Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከመንጫጫትና ከማንጫጫት?

እነሆ መንገድ ከመገናኛ ወደ ስድስት ኪሎ። የጎዳናው ጭብጥ ተደጋጋሚ ነው። ሕይወት ቀለም ያለቀባት ትመስላለች። በመንጋ ቅርፅ አሠልፋ የምትነዳው እልፍ ነው። ሲቃችን ተያያዥ ነው። ውክቢያው ለዓይን ያጭበረብራል። ደምቆ ካማረበት ይልቅ ገርጥቶ ያስቀየመው ልቋል። ወጣት አዛውንቱ፣ ጎበዙና ሰነፉ፣ ልማታዊና  ፀረ ልማታዊው ተፋጠዋል። በዚህች ምድር ለሆድ መኖር ዕውቅና የተቸረው ከዛሬ 3,000 ዓመት በፊት ይመስላል። አብሲቱን ተሸክሞ፣ ቅሉን አንጠልጥሎና ምጣዱን አሟሽቶ አይታይም እንጂ፣ ለወጪ ወራጁ የዕለት እንጀራ ጋጋሪነት የነፍሱ ጥሪ ይመስላል። ሐሳብና ሐሳበኞች ሲቀበሩ ትንሳዔያቸውም አብሮ ሳይቀበር አልቀረም መሰል። እዚያ ድንፋታሙ ለዘብተኛው ላይ ይጮሃል። ዝምታ በአቅም ማጣት የተመሰለበት ደግሞ አንገቱን እንደ ደፋ መሽቶ ይነጋል። ጊዜ ሄዶ ሄዶ ማለቂው የሌለው የከንቱነት አጥር ይመስለናል። ነገር ሁሉ ባለበት ላይዘልቅ ግድያችን ከማከማቸትና ከመጠውለግ ጋር የተያያዘ ነው። ፀሐይ በተንጠለጠለችበት እንደ ቀረ  ኳስ ቁልቁል ድምቀቷን ስትረጭ እዚህ ወሩ ሐምሌ ነውና ውርጭ ያርገፈግፈናል።

 “ወይኔ ብርዱ” ስትል አንዷ “ላሙቅሽ” ብሎ ከጎኗ ጠጋ ይላል። ሳቅ ይቀጣጠላል። መለካከፍና አጉል ጠጋ ጠጋ ያፋቀረን ይመስል በደቦ የሚወገዘውን በደቦ እናሞግሳለን። ያቺ ቢጫ ፀሐይ ይኼን ስትታዘብ ጭምር ሳትውል አትቀርም። ስለሰው ልጆች የታዘበችው ብዙ ታዝባ ቋንቋዋ ቋንቋችን ስላልሆነ ብቻ ቁጣዋን በግለቷ የምትለካው ይመስላል። አጠገባችን ከደጅ ታክሲያችን በራፍ ላይ የቆመ ገርጀፍ ያለ ምሁር፣ “ፀሐይን እዚያ የሰቀላት ማን ነው? እውነትን አብርቶ አልጋ ሥር የከተታትን ሰው ፈልጉልኝማ?” እያለ ይጮሃል። ታክሲ ጠባቂው ሠልፈኛ እርስ በርሱ ለመተያየት እንኳ አፍሮ ከንፈሩን ይመጣል። በጠዋቱ መርዶ ነጋሪ እንደተላከበት በጥቅምት ንፋስ የደረቀ ከንፈሩን ሲመጥ፣ እውነት በቅርፊት መልክ እየተላጠች የምትተፋ ይመስላል። ሕይወትና ‹አብስትራክት› ማለት ይኼ አይደል?

“ሾፌር አይበቃም? እንጓዝ እንጂ!” መጨረሻ ወንበር ላይ ከተቀመጥነው ተሳፋሪዎች አንዱ ተንጣጣ። “ይሰማኛል ብለህ ነው የምትደርቀው? ወይስ በሜዳችን የመናገር ነፃነትን እንለማመድ ብለህ?” ስትለው አጠገቡ የተቀመጠች ጎምላላ ዞሮ ዓይቷት አቀለጠው። ይተዋወቁ ኖሯል። “አፌ ቁርጥ ይበልልሽ! ባንቺ ቤት አያይዘሽኝ ሞተሻል እ? ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ እንዲህ አፍ የፈታሽልኝ?” ጎልማሳው ዓይን ዓይኗን እያየ ልጅትን በኃፍረት አንገት አስደፋት። “ቢናገሩ አፈኛ ዝም ቢሉ ሞኝ! ታዲያ አማራጭ ከሌለ ካለው አንዱን መምረጥ የለብኝም? ጊዜው ደግሞ የምርጫ ነው፤” አለችው። “አደራ እንዲህ እያልሽ ቆመሽ እንዳትቀሪ። ሰው ዘንድሮ ካለው የማይሻል አማራጭ እንዳለው ሁሉ፣ የያዘውን እያቃለለ ምርጫ ምርጫ ሲል ነው መላ ቅጡ የጠፋበት። ደህና ነሽ ግን?” እያላት ወደ ግል ጨዋታቸው አዘነበሉ። “ኧረ እናንተ ሰዎች ስለጉልበታችሁ እምላክ እንሂድ?” ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠች ቆፍጣና ረብሻ ጀመረች። ትዕቢተኛው ወያላችን ብቅ ብሎ ገላምጧት ሲያበቃ፣ “የት ለመድረስ ነው አሁን አንቺ እንዲህ የምትመናቀሪው? መሬት በነፃ እየጠበቀሽ ነው የተባለች አትመስልም? ካሬ ሜትር ሚሊዮን ገብቷል አርፈሽ ቁጭ በይ በሏት፤” ብሎን እየተጎማለለ ራቅ አለ።

ቆፍጣኒት ለካ እንዲህ ቀላል አይደለችም። (ማጣት ሲያቀለው እንጂ ድሮስ የሰው ቀላል አለው እንዴ?) ወርዳ ሸሚዙን ጨምድዳ ይዛ ካልደበደብኩ አለች። ደህና ተጠጋግቶ የተሟሟቀው ተሳፋሪ ሊገላግል ወረደ። ትርምሱ በገላጋዮች ብርታት ቢበርድም አፍ እላፊው ሊቆም አልቻለም። ይኼን የታዘበ መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ “አንቺ አትሻይም ከእሱ? ዝም በይ በቃ!” ብሎ ተቆጣና፣ “በጭንቅ የምንሞላት ሆዳችን በየመንገዱ በምንሰረዝረው ቡጢ እየጎደለችማ በምግብ ራስን መቻል አይታሰብም፤” ብሎ በምፀት ፈገግታው ቃኛት። ከእሱ በላይ ያሳቀን ግን ጎልማሳው፣ “በቀለበት መንገድ ምትክ መንግሥት መቧቀሻ ‘ሪንግ’ ቢያሠራልን ነበር ጥሩ፤” ማለቱ ነው። ሰው እኮ ይናገራል!

መጓዝ ከጀመርን ደቂቃዎች አልፈዋል። “ተንጫጩ ቢለን ነው። ማን ሊሰማን?” መጨረሻው ረድፍ ከተደረደሩ ተሳፋሪዎች አንደኛው ተናገረ። “ኧረ ማን ያንጫጫው የሚባልበት ጊዜ ይመጣል። ስለዚህ የመንጫጫት ዕድልን መጠቀም አንዳንዴ ጥሩ ነው፤” ትለዋለች ከጎኑ የተቀመጠች ባለአይፎን። “ግን ግን የመንጫጫት ሕግን ተከትሎ መንጫጫትና እንዲሁ ዝም ብሎ ማንጫጫት ይለያያል፤” ይላል ሌላው። “ወይ ጉድ። በድርድር ዘመን ጫጫታ? ደግሞ ጫጫታ ምን ሕግ አለው? ሕግም ካለው ሊሆን የሚችለው አለመንጫጫትን የሚከለክል  መሆን አለበት፤” ስትል እሷ ሁሉም ፈገግ አሉ። “እንኳን ሰው ቆርቆሮ ካልነኩት ይንቋቋል እንዴ ሳይነኩት? ወደን መሰላችሁ የምንጫጫው? ስለሚነካኩን እኮ ነው፤” የሚለው ደግሞ ጎልማሳው ነው። “የምንጫጫውማ የኢኮኖሚ ዕድገቱና ልማቱ ባመጣው ተፅዕኖ ምክንያት ነው። ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ መፈጠሩን የተጠራጠሩትን ለማሳመን ነው። አንጫጭ ተንጫጭ የለውም። ‹ፕሮግረሱ› ነው፤” ሲል  መዓት የወረዱበት ወጣት፣ ‹‹እሱን ሂድና ፔጅህ ላይ ፖስት አድርገው። ይኼ ታክሲ ነው። አይደለም እንዴ?››  ብሎ ወያላው ሊያያይዝ ሞከረ።

“እናንተ ምን አለባችሁ? ቀልዱ ግዴለም፤” ብለው አዛውንቷ አጉተመተሙ። ጎበዝ የሆነ ሆኖ ነገ ጫጫታው ካለፈ በኋላ በብዙ ቂም ተቆጣጥረን እንዳንገናኝ እያሰብን ብንጫጫ ጥሩ ነው። ዝም ተብሎ ‹ጊዜ ያመጣው ነው፣ ሒደቱ የፈጠረው ነው ወይም አንዳንድ አንጫጮችና ጫጫተኞች አዋክበውን ነው› ማለት ነገ አይሠራም። በማስተዋል እንጫጫ፤” ከማለቱ፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ ምንድነው የምታወሩት? የጫጫታ ሕጉ አንድ ነው፡፡ እሱም መንጫጫት ነው. . .›› ብሎ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ አቋረጠው። ጫጫታ ሕግ አለው? የለውም? በሚል ሙግት ታክሲዋ በጫጫታ አበደች። መደማመጥ ጠፍቶ መንጫጫት ሥጋ መንፈሳችንን ቃኘው። ጫጫታና ጫጫተኞች በነገሡበት ዘመን እኮ ተደራድረን ልናድር? ያድርግልና!

“እሺ እዚያ ጥግ. . .” ወያላው ጉዞ ከመጀመራችን ያጣድፈናል። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡ አንድ አዛውንት ሌላ ሦስቱ ይተዋወቃሉ። የሚጫወቱት ስለኬንያው የአልሸባብ ጥቃት ነው። “የአበራሽን ጠባሳ ያየ ‘አይስቅም’ ሆኖብኝ እንጂ እኔስ ሳቅ ሳቅ ይለኛል፤” ይላል አንደኛው። “ዋ ሰው ሲሞት የሚስቅ ቀጣዩ ሟች ብቻ ነው ይባላል። አይደል አባት?” አዛውንቱን ለፍርድ ያስገቡዋቸዋል። “ይባላል!” ይመልሳሉ ባጭሩ። “እኔ እኮ የምስቀው በሟቾች አይደለም። ምን ነክቷችኋል? ምንድነው የምድሩ አልበቃ ብሎ በሰማይ ቤት ስም ማጥፋት?” ካለ በኋላ፣ “እኔ ሳቅ ሳቅ ይለኛል ያልኩት የአሸባሪዎችና የተሸባሪዎች ነገር እየከረረ ስለመጣ ነው፤” ሲል አዛውንቱ አቋረጡትና፣ “እግዜር ሲጠብቅ ነዋ ልጄ። ሁሉንም እሱ ሲጠብቅ ነው። ‘እሱ ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይደክማል’ ይላል መክብብ። ምህላችን እያስጨነቀው ለቅሷችን ዙፋኑ ሥር እንደ ባህር ተንጣሎ እያየ፣ እንዲያ ላለ የሽብር ጥቃት እንዴት አሳልፎ ይስጠን? ቦምብ ስለማንሰማ ጥይት ስለማይጮህብን እንጂ በቀን ሦስቴ ካለመብላት የከፋ ሽብርስ አለ?” አሉት።

ነገሩ እየተያያዘ እንደ ሰደድ እሳት ወዴት እንደሚያመራ ወጣቶቹ ገብቷቸው አዛውንቱን ሊያናግሩ ይተነኩሳሉ። “እውነት ነው እንግዲህ ፆሙም አለቀ። መብላት ስናስብ ያሰብነውን ያህል መብላት እንደማንችል ትዝ ሊለን ነው፤” አለ ከሾፌሩ ትይዩ መስኮቱ አጠገብ የተቀመጠ። ጓደኛው ተቀበለና፣ “መንግሥት ሳይቸግረው ሃይማኖትና ፖለቲካን ለያይቶ እንጂ የተጀመሩት ልማቶች በሰላምና በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በማለት ሌላ ሁዳዴ ማሳወጅ ነበረበት፤” ብሎ ብቻውን ሳቀ። ሳቁ በትንታ ሲቆራረጥ ተሳፋሪው ደንግጦ ወደ እሱ ዞረ። ጓደኛው ደረቱን እየደቃ፣ “አይዞህ ይቺህን ሳቅማ እንደ ጀመርካት ትጨርሰታለህ! ይኼኔ እያለቀስክ ቢሆን ትን ባላለህ፤” ይለዋል። ተሳፋሪው ፈገግ ይላል። እውነት ግን የለቅሶ ትንታ የሌለው ለምድነው? ለመልካም ነገር እጅ ያጠራት ዓለም!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሰው እንደ ጫነ ለአፍታ ማሰብ የተሳነው ሾፌራችን እያክለፈለፈ ወደ መዳረሻችን አስጠግቶናል። ከፍጥነት እልቂት ብቻ ማትረፍ የመረረው ተሳፋሪ ዘግይቶም ቢሆን፣ “ኧረ ባክህ ቀስ በል?” ይላል። ጎልማሳው፣ “ምን ይደረግ በፍጥነት ተለክፈን እኮ ነው፤” ይላል። ‹‹ቴሌቪዥንና ሬዲዮው እኮ ነው የሚያስበላን። ማስታወቂያውና ማስጠንቀቂያው ሁሉ ከመኪና አደጋ ጋር የተያያዘ ሆኗል፤›› ሲል አንዱ ሁሉም ግር ብሎት ዓየው። ‹‹ታዲያ ጥሩ ነው እንጂ ምኑ ነው ክፋቱ?” ሲሉት ወይዘሮዋ፣  “ይኼው አያዩም እንዴ? የእኛ ሰው እኔ አውቃለሁ ካለ አለ ነው። መቼ ሲነገረን እንወዳለን? መቼ ሲነገረን እንሰማለን? ምክር አንወድም እኮ? ያ አይደለም እንዴ ወስዶ ወስዶ ከዓለም መጨረሻ የወረወረን?” ብሎ ዝም አለ።

ነገሩን የሚያሰፋለት ሰው ቢያጣ ራሱ ቀጠለ። “ስክነት የማይበጀን ነን። ሥራችን ሁሉ የዕለት። ፖለቲካው የዕለት፣ ዴሞክራሲው የዕለት (እሱም የይምሰል ለምርጫ ሰሞን ነው)፣ ፀሎታችን የዕለት፣ ዕቅዳችን የዕለት. . . አናሳዝንም? አርቆ ማየትና አርቆ ማሰብ ያልፈጠረብን እኮ ነው የምሰመስለው፤” ሲል ተረተረው።  ድንገት ወያላው “ውረዱ!” አለ በሩን ከፍቶ። ታክሲዋም ወዲያው ቆመች። ወይዘሮዋ ወያላውን ትኩር ብለው ዓይተው፣ “የመብራት፣ የውኃና ‘የኔትወርክ’ መጥፋት አንሶን ትህትናም ድራሹ ሊጠፋ?” አሉ። ዝብርቅርቁ ኑሯችን የሰለቸው ወጣት “እሱ መልካም አስተዳድርን፣ መብራትን፣ ውኃን፣ ፍትሕን ቀድሟቸው ጠፍቶ መስሎኝ እኛና መሻሻል ጀርባና ሆድ ሆነን መቅረታችን?” አላቸው። ጫጫታው በሁሉም መስክ ነው ለካ? ከመንጫጫትና ከማንጫጫት የቱ ይሻል ይሆን? መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት