በቀን ገቢ ግምት ሰበብ የተፈጠረው የሰሞኑ ግለት አሁንም አልበረደም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ የክልል ከተሞችም ጥያቄዎች እንደተሰኑ ስለመሆኑ እየሰማን ነው፡፡ አገማመቱ ግራ ያጋባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በእርግጥም በአንዳንዶቹ ንግድ ቤቶች ላይ የታየው የግምት አጣጣል ጉራማይሌነት እንዳለው የሚያመላክቱ ክስተቶች አሉ፡፡ የቅሬታ አፈታቱም በተሻሻለው ሕግ በተቀመጠው አሠራርና አካሔድ መሠረት እንደማይተገበር የሚገልጹም አሉ፡፡
ጉዳዩን በትክክል ተመልክቶ መፍትሔ ለመስጠት በሚያስችል ብቃትና ጥንካሬ የለውም የሚለው የግብር ከፋዩ አቤቱታ በየቦታው ይደመጣል፡፡ በአንድ ዓይነት ቢዝነስ፣ በተመሳሳይ አቅምና አቋም ላይ የሚገኙ ግብር ከፋዮች፣ አንዱ ከሌላው የተራራቀ የገቢ ግምት እንተጣለባቸው የሚጠቅሱ፣ የቀን ገቢ የግምት አሠራሩ ላይ ከሚነቀሱ አስተያየቶች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡
የቀን ሽያጫችሁ ይህንን ያህል ነው ተብለው የተመደደባቸው ግብር ከፋዮች ከሚያነሱት ቅሬታ ባሻገር፣ የቀን ገቢ ግምቱ መነሻ ስሌት ግራ ያጋባል፡፡ ቤት ኪራይ ለመክፈል የሚንገዳገዱ፣ የጀመሩት ንግድ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል በሚል ተስፋ የቆዩ፣ በቀን ታገኛላችሁ የተባሉትን የገቢ መጠን ሲያቃወሙ እየታዩ ነው፡፡ በአንፃሩ የደራ ገበያና ሽያጭ ያላቸው፣ ጥሩ ገቢ የሚያካብቱት ላይ የተጣለው የቀን ገቢ ግምት ይህ ቀመር መነሻውም ሆነ አጣጣሉ ላይ ቅሬታ እንዲነሳበት እያደረገ ነው፡፡ ከሰሞኑ ዕለታዊ የሽያጭ መጠናቸውን የሚያሳይ መረጃ ለመውሰድና በትክክል ምን ያህል ግብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ለማወቅ ወደ ግብር አስከፋዩ መሥሪያ ቤት ጎራ ያለ እንዲህ ያለውን አስተያየት መስማት ይችላል፡፡ በሽያጭም ሆነ በቀን ከሚያንቀሳቀሱት የገንዘብ መጠን አንፃር ፈጽሞ የማይገናኝ ጥያቄ እንደመጣባቸው የገለጹ አቤት በማለት ምላሽ እየጠበቁ ነው፡፡
የቀን ገቢ ግምቱን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታክስ ፕሮግራም የሥራ ኃላፊ በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት ያደመጥነው ቃል ‹‹ጫጫታ›› የሚል ሲሆን፣ ይኸው ጫጫታ የተፈጠረው ግን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መሆኑን አምኗል፡፡ ቅሬታዎቹንም በአግባቡ ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ነገር ግን ‹‹ጫጫታው›› እንዳይከሰት ለማድረግ ባለሥልጣኑ ቀድሞ መሥራት የነበረበት በርካታ ሥራዎች ባለመሠራታቸው የተፈጠረ ችግር ጭምር እንደሆነ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ጩኸቱና ብሶቱ ጎልቶ ሊሰማ የቻለው ግብር ከፋዩ በግብር አተማመን ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ባለማስጨበጡ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ለተጋጋለው ችግር መንግሥት ራሱንም ተጠያቂ በማድረግ የቀረቡበትን ቅሬታዎች በአግባቡ ማስተናገድ ግድ ይለዋል፡፡ በአግባቡ በማስተናገድ ምላሽ መስጠቱም ዘላቂ ግብር ከፋይ እንዲኖር አመቺ ዕድል የሚፈጥር ስለሆነ አጋጣሚውን እንደ መልካም ዕድል መጠቀሙ ብልህነት ነው፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የቀን ገቢ ግምቱ በትክክል የመዘናቸው ግብር ከፋዮች በዝቶብናል ሲሉ ማየት ደግሞ ያስተዛዝባል፡፡ አገማመቱ ክፍተት ሊኖረው ይችላል የሚለው ጉዳይ ካላጠያየቀ በስተቀር፣ የብዙዎች ግብር ከፋዮች ከሚሠሩት ቢዝነስ አንፃር የተገመተባቸውም ሆነ ክፈሉ የተባሉት ግብር መጠን አኳያ ሲታይ አደባባይ ወጥቶ የሚያስጮህ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም በርካቶች የተጣለውን አዲስ የታክስ መጠን መነሻ በማድረግ ጊዜው ሳያልፍባቸው ለመክፈል ሲሻሙ መታየታቸውም ነው የዚህ ማሳያው፡፡
ስለዚህ ግብር መክፈል ግዴታ መሆኑን መቀበል ድርድር የሌለው መሆኑን መቀበል ለመነጋገር ያመቻል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አብዛኞቹ ግምት የተጣለባቸው ነጋዴዎች የመንግሥት ሠራተኛ ከሚከፍለው በየትዬ ለሌ ያነሰ ግብር እየከፈሉ በዛብን ወዮልን ማለታቸውም ከምክንያታዊነት በመነሳት አግባብነቱን ቢመዝኑት ነገር ይለቃል፡፡ ሕዝቡም ያያቸዋል፡፡ ያውቃቸዋልና፡፡ በመሆኑም ትክክለኛ ጥያቄ ያላቸውን የግብር ከፋዮች አቤቱታ በፍጥነት እንዳይመለስ እንቅፋት ባለመሆን መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ አንዳንዴ ለራስ ጥያቄ ማቅረብ ለጥያቄውም ትክክለኛ መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለሰሞናዊ ትኩሳቱ አንዱ ምንጭ ግብር ከፋዩ በቂ ግንዛቤ አለማግኘት እንደሆነ ታምኖ በመንግሥትም ይህንን ክፍተቱን ማመኑ መልካም ነው፡፡ ይህንን እንደሚያርም ማሳወቁ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ችግር እንደማይኖር ይረዳል፡፡ ሆኖም አሁን ለተፈጠረው ውዥንብር ግን የቀረቡለትን ቅሬታዎች በአግባቡ በመፍታት ነገ ተመሳሳይ ሁኔታ እንደማይከሰት አሳማኝ ምለሽ መስጠት አለበት፡፡
ከዚህ ሌላ ግን ከሰሞኑ የታክስ ግምት አኳያ በአንዳንድ ቦታዎች የሚሰማው ነገር ሁላችንንም ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ይኸውም ብዙ ታክስ ክፈሉ ስለተባልን፣ ይህን ያህልም መክፈል ካለብን፣ አማራጫን በምንሰጠው አገልግሎት ወይም በምንሸጠው ዕቃ ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ነው ሲሉ መደመጣቸው አሳሳቢ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ተገቢ ያልሆነ ስሜት ሲንፀባረቅ ይታያልና ታክስ ጨመረብን በሚል ሰበብ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ማድረግ ይገባል፡፡ ዛቻው ዞሮ ዞሮ ሸማቾችን የሚጎዳ በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ አደጋ መሆኑን በመግለጽ ግብር ከፋዩ በትክክለኛው የግብይት ሥርዓት እንዲጓዝ ማስቻልም የመንግሥት የቤት ሥራ ነው፡፡
ገቢዎችም ሆነ ሌላውም መንግሥታዊ አካል ግብር ከፋዩ እንዲህ ያለውን ቅሬታ ከመመልከትና ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎን የታክስ ግመታው ሌላ ጦስ ይዞ እንዳይመጣ በመጠንቀቅ ወደፊት ተመሳሳይ ለውጥ ሲደረግ፣ ቀደም ብሎ ተገቢውን የማሳወቅ፣ የማስጠንቀቅና የማዘጋጀት ሥራ በመሥራት ታክስ ከፋዩን ማነቃነቅ ጥቅሙ ለራሱ ለመንግሥትም ነውና ይታሰብበት፡፡