Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሸጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ገናና ስም ከነበራቸው የአገር ውስጥ ተቋራጮች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ አኪር ኮንትራክሽን አክሲዮን ማኅበር ባለቤትነት ሙሉ ለሙሉ በሽያጭ ተላለፈ፡፡ 

ከ30 ዓመታት በላይ በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች ሲንቀሳቀስ የቆየውን አኪር ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የባለቤትነት ድርሻ ሙሉ ለሙሉ የገዙት፣ የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና እህት ኩባንያዎችን በሥሩ የያዘው የታፍ ኮርፖሬት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ሰይፉ አምባዬና ወንድማቸው አቶ ይኩኑ አምላክ አምባዬ ናቸው፡፡

የአኪር ኮንስትራክሽን ሽያጭን በተመለከተ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው የሽያጭ ውል ስምምነት ባለፈው ወር አጋማሽ ተፈጽሟል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአኪር ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በባለቤትነት ተመዝግበው የቆዩት ሁለት ባለአክሲዮኖች አክሲዮኖቻቸውን ሸጠው ወጥተዋል፡፡ አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ የተመሠረተበትና በሁለቱ ባለአክሲዮኖች የተመዘገበው ካፒታል 20 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ዋነኛ ባለአክሲዮኑ አቶ አወጣኸኝ ኪሮስ የአኪር 80 በመቶ ባለቤት ድርሻ የነበራቸው ሲሆን፣ ልጃቸው ደግሞ 20 በመቶውን ይዘው ቆይተው ነበር፡፡ በአዲሱ የሽያጭ ስምምነት የ20 ሚሊዮን ብር ዋጋ ካላቸው አክሲዮኖች ውስጥ 80 በመቶውን አቶ ሰይፉ፣ 20 በመቶውን ደግሞ አቶ ይኩኑ አምላክ ገዝተውታል፡፡

በዚሁ ስምምነት መሠረት የአኪር ኮንስትራክሽን ሽያጭና ስም የማዛወሩ ሒደት መጠናቀቁን የሚያረጋግጠው መረጃ፣ አጠቃላይ ግዥው ስለተፈጸመበት የገንዘብ መጠንና አከፋፈሉን አስመልክቶ ስለተደረሰው ስምምነት የሚለው ነገር የለም፡፡

 የአኪር ኮንስትራክሽን መሥራችና ባለቤት ከ31 ዓመታት በላይ የቆየውን ኩባንያቸውን ለመሸጥ የተገደዱት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ካጋጠማቸው የፋይናንስ እጥረት ጋር በተያያዘ በዘርፉ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት በማያስችሉዋቸው ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት አቅም ባለማግኘታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡

በእጃቸው ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶችንም ማስረከብ ባለመቻላቸው ተጨማሪ ጨረታዎችን ለማግኘት እንዳልቻሉ የሚጠቁሙት ምንጮች፣ በጅምር ያለውን ሥራ ለማስጨረስም ሆነ ያለባቸውን ለመክፈል ኩባንያቸውን ለመሸጥ እንደተገደዱ ቢገለጽም፣ አቶ አወጣኸኝ ግን በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጡም፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው ስምምነት የአኪርን ቢዝነስ ሙሉ ለሙሉ ያስተላለፈ ሲሆን፣ በሽያጩ ውስጥ በአኪር ኮንስትራክሽን ስም የተመዘገቡ በርካታ የግንባታ መሣሪያዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ወርክሾፖች፣ ሕንፃዎችና የመሳሰሉ ንብረቶችን ያካተተ በመሆኑ ሽያጩ በመቶ ሚሊዮን ብሮች ተገምቷል፡፡

ወንድማማቾቹ አኪርን ለመጠቅለል በተስማሙት መሠረት አኪር ያለበትን የባንክ ዕዳዎች አቶ ሰይፉ እንደሚከፍሉ የምንጮች መረጃ ይጠቁማል፡፡ አዲሶቹ የአኪር ባለቤቶች በአኪር የተያዙትን ጅምር ሥራዎችን ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ዋጋቸው በድምሩ 2.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት በተለያየ አፈጻጸም ደረጃ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በእጁ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ በተለይም ከሳላይሽ እስከ ኦሞ ያለውን መንገድና በወንዙ ላይ የሚገነባውን ድልድይ ጭምር፣ ደባርቅን ከቡሃይት (ሰሜን ተራሮች ፓርክ) እንዲሁም ሰምቦን ከግንደበር የሚያገናኙ መንገዶች በውላቸው መሠረት የማጠናቀቁ ኃላፊነትም ኩባንያውን ለገዙት የሚተላለፍ መሆኑ በግዥ ስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል ተብሏል፡፡

እንደ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭነቱ በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች ተሰማርቶ የቆየው አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከገነባቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች መካከል የጅግጅጋና የአሶሳ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የአዳማ፣ የመቐለና የድሬዳዋ አስፋልትና የቀለበት መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኩባንያው በአርባ ምንጭ፣ በጎንደርና በመቐለ ዩኒቨርሲቲዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የሠራ ሲሆን፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን የባንኮችና የኢንሹራንስ ኢንስቲትዩት (አሁን የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ)፣ የባህር ዳርና የመቐለ ዴፖዎች፣ የመተሐራ የውኃ መስመር ዝርጋታ፣ የዛምራ ወንዝ ድልድይ፣ እንዲሁም በአሶሳ ሚዛን ተፈሪና በአዲግራት የሚገኙት የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ገንብቶ ካስረከባቸው ፕሮጀክቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አኪርን የገዙት አዲሶቹ ባለቤቶች ኩባንያውን በመለወጥ በኢንዱስትሪው ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ ስለማቀዳቸው ተነግሯል፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ባለማግኘቱ ምክንያት ከጥቂት ወራት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ለመቀነስ እንደተገደደ ገልጾ የነበረው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ በቅርቡ በድምሩ ከሦስት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ዋጋ ያላቸውን አራት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ለመገንባት ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣናት ጋር ስምምነት ለመፈራረ በመብቃቱም ያሰናበታቸውን ሠራተኞች መልሶ እየቀጠረ መሆኑን በተጨማሪ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አዲስ የተገዛውም ኩባንያ ከተክለብርሃን አምባዬ ጋር ተማክሮ ሊሠራ ይችላል የሚል ግምትም አለ፡፡

የአኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ዋነኛ ባለድርሻ መሆን የቻሉት አቶ ሰይፉ በአሁኑ ወቅት ተክለብርሃን ኮንስትራክሽንና ወደ 11 የሚሆኑ ኩባንያዎችን የያዘው የታፍ ኮርፖሬት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ ግሩፑ እንዲቋቋም ያደረጉም ናቸው፡፡ የአኪርን 20 በመቶው ድርሻ የገዙት አቶ ይኩኑ አምላክ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በግሩፑ ሥር ካሉት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የታፍ አሉሚኒየም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡

ኢኮር ኮንስትራክሽን ኩባንያ በውስጣዊና በውጫዊ ተፅዕኖዎች ሳቢያ ቢዝነሱን ቢያስተላልፍም፣ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑ ይነገራል፡፡ በተለይ በውጭ ኮንትራክተሮች ተይዞ የቆየውን የኤርፖርቶች የአስፋልት ኮንክሪት ግንባታ ታሪክ የለወጠበትን፣ የመጀመሪያውን የኤርፖርት አስፋልት ኮንክሪት ግንባታ ያከናወነው በጅግጅጋ ኤርፖርት ነው፡፡ ከጅግጅጋ በኋላ አሶሳ ኤርፖርት የአስፋልት ኮንክሪት ግንባታን የሠራ ሲሆን፣ የሮቤ ኤርፖርት አስፋልት ኮንክሪት ግንባታን በማከናወን ላይ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

አኪር ኮንስትራክሽን የሚል ስያሜ ከመያዙ ቀደም ብሎ አወጣኸኝ ኪሮስ ኮንስትራክሽን በሚል መጠሪያ በ1978 ዓ.ም. የተቋቋመ ነው፡፡ አቶ አወጣኸኝ የራሳቸውን ኩባንያ የዛሬ 31 ዓመት ከማቋቋማቸው በፊት ለሦስት ዓመታት በሦስት የተለያዩ አገር በቀል ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው ሠርተው ነበር፡፡ የራሳቸውን ኩባንያ ካቋቋሙ በኋላ የመጀመሪያ ሥራቸውን የጀመሩት በ1978 ዓ.ም. በጎንደር ለስላሳ ፋብሪካ ግንባታ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በሁለቱም ወገኖች ያሉ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች