Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዘመነኛው የኪነ ጥበብ መገበያያ

ፊልም ኢቲ በቅርቡ የተመረቀ ድረ ገጽ ሲሆን፣ ፊልሞች፣ ዘፈኖች፣ ቀልዶች እንዲሁም ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ የጥበባዊ ሥራዎቹ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን የሚሸጡበት ድረ ገጽ ከመሆኑ በተጨማሪ ተጠቃሚዎች አካውንት ከፍተው የሚፈልጉትን የሚመለከቱበትና ምልከታቸውን የሚያንሸራሽሩበት ነው፡፡ ድረ  ገጹ ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ስለአጠቃቀሙና ለኪነ ጥበብ ስለሚኖረው አስተዋጽኦ የታፊ አድቫንስ ኮምፒውተር ሲስተምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አያሌውን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ በቅርቡ ያስመረቀው ፊልም ዶት ኢት (ፊልም ኢቲ) ድረ ገጽ እንዴትና ለምን ተቀረፀ?

አቶ ተፈራ፡- ድርጅታችን ከዚህ በፊት በቫት ሲስተምና ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንቶች ዙሪያ ሠርቷል፡፡ በቫት ሲስተም የምንሠራው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ሲሆን፣ 8678 የሚባል የስልክ ቁጥር አለ፡፡ መጀመርያ የለቀቅነው ሄሎ አድራሻን ሲሆን፣ ሄሎ አድራሻ በአጭር የፅሑፍ መልዕክት (ኤስኤምኤስ) የሚፈለገው አድራሻ በቀላሉ የሚገኝበት ነው፡፡ እስካሁን ወደ 1.5 ሚሊዮን መረጃዎች አሉን፡፡ መረጃ የምንሰበስበው ከመንግሥት አካላት ጋር ተጻጽፈን በሕጋዊ መንገድ ነው፡፡ በሄሎ አድራሻ ሥር ካሉት አንዱ በቅርቡ ያስመረቅነው ፊልም ኢቲ ነው፡፡ አሁን አገልግሎት ባይጀምሩም ከፊልም ኢቲ ጋር አብረው የሚሠሩ ኢቨንትኢቲን የመሰሉ ድረ ገጾችም አሉ፡፡ ፊልም ኢቲ የድረ ገጽ፣ የኤስኤምኤስና የሞባይል ባንኪንግ ወይም ኢኮሜርስ ሲስተምን ያካትታል፡፡ በኤስኤምኤስ አንድ ነገር መግዛት የሚቻልበት ሲስተም ፈጥረናል፡፡ በድረ ገጽ ረገድ ፊልም ኢቲ የማኅበራዊ ሚዲያ ባህሪ አለው፡፡ ሰዎች የኔነት ስሜት እንዲሰማቸው የወደዱትን ላይክ እንዲያደርጉ፣ አስተያየት እንዲሰጡ፣ መረጃ ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ (ሼር እንዲያደርጉ) ያስችላል፡፡ ሰዎች የመውደዳቸውን መጠን የሚገልጹበት (ሬቲንግ) እና የተቃውሞ መግለጫም አለ፡፡ በፌስቡክና ሌሎች ሚዲያዎች ያሉትንና የሌሉትንም በራሳችን ፈጠራ ጨምረን ዲዛይን አድርገነዋል፡፡ ባሙያው ማን ላይክ እንዳደረገ፣ ማን እየተከተለው (ፎሎወሩ እንደሆነ) ያውቃል፡፡ ሁለተኛው የኦንላየን ግብይት ባህሪ ነው፡፡ ማንኛውም ኦንላየን መቀመጥ የሚችሉ ይዘቶች ፖስት ይደርጋሉ፡፡ ሥዕል፣ ሙዚቃ ወይም ማንኛውም በኤሌክትሮኒክ ሲስተም መቀመጥ የሚችሉ ይካተታሉ፡፡ ያስቀመጠው ሰው ማነው? አድራሻው የት ነው? የሚለው መረጃ አብሮ ይካተታል፡፡ ፊልም ከሆነ ሲሠራ የተሳተፉ ተዋናዮችና ሌሎችም ባለሙያዎች ይመዘገባሉ፡፡ ፕላትፎርሙ ነፃ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ያለውን ማቅረብ ይችላል፡፡ ግብይቱ የሚፈጸመው በሦስት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ባለቤቱ በሚያገኘው የላይክ መጠን የምንከፍለው ክፍያ ነው፡፡ ሁለተኛው በተጎበኘለት መጠን የምንከፍለው ሲሆን፣ ሦስተኛው ሲሸጥ የሚያገኘው ገቢ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያነቱና የግብይቱ መድረክነቱ ተጣጥሞ እንዲሄድ የተፈጠረ ድረ ገጽ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ የተሞከሩ ድረ ገጾች አሉ፡፡ ፊልምኢቲ ይዟቸው ከመጣው የተለዩ ነገሮች መካከል ዶት ኢቲ መጠቀሙ ይጠቀሳል፡፡ አገራዊ ቃና ያለው ነገር ስለፈለግን ዶት ኢቲን መርጠናል፡፡ ፊልም ኢቲ፣ ሚዩዚክ ኢቲ፣ ኢቨንት ኢቲና ላይብረሪ ኢቲ በሚልም ሥራውን እናከናውናለን፡፡ ፊልም ኢቲ ማንም ሰው ሊጫወትበት የሚችል ሜዳ ወይም ፕላትፎርም ነው፡፡ በተሰጠው ወሰን ውስጥ እየተሽከረከረ ለተጠቃሚዎች አማራጭ ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኪነ ጥበብ ሥራዎች ሽያጭና ባለሙያዎች ከሕዝቡ አስተያየት የሚያገኙበት መንገድ ከማመቻቸት አንፃር ፊልም ኢቲ አሁን ያለውን ክፍተት ይሞላል?

አቶ ተፈራ፡- በበለፀጉ አገሮች ሁሉም ነገር የሚገለጸው በቁጥር ነው፡፡ የሰው ማንነት፣ ሽያጭና ሁሉም ነገር በቁጥር ይገለጻል፡፡ እኛ አገር በቁጥር መግለጽ ገና እየተጀመረ ነው፡፡ አንድ ነጋዴ የሚገዛውና የሚሸጠው በቲን ነምበር (ቁጥር) ቢሆንም፣ ምርቶችና አገልግሎቶች በቁጥር አይሸጡም፡፡ በቁጥር ማሰብ እስከምንችል ድረስ ሲስተሙን ማምጣት አንችልም፡፡ ሲስተሙ እንዲመጣ ትንንሽ ድርጅቶች የሚያድጉበት ሜዳ መዘርጋት አለበት፡፡ አሁን ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ገበያ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ጠንካራ ናቸው፡፡ ካሉት ድርጅቶች ጋር ለመወዳደር አዳዲስ ሐሳብ ማምጣት አለብን፡፡ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከተፈለገ መንግሥትና ሁሉም አካል በቁጥር ማሰብ አለበት፡፡ ፊልም ኢቲ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ አንድን ነገር ፖስት የሚያድረገው አካል ተጠያቂነት አለው፡፡ ፖስት ማድረግ፣ መሸጥ፣ የሚገዛውን ሰው ማወቅ፣ ፖስት የተደረገውን በማውረድ መቆጣጠር ስለሚችል ግልጽነት አለው፡፡ በኦንላየን ግብይት ሲስተም አንድ ሰው ኤስኤምኤስ ሲልክ እኛ ኪውን ጄነሬት አድርገን ግዥ ይፈጸማል፡፡ ቴሌ የራሱ አሠራር አለው፡፡ እኛም የቴሌ የቢዝነስ አጋር ነን፡፡ ከባንኮች ጋርም በቀላሉ የኦላየን ሽያጭ ስለሚካሄድበት መንገድ እያወራን ነው፡፡ አንድ ሰው የገዛቸው ነገሮች ባጠቃላይ ሚዲያው ላይ ስለሚመጡለት በፈለገበት ሰዓት ያጫውታቸዋል፡፡ የሚፈልገውን ሲያወርድ በሲግኔቸር ማለትም የገዥውና የሻጩ መለያ ተካቶ ስለሆነ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሻጩ አንድ ሰው ያልገዛውን ነገር ሲጠቀም ካየ መክሰስም ይችላል፡፡ ሲስተሙ እኛ የፈጠርነው ሳይሆን በዓለም ያለ ነገር ነው፡፡ ሲግኔቸር መጠቀም የማይችሉ ነገሮችን አፕሎድ ለማድረግ ሲስተሙ ስለሚከለክል መረጃው ደኅንነቱ በተጠበቀ ፎርማት መቅረብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢኮሜርስ ባልተስፋፋበት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ድረ ገጹን ስታዘጋጁ የኪነ ጥበብ ባለሙያችን እንዲሁም ሕዝቡን ምን ያህል ታሳቢ አድርጋችኋል? የሐሳቡ አለመስፋፋትስ በድረ ገጹ ትግበራ ክፍተት አይፈጥርም?

አቶ ተፈራ፡- ክፍተት አለ፡፡ ለምሳሌ የባንኮች ሲስተም ኦንላየን ግብይት ማድረግ ቢያስችልም ከቴክኖሎጂ እጥረት፣ ካለመሞከር ወይም ከፍራቻ የተነሳ ሲስተሙ ክፍት አይደለም፡፡ ባንኮች ኤፒአይ በተባለ ሲስተም ከተለያዩ ድረ ገጾች፣ የገበያ ማዕከሎች ጋር መገናኘት ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው የባንኮች ኔትወርክ ሲስተም መሠራትም ይችላል፡፡ አማራጩ ስላለ እንሥራ ብለን የባንኮችን በር እያንኳኳን ነው፡፡ ጭላንጭል ብናይም ያገኘነው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም፡፡ ባንኮች የሚሠሩት ከውስን ድርጅቶች ጋር ከሆነ ቢዝነሱ አያድግም፡፡ ሕዝቡ የሚጠቀመው ሁሉም ድርጅት መሳተፍ ሲችል ነው፡፡ ውድድሩ ሲሰፋ የተሻለ ነገር ያለው ድርጅት በገበያው ይቆያል፡፡ ሕዝቡ በድረ ገጹ እንዲጠቀም የተለያዩ ማበረታቻዎች በማዘጋጀት ለማስተዋወቅ እየሞከርን ነው፡፡ አንዱ ማበረታቻ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. 100 ሺሕ ላይክ ለሚያገኝ ሰው 10 ሺሕ ብር እንሰጣለን፡፡ ጉግልና ዩቲዩብ ከሚከፍለው ጨምረን ክፍያ የምናካሂደው ድርጅቱ ያን ያህል አትራፊ ይሆናል ብለን ሳይሆን ድረ ገጹ መታወቅ ስላለበት ነው፡፡ ሲስተሙ ጋባዥ እንዲሆን አድርገናል፡፡ አንዱ ላክይ ሲያገኝ ሌሎች ላይክ ያገኙትን ይጋብዛል፡፡ እነ ፌስቡክና ዩቲዩብ እንደታወቁት ፊልም ኢቲም ቀስ በቀስ ያድጋል፡፡ ሕዝቡ ቴክኖሎጂ እየገባው መምጣቱ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ እኛም ለማትረፍ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ ዋጋውንም እናያለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያላችሁ ስምምምነት ምንድነው?

አቶ ተፈራ፡- ከባንኮች ጋር መሥራት ካልቻልን ያለን አማራጭ ከቴሌ ጋር መሥራት ነው፡፡ ባንኮች ወደ ቴክኖሎጂው እየሄዱ ያሉት በቀስታ ነው፡፡ እነሱን አሳምኖ አብሯቸው መሥራት ከባድ ነው፡፡ እነሱ ፈልገው ሳይሆን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አብሮ መሥራት ግዴታቸው ነው፡፡ አገሪቱ እንድታድግ ከተፈለገ በቴክኖሎጂው መሠራት ያለበት ነገር ያለ ገደብ መሠራት አለበት፡፡ በኦንላየን ግብይት ረገድ ከባንኮች ጋር መሥራት ለሚፈልግ ተቋም መፈቀድ አለበት፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የራሱ ውስንነት አለው፡፡ ያላግባብ በርካታ ብር ይወስዳል፡፡ አንድ ሥራ በሦስት ብር ተሽጦ ባለቤቱ 40 በመቶ፣ ኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ይወስዳል፡፡ እኛ የምንወስደው 20 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ የኛ ትልቅ ገቢ ከማስታወቂያ የምናገኘው ነው፡፡ ሥራው አትራፊ ነው፡፡ አቅሙ ያላቸው ድርጅቶች ወደ ቢዝነሱ እንዲገቡ ግን ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጥበባዊ ሥራዎቹ ለገበያ የሚቀርቡበት ዋጋ ተተምኗል?

አቶ ተፈራ፡- ማንኛውም ሰው ሲስተሙን መጠቀም ይችላል፡፡ የሚሸጠው ሰው ከሦስት ብር ጀምሮ የፈለገውን ዋጋ ያስቀምጣል፡፡ በእርግጥ የኢትዮ ቴሌኮምን ኔትወርክ ስለምንጠቀም ገደብ አለው፡፡ ሻጩ በነፃ ማድረግ፣ ፖስት ያደረገውን ማውረድም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኮፒራይት መብታቸው እየተጣሰ ከሥራዎቻቸው ተገቢውን ጥቅም ባለማግኘታቸው ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ በድረ ገጹ ከሥራዎቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሽያጩን የሚቆጣጠሩበት መንገድ አለ?

አቶ ተፈራ፡- አንድ ሙዚቃ ቁጥር ተሰጥቶት ሽያጩ ሲካሄድ የገዛው አካልም በቁጥር ይታወቃል፡፡ ይህንን የሚቆጣረው የመንግሥት አካል ነው፡፡ በቁጥር ማሰብ እንዲኖር ከዚህ በፊት ድርጅታችን ለንግድ ሚኒስቴር ይህን ሐሳብ አቅርቦ ፈቃድ አግኝተን ነበር፡፡ በየጊዜው አዋጅ ይታወጃል፤ ማኅበራትም ይቋቋማሉ፡፡ የችግሩ መሠረት ግን አልተገኘም፡፡ መንግሥት ተገቢውን ታክስ እንዲሰበስብና ትክክለኛውን የገበያ ሥርዓት እንዲቆጣጠር ከተፈለገ ወደ ቁጥር አስተሳሰብ መምጣት አለብን፡፡ ገበያው የሚተዳደረው በአይደንቲፊኬሽን ነምበር (የመለያ ቁጥር) ከሆነ ትርፍና ኪሳራውን መንግሥት ያውቃል፡፡ አንድ ባለሙያ ፊልሙን ፖስት ሲያደርግ ማን በምን ያህል እንደገዛ በኛ ሲስተም ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ሲስተምም ይታያል፡፡ እኛ ሱቅ የማከራየት ዓይነት ሚና ነው ያለን፡፡ የምንቀበለው የሱቅ ኪራይ ነው እንጂ ዕቃው የባለቤቱ ንብረት ነው፡፡ ባለቤት ነኝ ብሎ ሥራውን ፖስት ሲያደርግ ተጠያቂነቱን አዘጋጅተንለታል፡፡ የገዛው ግሰለብ ማን እንደሆነ እንዲያውቅም ሲስተሙን አዘጋጅተናል፡፡ ያዘጋጀነውን ሜዳ ደኅንነት በአንደኛ ደረጃ መንግሥት መጠበቅ አለበት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከቴክኖሎጂው ዓለም ሰዎች ጋር መነጋገር አለባቸው፡፡ ሌላው ዓለም ላይ እንዴት እየተሠራ ነው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች ሲጎዱ ለምን ይኼ ሆነ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ ችግሩን ሲስተሙ ራሱ ይቀርፈዋል፡፡ አደጉ የሚባሉ አገሮች መቆጠጣሪያ መንገዳቸው ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ አሜሪካ ዕቃ ለማስገባት ቁጥር መሰጠት አለበት፡፡ አገልግሎት ሲሰጥም ቁጥር ይሰጠዋል፡፡ ሰውም በሴክዩሪቲ ነምበር ይለያል፡፡ እኛ ጋም ይህ መጀመር አለበት፡፡ የፊልምና ሌሎችም የሙያ ማኅበራት ሐሳብ እንዲተገበር ከተፈለገ የቴክኖሎጂ ሒደቱ መፋጠን አለበት፡፡ ማኅበራቱም በቴክኖሎጂው ረገድ አሠራሩ የሕግ ማዕቀፍ እንዲያገኝ መንግሥትን መገፋፋት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በድረ ገጹ በዋነኛነት የሚጠቀሙት የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች እንደመሆናቸው ሥራችሁን በሙያተኞች ዘንድ ምን ያህል አስተዋውቃችሁታል?

አቶ ተፈራ፡- ባለሙያዎችን እንዲህ አድርጉ ብለን መንገር ባንችልም፣ ባለን ዕውቀት ድረ ገጹን አዘጋጅተናል፡፡ ለፊልም ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዘርፎች እንዲውል አድርገናል፡፡ ችግሮች እንዲቀረፉ ከተፈለገ ባለሙያዎቹ ከሌሎች ዘርፎች ባለሙያዎች ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት አለባቸው፡፡ ሲስተሙ እንዳለ አሳውቀናል፡፡ በእርግጥ ሥራ የጀመረውም በቅርቡ ነው፡፡ ባለሙያዎች የሥራውን አብዛኛውን ፐርሰንት የሚወስዱ ግማሽ አካሎቻችን ስለሆኑ በቀጣይም አብረን እንሠራለን፡፡  

ሪፖርተር፡- እናንተ ከምትሰጡት አገልግሎት ጋር ተቀቀራቢ ሥራ ከሚሠሩ ተቋሞች በተለየ ምን ይዛችሁ መጥታችኋል?

አቶ ተፈራ፡- በመካከላችን ጤናማ ውድድር መፈጠር አለበት፡፡ ያሉት ድርጅቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ከኛ በፊት ያሉት መስመሩን ባይቀዱት ይህን ማድረግ አንችልም ነበር፡፡ ባለው የኢትዮጵያ ገበያ ኦንላየን ግብይት ማድረግ ስለማይቻል የኤስኤምኤስ መንገድን እንደ አማራጭ ወስደናል፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጽን ከቢዝነስ ጋር ማዋሃዳችንም የተለየ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድረ ገጹ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠ ነው? ተጠቃሚዎችስ ምን ማሟላት ያስፈልጋቸዋል?

አቶ ተፈራ፡- ከተመረቀበት ሐምሌ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ሰው አካውንት መፍጠርና ፖስት ማድረግ ይችላል፡፡ አንድ ሰው ወደ ፊልም ዶት ኢቲ ገብቶ የሚፈልገውን ዓይቶ ብቻ መውጣት ይችላል፡፡ ላይክ ማድረግና ሼር ማድረግ እፈልጋለሁ ካለ መመዝገብ አለበት፡፡ መሸጥ እፈልጋሁ ካለ ኮንፈርሜሽን (ማረጋገጫ) ይጠየቃል፡፡ እያንዳንዱ ነገር ደረጃ አለው፡፡ ሕዝቡ መርሳት የሌለበት ለጊዜው ኮንፈርሜሽኑን አለመጀመራችንን ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ሰዎች ስለ ድረ ገጹ እንዲያውቁና እንዲገቡ እንፈልጋለን፡፡ በሒደት አውተንትኬሽን እንጀምራለን፡፡ የምንፈልገው ተጠቃሚ ቁጥር ሲሞላ ለእያንዳንዱ ነገር አውተንትኬሽን እንጠይቃለን፡፡ አሁን ባለው ሲስተም የሚታወቁት ገዥና ሻጭ ናቸው፡፡ ሰው ማድረግ ያለበትና የሌለበት (ተርምስ ኤንድ ኮንዲሽንስ) አሉ፡፡

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...