ኳታር ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በማለት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬንና ግብፅ ከኳታር ጋር ያላቸውን ማናቸውም ግንኙነት ካቋረጡ ከ50 ቀናት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ አገሮቹ ኳታር ሽብርተኝነትን ትደግፋለች ያሉትም፣ ግንኙነታቸውን ከማቋረጣቸው ሁለት ሳምንታት አስቀድሞ የኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም አል ሐማድ አልታኒ፣ ‹‹ኢራን ለእስልምና የጀርባ አጥንት ናት፤›› በማለት አሜሪካ በኢራን ላይ ያላትን አቋም አጣጥለው በሚዲያ ተናግረዋል በማለት ነበር፡፡
በወቅቱ ዘገባው በውሸት የተቀነባበረ እንደሆነና የተላለፈበት ጣቢያም በኢንተርኔት ጠላፊዎች (ሀከርስ) ተጠቅቶ እንደነበር የኳታር መንግሥት ቢያሳውቅም፣ ጆሮ የሰጠው አልነበረም፡፡ ኳታርን ጨምሮ የባህረ ሰላጤው አገሮች ትብብር ምክር ቤት አባል አገሮች ከሆኑት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬን፣ ኦማንና ኩዌት መካከልም ከኦማንና ከኩዌት በቀር ሁሉም አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን የየብስ፣ የባህር፣ የአየርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያቋረጡት የኳታር አሚር መግለጫውን በቴሌቪዥን ሰጡ በተባለ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ዕገዳውም ማንኛውንም ከኳታር የሚተላለፍ ሚዲያንም ያካተተ ነው፡፡
በባህረ ሰላጤው በተለይም በካውንስሉ አባል አገሮችና በኳታር መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ፈረንሣይ፣ ኩዌት፣ አሜሪካና ሌሎችም ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ለጊዜው መፍትሔ አልተገኘም፡፡
ሆኖም ኳታርን ከጎረቤቶቿ ያጣላትንና ከኳታር ቴሌቪዥን ጣቢያ ተወስዷል ተብሎ በፓን ዓረብ ስካይ ኒውስና በዓረቢያ ቴሌቪዥን የተላለፈው አወዛጋቢና ሐሰተኛ የተባለው ዜና በኢንተርኔት ጠላፊዎች የተቀነባበረ መሆኑን የሚያጠናክር ዘገባ፣ ዋሽንግተን ፖስት ሰሞኑን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡
እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ የኳታር ዜና አገልግሎትን በመጥለፍ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከፍተኛ የኤምሬትስ ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል፡፡ ይህንንም ኳታር የገለጸችው፣ ‹‹የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የኳታር ዜና አገልግሎትን በመጥለፍ ወንጀል በመሳተፍ ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሷል፤›› በሚል ነው፡፡
የኳታር ዜና አገልግሎትንና ማኅበራዊ የዜና ገጾችን ጠለፋ ያቀነባበረችው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ናት መባሉን የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አንዋር ጋርጋሽ ‹‹ሐሰት›› ቢሉትም፣ የኳታር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በሰጠው መግለጫ፣ ‹‹የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያለምንም ጥርጥር የኢንተርኔት ጠለፋ ወንጀል መፈጸሙን ያረጋገጠ ነው፤›› ብሏል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተሩ ሼክ ሰይፍ ቢን አህመድ አል ታኒ እንደሚሉት፣ ወንጀሉ ዓለም አቀፍ ሕግ መጣሱን ከማሳየቱ በተጨማሪ በባህረ ሰላጤው የትብብር ካውንስል አባል አገሮች መካከል የተደረጉ የሁለትዮሽና የቡድን ስምምነቶች፣ ከዓረብ ሊግ፣ ከኢስላሚክ ኮኦፖሬሽን እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ካውንስሉ ያደረገውን ስምምነትም ወደ ጎን ያለ ነው፡፡ በመሆኑም የኳታር መንግሥት ምርመራ እያካሄደ ሲሆን፣ የመንግሥት ዓቃቢያንነ ሕግም በአገርና በውጭ ሕጋዊ ዕርምጃ ለማስወገድ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ቀድሞውንም የኢንተርኔት ጠለፋ ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ የኳታር ኢሚርም በኢራን፣ በአሜሪካም ሆነ በሐማስ ላይ የሰጡት መግለጫ የለም፤›› ሲል የኳታር መንግሥት ያሳወቀ ሲሆን፣ ዋሽንግተን ፖስትም በጠለፋው የተሳተፉ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣናት ናቸው ብሏል፡፡ ይህን የተቃወሙት የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ጋርጋሽ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በጉዳዩ እጁ የለበትም ብለዋል፡፡
ኳታር የአገሪቱ ኢንተርኔት መረብ ተጠልፎ እንደነበር የአሜሪካ ደኅንነት ቢሮ ጠይቃ የነበረ ሲሆን፣ ዘገባው ያሠፈረውም የደኅንነት ቢሮው ባደረገው ምርመራ እ.ኤ.አ. በግንቦት 2017 ማብቂያ የኳታር ኢንተርኔት መረብ ከመጠለፉ አንድ ቀን አስቀድሞ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣናት ስለጠለፋው ዕቅድ መክረው እንደነበር ነው፡፡ ባለሥልጣናቱ የኳታርን ኢንተርኔት ስለመጥለፍ መክረዋል በተባለ ማግሥት ደግሞ በኳታር ላይ የኢንተርኔት ጠለፋው ተከናውኗል ይላል ዘገባው፡፡
ባለሥልጣናቱ ግን በዘገባው ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በራሷ የኢንተርኔት ጠለፋ ማካሄዷን ወይም ከፍላ ማሠራቷ እንዳልተገለጸ፣ ከአሜሪካ ደኅንነት ቢሮ ተገኘ ስለተባለው መረጃ ከቢሮው ማረጋገጫ የሰጠ አለመኖሩን በክፍተትነት አንስተዋል፡፡
ግንኙነታቸውን ከኳታር ጋር ያቋረጡ የዓረብ አገሮችን ለማስማማት የተጀመረው ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈተና እየገጠመው ይገኛል፡፡ በጆርጅ ማሶን ዩኒቨርሲቲ የግጭት አፈታት ፕሮፈሰር መሐመድ ቸርካው ለአልጄዚራ እንደገለጹት፣ ዋሽንግተን ፖስት ይዞት የወጣው ዘገባ በባህረ ሰላጤው አገሮች ውስጥ ባለው ውጥረት ላይ ሌላ ውጥረት የጨመረ ነው፡፡ በአገሮቹ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመቀበልም ሆነ አዎንታዊ አመለካከት ለመገንባት እንዴት እንደሚቻልም ግራ የሚያጋባ ነው ብለው፣ እስካሁን ባለው ሒደት በአካባቢያዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግር እየገጠማቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያና አጋሮቿ በኳታር ላይ ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ መጣላቸው፣ ውጤታማ ድርድር ሊያስገኝ እንደማይችል በአውሮፓ ኅብረት እንግሊዝን የወከሉት ዳንኤል ሃናን ይናገራሉ፡፡ በባህረ ሰላጤው አገሮች መካከል የተፈጠረው ቀውስ በኳታር ላይ የተጣለው ማዕቀብ ካልተነሳ መፍትሔ እንደማያገኝ በመናገር፣ ‹‹ለብሔራዊ ሉዓላዊነትና ለፕሬስ ነፃነት ክብር የሚሰጥ መፍትሔ በአፋጣኝ መገኘት አለበት፤›› ብለዋል፡፡
በኳታር ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በአስቸኳይ ማንሳት ለንግግር መንገድ ይከፍታል ያሉት ሃናን አያይዘውም፣ ‹‹ጠመንጃ ግንባር ላይ ተደግኖ ድርድር ማካሄድ አዳጋች ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዥን ለ ድሪያን፣ በኳታርና በአራት ዓረብ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከኩዌት ጋር መክረዋል፡፡ በአቡዳቢ በነበራቸው ቆይታም አገሮቹ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዲያረግቡና ስምምነቶችም በተመቻቸ ድባብ እንዲደረጉ ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከአቡዳቢ በተጨማሪ ኳታርና ሳዑዲ ዓረቢያም ተጉዘው ነበር፡፡ ኩዌት የጀመረችውን አገሮቹን የማግባባት ሥራ ለመደገፍ ወደ ኩዌት ያቀኑት የፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በኳታርና በአራት የዓረብ አገሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መክረዋል ተብሏል፡፡
ኳታር ራሷን ለመከላከል ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) መውሰድ እንዳለባትም ተነግሯል፡፡
የዓለም አቀፍ ሕግ ኤክስፐርቱ ቶቢ ኪድማን እንደሚሉት፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ሦስት የዓረብ አገሮች በኳታር ላይ የጣሉት ማዕቀብ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለውም፡፡ አገሮቹ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማደስ ያስቀመጡት ጥያቄም እንዲሁ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና አጋሮቿ ኳታር አልጄዚራን ጨምሮ፣ ‹‹ዓረቢያ 21፣ ራሳድ፣ አል ዓረቢያ አልጃዲድና ሚድል ኢስት አይ›› የተባሉትን መገናኛ ብዙኃን እንድትዘጋ፣ ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንድታቋርጥና አሜሪካ ከጣለችው ማዕቀብ ጋር የተስማማ የንግድ ግንኙነት እንዲኖራት፣ ከሙስሊም ብራዘርሁድ፣ ከአይኤስና ከሒዝቦላህ ጋር አላት የሚባለውን ግንኙነት እንድታቋርጥ የሚሉትን ጨምሮ 13 ጉዳዮችን እንድትፈጽም ጥያቄ ካቀረቡ የሰነበቱ ሲሆን፣ ኪድማን ይህንን አግባብ አይደለም ይሉታል፡፡
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረትም ሳዑዲ ዓረቢያና አጋሮቿ ከኳታር የጠየቋቸው 13 ፍላጎቶች፣ ሕገወጥና ለቅጣት የታለሙ ናቸው ሲሉም ገልጸዋቸዋል፡፡ ጉዳዩ በአይሲሲ መታየት እንዳለበት፣ ከዚህ ሲያልፍም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ሊደርስ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡