Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በባንክ ሒሳብ መግለጫ ላይ ሰርኩላር ወጣ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ሥራ እንደ መረጃ ምንጭነት ሲጠቀምበት የነበረው የግብር ከፋዮች የባንክ ሒሳብ መግለጫ፣ በንግድ ማኅበረሰቡ ላይ የፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታት ያስችላል የተባለ ሰርኩላር ወጣ፡፡

ከዚህ ቀደም ለቅሬታው መፍትሔ ለመስጠት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ሰርኩላሩ ሊፀድቅ ችሏል፡፡

የባንክ ሒሳብ መግለጫን መሠረት በማድረግ ሌሎች መረጃዎችን ወይም ግኝቶችን ሳይገናዘቡ ግብር ወይም ታክስ የተወሰነባቸው ግብር ከፋዮች፣ አሠራሩ አግባብ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሲያቀርቡ ነበር፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የንግድ ሥራዎችን ለማከናወን የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከወዳጅ ወይም ከዘመድ ብድር እንደሚወስዱ፣ ነገር ግን ይኼ ብድር ወደ ባንክ አካውንታቸው ሲገባ ከሽያጭ እንደተገኝ ገቢ ስለሚቆጠር ግብርና ታክስ እንደሚወሰንባቸው ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ዕቁብ ሲደርሳቸው የሚቀበሉት ገንዘብ ቀደም ሲል በሽያጭ ገቢ ላይ ያሳዩትና ግብር ወይም ታክስ የከፈሉበት ሆኖ ሳለ፣ የዕቁቡ ገንዘብ  በባንክ ሒሳብ ገቢ ሆኖ ሲታይ እንዳልተገለጸ ገቢ ተይዞ በድጋሚ ግብር ወይም ታክስ እንዲከፍሉበት እንደሚጠየቁም በመግለጽ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር፡፡

ሌላው አስመጪዎች ከውጭ ለሚያስገቧቸው ዕቃዎች ኤልሲ በተለያዩ ባንኮች፣ እንዲሁም  አንዱ ባንክ ውጭ ምንዛሪ ማግኘት ካልቻሉ ሌላ ባንክ ሄደው ሌላ ኤልሲ እንደሚከፍቱ፣ ገንዘቡን ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ በሚያስተላልፉበት ጊዜ ያላግባብ ከሽያጭ የተገኘ ገቢ ሆኖ እንደሚመዘገብባቸው ቅሬታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ባለሥልጣኑ ባደረገው ማጣራት የባንክ መግለጫን እንደ መረጃ መጠየቅ ላይ አንድ ወጥ አሠራር እንደሌለና የተጠቀሱት ችግሮችም እንዳሉ አረጋግጧል፡፡

በዚህም መሠረት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በባንክ መግለጫ መሠረት በግብር ከፋዮች (ግለሰብና ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች) ላይ ከዚህ ቀደም የተወሰነ፣ በማናቸውም የአፈጻጸም ደረጃ የሚገኝ የተለያየ የግብር አወሳሰን እንደገና ተጣርቶና ተስተካክሎ እንዲወሰን ተወስኗል፡፡ በድጋሚ በሚወሰንበት ወቅትም በባንክ ሒሳብ መግለጫው ተገኘ የተባለው በግብር ከፋዩ የሒሳብ መግለጫ በሙሉ ያልተገለጸ ገቢና ግብር ሊከፈልበት የሚገባ ገቢ ስለመሆኑ በኦዲተር በማስረጃ ካልተረጋገጠ፣ በዚህ መረጃ መሠረት ቀድሞ የተጣለው ግብር ወይም ታክስ ሙሉ በሙሉ ቀሪ እንዲደረግ የባለሥልጣኑ ሰርኩላር ደንግጓል፡፡

ቀደም ሲል የግብርና የታክስ ውሳኔ ደርሷቸው ክፍያ የፈጸሙ በዚህ ውሳኔ መሠረት የግብር አወሳሰኑ በድጋሚ ሲታይ መክፈል ካለበት ጋር ሲነፃፀር ክፍያው እኩል ከሆነ ወይም በልጦ ከተገኘ የከፈሉት የመጨረሻ እንዲሆን፣ ክፍያው አንሶ ከተገኘ ግን በልዩነት የሚፈለግባቸውን ግብር ወይም ታክስ፣ ወለድና መቀጮን ጨምሮ እንዲከፍሉ ያዛል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የሚተላለፉ የግብር ወይም የታክስ ውሳኔዎች ደግሞ በአዲሱ አሠራር መሠረት እየተፈተሹ ውሳኔ ይሰጥባቸዋል ተብሏል፡፡ መረጃ ሊቀርብበት ያልቻለ በሽያጭ ገቢ ሳይመዘገብ በባንክ የተገኘ ገንዘብ በንግድ ሥራ እንደተገኘ ገቢ ተቆጥሮ፣ ግብርና ታክስ እንዲከፈልበት እንደሚደረግበትም ሰርኩላሩ ይገልጻል፡፡

ሰርኩላሩ በውል የተያዙ የግለሰብ ብድሮች እንደ ገቢ ከመወሰናቸው በፊት ተያያዥ መረጃዎችን መመልከት እንደሚያስፈልግም ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ባህል በተለምዶ ውል የሌላቸው የግለሰብ ብድሮች ሲያጋጥሙ ተጨማሪ መረጃዎች፣ ማለትም ብድሩ ሲከፈል ከባንክ ወጪ የተደረገበትን ማስረጃ ማየት እንደሚያስፈልግ በሰርኩላሩ ተጠቅሷል፡፡

ከ ኤልሲ ጋር በተያያዘ ግብር ከፋዮች አንዱ ባንክ የከፈቱትን ኤልሲ ሰርዘው ሌላ ባንክ በሚከፍቱበት ጊዜ፣ መጀመርያ ሲከፍቱ ከነበረበት ባንክ ኢንሹራንስ እንዲሰረዝ ጥያቄ ያቀረቡበትን መረጃ እንዲያቀርቡ ያዛል፡፡ በተጨማሪም ከዕቁብ የተገኘ ገንዘብን በተመለከተ፣ ነጋዴው ገንዘቡ በትክክል ከዕቁብ የተገኘ ገቢ መሆኑን በዕቁብ ኮሚቴዎች ማስረጃ ማረጋገጥ ከተቻለ፣ በቀጣይ ከዕቁብ የተገኘው ገቢ ለግብር ከፋዩ ካፒታል ማሳደጊያነት ታሳቢ የሚደረግ መሆኑን ግንዛቤ እንዲያዝም ያስገነዝባል፡፡ በሌላ በኩል ገቢው ዕቁብ መሆኑ ከተረጋገጠ በየወሩ የሚከፈለው የዕቁብ ክፍያና በብድር መልክ የተሰበሰበው ዕቁብ መልሶ ሊጣጣ የሚችልበት ሁኔታ በመኖሩ፣ ይኼው ቀጥታ እንደ ሽያጭ ገቢ ሊታይ የሚችልበት ሁኔታ አለመኖሩ ግንዛቤ መወሰድ አለበት ሲል ሰርኩላሩ ያብራራል፡፡

በመጨረሻም ሰርኩላሩ የግብር ከፋዮች የባንክ አካውንት ለባንክ ሥራና ለግል ጉዳይ እንቅስቃሴ ተለይቶ መከፈት እንዳለበት ያሳስባል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች