Monday, July 22, 2024

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የሥራ ቀጣሪዎች ትስስር ገፊዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአዲስ አበባ ከተማ ሁሌም በሰዎች ከሚጨናነቁ ቦታዎች መካከል አራት ኪሎ ጆሊ ባር አጠገብ የሥራ ማስታወቂያ የሚለጠፍባቸው ሰሌዳዎች የሚገኙበት ቦታ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ በአብዛኛው አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች የሚታዩ ቢሆንም፣ እንደ ቅዱስ ሥፍራ ለዓመታት የተመላለሱበትን ወጣቶች ማግኘት ብርቅ አይደለም፡፡ ለእነዚህ ወጣቶች ከዚህ ስፍራ በቅርብ ርቀት የሚገኙት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ፓርላማው በቂ ምላሽ የሰጧቸው አይመስልም፡፡

ከእነዚህ ተመራቂዎች መካከል ‘ዕድለኛ የሆኑት’ ጥቂቶች ቶሎ ሥራ ያገኛሉ፡፡ ‘ዕድለኛ ያልሆኑት’ ብዙኃኑ ደግሞ ለዓመታት በሥራ ፍለጋ ይንከራተታሉ፡፡ የአገሪቱ ገበያ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ለመጣው ተመራቂዎች ሥራ ለማቅረብ አቅም እንደሌለው ለዓመታት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ችግሩ ከመሠረቱ ስለመፈታቱ አሁንም ማሳያ ማቅረብ አይቻልም፡፡

በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የሚሰጡትን መፍትሔዎች እንዳይታዩ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ ዘንድሮም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በ2009 ዓ.ም. በአገሪቱ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ብቻ 126 ሺሕ ተመራቂዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮችና ደረጃዎች ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚሁ ውስጥ 109 ሺሕ ተመራቂዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡

በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በአገሪቱ የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሁለት ብቻ ነበሩ:: በወቅቱ በመላው አገሪቱ የነበሩት 16 ኮሌጆችም የቅበላና የማስመረቅ አቅማቸው ደካማ የሚባል ነበር:: በ1993 ዓ.ም. መንግሥት ሰባት ተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችን ሲከፍት በተለያዩ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የሚተዳደሩ ሦስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅና ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ) ሥራ ጀምረው ነበር:: በክልል መንግሥታት የሚተዳደሩ ስምንት የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆችም የማይናቅ ሚና መጫወት ጀምረው ነበር:: በ1996 ዓ.ም. ግንባታቸው የተጀመረው አሥራ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎችም በ1999 ዓ.ም. ሥራ ጀምረዋል:: በሦስተኛው ዙር ማስፋፊያ አሥር ተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች በ2003 ዓ.ም. ሥራ የጀመሩ በመሆኑ፣ በጠቅላላው አሁን በአገሪቱ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር 33 ደርሷል:: ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸው ከስልሳ በላይ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሉ:: የክልል መምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆች ቁጥርም ከ30 በላይ ደርሷል:: በቅርቡ ደግሞ 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመገንባት መንግሥት ዕቅድ ይዟል፡፡

የእነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መብዛት የቅበላ አቅምንና የተመራቂ ተማሪዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮታል:: የቁጥሩ ጭማሪ እንደ ትልቅ ዕርምጃ የሚታይ ቢሆንም፣ የትምህርት ጥራትና የምሩቃን ሥራ አጥነት ጥያቄ ሆኖ መነሳቱ ግን አልቀረም::

                   

በ1987 ዓ.ም. ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የገቡ ተማሪዎች ቁጥር 35,000 ብቻ ሲሆን፣ በ2005 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲዎች የቅበላ አቅም ወደ 99,973 አድጎ ነበር:: 2005 ዓ.ም. ብቻ 67,595 አዲስ ምሩቃን ሥራ ፈላጊ ሆነው ገበያውን ተቀላቅለዋል::

በሌላ በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውና ተመርቀው መውጣታቸው ያለ በቂ ዝግጅት የተደረገ ለውጥ እንደሆነ በመጠቆም፣ ጥራት ለመጓደሉና ለሥራ ዓለም ብቁና ዝግጁ ያልሆኑ ተመራቂዎች ለመውጣታቸው ቁጥሩ ምክንያት መሆኑን የሚሞግቱም አሉ::

የአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያም ማክሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ካስተላለፋቸው ዜናዎች መካከል በአንዱ፣ የተመራቂዎች ቁጥርና የአገሪቱ የሰው ኃይል የመቅጠር አቅም ያልተመጣጠነ ስለመሆኑ ገልጿል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ተክለ ማርያም (ዶ/ር) ይህን ክፍተት ለመሙላት መንግሥት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

መንግሥት ለወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉ ከኢኮኖሚ ችግርነት በመዝለል የፖለቲካ ችግር እየሆነ መምጣቱን ያምናል፡፡ በተለይ በቅርቡ አገሪቱ በተቃውሞና አመፅ ወደ አለመረጋጋት በገባች ወቅት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነትን በዋና መነሻ ምክንያትነት የለየው መንግሥት ይህንን ክፍተት ለመሙላት እንደሚሠራ ቃል መግባቱም ይታወሳል፡፡

መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር የሥራ ፈጠራ ፈንድ በመመደብ ይህንኑ ቃሉን ለማክበር መንገድ መጀመሩንም መግለጹ አይዘነጋም፡፡ ወጣቶች አምስትና ከዚያ በላይ ሆነው በመደራጀት የቢዝነስ ዕቅድ አቅርበው አዋጭነቱ ተቀባይነት ካገኘ ብድር እንዲያገኙ ፈንዱ ያስችላል፡፡ አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራርና አስተዳደር ላይ ትኩረት አድርገው የሚመራመሩ የትምህርት ኤክስፐርት፣ ለሥራ ፈጠራ ገንዘብ ሲመደብ ሥራ እንዴት ነው የሚፈጠረው በሚለው ጥያቄ ላይ በቅድሚያ መግባባት እንደሚያፈልግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሥራ በሁለት ዓይነት መንገድ ነው ሊፈጠር የሚችለው፡፡ አንደኛው ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሰፋ ያሉ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ተቋማት በአገሪቱ እንዲንቀሳቀሱ ማመቻቸት ነው፡፡ ሁለተኛው ራሳቸው ተመራቂዎቹ ሥራ እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው፡፡ ይኼ በዋነኛነት አነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶችን ነው በመሣሪያነት የሚጠቀመው፡፡ ስለዚህ ይኼ የተመደበ ገንዘብ በምን ዓይነት መንገድ ነው ሥራ ላይ የሚውለው ወይም እንዴት ሆኖ ነው ሥራ የሚፈጥረው የሚለውን በተመለከተ፣ እስካሁን ምንም ያየሁት ወይም የሰማሁት ነገር የለም፡፡ የተመደበው ገንዘብ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን በምን መንገድ እንደሚጠቀመው ይፋዊ የሆነ የመንግሥት ስትራቴጂ ወይም የፖሊሲ ለውጥ አላየሁም፤›› ብለዋል፡፡

ይኼ ገንዘብ ራሱ የተመደበው ከፖለቲካ ቀውሱ በኋላ መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ መሆኑ ሌላው የችግሩ ምንጭ እንደሆነም ኤክስፐርቱ አመልክተዋል፡፡ ቀድሞ ተገቢ የሆነ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶለት የመጣ ቢሆን ኖሮ የግልጽነት ጥያቄ ሊነሳበት እንደማይችልም ተከራክረዋል፡፡ ‹‹እንደ ፖለቲካዊ ምላሽ እንጂ እንደ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ለመውሰድ ይከብደኛል፤›› ብለዋል፡፡

 

ኤክስፐርቱ አገሪቱ ለአዳዲስ ተመራቂዎች ተጨማሪ ሥራዎችን ለማቅረብ ተስፋ ያደረገችው የኢኮኖሚ ዕድገቷን፣ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መስፋፋትንና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መስህብን እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም ዘርፎች የሚጠበቀው ዕድገት እንዳልታየ ራሱ መንግሥት እንደሚገልጽም አመልክተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው አለመረጋጋት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየተሸማቀቀ መምጣቱ አዲስ ሥጋት መሆኑንም አክለዋል፡፡

የ27 ዓመቱ ደረጀ ለሚ ከሁለት ዓመት በፊት ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በቴክስታይል ኢንጂነሪንግ የተመረቀ ነው፡፡ ደረጀ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎች ተግባራዊ ሥልጠና የወሰደ ቢሆንም፣ በአብዛኛው በንድፈ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ሥልጠና መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ይሁንና እሱና ጓደኞቹ ወደ ቻይና አቅንተው በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ አሠራር ላይ ለስድስት ወራት ተግባራዊ ሥልጠና መውሰዳቸው ትልቅ ዕድል እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ደረጀ አሁን በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙት ፋብሪካዎች ውስጥ በአንዱ በቻይናው ጀይፒ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህን የሥራ ዕድል ከማግኘቱ በፊት ተጨማሪ ሥልጠና መውሰዱንም ይናገራል፡፡ ጀይፒ ጨርቃ ጨርቅን የሚቆጣጠረው የውክሲ ጅንማኦ ኃላፊነቱ የተወሰነ ፋብሪካ የቦርድ ሊቀመንበር ሚስተር ያንግ ናን፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ተመራቂ አንድ ቻይናዊ የጨርቃ ጨርቅ ሠራተኛ 40 በመቶ ብቃት ላይ ለመድረስ የስድስት ወራት ሥልጠና፣ 80 በመቶ ብቃት ላይ ለመድረስ ደግሞ የሁለት ዓመታት የሥራ ላይ ሥልጠና እንደሚያስፈልገው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ደረጀ በኢትዮጵያዊ ሠራተኞችና በቻይናዊ ኤክስፐርቶች መካከል ድልድይ ሆኖ ያገለግላል፡፡ አብዛኛዎቹ ምሩቃን ዘርፉ የሚጠብቀው ክህሎት እንደሌላቸውም አመልክቷል፡፡

በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን እየሳበ የሚገኘው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ60,000 ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ባለፈው ሳምንትም የመቐለነ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርቀዋል፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታትም 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመገንባት ዕቅድ ተይዟል፡፡

በእነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተቀጠሩትን ጨምሮ ተጨማሪ ሥራ መፍጠሩን መንግሥት በየዓመቱ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ አንዳንዶች የመንግሥት ቁጥሮችን እንዳለ መውሰድ ቢቻል እንኳን የተወሰኑ ሥራዎችን ዓይነትና የዜጎችን ሕይወት ምን ያህል ይቀይራሉ የሚለው ግምት ውስጥ እንዲገባ ይጠይቃሉ፡፡ ኤክስፐርቱ፣ ‹‹በመንግሥት ሪፖርት ውስጥ ኮብልስቶንና አነስተኛና ጥቃቅን ይካተታሉ፤›› ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚወስዱት ሥልጠና ከዚያ ወጥተው ሥራ ላይ የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንዳልሆነም ኤክስፐርቱ ሞግተዋል፡፡ ‹‹ሥልጠናው አሁንም ድረስ ንድፈ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የሥልጠናው ደረጃ ራሱ ደግሞ በጣም ዝቅ ያለ ነው፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ ከዝቅተኛው መሥፈርት ውስጥ ከ50 በመቶ በታች ያመጡ እንደሆኑ የመንግሥት ሰነድ ያሳያል፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ኃላፊዎችም የሚመጡትን ተማሪዎች ምንም ልናደርጋቸው የማንችላቸው ዓይነት ናቸው በማለት ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ቀጣሪዎች ደግሞ ተመራቂዎች የሚፈልጉትን ክህሎት ወይም አመለካከት ያላቸው አይደሉም ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ለእኔ መሠረታዊ ችግር የሚመስለኝ የሥልጠናው ተፈጥሮ ነው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ግብዓትና ሒደት ስለሌለው ጥራቱን የጠበቀ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት የአዳዲስ ተመራቂዎች ሥራ አጥነት ጉዳይ ሲነሳበት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ሥራ እንዲሰጣቸው ከመጠበቅ ተላቀው ራሳቸው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ሲመክር ይስተዋላል፡፡ ከላይ የተገለጸው የብሔራዊ ቴሌቪዥን ዜና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው የሥራ ፈጠራ ትምህርት በሚፈለገው ልክ ለውጥ አለማምጣቱን ለዘርፉ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች ስለመግለጻቸው ያትታል፡፡ ባለሙያዎቹ የተመራቂዎች ቁጥርና የአገሪቱ የሰው ኃይል የመቅጠር አቅም ያልተመጣጠነ በመሆኑ፣ ተመራቂዎች ሥራ ፈጠራ ላይ እንዲያተኩሩ መክረዋል፡፡

ኤክስፐርቱ፣ ‹‹ዝም ብለህ ተመራቂዎችን ሥራ ፍጠሩ ስላልካቸው ሥራ አይፈጥሩም፡፡ በሥራ መፍጠር ሒዶት ላይ ያሉ እንቅፋቶች ካልተነሱ፣ በደንብ የተሳለጠ ተቋማዊ አሠራር እንዲቋቋም ካልተደረገ ሥራ ፈጠራ ዝም ብሎ በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡  

የትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ተክለ ማርያም (ዶ/ር) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት የሥራ ፈጠራ ክህሎትን በማዳበር ላይ መሠረት አድርጎ ለውጥ እንዲያመጣ እየተቃኘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በሙያና ቴክኒክ ማሠልጠኛ ኮሌጆች የተግባር ትምህርት ድርሻ 70 በመቶ፣ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ የንድፈ ሐሳብ እንዲሆን መደረጉ ተመራቂዎችን ሥራ ፈጣሪ ለማድረግ የታለመ ነው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ጅምሮች ቢኖሩም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት የሚያገለግል የሥርዓተ ትምህርቱን ክፍተቶች የሚለይና የሚሞላ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተሳስረው እንዲሠሩ ማድረግና ሌሎች ጅምሮችም የሥራ ፈጠራ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡ 

መንግሥት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የጥራት ችግር መኖሩን ባይክድም፣ የትምህርት ተደራሽነት ከትምህርት ጥራት ያልተናነሰ ትኩረት የሚያሻው ችግር እንደሆነ ያስገነዝባል:: በዚህም ምክንያት የትምህርት ፖሊሲው የትምህርት ዕድልን ማስፋትንና የትምህርት ጥራት የማረጋገጥን ጉዳይ ጎን ለጎን እንዲካሄዱ የሚያደርግ መሆኑን ያመለክታል:: ሥራ አጥ ተመራቂ ተማሪዎችን በተመለከተም እንደ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉ የሥራ ዕድል የሚያስፋፉ ስትራቴጂዎችን ከመንደፍ ጎን ለጎን፣ ሥራ ፈጣሪ ምሩቃንን ለማፍራት አመቺ ሁኔታዎች መፍጠሩንም ይገልጻል::

የሥራ አጥ ምሩቃን መበራከትና በመንግሥት የተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ከሠለጠኑበት የትምህርት መስክና ከወሰደው ጊዜ ጋር የማይጣጣሙ እንደሆኑ በመግለጽ የሚተቹ አካላት፣ የመንግሥት 70/30 ፖሊሲ ምሩቃኑን የመቅጠር አቅም ያለው የማኑፋክቸሪንግ ሴክተር መፈጠርን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ አለማደጉን ይጠቁማሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ሥልጠናና በገበያው መካከል የላላ ግንኙነት መፈጠሩ የሥራ አጥ ምሩቃንን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉንም ያስረዳሉ::

መንግሥት ለትምህርት ዘርፍ በአጠቃላይ የሰጠው የተለየ ትኩረት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ማምጣት መጀመሩን ይገልጻል:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰፊ የትምህርትና የሥልጠና ሥርዓት ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማት ጋር የተቀናጀና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ማኅበራዊ ልማት እያመጣ እንደሆነም ይከራከራል:: ዩኒቨርሲቲዎቹ ምሩቃኑን የቀለም ትምህርትና ዕውቀት ብቻ ሳይሆን በሙያዊ ክህሎት የተካኑ፣ ሥራ ፈጣሪና አምራች ጭምር እንዲያደርጉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ እንደሚገኝም ይገልጻል:: ለ2010 ዓ.ም. ለመንግሥት ከተፈቀደው በጀት ውስጥ ለትምህርት ዘርፍ የሚውለው 43 ቢሊዮን ብር መሆኑ ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አመላካች እንደሆነም መንግሥት ይሞግታል:: በእርግጥም መንግሥት ለትምህርት ዘርፍ የሚመድበው በጀት እየጨመረ መሄዱን የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ::

የትምህርት ዘርፍ ተመራማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከፍቷቸው የጥናት ዘርፎች በገበያው የሚፈለጉ ስለመሆናቸው የተጠና እንደማይመስላቸውም ያመለክታሉ:: በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ የትምህርት ክፍሎች መኖርንም ለዚህ እንደ ዋቢነት ይጠቅሳሉ:: ነገር ግን የመንግሥት ፖሊሲ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ የትምህርት ክፍሎች እንዲከፍቱ አያስገድድም:: በ70/30 ፖሊሲም ቢሆን ከአጠቃላይ የትምህርት ዘርፎች ውስጥ ምን ያህል በመቶው ሳይንስ፣ ቢዝነስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ መሆን እንዳለበት ብቻ ነው የሚያስቀምጠው::

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፍን ለመከታተልና ለመምራት የተቋቋመ የፌዴራል ተቋም ሲሆን፣ የግልም ሆነ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራትና ተፈላጊነት ያላቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ያረጋግጣል:: ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው፡፡ ይህን ሹመት ከማግኘታቸው በፊት በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ክፍል ዳይሬክተር ነበሩ:: በወቅቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚያገኙት ትምህርት ለገበያው ዝግጁ እንዲያደርጋቸው ሲባል የሚማሩት ትምህርት ካሪኩለም ሲዘጋጅ ጀምሮ የገበያው አስፈላጊ ባለድርሻ አካላት ፍላጎት እንዲያካትት ተደርጎ ነው የተቀረፀው:: ተማሪዎቹ አስፈላጊው ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል::

ዶ/ር ሳሙኤል መንግሥት ለምሩቃኑ ሁሉ ሥራ ባለማዘጋጀቱ እንደሚተች ግንዛቤው እንዳላቸው ገልጸው፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ለዚህ ክፍተት በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጥ ተስፋቸው እንደሆነ ገልጸዋል:: ‹‹የትም አገር የሚመረቀውን ተማሪ ሁሉ የሚቀጥር ገበያ የለውም:: ስለዚህ የሥራ ፈጠራ ክህሎት አንዱ የሚማሩት መሠረታዊ ነገር ነው:: መንግሥት በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች አማካይነት የሥራ ፈጠራ ክህሎታቸውን ሥራ ላይ እንዲያውሉ እያደረገ ነው:: ሥራ ፈጠራው ሀብት መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ለሀብት ክፍፍልም መሣሪያ በመሆኑ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ አንድምታም አለው:: እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎችም ድጋፍ ናቸው፤›› በማለት ዶ/ር ሳሙኤል አብራርተዋል::

የተመራቂ ተማሪዎች ቁጥር በምንም መመዘኛ ትልቅ እንዳልሆነ ያስታወሱት ዶ/ር ሳሙኤል፣ ለትምህርት ዕድሜአቸው ብቁ ከሆኑት ውስጥ ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑትን በዚህ ወቅት ለማስመረቅ ዕቅድ ቢያዝም የተሳካው ከስድስት በመቶ ያነሰ እንደሆነም ጠቁመዋል:: መንግሥት የትምህርት ጥራትና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን ጎን ለጎን እያካሄደ መሆኑንም በማውሳት፣ የምሩቃኑ ቁጥር ትርፍ ቢመስልም ይኼ የአጭር ጊዜ ነፀብራቅ እንደሆነና በአገሪቱ የረዥም ጊዜ ራዕይ ኢኮኖሚው እየተስፋፋ የመጣውን የተማረ የሰው ኃይል ለማስተናገድ የሚችል አቅም እየተፈጠረ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች እንዳሉ ገልጸዋል::

የትምህርት ጥራት በዋነኛነት ለተመራቂዎች ሥራ ማጣት እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱ አስተያየት ሰጪዎች ግን፣ መንግሥት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስፋፋት ላይ ዓይኑን አዙሮ ወደ ትምህርት ጥራትና የሥራ ዕድል ማስፋፋት ላይ የማተኮሪያ ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ይመክራሉ::

በትምህርት ዘርፍ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ያበረከቱት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን በብዛት መክፈት ላይ ትኩረት ያደረገው በፖለቲካ ስሌት ተነሳስቶ እንደሆነ እንደሚያምኑ ገልጸው፣ ‹‹የትምህርት ተደራሽነት ግን በጣም አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ነገር ግን የትምህርት ጥራትና ፍልስፍናው ራሱ ችግር አለበት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እየተመሩ ያሉት በካድሬዎች ነው፡፡ ለትምህርት ተቋማቱ አንፃራዊ ነጻነት መሰጠት አለበት፤›› ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፣ በተለይ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን ዋነኛ አጀንዳዬ የሚለው የልማት መሣሪያዎች አድርጎ መውሰዱ መሠረታዊ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ቁሳዊ ዕድገት ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በመሰጠቱ በሌሎች ዘርፎች ለዩኒቨርሲቲዎች የተሰጠው ኃላፊነት እንደተዘነጋ ጠቁመዋል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ በአጠቃላይ ከፍተኛ የጥራት ችግር ስላለበት በቂ ጊዜ ወስደው የማይማሩ ተማሪዎች ሲመረቁ በቂ ዕውቀትና የራስ መተማመን እንደማይኖራቸው ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ መሠረታዊ ችግር እንዳለባቸው የማይክዱት ዶ/ር ዳኛቸው፣ የዩኒቨርሲቲዎቹ አደረጃጀትና አሠራር ግን ተማሪዎቹ ይዘውት የገቡትን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

ተማሪዎች የራሳቸው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ቅድመ ዝግጅት እስከተደረገ ድረስ፣ ለሌሎች የመፍትሔ ሐሳቦች አጋዥና አንድ አማራጭ መንገድ ሆኖ መዝለቁ  አይቀርም፡፡ ይሁንና ተመራቂዎች ሥራ እንዲፈጥሩ እየተጠየቁ ያሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ቀድመው ሳይመለሱ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥትን የሚተቹ አሉ፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር የሚያያዘው አንድ ነጥብ የአገሪቱ ዩንቨርሲቲዎች የፖለቲካው ምኅዳር ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳረፈባቸው መገኘቱ ነው፡፡ ተማሪዎች ከካምፓስ ከመውጣታቸው በፊት በአንድም ይሁን በሌላ በጎሳ ፀብ ይካፈላሉ፣ አልያም ሌሎች ሲካፈሉ ያያሉ፡፡ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ባልተናነሰ በገዥው ፓርቲ ፖለቲካ ሲጠመዱም ይስተዋላሉ፡፡ ኢሕአዴግ በሐሳብ ያልተስማሙትን የዩንቨርሲቲ መምህራን ከማባረር ጀምሮ የተለያዩ ተፅዕኖዎች እንደሚያደርግባቸውም የተለያዩ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከትምህርትና ከዕውቀት አዘል ጉባዔዎች ወይም ውይይቶች ይልቅ፣ የፖለቲካና የኢንዶክትሪኔሽን ዓላማ ያላቸው ስብሰባዎች ይበልጥ ይስተዋላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ በመላ አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት እንዳሉትና በእያንዳንዱ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ህዋስ እንደዘረጋ ይነገራል፡፡ በዚህም አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሥርዓቱ አካልና አስፈጻሚ መሆናቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደማምረው የሥራ አጥነት ችግሩን እንዳባባሱት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተመሳሳይ የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከ15 ቀናት በፊት ያፀደቀው የባንኩና የኢትዮጵያ የቀጣይ አምስት ዓመታት የግንኙነት ማዕቀፍም፣ በአገሪቱ ሥራ ፈጠራ እያደገ የመጣ ተግዳሮት መሆኑን ይገልጻል፡፡ የአገሪቱ ሕዝብ የዕድሜ ስብጥር ላይ እየታየ ያለው ፈጣን ለውጥ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገውም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1985 እስከ 2010 ድረስ ከአጠቃላይ ሕዝቡ መካከል ግማሽ ያህሉ ለሥራ ዝግጁ የሆኑ አምራች ኃይሎች መሆናቸውን የሚጠቁመው ሪፖርት፣ ይኼ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2055 ወደ 67.5 በመቶ እንደሚያሻቅብ እንደተተነበየም አመልክቷል፡፡ ይህ ፈጣን ሽግግር ፈጣን ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም፣ ለአዳዲስ ሥራ ፈላጊዎች ግን ሥራ ማግኘት ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነባቸው አስገንዝቧል፡፡ በተጨማሪም በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በአገሪቱ ለሥራ ዝግጁ የሆኑ አምራች ኃይሎች ቁጥር በየዓመቱ በሁለት ሚሊዮን እንደሚጨምርና እ.ኤ.አ. በ2025 ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ያሉ ወጣቶች ቁጥርም በተመሳሳይ በ8.5 ሚሊዮን እንደሚጨምር ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ወጣቶች ባላቸው ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ፣ የፆታ እኩልነት ባለመረጋገጡና እየጨመረ በመጣው የመሬት እጥረት የተነሳ በአብዛኛው ክህሎት ለሌለው ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል የሥራ ዕድል መፍጠርን አዳጋች እንዳደረገውም አክሏል፡፡

የዓለም ባንክ ሪፖርት የግሉ ዘርፍ የተለያዩ ማነቆዎች ስላለበት ሥራ በመፍጠር ረገድ የሚጠበቅበትን ያህል እያገዘ እንደማይገኝ አመልክቷል፡፡ ዘርፉ ከብድር አቅርቦት ውስንነት፣ ከንግድና ሎጂስቲክስ ውጤታማነት፣ ከአቅርቦት ተደራሽነት፣ ከታክስና ግብር አስተዳደር፣ ከሕግ ማዕቀፎች ተገማችነት፣ ጥራትና ጫና፣ ከውጭ ምንዛሪ፣ ከመሬትና ጫና ከሚያሳርፉ የመግቢያ መሥፈርቶች ምክንያት ማነቆዎች እንዳሉበትም ጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ ለወጣቶች ሥራ ማግኘት አዳጋች መሆኑን ያብራራው ይኼው የዓለም ባንክ ሪፖርት፣ መንግሥት 100 ሺሕ ለሚሆኑ በኢትዮጵያ ለተጠለሉ ስደተኞች በአገር ውስጥ በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ ዕድል ለመስጠት ማቀዱንም ይጠቅሳል፡፡

በኢትዮጵያ 800 ሺሕ የሚሆኑ የጎረቤት አገሮች ስደተኞች በተለያዩ የአገሪቱ የድንበር አካባቢዎች በተከለሉ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ፣ በሰነዱ ያካተተው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ እነዚህ ስደተኞች የተወሰነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እንዲያገኙ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀድሞውንም ቢሆን የፈቀደ እንደነበር በማስታወስ፣ በቀጣይ ግን እነዚህ ስደተኞች ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማግኘት እንዲችሉ ዕቅድ መነደፉን ይገልጻል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘጠኝ ነጥቦችን የያዘ ዕቅዳቸውን እንዳቀረቡ የዓለም ባንክ ሰነድ የገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አሥር በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች ቀስ በቀስ ከካምፕ ወጥተው እንዲኖሩ ማድረግ፣ እስከ 100 ሺሕ ስደተኞችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲቀጠሩ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሥር ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት በማቅረብ በእርሻ እንዲተዳደሩ ማድረግ፣ እስከ 213 ሺሕ ለሚደርሱ ስደተኛ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል መስጠት፣ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከ20 ዓመታት በላይ የኖሩ ሕጋዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲፈጥሩ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥትን ዕቅድ ያደነቀ ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ሥጋቶቹንም አልሸሸገም፡፡ ከእነዚህም መካከል በአገር ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ፖለቲካዊ ተቀባይነት አንዱ ነው፡፡ ሌላው ሥጋት የክልል አስተዳደሮች ምን ያህል ዕቅዱን ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉታል የሚለው ይገኝበታል፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶቿን በተለይ በከተሞች አካባቢ ሥራ ማስያዝ እንዳልቻለች በአደባባይ የምትናገር አገር፣ ለ100 ሺሕ ስደተኞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዷ ለብዙዎች እንቆቅልሽ መሆኑ አልቀረም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -