Friday, June 2, 2023

የአማራ ክልል ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት የተጋረጡ መሰናክሎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአማራ ክልል በፌዴራል ሥርዓቱ ከተዋቀሩ ዘጠኝ ክልሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በውስጡ የጣና ሐይቅን፣ የስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርኮችን፣ የፋሲል ግንብን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንና ሌሎች ታላላቅ የቱሪስት መስህቦችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡ የመልከዓ ምድር አቀማመጡ ሜዳማ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ለእርሻና ሌሎች የልማት ሥራዎች ምቹ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ የራስ ዳሽን ተራራ የሚገኝበት ይህ ክልል፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ ከሱዳን፣ በሰሜን ከትግራይ፣ በምሥራቅ ከአፋር፣ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ከቤንሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ አቅጣጫ በኩል ደግሞ ከኦሮሚያ ክልሎች ጋር ይዋሰናል፡፡

ይህ አካባቢ በንጉሠ ነገሥቱና በደርግ ዘመናት በተለያዩ አውራጃዎችና ግዛቶች ተከፍሎ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግሥት የክልሎች አወቃቀር መሠረት በ11 ዞኖች የተከፋፈለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የዛሬ አሥር ዓመት ባወጠው መረጃ መሠረት የክልሉ ሕዝብ ከ17 ሚሊዮን የማይበልጥ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከ25 ሚሊዮን በላይ እንደ ደረሰ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ሆኖ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጩ እርሻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማ የሚኖረው የክልሉ ሕዝብ ቁጥር 20 ከመቶ በላይ እንዳልዘለለ በቅርብ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በገጠር የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል በእርሻ ሥራ የሚተዳደር በመሆኑ መሠረታዊ የሆኑ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የኃይል፣ የጤናና የትምህርት አቅርቦት ችግሮች በስፋት እንዳሉበት ይነገራል፡፡ ይህን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሥት የሚጀማምራቸው ሥራዎች ቢኖሩም፣ ከዳር ደርሰው የሕዝብን ተጨባጭ ችግሮች ከመፍታት አኳያ ብዙ ውስንነቶች እንዳሉ ይገለጻል፡፡

በከተማ የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል በቁጥር አነሰተኛ እንደሆነ ቢገለጽም፣ እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶች ከማሟላት አኳያ አሁንም ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ ነዋሪዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ በክልሉ የተንሰራፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የመሠረተ ልማቶች በበቂ ደረጃ አለመሟላት በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችን ለከፍተኛ ጉዳትና እንግልት እየዳረገ እንደሆነ ነዋሪዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ተቀስቀሶ የነበረው ሁከትና ተቃውሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ያደረሰው ጉዳትና ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም፣ በአማራ ክልል በተለይም ከቱሪዝም ዘርፉ ይገኝ የነበረው የገቢ መጠን በእጅጉ ቀንሷል፡፡ ሰሞኑን የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔውን በባህር ዳር ሲያካሂድ በጉባዔው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደተናገሩት፣ ባለፈው ዓመት ተቀስቀሶ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ በክልሉ ከነበረው የቱሪዝም ፍሰት ከዚህ በፊት ይገኝ የነበረው ገቢ 53 በመቶ ቀንሷል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሰባተኛ መደበኛ ጉባዔውን ሰሞኑን ሲያካሂድ፣ የ11 ወራት የበጀት ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ ጉባዔው በዋናነት በአሁኑ ወቅት ክልሉን በከፍተኛ ደረጃ ሥጋት ላይ በጣሉ ጉዳዮች ላይ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡ እነዚህ ጉዳዮችም በክልሉ ተካሂዶ በነበረው የቀን ገቢ ግምት ጥናት፣ እንቦጭ ዓረም በጣና ሐይቅ ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት፣ አደገኛና ሁሉን አውዳሚ ስለሆነው ተምችና በክልሉ ስላለው የኃይል አቅርቦት ችግሮች ውይይት ተደርጓል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አባላት በክልሉ ውስጥ ስለሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉን አቀፍ የሆነ ጥያቄና አስተያየት ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ብቻ በተቆጣጠረው በዚህ ምክር ቤት እጅግ የመንግሥትን ኋላ ቀር የአሠራር ሥርዓት የሚተቹ የምክር ቤት አባላት እንደነበሩ መታዘብ ተችሏል፡፡ የክልሉን መንግሥት የሚተቹ፣ የሚሞግቱ፣ የሚቃወሙና የሚደግፉ አስተያቶችና ጥያቄዎች ሲሰነዘሩ ነበር፡፡

በክልሉ ለረጅም ዓመታት ሲንከባለል የመጣና አሁንም ድረስ ሊፈታ ያልቻለው አንዱ የኃይል አቅርቦት ሲሆን፣ በክልሉ ያለው የኃይል አቅርቦት እጅግ ከማነሱ የተነሳ መለስተኛ ፋብሪካዎች እንኳ ሥራቸውን በማቆም ላይ እንደሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ ችግር የተነሳ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በልተው ማደር እንኳ እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡

በፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቢያድግልኝ ጫኔ (የአባታቸው ስም ተቀይሯል) የእህል ወፍጮ ያላቸው ሲሆን ከአምስት ዓመት በላይ ኃይል የሚለቀቅላቸው በፈረቃ እንደሆነ ለሪፖርተር በስልክ ተናግረዋል፡፡ ከሳምንት ሁለት ቀናት ብቻ ኃይል እንደሚመጣላቸውና በእነዚህ ቀናት ብቻ እንደሚፈጩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ ቀናት ብቻ እየሠራን እንዴት ነው መኖር የምንችለው? እንዴትስ ነው መንግሥት በአሁኑ ጊዜ አደግንና ተለውጠን የሚለው? በምንስ ሁኔታ ነው ለክልላችን ብሎም ለአገራችን አስተዋጽኦ የምናደርገው?›› በማለት አስተያየታቸውን በቅሬታ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ ያለው የኃይል አቅርቦት ባለመፈታቱ ምክንያት የተለያዩ ኢንቨስተሮችና ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው ኢንቨስት ለማድረግ እንዳልቻሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ2009 ዓ.ም. ብቻ ከ1,700 በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቢወስዱም፣ በኃይል አቅርቦት ችግር የተነሳ አብዛኛዎቹ ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ የክልሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሙያዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ20 የማይበልጡ ማከፋፈያዎች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህ ማከፋፈያዎች የተገነቡት ከዛሬ ዘጠኝና አሥር ዓመት በፊት እንደሆነ ሲነገር ተደምጧል፡፡ እነዚህ ማከፋፈያዎች በአሁኑ ጊዜ ሌላ ኃይል መሸከም ስለማይችሉ በክልሉ የኢንዱስትሪዎችንና የፋብሪካዎችን መስፋፋት የገታ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገሮች በመሸጥ ላይ ብትሆንም፣ በአገር ውስጥ ያሉ ክልሎች በዚህ ችግር ከፍተኛ እየተመቱና ለማደግ በሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት እየሆነባቸው መምጣቱን ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ በክልሉ ከመቶ የማይበልጡ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የሚደርሱ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ ታቅዶ ባለሀብቶችም ፍላጎት እንዳላቸው ያሳዩ ቢሆንም፣ ወደ ተግባር ለመግባት እንቅስቃሴ እንዳልተጀመረ እየተነገረ ነው፡፡ አሁን ያለው የኃይል አቅርቦት ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር እጅግ የማይጠጣም መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህም የተነሳ ከዚህ በፊት መለስተኛ ፋብሪካ ከፍተው ሥራ የጀመሩ መለስተኛ ባለሀብቶች ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ እየደረሰባቸው መሆኑን፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የክልሉ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ለመረዳት እንደተቻለው፣ በክልሉ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የክልሉን ሕዝብ በመለወጥ በኩል ያላቸው ሚና እስካሁን ዝቅተኛ ነው፡፡ ምንም እንኳ የክልሉ ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ በብአዴን የተያዘ ቢሆንም፣ የተለያዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ ከወሬ ያለፈ ተጨባጭ ሥራ በማከናወን በክልሉ ውስጥ የተጋረጠውን ችግር በቁርጠኝነት መፍታት ተገቢ እንደሆነ ከርር ያሉ አስተያቶች ተደምጠዋል፡፡

በክልሉ አሳሳቢ የሆነውን የኤለክትሪክ ችግር ለመፍታት ሰሞኑን የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዜብ አስናቀን (ኢንጅነር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት ከአማራ ክልል ከተውጣጡ ባለሀብቶች፣ ከሥራ ኃላፊዎችና ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ጋር የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አቅምን ለማሳደግ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም፣ ለጎረቤት አገሮች ጭምር በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ቢጀመርም፣ ከዚህ ዘርፍ ክልሉ ተጠቃሚ እንዳልሆነ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት አንድም የኃይል ማከፋፈያ በክልሉ ባለመሠራቱና ከዚህ ቀደም የነበሩት የኃይል ማከፋፈያዎች ኃይል የመሸከም አቅማቸው ዝቅተኛ ስለሀሆነ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ለጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ማሳቸውን የሰጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሻይ አፍልተው መጠጣት እንኴ እንዳልቻሉ ለኃላፊዎች አስረድተዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ ስኬታማ የኢንዱስትሪ ልማት የማይታይበትም አንዱ ምክንያት ይህ እንደሆነ  ተገልጿል፡፡

በክልሉ ያለው የኃይል አቅርቦት ችግር ከክልሉ አቅም በላይ እንደሆነና መሠረተ ልማቶችን ለማከናወን እንቅፋት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ችግር ለመፍታት የፌዴራሉ መንግሥት መጠየቁንና መቼ ምላሽ እንደሚሰጥ ግን አይታወቅም ተብሏል፡፡

በዘንድሮው ጉባዔ ትኩረት ከተሰጣው ጉዳዮች መካከል በክልሉ ተካሂዶ የነበረው የቀን ገቢ ግምት ጥናትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣውን የሕዝብ ቅሬታ የተመለከተ ነው፡፡

ዘንድሮ በአገሪቱ በተካሄደው የቀን ገቢ ግምት ጥናት መሠረት ከ100 ሺሕ የሚበልጡ ነጋዴዎችን ወደ ታክስ ሥርዓቱ ማስገባት እንደተቻለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአማራ ክልልም በተካሄደው የቀን ገቢ ግምት ጥናት በዚህ ዓመት ከ30 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ወደ ታክስ ሥርዓቱ እንዲገቡ መደረጉን ምንጮች ቢጠቀሙም፣ ግመታው የተጋነነና የነጋዴዎችን የዕለት ገቢ በትክክል መሠረት ያደረገ አይደለም ተብሎ የተለያዩ ቅሬታዎች እየተደመጡ ነው፡፡

 ለአብነት ያህል ዘንድሮ በኦሮሚያ ክልል ከ46 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ወደ ታክስ ሥርዓቱ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፣ ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በተነሳው የሕዝብ ቅሬታና ተቃውሞ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡

በአማራ ክልልም እነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው እየተነሱ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ከላይ ታች ሲል ተስተውሏል፡፡ ጉዳዩ ወቅታዊና አንገብጋቢ ከመሆኑ አንፃር የክልሉ ምክር ቤትም በስፋት ተወያያቶበታል፡፡ የክልሉ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱ፣ ‹‹በክልሉ ያሉ መሠረት ልማቶችን ከግብ ለማድረስ ገቢ መሰብሰብ ግድ ይላል፡፡ በዚህም በክልሉ የቀን ገቢ ግምት ጥናት ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ነጋዴዎች ግብር በዛብን እያሉ ጥያቄ ሲያነሱ፣ ይኼንን አጋጣሚ ተጠቅመው የሚያጯጩሁ ኃይሎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ይርሳው ታምሬ ለሪፖርተር በስልክ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በአሁኑ ወቅት በነጋዴዎች ላይ ያላግባብ ተጣለ የተባለውን ግብር የክልሉ መንግሥት በጥንቃቄ መፍታት እንዳለበት በጉባዔው መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ ቅሬታ ካለ ቅሬታውን በመስማትና ችግሮችን በመፍታት ነጋዴዎች ተገቢውን ግብር ብቻ መክፈል እንዳለባቸው በምክር ቤቱ መወሰኑን፣ ለዚህም የክልሉ መንግሥት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ይርሳው አስረድተዋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የክልሉ ምክር ቤት ትኩረት ሰጥቶ ከተወያየባቸው መካከል ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ መጤ የሆነው የእንቦጭ ዓረም በጣና ሐይቅ ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት ነው፡፡ የእንቦጭ አረም በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺሕ ሔክታር በላይ ስፋት ያለውን የጣና ሐይቅ እንደሸፈነና የውኃውን መጠን እንደቀነሰ ይነገራል፡፡ የእንቦጭ አረም በባህሪው የውኃ ትነትን በእጥፍ የሚጨምርና ውኃን በቶሎ የሚያደርቅ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመከላከል በባህር ዳርና በጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ሙከራዎችና ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጣናን የታደገው አካል እንደሌለ እየተገለጸ ነው፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየጨመረና እየተስፋፋ ነው፡፡ የምሁራኑ አስተያየትና በአካባቢው ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ይኼ ቢሆንም የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የዱር እንስሳት ቢሮ ኃላፊ በላይነህ አየለ (ዶ/ር) ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት፣ ጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም የተወረረበት መጠኑ ካለፈው ዓመት የበለጠ አየደለም ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር በላይነህ ገለጻ፣ ጣና ሐይቅ ሀብትነቱ የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካ እንደሆነና ሐይቁን ከሚፈታተኑ ለመጠበቅ ችላ እንደማይባል አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ልዩ አጀንዳ ያላቸው ወገኖች መነጋገሪያ እያደረጉት ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በጣና ሐይቅ ዙሪያ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን በማነቃነቅ በእንቦጭ አረም የተወረረውን 21 ሺሕ ሔክታር ስፋት ካለው የሐይቁ አካል በሕዝብ ንቅናቄ ለማስወገድ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

 የክልሉ አፈ ጉባዔ አቶ ይርሳው ይኼ ችግር ከተከሰተ ዕለት ጀምሮ የክልሉ መንግሥት እየጣረ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸው፣ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ችግሩን ለመከላከል እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ችግሩ ከተከሰተ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ ከሠራ የመስፋፋት ዕድል እንዴት አገኘ? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ የክልሉ ምክር ቤት በዚህ ላይ እንዳልተወያየ ለዚህ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልጽ የሆነ መረጃ የለኝም ብለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዚግ ጉዳይ ላይ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ምላሽ፣ ጣና ሐይቅ የክልሉን ቅርስ አቅፎ የያዘና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አረም ሐይቁ ክፉኛ እየተጎዳ መሆኑን አስረድተው፣ አረሙን ሙሉ በመሉ በክልሉ አቅም ማስወገድ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

የጣና ሐይቅ መጤ በሆነው የእንቦጭ አረም ክፉኛ እየተጎዳና አፋጣኝ መፍትሔ እየተሰጠው እንዳልሆነ በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ቢገለጽም፣ እስካሁን ድረስ የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሉ መንግሥት በቅንጅት ሆነው በመሥራት ረገድ የቁርጠኝነት ማነስ እንደሚታይባቸው እየተገለጸ ነው፡፡ ይኼ አረም በተፈጥሮው እጅግ ከባድና በቀላሉ ሊወገድ የሚችል ባለመሆኑ ዛሬ ነገ ሳይባል የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወሰድ እየተጎተጎተ ነው፡፡

ምክር ቤቱ በአራተኛ ደረጃ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች ሌላው ሁሉን አውዳሚ ሰለሆነው ተምች ነው፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት በክልሉ በተለይም በምዕራብ አካባቢ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በጉባዔው ተጠቅሷል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አይተነው እንዳሻው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ፣ ‹‹ሁሉን አውዳሚ የሆነው ተምች በክልሉ በ57 ወረዳዎችና በ715 ቀበሌዎች የተከሰተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር ውሏል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ አይተነው ይኼን ይበሉ እንጂ፣ በምዕራብ ጎጃም በተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው፡፡

 አቶ ይርሳው በበኩላቸው ጉባዔው ይኼንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ መነጋገሩን  ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የመንግሥት አመራሮችና ባለሙያዎች ዘንድ መዘናጋት እየተፈጠረ መሆኑን ምክር ቤቱ እንደገመገመ አስረድተዋል፡፡

‹‹ክረምቱ በመግባቱ ዝናብ እየዘነበ ቢሆንም፣ ተምቹ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋና በክልሉ ባለሙያዎች እስኪረጋገጠ ድረስ ባለመዘናጋት መሥራት እንደሚገባ ምክር ቤቱ ስምምነት ላይ ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ገዱ በበኩላቸው፣ ‹‹ይኼ ሁሉን አውዳሚ መጤ ተምች በቀን ከ200 እስከ 250 ኪሎ ሜትሮች የሚጓዝ ፈጣን ፀረ ሰብል ተባይ በመሆኑ በትኩረት ሊሠራ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ የኅብረተሰብ በርካታ ፍላጎቶች ሲኖሩ፣ እነዚህን ፍላጎቶች መሠረት አድርጎ መፍትሔ ከመስጠት አኳያ ውስንነቶች እንዳሉ እየተገለጸ ነው፡፡ ከወጣቶች ሥራ አጥነትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ውድመት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከዚህ አገር አቀፍ ረብሻና ሁከት በኋላ የፌዴራሉ መንግሥት የክልል መንግሥታትን ጨምሮ በጥልቅ ውስጥ ተሃድሶ በማለፍ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ተገቢ እንደሆነ አቅጣጫ ያቀመጡ ቢሆንም፣ በክልሉ ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን በአፋጣኝና በተቀላጠፈ ሁኔታ መፍታት እንዳልተቻለ የክልሉ ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡ በክልሉ ለተንሰራፋው ሁለንተናዊ ችግር በይዋል ይደር ምክንያት ሕዝቡ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ ሲያሰማ ተደምጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -