Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድ ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ተከሰሱ

መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድ ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ተከሰሱ

ቀን:

  • የሰው ሕይወት ማጥፈታቸውና ንብረት ማውደማቸው ተጠቅሷል

በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በኃይል ከሥልጣን ለማውረድ በኤርትራና በተለያዩ ቦታዎች ሲሠለጥኑ ቆይተው በደቡብ ሱዳን በኩል ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል የተባሉ የጋምቤላ ሕዝቦቸ ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) አባላት፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ዓርብ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የጋሕነን ዋና ጸሐፊ ፖል ኡኬች ኡለያንግን ጨምሮ 14 ተከሳሾች በጋምቤላ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪዎች መሆናቸውንና የአገሪቱን መሠረታዊ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት ከጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር 2009 ዓ.ም. ድረስ በጋምቤላ ክልል አኝዋ ዞን የተለዩ ወረዳዎች ውስጥ ሲዘዋወሩ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ውስጥ ለወታደራዊ አገልግሎቶች የሚሆኑ ቦታዎችን በመምረጥ፣ አባላትን በመመልመልና በውጭ አገር ከሚገኙ የጋሕነን አመራሮችና አባላት የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን መግዛታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ተከሳሾቹ ሉክ ጋነ ኡቻላ፣ ኡጁሉ ኡቻን፣ ዋልዬ ኦርዬ፣ አላየሁም ኦኬሎ፣ ኦቶ ኡጁሉ፣ ኢንስፔክተር ዲዲሞ ዌሎ፣ ኡመድ ኦዌል፣ ኡጁሉ ናግዋ፣ ኦፒዬ ኡመድ፣ ኦቦዲ አሪያሚ፣ መናኞት ኦቦዲ፣ ኡማን ኦኛንጎና ኦደሬ ኡማን የሚባሉ ሲሆኑ፣ በጋምቤላ ክልል በኑዌር ተወላጆች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ተስማምተው  እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

ተከሳሾቹ ከኑዌር ተወላጆች በተጨማሪ ከሌሎች ክልሎች ወደ ጋምቤላ በመጡ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ፣ በልማት ድርጅቶች ላይ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ ሥራ በመከፋፈል፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ መንግሥትን በኃይል ከሥልጣን ለማውረድ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ የጋምቤላ ሕዝብ የጋሕነንን እንቀስቃሴ መደገፍ እንዳለበት፣ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ከጋምቤላ መውጣት እንዳለባቸው፣ የጋምቤላ ክልል የደቡብ ሱዳን ባንዲራ የሚሰቀልበት ሳይሆን የጋሕነን ባንዲራ መሰቀል እንዳለበትና የጋሕነን ምሥል ያለበት አመፅ ቀስቃሽ ጽሑፍ በጋምቤላ ከተማ ውስጥ እንዲበተን ያደርጉ እንደነበር በክሱ ተብራርቷል፡፡

የጋሕነን ዋና ጸሐፊ መሆኑ የተገለጸው ፖል ኡኬች አሊያንግ፣ ኝዬለ አሌሮ በተባለ የሽብር ቡድን አመራር የሚመራ 15 አባላት ያሉት የሽብር ቡድንና ካውንዳ አማን በተባለ የሽብር ቡድን የሚመራ 11 አባላት ያሉት የሽብር ቡድን ከኤርትራ ማስገባቱን ክሱ ገልጿል፡፡ የሽብር ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ በጋምቤላ ክልል አኝዋ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች፣ በክልሉ ንብረት አፍርተው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች (ከሌላ ክልሎች የመጡ)፣ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና በመሠረተ ልማት ላይ የሽብር ጥቃት እንዲያደርሱ ዋና ጸሐፊው አስታጥቆ መላኩን ገልጿል፡፡ የጦር መሣሪያዎች በደቡብ ሱዳን በኩል ለማስገባት ስምምነት ላይ  ደርሰው እንደነበረም ክሱ አክሏል፡፡

በጋምቤላ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ኡጁሉ ኡመድና ኬሎ የተባሉ ግለሰቦችን በመመልመልና ለእያንዳንዳቸው 2,000 ብርና ሽጉጥ በመስጠት አሰማርተው የነበረ ቢሆንም፣ በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አስታወቋል፡፡

ተከሳሾቹ ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን የሚሄዱ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ የሽብር ተግባር እንዲፈጸም ወሳኔ በማሳለፍና የሽብር ቡድን አባላትን በማሰማራት፣ ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን ዋን ቱሃ ሲጓዝ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በኢንታንግ ልዩ ወረዳ ቦታው ካሩቱሪ እርሻ ልማት አካባቢ ተኩስ በመክፈት፣ አምስት ሰዎችን መግደላቸውንና ዘጠኝ ሰዎችን ማቁሰላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የጋሕነን አባልና አመራር በመሆን፣ የሽብር ድርጅቱ ታጣቂዎች ሥልጠና የሚወስዱበትን ጫካ በመምረጥ፣ አባላትን በመመልመልና በማሠልጠን፣ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ በሰውና በንብረት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በመወሰንና የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍና የአካል ጉዳት እንዲደርስ  ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1 ሀና ለ)፣ 38 (1)፣ 27 (1) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)፣ 4 እና 5 (2) ሥር የተደነገገውን ተላልፈው የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በማለት፣ ዓቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ላይ ዋና ተካፋይና ድጋፍ መስጠት ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...