Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አኅጉራዊው የቱሪዝም ፍሰት ለአገሮች ኢኮኖሚ የኋላ ደጀንነቱን እያሳየ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከዓለም አቀፍ አሥር ጎብኚዎች አራቱ አፍሪካውያን ናቸው
  • አዲስ አበባ ከሆቴል ፎረም የ5.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች

ከጥቂት ቀናት በፊት ይፋ የተደረገውና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ (UNCTAD) የተሰናዳው ሪፖርት፣ የአፍሪካ ቱሪስቶች ለአኅጉሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ እያበረከቱ የሚገኙትን አስተዋጽኦ ተንኗል፡፡ አፍሪካያውን ቱሪስቶች በሚጎበኟቸው አገሮች የኢኮኖሚ ደጀን በመሆን ለሥራ ዕድልና ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ማደግ ሚናቸው እየጎላ እንደመጣም ሪፖርቱ አትቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በመገኘት ሪፖርቱን ያቀረቡት (በተመድ) የንግድና ልማት ጉባዔ የአፍሪካ ክፍል ዋና ኃላፊ ጁኒየር ዴቪስ (ዶ/ር) ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርጉ እንዳስታወቁት ከሆነ፣ እያደገ የመጣው የአፍሪካ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከ21 ሚሊዮን በላይ ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል አስገኝቷል፡፡ ይህም ማለት ከእያንዳንዱ 14 የሥራ ዕድል ውስጥ አንዱ በቱሪዝም መስክ የተፈጠረ እንደሆነ ያመላክታል ብለዋል፡፡ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥም 12 ሚሊዮን ተጨማሪ የሥራ ዕድሎች ከዚሁ ከቱሪዝም ዘርፍ እንደሚመነጩ የተመድ ሪፖርት ይተነብያል፡፡

ይኼ እንዲሆን ምንክንያት ከሆኑት መካከል፣ ዜጎች በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚያደርጉት ጉብኝት አንዱ የሚጠቀስ ነጥብ ነው፡፡ ተመድ ‹‹Tourism for Transformative and Inclusive Growth›› በተሰኘው ሪፖርቱ ውስጥ በጥናት አጣቅሶ እንዳሰፈረው፣ የአፍሪካ አገሮችን ከጎበኙ አሥር ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ውስጥ አራቱ አፍሪካውያን ሆነዋል፡፡

በአፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በኩል የስድስት በመቶ እንዲሁም በቱሪዝም ገቢ ረገድ የዘጠኝ በመቶ ዓመታዊ ዕድገት እንዲታይበት ያስቻሉ ከተባሉት ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ አፍሪካውያን በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚያደርጉት ጉብኝትና ዝውውር ነው፡፡ ምንም እንኳ አፍሪካውያን በአኅጉራቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴና ጉብኝት አስዋጽኦው እየጎላ መምጣቱ ቢነገርለትም፣ በአንፃሩ ከሌሎች አኳያ ሲታይ ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ ለአብነት ጁኒየር ዴቪስ የሚጠቅሱት በአውሮፓ አገሮች መካከል አውሮፓውያኑ ይጎላሉ፡፡ ከአውሮፓ ዜጎች አምስቱ አራቱ እዚያው አውሮፓ ውስጥ በመዘዋወርና በመጎብኘት የአኅጉሩን የቱሪዝም እንቅስቃሴ አጠናክረዋል ያሉት ዴቪስ፣ በአፍሪካ ይህ አነስተኛም ቢሆን እያደገ መምጣቱን ግን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአፍሪካ በተመዘገበው የ52 በመቶ የአገልግሎት ወጪ ንግድ ውስጥ ከግማሽ በላዩ የተመዘገበው ከቱሪዝም ዘርፍ መሆኑም ሌላኛው አወንታዊ ጎኑ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገሮችን የቅርብ ጊዜ መረጃ ማካተት እንዳልተቻለ ዴቪስ ቢያብራሩም፣ በአፍሪካ ከቱሪዝም ዘርፍ ብቻ የ47 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊመዘገብ ችሏል፡፡

ምንም እንኳ የዚህን ዓመት የተጠቃለለ የቱሪዝም ዘርፍ አፈጻጸም መረጃ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሪፖርተር ለማግኘት ሞክሮ፣ ገና እየተጠናቀረ እንደሚገኝ ቢገለጽለትም ከዘርፉ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ፣ ከ685 ሺሕ በላይ የውጭ ጎብኝዎች ከ2.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይሁንና ለ2009 በጀት ዓመት የተያዘው አጠቃላይ የገቢ መጠን ከ3.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን መታቀዱም ይታወሳል፡፡ ይሁንና እንዲህ ያለውን ዓይነት ወቅታዊ መረጃ የተመድ ተቋማት ማግኘት እንዳልቻሉ እየጠቀሱ ነው፡፡ ዴቪስ እንደሚገልጹት፣ ኢትዮጵያንና ሌሎችም አገሮች ሪፖርቱ በሚጠናቀርበት ወቅት የተጠየቋቸውን የዓምና እና የካቻምና የዘርፉን መረጃዎች ሊያቀርቡ ባለመቻላቸው ምክንያት የሪፖርቱ ዳራ እ.ኤ.አ. እስከ 2014 የነበረውን የአፍሪካን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማሳየት ላይ ብቻ እንዲገደብ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

     የመረጃው አለመካተት ደግሞ በአፍሪካ የታዩ ወቅታዊ ክስተቶች በዘርፉ ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ በሚገባ ለማሳየትና ለመተንተን አለማስቻሉ አንዱ ጉድለት ሆኗል፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ የተከሰተው ሕዝባዊ አመጽ፣ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የነበረውን አሉታዊ ጫና በዝርዝር ማሳየት ባይቻልም፣ በርካታ አገሮች የጉዞ ክልከላዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን ሲያወጡ መታየታቸው ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የሪፖርቱ አቅራቢ ገልጸዋል፡፡

ይህም ቢባል ግን በአፍሪካ የተከሰቱ ፖለቲካዊ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ የበሽታ ወረርሽኞችና ሌሎችም ክስተቶች በጅምላ አፍሪካን የጎዱበት ክስተት መስተናገዱን ዴቪስ ሲጠቅሱ ዋቢ ያደረጉት የኢቦላ ወረርሽኝን ነበር፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው ይህ በሽታ፣ በዋናነት የጎዳው ሦስት አገሮችን ቢሆንም ከደቡብ እስከ ምሥራቅ አፍሪካ የተዛመተ የጎንዮሽ ተፅዕኖ አሳድሮ አልፏል፡፡ በሽታው ባልታየባቸው አገሮች ውስጥ ሳይቀር ቱሪስት አመንጪ አገሮች የጉዞ ዕቀባ በመጣል የቱሪዝም ዘርፉን ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል ዕርምጃ ሲወስዱ ታይተዋል፡፡

በኬንያ የተደረጉ የአሸባሪዎች አደጋ ወይም በናይጄሪያ በአሸባሪው ቦኮሐራም ወይም በሶማሊያ የተደረጉ የአልሻባብ ጥቃቶች መላ አፍሪካን የሚመለከቱ በማስመሰል የሚወሰዱ የጉዞ ማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች የአፍሪካ ቱሪዝም ዘርፍ የሚፈታተኑ ተደርገው ቢታሰቡም፣ ቱሪስቶች ግን በዚህ ሁሉ ሳይሸበሩ እየመጡ እንደሚገኙ ዴቪስ አጣቅሰዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን ቱሪስቶች እንደልብ ወደ አፍሪካ እንዳይመጡ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ከሚነገርላቸው ውጫዊ ምክንያቶች (በቀጥታ ከዘርፉ ጋር ተያያዥ ያልሆኑ ጉዳዮች) መካከል፣ የአካባቢ ብክለት፣ የመሬት ባለቤትነት መብት በአግባቡ አለመከበር፣ የመሬት ተጠቃሚነት፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት አለመዳበር፣ እንዲሁም ለዘመናት የቆዩት የበሽታና የግጭት ክስተቶች ይገኙበታል፡፡ እንዲህ ያሉትን ጨምሮ ሌሎችም የዘርፉ ድክመቶች ተደራርበው የአኅጉሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ከዝቅተኛ ደረጃ በመነሳት ላይ የሚገኝ ታዳጊ ዘርፍ እንዲሆን አስገድደውታል፡፡

በመሆኑም እንደ ዛምቢያና ሩዋንዳ ያሉ የባህር በር የሌላቸው አገሮች ከሚያስተናግዷቸው የውጭ ጎብኚዎች ውስጥ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚደርሱት ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከሚመጡ ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻሉን ዴቪስ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ሩዋንዳ ያሉት አገሮች ከኮንፈረንስ ቱሪዝም በተለይ ተጠቃሚ በመሆን የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ የአፍሪካውያን የገቢ መጠን እየጨመረ መምጣቱም በእርስ በርስ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለማበርከት የተጫወተው ሚና እንደሚጎላ ተብራርቷል፡፡ እንደ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሞሪሺየስ ያሉ አገሮች በቱሪዝም ዘርፍ ውስ ጥራት ያላቸውን የመሠረተ ልማት አውታሮች በመገንባት ረገድ በአፍሪካ ጉልህ ኢንቨስትመንት በማድረግ ላይ የሚገኙ አገሮች ተብለዋል፡፡

በአንፃሩ ከአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደ ሲሺዬልስ፣ ካቦ ቨርዴ እንዲሁም ሞሪሺየስ ከአፍሪካ አገሮች ዋና ዋና የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ አገሮች ግንባር ቀደምቶቹ ሆነዋል፡፡ ሲሺዬልስ ከኢኮኖሚዋ 61.5 በመቶውን ድርሻ የያዘው ቱሪዝም ነው፡፡ ካቦ ቨርዴና ሞሪሺየስም በ43.4 በመቶና በ26.7 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ ተከታዮቹን ደረጃዎች በመያዝ በአፍሪካ ተቀዳሚ የዘርፉ ተጠቃሚ አገሮች ሆነዋል፡፡ በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርፆችን በዓለም ያስመዘገቡ፣ ነገር ግን እንደሚገባቸው ዘርፉን ያልተጠቀሙበትና ያላስተዋወቁ አገሮች ለኢኮኖሚያቸው የሚያበረክተውን ድርሻ አነሳ እንዳደረገው ከሪፖርቱ መረዳት ይቻላል፡፡    

በሌላ በኩል በአፍሪካ እየተዘወተረ የመጣው የሆቴሎች ኢንቨስትመንትን የተመለከተው ስብሰባም አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቀሷል፡፡ በአፍሪካ የሆቴል ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ መደበኛ ጉባዔዎችን የሚያሰናዳው ቤንች ኤቨንትስ የተባለው የእንግሊዙ ኩባንያ ባወጣው ሪፖርት መሠረትም፣ ጉባዔውን ያስተናገዱ አገሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከ16.8 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ አትቷል፡፡

ቤንች ኤቨንትስ ግራንት ቶርንቶን በተባለ አጥኚ ተቋም አማካይት ባስጠናው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ አዲስ አበባ እ.ኤ.አ. በ2014 እና በ2015 በተከታታይ ባስተናገደችው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም አማካይነት ብቻ የ2.4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ፣ ከሌሎች ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታዎች አኳያ ያገኘችው ገቢ ከ3.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ አዲስ አበባ ጨምሮ ካዛብላንካ፣ ናይሮቢ (ሁለት ጊዜ ጉባዔውን አስተናግዳለች)፣ አዲስ አበባ (ሁለት ጊዜ ጉባዔውን አስተናግዳለች)፣ ሎሜና ኪጋሊ ከተሞችም በስብሰባው አማካይነት በተፈጠሩ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ምንጮች የየራሳቸውን ገቢ ማግኘት የቻሉ ከተሞች ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች