Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአወዛጋቢው የዕድሜ ጉዳይ

አወዛጋቢው የዕድሜ ጉዳይ

ቀን:

ኬንያ ያስተናገደችው አሥረኛው ከ18 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሐምሌ 5 እስከ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ተካሂዶ ባለፈው እሑድ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ ለምሥራቅ አፍሪካውያኑ ትልቅ ትርጉም የነበረው ይህ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ለኢትዮጵያ የጥሩ ውጤት ማሟሻ ሆኖ ቢጠናቀቅም፣ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ግን መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም፡፡

ከ131 አገሮች የተውጣጡ የዓለም አትሌቶች በተሳተፉበት መድረክ 24 ስፖርተኞችን ያሳተፈችው ኢትዮጵያ በአራት የወርቅ፣ በሦስት ብርና በአምስት የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊየዎችን አስመዝግባ ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡ በሞይ ኢንተርናሸናል የልቀት ማዕከል በድምቀት በተጀመረው በዚሁ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ50 ሺሕ በላይ ኬንያውያን ተመልካቾች በታደሙባቸው የሩጫ ውድድሮች፣ ኢትዮጵያውያኑ በመድረኩ የምንጊዜም ተቀናቃኞቻቸውን በገዛ ሜዳቸው አስከትለው ሲገቡ የታየበት ክስተት በድል አድራጊነት ነፀብራቅ የሚያጎላና የአሸናፊነት ታላቅነት የሚያሳይ አጋጣሚም ነበር፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ የአፍሪካ አትሌቶች በአብዛኛው የተወቀሱባቸው አጋጣሚዎችም ታይተዋል፡፡ ከተለያዩ ዘገባዎችና ከማኅበራዊ ድረ ገጾች ለመረዳት እንደተቻለው፣ የዕድሜ ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖም ሰንብቷል፡፡ አትሌቶቹ የዕድሜ ተገቢነት ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበረው በአብዛኛው ከተክለ ሰውነታቸውና አቋማቸው፣ ካሳዩት የውድድር እንቅስቃሴ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በሌሎች እንደ ማራቶን ባሉ የውድድር ዘርፎች ሳይቀር ተሳትፈው የሚታወቁ በተለይ ከኢትዮጵያ ወገን ‹‹ተካተዋል›› የሚል ሐሜት ውስጥ ውስጡን ሲነገር ሰነብቷል፡፡

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጂሎ የዕድሜን ጉዳይ በተመለከተ ተቋሙ በተገቢው መስፈርት፣ በስፖርተኞቹ ፓስፖርት፣ ከወላጆቻቸው በሚቀርቡ ማስረጃዎች በመታገዝ ዕድሜያቸውን ለማረጋገጥ እንደተሞከረ ነው ያስረዱት፡፡ 

በአንፃሩ ግን ትክክለኛው የዕድሜ መለኪያ ሳይንሳዊ ምርመራ ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ ተችዎችም ያለ ገደብ ከሚያዘንቡት ትችት፣ ስፖርተኞቹንም ያላግባብ ከሚወርድባቸው ወቀሳ ለመታደግ ይቻል እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንደነዚህ የመሰሉ ሻምፒዮናዎች ተልዕኮዋቸው በዋናነት ሜዳሊያ መሆን እንደሌለበትና በቀጣይ ለሚከናወኑ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች በተለይም ለዋናው ቡድን መሠረት መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ መታየት ይኖርበታል የሚሉ አሉ፡፡ ትክክለኛው ዕድሜ ላይ ተመሥርቶ መቅረብ ለአትሌቲክሱ ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ለአትሌቶቹ ትልቅ ጥቅም እንዳለው የሚናገሩት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ ከዚህ ባልተናነሰ ዕድሜያቸው በማይመጥን በተለይ እንደ ማራቶን በመሳሰሉት ውድድሮች ታዳጊ አትሌቶች እንዲሳተፉ የሚደረግበት አግባብ በተለይ በኢትዮጵያ እየተለመደ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከሻምፒዮናው ይልቅ የተወዳዳሪዎች ዕድሜ ጉዳይ ሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ይህ የታዳጊዎች ሻምፒዮና በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) እምነት እንዲያጣ ሆኖም መጠናቀቁ ተነግሯል፡፡ በዚህ ያላበቃው አይኤኤኤፍ ውድድሩ እስከዛሬ በነበረበት እንዳይቀጥልና የሻምፒዮናው ይዘትም ወደ አህጉራዊ ደረጃ ዝቅ ብሎ እንዲከናወን ውሳኔ ላይ መድረሱን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ የዓለም አቀፉ ተቋም ከሚፈቅደው ዕድሜ ገደብ በላይ በሚል የሚያደርገውን ቁጥጥር ያለ ዕድሜያቸው በተለይ በማናጀሮች ተፅዕኖ ትልልቅ መድረኮች እንዲወዳደሩ እየተደረጉ ለሚገኙ አትሌቶችም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተመሳሳይ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊያስቀምጥ እንደሚገባውም ይጠቁማሉ፡፡ ይህንኑ ሕገወጥ አካሄድና አሠራር በተለይ በውድድር ዓመቱ ወደ ኃላፊነት የመጣው የተቋሙ አመራር ጉዳዩን ጠንቅቆ የሚያውቀው እንደሆነ ጭምር ይናገራሉ፡፡

ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አመራር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ታዳጊ አትሌቶች ዕድሜያቸው በማይፈቅድላቸው ትልልቅ ውድድሮች ላይ እንዲወዳደሩ ትልቅ ድርሻ ያላቸው የአትሌት ማናጀሮች ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ፌዴሬሽኑና የአትሌት ማናጀሮች ተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡ ይሁንና ድርጊቱ አሁንም ድረስ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፤›› ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ በመነጋገሪያነቱ የቀጠለውን የዕድሜ ጉዳይ ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረውን የቡድን ስሜት ማምጣት እንደሆነና የዕድሜው ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ ያለውን ችግር በክፍተትነቱ ተወስዶ በሒደት የሚስተካከል እንደሚሆንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኬንያ ከሐምሌ 5 እስከ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎ አድርጎ ለተመለሰው ቡድን፣ ከ340 ሺሕ ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡

ሐምሌ 11 ቀን በኢትዮጵያ ሆቴል ባዘጋጀው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ካበረከተው የገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴና ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እንዲሁም በሥነ ሥርዓቱ የታደሙት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ለልዑካን ቡድኑ የገንዘብ ሽልማት ማበርከታቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...