ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በሚደረገው ሕገወጥ ስደት ብዙዎች ባህር ውስጥ ሰምጠው ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱትን እንደ ኮንትሮባንድ ዕቃ ጭነው ባህር የሚያቋርጡ ጀልባዎች በማዕበልና በጭነት ብዛት የመስመጣቸው ዜናም በየጊዜው ይሰማል፡፡ ዕድል ቀንቷቸው ከሞት የተረፉ ወደ አውሮፓ ይገባሉ፡፡ ከዚህ በፊት ግን እንደ እሳት የሚፋጀውን የሰሀራ በረሀ ማለፍ ግድ ነው፡፡
በሰሀራ በረሀ በመርዛማ እንስሳት ተነድፈው፣ በአውሬ ተበልተው አልያም በተለያዩ የበረሀ በሽታዎች ተይዘው የጀመሩትን ጉዞ በሞት የሚያቋርጡ ብዙ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ያለውኃ ከአንድ ሳምንት በላይ በሕይወት ሊቆይ አይችልም፡፡ ለዚህም የአብዛኛዎቹ ስደተኞች ዋናው ስንቅ ውኃ ነው፡፡ በበረሀ በሚደረግ ጉዞ ውኃ እንደ ውድ ማዕድን ነው፣ ጠብታውም ልዩ ትርጉም አለው፡፡ በበረሀ ነፍስ የሚዘራውን ውኃ ጥም እስኪቆርጥ መጠጣትም አይታሰብም፡፡ እንዲያም ሆኖ እስከ ጉዟቸው መቋጫ ድረስ ላያደርሳቸው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡
በዚህ መካከል በውኃ ጥም ለሞት የሚዳረጉ ብዙ ናቸው፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ 40 ሰዎች በሰሀራ በረሃ በውኃ ጥም መሞታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የሰው ልጅ ምግብ ሳይመገብ ለሦስት ሳምንታት መቆየት እንደሚችል፣ በህንዱ የነፃነት ታጋይ በማህተመ ጋንዲ ታሪክ ማወቅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ያለውኃ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየት እንደማይችሉ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡
ከመሬት ውጪ ባሉ ፕላኔቶች ሰዎች መኖር ይችላሉ አይችሉም? የሚለውን ለመገመት ሳይንቲስቶች ውኃን እንደ አንዱ መስፈርት ያቀርባሉ፡፡ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የአዋቂዎች አካል በውኃ የተሞላ ሲሆን፣ በሰውነት ውስጥ ያሉ ህዋሳት ሚናቸውን እንዲጫወቱም ወሳኝ ነው፡፡ በመገጣጠሚያ አካባቢ ላሉ አጥንቶችም እንደ ቅባት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ውኃ የሰውነት ሙቀትን ይቆጣጠራል፣ አላስፈላጊ ነገሮችን በተለያዩ መንገዶች እንዲወገዱ ያደርጋል በሰው ልጆች ጤና ላይ ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
በመሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ኪሎሜትር ውኃ እንዳለ ይነገራል፡፡ 97 በመቶ የሚሆነው ጨዋማ፣ 2.1 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በምድር ዋልታ አካባቢዎች የበረዶ ግግር ሆኖ ይገኛል፡፡ ንፁህ ውኃ ተብሎ አገልግሎት ላይ እየዋለ የሚገኘው ከአጠቃላዩ አንድ በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ለግብርና ሲሆን፣ ከግብርና ቀጥሎ አብዛኛው የውኃ መጠን ለሀይል ማመንጫነት ይውላል፡፡
የቀረው ለመጠጥና ለቤት ውስጥ መገልገያነት የሚውለው ሲሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች በቂ አለመሆኑና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ንፁህ ውኃ አንደማያገኝ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ በ2015፣ በዓለም 2.1 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የንፁህ ውኃ አቅርቦት አልነበራቸውም፡፡ ከእነዚህ መካከል 263 ሚሊዮን የሚሆኑት ንፁህ ውኃ ለማግኘት ቢያንስ የ30 ደቂቃ መንገድ ከቤታቸው ርቀው ይሄዳሉ፡፡ 844 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ንፁህ ውኃ ማግኘት የሚያስችላቸው መሠረተ ልማት አልተሟላላቸውም፡፡ 159 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የሚጠጣ ውኃ የሚያገኙት ከምንጭና ከኩሬ ነው፡፡
‹‹ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ወርልድስ ወተር 2017›› በሚል በቅርቡ በወተር ኤድ ይፋ የተደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ፣ 51 በመቶ የሚሆኑ በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንፁህ ውኃ አያገኙም፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ፣ በቁጥር ሲሰላ 40.9 ሚሊዮን የንፁህ ውኃ ችግር ያለባቸው የገጠር ነዋሪዎች መገኛ በመሆን ከህንድ፣ ከቻይናና ከናይጄሪያ ቀጥላ ከቀዳሚዎቹ ችግር ካለባቸው አገሮች በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በመቶኛ ሲሰላ ደግሞ በሪፖርቱ ከተካተቱት አገሮች በ15ኛ ደረጃ ላይ ተመድባለች፡፡
በንፁህ ውኃ ተደራሽነት ረገድ ከመጨረሻዎቹ አሥር አገሮች ተርታ የተሰለፈችው ኢትዮጵያ ትልቅ መሻሻልን እያሳየች መሆኑም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ እ.ኤ.አ. 2000 በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የነበረው የንፁህ ውኃ ተደራሽነት 18.9 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ 48.6 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል፡፡ ይህም ባለፉት 15 ዓመታት በገጠር የነበረው የንፁህ ውኃ ተደራሽነት በ29.7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የሚያመለክት ነው፡፡
በዚህ መሠረትም አገሪቱ የገጠር የንፁህ ውኃ አቅርቦታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ካሻሻሉ 10 የዓለም አገሮች ውስጥ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ፓራጓይ፣ ማላዊ፣ ሌዎ ፒፕልስና ካምቦዲያ ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከውኃ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ለውጥ ማስመዝገብ ቢቻልም አሁንም በርካታ አገሮች ከፍተኛ የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር አለባቸው፡፡ ችግሩ በይበልጥ ጐልቶ የሚታየውም በአፍሪካ ነው፡፡
በአንጎላ ገጠራማ አካባቢዎች 71.8 በመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎች ንፁህ ውኃ አያገኙም፡፡ ይህም አንጎላን ከፍተኛ የንፁህ ውኃ ችግር ካለባቸው የዓለም አገሮች ተርታ የመጀመሪያዋ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ኮንጐ 68.8 በመቶ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ 68.5 በመቶ በመሆን በተከታታይ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል፡፡
ከንፁህ ውኃ አቅርቦት ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ችግሮች መካከል የአካባቢና የግል ንፅህና ጉዳይ ነው፡፡ በቂ ውኃ በሌለባቸው ቦታዎች የግልና የአካባቢ ንፅህና ከቅንጦት ሊቆጠር ይችላል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች እጃቸውን በሳሙና የመታጠብ ዕድሉ ያላቸው ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው፡፡ ከሰሀራ በታች ባሉ አገሮችም ተገቢው የንፅህና መጠበቂያ ግብዓቶች የተሟላላቸው 14 በመቶ ለሚሆኑት ነዋሪዎች ብቻ ነው፡፡
የመፀዳጃ ቤት ችግርም የሪፖርተሩ አካል ነበር፡፡ 4.5 ቢሊዮን የሚሆኑ የዓለም ሰዎች መፀዳጃ ቤታቸው በንፅህና የተያዘ አይደለም፡፡ 892 ሚሊዮን ሰዎች ሜዳ ላይ እንደሚፀዳዱና 600 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የጋራ ሽንት ቤት እንደሚጠቀሙ ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በአገሪቱም ችግሩ በስፋት ይታያል፡፡ በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ከመፀዳጃ ቤት ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች የከፉ ናቸው፡፡ በተለይም ተጨናንቀው በተሠሩ መንደሮች አካባቢ ችግሩ ይበረታል፡፡ ሴፕቲክ ታንኮች በየጊዜው እንዲመጠጡ አይደረግም፡፡ በአቅራቢያ ከሚገኙ ወንዞች ጋር እንዲቀላቀሉ የሚደረጉም አሉ፡፡ ካለው የመፀዳጃ ቤት ችግር ጋር ተያይዞ በላስቲክ ተፀዳድተው ሜዳ ላይ የሚወረውሩ እንዲሁም በየመንገዱ የሚፀዳዱ ያጋጥማሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ዓይነተኛ መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነሱም የተለያዩ ችግሮች እንዳሉባቸው ከወራት በፊት ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ የከተሞች ጤና ማጠናከሪያ ፕሮግራም የዳሰሳ ጥናት ያመለክታል፡፡
ጥናቱ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በሐረር፣ በድሬደዋና በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ሁኔታ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ 335 የሚሆኑ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች በዳሰሳ ጥናቱ ተካተዋል፡፡ 25 በመቶ የሚሆኑት በደቡብ ክልል፣ 20.9 በመቶ በትግራይ፣ 20.6 በመቶ በኦሮሚያ፣ 17 በመቶ በአዲስ አበባ፣ 11 በመቶ በአማራ፣ 4 በመቶ ድሬደዋና 1 በመቶ በሐረር ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡
በጥናቱ መሠረት አብዛኛዎቹ መፀዳጃ ቤቶች ዕድሜ ጠገብና ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ 71 በመቶው የሚሆኑት የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ከ20 ዓመታት በፊት የተገነቡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በጥናቱ የተካተቱት 22 በመቶ የሚሆኑት መፀዳጃ ቤቶች ጥቅም እየሰጡ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ተሠርተው ከዓመት በፊት ሥራ የጀመሩትን ሳይጨምር ሌሎቹ ከፍተኛ የፅዳትና የአጠቃቀም ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡