- በ2009 በጀት ዓመት ከ5.4 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦለት ነበር
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በ2010 በጀት ዓመት 101 ፕሮጀክቶችን ለመተግበር መነሳቱንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የ6.38 ቢሊዮን ብር በጀት እንዳፀደቀለት አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ በ2010 በጀት ዓመት ለማከናወን ካቀዳቸው 101 ፕሮጀክቶች ውስጥ 30ዎቹ ካለፈው በጀት ዓመት የዞሩ ናቸው፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ ከሆነ፣ በበጀት ዓመቱ 32 አዳዲስ የመንገድ ግንባታዎችን የሚያከናውን ሲሆን፣ ከ20/80 እና ከ40/60 የኮንዶሚኒየም ግንባታዎች ጋር የተያያዙ 18 የመንገድ ሥራዎችንም እንደሚገነባ አስታውቋል፡፡ የተጓተቱ የስምንት መንገዶች ግንባታም በዚሁ በጀት ዓመት ከሚከናወኑ ሥራዎች ውስጥ ተካትተዋል፡፡
በያዝነው በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለባለሥልጣኑ 5.1 ቢሊዮን ብር የሚለቅለት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 4.83 ቢሊዮን ብር ለካፒታል በጀት፣ 264.29 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለመደበኛ በጀት የሚውል ነው፡፡
ቀሪው ለባለሥልጣኑ የተፈቀደው በጀት የሚሸፈነው ከመንገድ ፈንድና ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ የብድር ገንዘብ ነው፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ ከሆነ፣ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተፈቀደውና በባለሥልጣኑ በጀት ውስጥ የተካተተው ገንዘብ 1.21 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት የሚበጅትለት ደግሞ 67.38 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ በድምሩ 6.38 ቢሊዮን ብር በጀት ለዚህ ዓመት ሥራዎቹ ማከናወኛ ሊመደብለት ችሏል፡፡
በ2010 በጀት ዓመት ይጀመራሉ ተብለው ከተያዙት አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፑሽኪን አደባባይ-ጎፋ ማዞሪያ፣ ቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ-ቱሉ ዲምቱ አደባባይ፣ ቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ-ቡልቡላ ቂሊንጦ አደባባይ 2ኛው ቀለበት መንገድ፣ ከአያት ኮንዶሚኒየም-ቦሌ በሻሌ፣ ከሽሮ ሜዳ-ቁስቋም፣ ከአበበ ቢቂላ ስታዲየም መግቢያ-አዲሱ ሚካኤል-ሰሜን ሆቴል የሚከናወኑት ግንባታዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ከመብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም-ቦሌ ሆምስ፣ ከሃይኒከን-ወርቁ ሰፈር-ቀለበት መንገድ፣ ከሃያሁለት-ዋና መንገድ-አዲሱ ብሔራዊ ስታዲየም፣ አየር ጤና-አደባባይ-ወለቴ-ዓለምገና አደባባይ፣ ከአውቶቡስ ተራ-ፓስተር፣ ከመሳለሚያ-ኮካ አደባባይ፣ ቦሌ አያት 1፣ 2፣ 3 እና 4 ኮንዶሚኒየም በዚሁ ዕቅድ ውስጥ እንደተካተቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሃያሁለት ማዞሪያ-እንግሊዝ ኤምባሲ ‹‹በራስ ደስታ ሆስፒታል-ቀጨኔ መድኃኔዓለም አስፓልት ፕሮጀክት፣ ሽሮ ሜዳ-ቁስቋም ፕሮጀክት ዲዛይናቸው ተጠናቆ በ2010 በጀት ዓመት ግንባታቸው ከሚጀመሩት መንገዶች መካከል ይገኛሉ፡፡
ከመንገድ ግንባታ ሥራው ባሻገር፣ በ2009 በጀት ዓመት በብዛት ሲያካሒድ የነበረውን የመንገድ ጥገና ሥራም በአዲሱ በጀት ዓመትም እንደሚቀጥልበት ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ ተከታታይና ወቅታዊነቱን የጠበቀ የመንገድ ጥገና ሥራ ለማከናወን ከከተማው አስተዳደር 150 ሚሊዮን ብር የተመደበለት ሲሆን፣ ከመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት 67.3 ሚሊዮን ብር እንደሚያገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለመንገድ ጥገና ሥራው ከከተማ አስተዳደሩና ከመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት የተገኘው በጠቅላላው ከ273 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጠጠር መንገድ ግንባታን ጨምሮ በባለሥልጣኑ አቅም በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ለሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ለኢንዱስትሪ መንደሮች የአገናኝ መንገዶች ግንባታ ማካሔጃ የ110 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘም ባለሥልጣኑ ጠቅሷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በ2009 በጀት ዓመት ከአስተዳደሩ፣ ከመንገድ ፈንድና ከብድር ከተገኘ ገንዘብ ውስጥ የ5.4 ቢሊዮን ብር በጀት ተለቆለት ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 5.2 ቢሊዮን ብር ለካፒታል በጀት፣ 166 ሚሊዮን ብር ለመደበኛ እና 61 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለጥገና በመመደብ ዓመቱን አሳልፏል፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ከፀደቀለት ከዚህ በጀት ውጪ፣ ለመንገድ ጥገና ሥራዎች የ280 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ተፈቅዶለት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንንም ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ እንዳዋለው አስታውቋል፡፡