በነአምን አሸናፊ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትና ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች ማኅበር፣ ለአቶ ክፍሌ ወዳጆና ለሪፖርተር ጋዜጣ መሥራች አቶ አማረ አረጋዊ ለአገሪቱ የሚዲያ ዘርፍ መጠናከርና ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና ሰጠ፡፡
የዕውቅና አሰጣጡ ሥነ ሥርዓት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በተገኙበት፣ ሐሙስ ዕለት ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ነው የተከናወነው፡፡
በዕውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት በአገሪቱ የሚዲያና የተለያዩ ዘርፎች ጉልህ ሚና የተጫወቱ የሙያው ባለቤቶችና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝው ነበር፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ወቅት አንጋፋዎቹ ጋዜጠኛ አቶ ማዕረጉ በዛብህ፣ የቢዝነስ ሰው አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ፖለቲከኞቹ አቶ ቡልቻ ደመቅሳና አቶ ስብሀት ነጋ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚክስ ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በረሀ (ዶ/ር) ከተገኙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ፣ ‹‹ዕውቅናው የተሰጣቸው ግለሰቦች በአገሪቱ የሚዲያ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚገባቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
የግል ፕሬስን የፈቀደውና ቅድመ ምርመራ በአዋጅ የቀረቡትን 25ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በዕለቱ መሰባሰባቸውን የገለጹት ወ/ሮ መዓዛ፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የታዩ ተስፋዎችንና የገጠሙ ሥጋቶችን ገልጸዋል፡፡
‹‹በአገራችን ያለፉት 25 ዓመታት በተለይ የግል ሚዲያዎች እንቅስቃሴ ረገድ ትልቅ ለውጥ የታየባቸው በመሆኑ በበጎ ጎኑ ብናነሳም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወጣት ጋዜጠኞች ለእስርና ለስደት መዳረጋቸውና ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው የኅትመት ውጤቶች ገና በለጋነታቸው መጨንገፋቸውን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት የተከሰቱት ተግዳሮቶች በሦስት ምክንያቶች ሊመነጩ እንደሚችሉ ወ/ሮ መዓዛ ገልጸዋል፡፡ እነዚህም የወጣቶችን ትኩስ መንፈስ እስከ መጨረሻው ያለመታገስ ችግር፣ የሚዲያው መደራጀት በአገሪቱ ፖለቲካ ትኩሳት በመጠመዱና የኅብረተሰቡ ልክ ልኩን ንገረው ባይነትና የሚዲያ ተቆርቋሪ ሆኖ ለመቆም ብልኃቱን ማጣቱ ናቸው፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ማቋቋም ተገቢ እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ መዓዛ፣ ይህንንም ምክር ቤት ለማቋቋም የተደረገው ጉዞ ከአምስት ዓመታት በላይ ፈጅቶ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ 29 አባላትን በመያዝ መቋቋሙን አውስተዋል፡፡
ምንም እንኳን ምክር ቤቱ ተቋቁሞ የሥራ አስፈጻሚውም የተለያዩ የማደራጀት ሥራዎች ቢጀምርም፣ ውጥኖቹ በምክር ቤቱ የምዝገባ ሒደት መጓተት ምክንያት ሳይሳኩ እንደቀሩ ወ/ሮ መዓዛ አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ የተከናወነው ሥነ ሥርዓትም ምክር ቤቱ እፈጽማቸዋለሁ ከሚላቸው ተግባራት መካከል አንዱ፣ የሚዲያ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎችን ዕውቅና ለመስጠት የሞከረ የጀማሪ መጠነኛ ጥረት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ዕውቅና የተቸራቸው ግለሰቦች አስተዋጾአቸው ከፍተኛ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ‹‹አቶ ክፍሌ ወዳጆ በሰኔ ወር 1983 ዓ.ም. የወጣው የሽግግር ቃል ኪዳን ቻርተር የቅድመ ምርመራ ሥርዓትን ማገድ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም በሕጋዊም ሆነ በአስተዳደራዊ መንገድ እንዳይተገበር የከለከለው ሰነድ ሲፈረምና እርሱን የተካው ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ በሙያቸው፣ በልምዳቸውና በዕውቀታቸው ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ካበረከቱት ኢትዮጵያውያን ውስጥ ግንባር ቀደም ነበሩ፤›› በማለት ወ/ሮ መዓዛ አቶ ክፍሌን ገልጸዋቸዋል፡፡
የአቶ ክፍሌን ዘመን ተሻጋሪ ባለውለታነት ለመግለጽ የፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴን አንደበት የተዋሱት ወ/ሮ መዓዛ፣ ‹‹ጋሽ ክፍሌ ለውጭ ሕዝብና መንግሥት የማንነታችን አስተርጓሚ፣ ለገዛ ሕዝቡና መንግሥቷ ደግሞ ህሊናና ፍትሐዊ ዳኛ ነበር፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ አማረ አረጋዊ ከሽግግሩ መንግሥት ወቅት ጀምሮ በነበሩት ጥቂት ዓመታት በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙትን የሚዲያ ተቋማት በመምራት በወቅቱ የተመሰገኑ ለውጦችን ከማምጣቱ በተጨማሪ፣ የሪፖርተር ጋዜጣን መሥርቶ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ዘልቆ እንዲቆይ ላደረገው አስተዋጽኦ ዕውቅና እንደሰተጠው ገልጸዋል፡፡
‹‹አማረ ከሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ጀምሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በኪነ ጥበብ ዘርፍ የነበሩ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የተጀመሩ ፕሮግራሞች ዛሬም ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የባለጉዳይ ድራማና ሌሎች ዝግጅቶች አማረ በከፈተው በር የገቡ ናቸው፤›› በማለት አውስተዋል፡፡
በዕለቱ ተገኝተው ስለአቶ አማረ አስተዋጽኦ ንግግር ካደጉት ግለሰቦች መካከል አቶ ሙሉጌታ ገሠሠ አንዱ ሲሆኑ፣ እርሳቸውም የአቶ አማረን አስተዋጽኦ ከትጥቅ ትግል አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድረስ የዘለቀው ጉዞ ላይ ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡ እርሳቸውም የ120 ፕሮግራምንና የባለጉዳይ ድራማን እንደ ምሳሌ አውስተዋል፡፡
ሌላው በዕለቱ አስተያየታቸውን ከሰጡ የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል አቶ ዘሪሁን ተሾመ አንዱ ሲሆኑ፣ እርሳቸውም አገሪቱ በሳንሱር ምክንያት ያጣችውን የተለያዩ የጥበብና የመረጃ ሥራዎች በወፍ በረር አስቃኝተዋል፡፡
ሳንሱር የጭንቅላት ፈጠራ ፍሬን ብቻ ሳይሆን የማሰብ አድማስንም የሚያቀጭጭና እውነቶች ለእርሱ እስካልተስማሙ ድረስ የሚቆርጥ መሆኑን ያስረዱት አቶ ዘሪሁን፣ የሳንሱር መቀስ ከጎበኛቸው ሥራዎች ውስጥ ለማሳያነት አቅርበዋል፡፡
‹‹ሳንሱር ሰውነትን፣ ፈጠራን፣ እኔነትን፣ ታሪክን እንዲሁም በድንገት ሳይመረጡ መመሳሰልን ሊያስቆርጥ የሚችል ነው፡፡ ከዚያ ዘመን አልፈን አማረ አረጋዊን ብንወደውም ባንወደውም፣ በክቡር ሚኒስትር ቢሸነቁጠንም፣ በተስፍሽና ገብርሽ ቢያንጓጥጠንም 25 ዓመታት ዘልቆ እንዲቀጥል ያስቻለን ሜዳ የተፈጠረበት ነውና ዛሬ ላይ እርሱን ስንዘክር የሳንሱር ዘመን የሚያምራቸው የተወሰኑ ባለሥልጣናት ቢኖሩ እንደ አማራቸው ይቀራል እንጂ፣ የማይመለስበት ዘመን ነው እንላቸዋለን፤›› በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡
አቶ ክፍሌ ወዳጆ ያልተዘመረላቸው ጀግና እንደሆኑና በዕለቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ በተገኙበት ዕውቅና ማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው የገለጹት ደግሞ፣ የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡
የሕጉን ፅናት፣ የጥበቃውን ዓይነት፣ የከለላውን ጥልቀት በተግባር የፈተሹ ብዙ የሚዲያ ባልደረቦቻችን አሉ ያሉት አቶ ታምራት፣ ‹‹ሙያቸውን በመወጣት ሒደት የተከሰሱ፣ የታሰሩ፣ የተሰደዱ ከዚያም አልፎ የተደበደቡና መከራን የተቀበሉ የሙያ አጋሮቻችንን ሁሉ ለማሰብና ለመዘከር እወዳለሁ፤›› በማለት በአገሪቱ የሚዲያ ዘርፍ የተስተዋሉ እንግልቶችን አውስተዋል፡፡
‹‹ንዋይ በራቀውና መለመጥ በሚያጠቃው ምኅዳር ውስጥ እየዳከሩ እነዚህን ያህል ዓመታት በፅናት ያገለገሉት አቶ አማረ፣ የተሰጣቸው ዕውቅና ቢያንሳቸው ነው እንጂ አይበዛባቸውም፡፡ ነገር ግን የረፈደ ምሥጋና እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ያለፉትን ዓመታት የግል ሚዲያ ተጋድሎ ሪፖርተር የሚለውን ስም አውጥቼ ሳስበው የሚታየኝ ባዶ ሥፍራ ስፋቱ ብዙ፣ ጥልቀቱ ደግሞ እጅግ ረጅም ነው፤›› በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሬዚዳንት ሙላቱም፣ ‹‹በሩብ ምዕተ ዓመት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ነፃነት መሠረት ከጣሉና ለተግባራዊነቱም ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት በርካታ ባለታሪኮቻችን መካከል፣ በፕሮግራሙ ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው ዛሬ በሕይወት የሌሉት አቶ ክፍሌ ወዳጆና በመካከላችን የሚገኙት አቶ አማረ አረጋዊ በእርግጥም በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው፤›› በማለት ለዕውቅናው ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱ የሚዲያ ምኅዳር ከሁለት ተቃራኒ ፅንፎች ወጥቶ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ ምንም እንኳን መሠረታዊው ሕገ መንግሥቱም ሆነ ፕሬስን የተመለከቱ ሕጎች ዋነኛ ዓላማቸው መገናኛ ብዙኃኑ ለአገሪቱ ዕድገትና ብልፅግና የሚበጁ ሐሳቦች የሚንሸራሸርባቸውና ለማኅበረሰቡ ለውጥ ሁነኛ መሣሪያ ማድረግ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ የፕሬስ ውጤቶች ግን በሁለት የተለያዩ ጫፎች እንደቆሙ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ጠቁመዋል፡፡
‹‹በአንድ በኩል በጭፍን ጥላቻ በሌላ በኩል ደግሞ ጭፍን ድጋፍና የማሞካሸት ሁኔታዎች እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሁለቱም ፅንፎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታችን እንቅፋት መሆናቸውን ማውሳት ተገቢ ይሆናል፤›› በማለት ኃላፊነቱን የሚወጣ የመገናኛ ብዙኃን መገንባት አስፈላጊነት ላይ አፅንኦት በመስጠት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡