡ የሱዳን ነዳጅ ምርት በመቀነሱ የተፈጠረ ክፍተት እንጂ የነዳጅ እጥረት የለም ተብሏል፡፡ እንደ እኔ ግን ይህ ምክንያት አጥጋቢ አይደለም፡፡ የቅድመ ግዥ ስምምነት የተፈጸመበት ሸቀጥ እንዲህ ያለ ሰበብ ይፈጠርበታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የምክንያቱን ትክክለኛነት ብንቀበል እንኳ፣ በየቦታው የተገነቡት መጠባበቂያ የነዳጅ ማከማቻዎች ክፍተቱን እንዲሞሉ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ አፋጣኝ መፍትሔ የማበጀት ባህላችንና አቅማችን ዝቅተኛ በመሆኑ ሳቢያ ግን በቂ ምርት በእጃችን እያለ እንኳ ለአቅርቦት ችግርና ግርግር ሰበብ የሚኮንበት ሁኔታ ሲደጋገም ማየት ተለምዷል፡፡
የነዳጅ ሥርጭት ሥርዓታችን ብዙ የሚቀረው ከመሆኑም በላይ መጠነኛ ችግር በተፈጠረ ቁጥር የሚከሰተው ውጥረትና የሚደርሰው ጉዳት ሲደማመር ከፍተኛ እየሆነ ነው፡፡ ጊዜ ይቃጠላል፡፡ ሀብትና ገንዘብ ይባክናል፡፡ ተገልጋዩ ያማርራል፡፡ ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ይሆናል፡፡ ሲብስም ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተማማኝ ባልሆነበት ወቅት በጄኔሬተር ጭምር የሚገለገሉ ተቋማት በነዳጅ እጥረት የሚፈጠርባቸው ቀውስ በሒሳብ ቢሰላ ጥቂት የሚባል አይሆንም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ባለመሆኑ ምክንያት፣ አነስተኛም ከፍተኛም ድርጅቶች ጄኔሬተር መጠቀም ግድ እየሆነባቸው ነው፡፡ መደበኛውን ኃይል ሲያጡ በጄኔሬተር ሥራቸውን ለመግፋት የሚታትሩም ነዳጅ ካላገኙ አማራጫቸውን ምን ሊሆን ነው? መጠባበቂያ እንዲሆናቸው ነዳጅ በየጀሪካኑ ሞልተው የሚያስቀምጡም አልታጡም፡፡ ይህም ለእሳት አደጋና ለሌላውም መንስዔ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል የለበትም የሚባለው እንዲህ ካለውም ችግር አንፃር ነው፡፡ በአገሩ ነዳጅ ሲጠፋ፣ እንዴት እንደሆነ ባይታወቅም ከማደያ ውጪ ነዳጅ የሚቸበችቡ አልታጡም፡፡ በግላጭ ነዳጅ የሚነግዱ “የነዳጅ ኪዎስኮች” በየቦታው የሚያካሂዱት ሽያጭ ምን ያህል ሕጋዊ ነው የሚለው ጉዳይ የሚያነጋግር ቢሆንም፣ ነዳጅ በጠፋ ሰሞን ገበያው ይደራላቸዋል፡፡
እኔው ራሴ እንደታዘብኩት፣ አንዱ “የነዳጅ ኪዎስክ” ነደጅ የሚሸጠው ጥቅም ላይ በዋለ የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙስ ነው፡፡ በባለሁለት ሊትር የውኃ ጠርሙስ የሚሸጥበት የራሱ ስያሜ አለው፡፡ ‹‹አራዳው›› ይሉታል፡፡ በባለሁለት ሊትር መያዣ ፕላስቲክ መያዣ ተሞልቶ የሚሸጠው ቤንዚን ዋጋው 50 ብር ነው፡፡ ለአንድ ሊትር 25 ብር ማለት ነው፡፡ የኪዋስኮቹ ‹‹መልካም ነገር›› ጄሪካን ፍለጋ አለማንከራተታቸው ነው፡፡ ማሸጊያው ከእነርሱ ሲሆን ዋጋው ለአንድ ሊትር ቤንዚን ከተተመነውም በላይ ይሆናል፡፡ በኪዎስኮቹ ተመን መሠረት አንድ ሊትር ቤንዚን በ25 ብር ይሸጣል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሕጋዊ የቤንዚን መሸጫ ዋጋ አኳያ ያለው ልዩነት ለተጠቃሚው ግልጽ ይመስለኛል፡፡ የነዳጅ ሥርጭቱ ችግር ለሕገወጥ ግብይት መስፋፋት ሰበብ እየሆነ ነው፡፡ ይሁንና ግን ቸርቻሪዎቹ ነዳጁን ከየት ይሆን የሚያመጡት? አጠያያቂ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር እንዲህ ባለው መንገድ የሚሸጠው ነዳጅ የጥራት ደረጃው አስተማማኝነት እስከምን ድረስ ነው የሚለውም ምላሽ ያሻዋል፡፡ የነዳጅ ሥርጭቱ መዘዝና ጉዳቱ ብዙ ስለሆነ የሚመለከታቸው ያስተካክሉልን፡፡