Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቀን ገቢ ግምት ሳቢያ በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች የንግድ ተቋማት ተዘጉ

በቀን ገቢ ግምት ሳቢያ በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች የንግድ ተቋማት ተዘጉ

ቀን:

   ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ተቃውሞ በተወሰኑ አካባቢዎች የንግድ ተቋማት መዘጋታቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በተነሳው ተቃውሞ በአምቦ፣ በወሊሶና በጊንጪ ከተሞች ነጋዴዎች የንግድ ተቋማቸውን ዘግተዋል፡፡

የቀን ገቢ ግምት መካሄድ የነበረበት በየሦስት ዓመቱ እንደነበር የገለጹት አቶ አዲሱ፣ ዘንድሮ የተካሄደው ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በመሆኑ ነጋዴዎች ግራ በመጋባታቸው በተለያዩ አካባቢዎች ጥያቄ እያስነሳ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ ጨፌ (ምክር ቤት) ለሚቀጥለው ዓመት ከ5.8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንዳፀደቀ የገለጹ ሲሆን፣ ክልሉ ከግብር መሰብሰብ የቻለው ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ እንደማይበልጥ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያለው የመሠረተ ልማት ፍላጎትና የሚሰበሰበው ገቢ የተጣጣመ እንዳልሆነ የገለጹት የቢሮ ኃላፊው፣ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ከግብ ለማድረስ ግብር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ያላግባብ እንዲከፍሉ የተጠየቁ ነጋዴዎች ካሉ ክልሉ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አቋቁሞ ችግሩን ለመፍታት እየሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከቀን ገቢ ግመታ ጋር ተያይዞ ባለፈው ሳምንት በአምቦ ከተማ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ በሁለት የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የዚህ አካል የሆነው ቅሬታ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች ከተሞች በመጠኑም ቢሆን እየተስፋፋ እንደመጣ የተናገሩት አቶ አዲሱ በወሊሶ፣ በጊንጪና በአምቦ ከተሞች  ሆቴሎች፣ ትልልቅ የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ መደብሮችና ሌሎች ተቋማት መዘጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው የመንግሥት መዋቅሮች ጋር በመቀራረብ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህ ተቃውሞ ወደ ሌሎች ከተሞች እንዳይስፋፋ የክልሉ መንግሥት እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በሰላማዊ መንገድ መሆን እንዳለባቸው፣ ቅሬታ ያለው አካልም በሕጋዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ተገን አድርገው ሌላ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ አካላት ካሉ የክልሉ  መንግሥት ዕርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቀዋል፡፡

ይህን ዓይነት ተቃውሞ ማቅረብ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚበልጥ በመሆኑ በተገቢ መንገድ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል አሳስበዋል፡፡

ትልልቅ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባቸው እንደ አዳማ ያሉ ከተሞች በአሁኑ ወቅት ያለምንም ችግር የንግድ ሥራቸውን እያካሄዱ እንደሆነ የገለጹት አቶ አዲሱ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በሕጋዊ መንገድ በመክፈል የክልሉን ሁለንተናዊ ዕድገት ማፋጠን ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ከዓመት በፊት አዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን በአንድ ላይ ከሚያካትተው የጋራ ማስተር ፕላንና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተከስቶ በነበረው  ተቃውሞና ሁከት፣ የበርካቶች የሰው ሕይወት ከመጥፋቱ በላይ ከፍተኛ ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...