ሁለት ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ሽያጭ ያለው የካንቤቢ ዳይፐር አምራቹ ኦንቴክስ ኩባንያ በኢትዮጵያ ሥራ ጀመረ፡፡ ከሳሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች የመጀመሪያው በሆነው ፋብሪካው፣ በደቂቃ 700 ዳይፐሮች የሚያመርት ማሽኑን የተከለው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ነው፡፡ በአሥር ወራት ጊዜ ውስጥም ሁለተኛውን ማምረቻ በመተከል ምርቱን እንደሚያስፋፋ ታውቋል፡፡
የምርቱን 40 በመቶ ለአገር ውስጥ ገበያ፣ 60 በመቶውን ደግሞ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችለውን የምርት ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኩባንያው እያመረተ የሚገኘው ከጠቅላላ የማምረት አቅሙ 60 በመቶው ሲሆን፣ በቅርቡም ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ማምረት እንደሚጀምር በኢትዮጵያ የኩባንያው ዋና ኃላፊ አቶ ዳንኤል ገብረ ጊዮርጊስ ገልጸዋል፡፡ ወደ ውጭ የሚልከውን የምርት መጠንም ወደ 80 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው፣ ከምሥራቅና ደቡባዊ የአፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አባላት ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
የአዋቂዎችና የልጆች ዳይፐር እንዲሁም የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) ማምረት የሚችለው ፋብሪካው፣ በአሁኑ ወቅት ግን እያመረተ የሚገኘው የሕፃናት ዳይፐር ብቻ ነው፡፡ ወደፊት የገበያውን ሁኔታ እያየ ሌሎችም የሚታወቅባቸውን ምርቶች በኢትዮጵያ እንደሚያመርት፣ አንድ ዳይፐር ለማምረት 14 ዓይነት ጥሬ ዕቃዎች እንደሚያስፈልጉት፣ እነዚህ በሙሉ ግን አገር ውስጥ ስለማይገኙ ከካናዳ፣ ከአሜሪካና ከኮሪያ በማስመጣት እንደሚጠቀም አቶ ዳንኤል አብራርተዋል፡፡
አንደኛው የምርት መስመር ብቻ በዓመት 250 ሚሊዮን ዳይፐር የማምረት አቅም እንዳለው የተናገሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር)፣ ኩባንያው እ.ኤ.አ. በ2020 ብቻ 400 ሚሊዮን ዩሮ የሚገመት ምርት ወደ ውጭ እንደሚልክ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ዳይፐር ለማምረት በግብዓትነት የሚውለውን የፐልፕ ግብዓት በአገር ውስጥ ማምረት በመጀመር ከውጭ የሚገባውን የጥሬ ዕቃ ፍጆታ ለመቀነስ እንደታሰበም ተናግረዋል፡፡
በ27 አገሮች ውስጥ ባሉት ፋብሪካዎቹ ከ11000 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው ኦንቴክስ ኩባንያ፣ በ110 አገሮች ውስጥ ከሚያሰራጫቸው ብራንዶቹ መካከል ቢቢቲፕስ፣ ባዮቤቢ፣ ፖምፖም፣ ቢግፍራል፣ ካንፔድ፣ አይዲ ኤንድ ሴሬኒቲ እንዲሁም በኢትዮጵያ መመረት የጀመረውን ካንቤቢ ዳይፐርን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን እያመረተ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡
ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በኢትዮጵያ የተከለው ፋብሪካ የመጀመሪያው እንደሆነ በማብራራት፣ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች እዚህ ከተመረተው እንደሚላክላቸው የጠቀሱት አርከበ፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2025 ከአፍሪካ ትልቋ የማኑፋክቸሪንግ እምብርት ለመሆን የያዘችውን ውጥን ለማሳካት፣ እንዲህ ያሉ ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች በብዛት መግባታቸው ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ በመንግሥት ጥሪ የተደረገላቸውና ፈቃደኛ የሆኑ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችም ተመዝግበው ልዩ ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ እንደተመቻቸ ተናግረዋል፡፡
ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት በተገነባው ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እስካሁን 18 ኩባንያዎች እንደገቡ ሲታወቅ፣ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ ከጀመሩ አምስት ወራት ማስቆጠራቸውን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ ገልጸዋል፡፡
የስምንት ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ሽያጭ ያለው የአሜሪካው ፒቪኤች ፓርኩን ከተቀላቀሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ነው፡፡ የህንዱ ሬይመንድና የሸሚዝ ጨርቆች በማምረት የሚታወቀው ዉሽ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ አቶ ፍጹም ገለጻ፣ እስካሁን ድረስ አገሪቱ ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝታ አታውቅም፡፡ ይሁንና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ከሚገኙ አምራቾች ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ከጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድ እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡
ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ታሪክ የፈጠረው የሥራ ቅጥር ከ53,000 በልጦ አያውቅም፡፡ ይሁንና በቅርቡ ሥራ የጀመረው የሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ብቻውን ለ60,000 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ እስካሁንም ለ10,000 ዜጎች የሥራ ዕድል አስገኝቷል፡፡
ኦንቴክስ በበኩሉ ከ30 ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በ14 አገሮች ፋብሪካዎቹን አቋቁሞ የሚሠራው ኩባንያው ምርቶቹ በ110 ከተሞች ተደራሽ ናቸው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ትራኮን ትሬዲንግ የድርጅቱ ወኪል በመሆን ምርቱን በአገር ውስጥ ሲያከፋፍል መቆየቱን፣ ኩባንያው ሥራ መጀመሩን ማክሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ወቅት አስታውቋል፡፡ ኩባንያው በረጅም ርቀት ሩጫ የምትታወቀውን አትሌት መሠረት ደፋርን የብራንድ አምባሳደር በማድረግ ሰይሟል፡፡